Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናፌዴራል ዋና ኦዲተር በኤሌክትሪክ አገልግሎት ላይ የሚታዩ ችግሮችን በፅኑ ተቸ

  ፌዴራል ዋና ኦዲተር በኤሌክትሪክ አገልግሎት ላይ የሚታዩ ችግሮችን በፅኑ ተቸ

  ቀን:

  የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከአሥር ዓመታት በላይ እየተንከባለሉ የመጡ ያልተከፈሉ የአገልግሎት ክፍያዎችን መሰብሰብ እንዳልቻለ፣ ለማስከፈልም ምንም ዓይነት ዕርምጃዎች እንዳልተወሰዱ አስታወቀ፡፡ ይህ የተባለው የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በአገልግሎቱ ከ2006 ዓ.ም. እስከ 2008 ዓ.ም. የደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋነትንና ውጤታማነትን ለመገምገም ያካሄደውን ኦዲት ሪፖርት፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴ ጥር 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ባቀረቡበት ጊዜ ነው፡፡

  በኤሌክትሪክ አገልግሎት መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት መሰብሰብ የነበረበት 133 ሚሊዮን ብር እንዳልተሰበሰበ፣ 97 የተለያዩ ደንበኞች የተጠቀሙበትን 81 ሚሊዮን ብር ለመክፈል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው እንዲከፍሉ ለማድረግ ምንም ዕርምጃ እንዳልተወሰደም የዋና ኦዲተር ሪፖርት ያሳያል፡፡

  አዳዲስ ደንበኞች አገልግሎት ፈልገው በሚመጡበት ጊዜ ክፍያ በፈጸሙበት ቀን ቅደም ተከተላቸው ተጠብቆ የማይስተናገዱ መሆኑን፣ በአሠራሩ መሠረት ለደንበኞች የቆጣሪ፣ የትራንስፎርመር ተከላና ማሻሻያ ቀልጣፋ አገልግሎት የማይሰጥ በመሆኑ ለዓመታት አገልግሎት ለማግኘት የሚጠብቁ እንዳሉ ዋና ኦዲተር በሪፖርቱ ገልጿል፡፡

  ከዚህ በተጨማሪም በኤሌክትሪክ አገልግሎት የኃይል መቋረጥ ሲኖር በጊዜ መፍትሔ ለመስጠት መዘግየት እንደሚታይና የጥቆማ ስልክ እንደማይነሳ በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡ በተደጋጋሚ የኃይል መቆራረጥ የተነሳም የተለያዩ ድርጅቶች ኪሳራ እየደረሰባቸው እንደሆነ፣ በተለይም ፈጣን ምላሽ ባለመሰጠቱም ለአብነት በምርት ወቅት ኃይል በመቋረጡ የድሬዳዋ የምግብ ኮምፕሌክስ ከ36.2 ሚሊዮን ብር በላይ፣ የድሬዳዋ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ደግሞ ከ2.2 ሚሊዮን ብር በላይ ለኪሳራ መዳረጋቸውን ሪፖርቱ አሳይቷል፡፡

  የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጎሳዬ መንግሥቱና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች በሰጡት ማብራሪያ፣ ከ140 ሺሕ በላይ ወረፋ የሚጠብቁ ተገልጋዮችን ወደ 25 ሺሕ መቀነስ እንደተቻለና ለእነዚህ ምላሽ ከተሰጠ በኋላ በቀጣይ ደንበኞች በመጡበት ቅደም ተከተል መሠረት እንደሚስተናገዱ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ቅድሚያ የሚሰጣቸው የኤክስፖርት ኢንዱስትሪዎችና ማኅበራዊ አገልግሎቶች አሁንም ያለወረፋ እየተሰጣቸው ያለው አገልግሎት እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

  ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከ2006 እስከ 2008 ዓ.ም ባሉ የኦዲት ግኝቶች ላይ በሚሰጠው የማሻሻያ ሐሳብ መሠረት ወቅታዊና አስተማሪ ዕርምጃዎችን ወይም ዕርምቶችን የማይወሰድ መሆኑም በኦዲቱ ተገልጿል፡፡

  የአገልግሎቱ ኃላፊዎች በቆጣሪ አንባቢዎች ላይ የሚታይ የአመለካከት ችግር እንዳለ፣ ስህተት ሲፈጽሙ ዕርምጃ የሚወሰድበት ሁኔታ እንደነበረ፣ ከኦዲቱ በኋላም መተዳደሪያ ደንብ እንደተዘጋጀላቸው፣ አንድ ቆጣሪ አንባቢ 2,200 ደንበኞች በወር መሸፈን የሚጠበቅበት ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ከዚያም በላይ የሚሸፍንበት ሁኔታ እንዳለና ይህንን ለማካካስም የማትጊያ ሥርዓት እንደተበጀና ከዚህ ሌላም ተጨማሪ ቆጣሪ አንባቢዎች እንደተቀጠሩ አስረድተው፣ ዋነኛው የችግሩ መፍትሔ ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ቆጣሪዎችን መጠቀም በመሆኑ ይህንን ለማከናወን እየተሠራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለቆጣሪ ግብር 53 ብር ብቻ ይከፍሉ የነበሩት የኢንዱስትሪ ደንበኞች ክፍያ መስተካከሉን አስረድተዋል፡፡

  የፌዴራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ የመብረቅ መከላከያ የሌላቸው 40 በመቶ የሚሆኑ ትራንስፎርመሮች መኖር የሚያመጣውን ችግር በሚገባ በመገንዘብ ከአገልግሎት ማስፋፊያው ጎን ለጎን መፍትሔ እየሰጡ መሄድ እንደሚያስፈልግ፣ የኃይል ስርቆት ላይ የሚሠራውን ቁጥጥር ማጠናከር እንደሚገባ፣ አሁን እየባከነ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል ከፍተኛ በመሆኑ የኃይል ብክነት የሚፈጠርባቸውን ሁኔታዎች ለመቀነስ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት እንደሚያሻ አስገንዝበዋል፡፡

  የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ት ወይንሸት ገለሶ በማጠቃለያ አስተያየታቸው፣ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ችግሮችን በመለየት ለመፍታትና አሠራርንና አደረጃጀትን በማስተካከል ላይ ትኩረት መስጠቱ በጥንካሬ እንደሚታይ ገልጸዋል፡፡

  የኤሌክትሪክ ኃይል ሽፋንን ወደ 70 በመቶ ማድረስ ከመታቀዱ ጋር በተያያዘ ይህንን ለማስፈጸም የሚያስችል የረጅም ጊዜ ዕቅድን ከወዲሁ ማሰብ እንደሚያስፈልግ፣ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ያሉ የአሠራር ችግሮችን መፍታትና ቅንጅታዊ ሥራን የጋራ አቅም አድርጎ መሥራት እንደሚገባ፣ ከክልል በየደረጃው ካሉ አመራሮች ጋርም በቅርበት መሥራት እንደሚያሻ፣ የተቋሙንና የሠራተኛውን አቅም መገንባት በተለይም በመልካም አመለካከት የተገነባ ወጥ አመለካከት ያለው ኅብረተሰቡን ማገልገል የሚችል የሰው ኃይል ላይ መሥራት እንደሚገባ፣ የአገልግሎቱ የውስጥ ኦዲት የሚሰጣቸውን አስተያቶች በመውሰድ ቀድሞ መተግበር እንደሚያስፈልግ፣ የውስጥ ኦዲቱን በአቅምና በሰው ኃይል ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ወ/ት ወይንሸት አሳስበዋል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ኃይሎች ላይ ጥቃት አልፈጸምኩም አለ

  የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ...

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...