Tuesday, August 9, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናሙለር ሪል ስቴት የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እከሳለሁ አለ

  ሙለር ሪል ስቴት የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እከሳለሁ አለ

  ቀን:

  • የራስ አበበ አረጋይ መኖርያ ቤት ፈርሶ የተጀመረው ግንባታ ታገደ

  የራስ አበበ አረጋይ መኖርያ ቤት ቅርስ ነው ተብሎ የተመዘገበ በመሆኑ መፍረስ አልነበረበትም በሚል ምክንያት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እየተካሄደ የነበረውን የአፓርትመንት ግንባታ እንዲታገድ ማድረጉን የተቃወመው ሙለር ሪል ስቴት፣ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንደሚወስደው አስታወቀ፡፡

  በተለያዩ የኢንቨስትመንት ሥራዎች የሚታወቀው ሙለር ሪል ስቴት ኩባንያ ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ የራስ አበበ አረጋይ መኖርያ ነው የተባለው ቤት ከቤተሰቦቻቸው በሽያጭ ወደ ሌላ ግለሰብ የተዛወረና በተደጋጋሚም ተሸጦ የስም ዝውውር የተካሄደበት ነው፡፡ ሙለር ሪል ስቴትም ለሦስተኛ ጊዜ ለሽያጭ ሲቀርብ ገዥ ሆኖ በመቅረቡ በፍትሕ ሚኒስቴር የሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ጽሕፈት ቤት በፀደቀ ውል የራሱ አድርጎ ካርታ መያዙን አስታውቋል፡፡

  ቤቱ ሥልጣን ባለው አካል በቅርስነት ያልተመዘገበና ከተማው በሚመራበት ማስተር ፕላን ዕውቅና የተሰጠው አለመሆኑን፣ በቅርስነት የተመዘገበ ቢሆን እንኳ በተደጋጋሚ ሲሸጥና ሲለወጥ ገዢዎቹ ባለሀብቶች ታሪካዊ ቅርስ መሆኑን አውቀው እንዲጠብቁት የተደረገ ወይም ቅርስ መሆኑን እንዲያውቁት አለመደረጉን፣ በቦታው ላይም ግንባታ እንዳይካሄድና ቤቱ እንዳይፈርስ ሕጋዊ ክልከላ የተደረገበት አይደለም፤›› በማለት ሙለር ሪል ስቴት ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

  ሙለር ሪል ስቴት ጨምሮ እንደገለጸው፣ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ የፈረሰውን ቤት ቅርስ ነው በማለት ሕጋዊ የግንባታ ፈቃድ ያለውን ፕሮጀክት ያላግባብ እንዲቆም ያደረገው በሕግ ከተሰጠው ሥልጣን ውጪ ብዙ ርቀት ሄዶ ነው፡፡ ስለቅርስ ጥናትና አጠባበቅ በወጣው አዋጅ ቁጥር 205/1992 ቤቱ ስለቅርስ የተሰጡ ትርጓሜዎችን የሚያሟላ ከሆነ እንኳ፣ ተገቢ ጥበቃ እንዲደረግለት ለከተማው ማስተር ፕላን ባላስታወቀበትና ባላስመዘገበበት፣ ከዚህ በተጨማሪም ስለቅርስ ጥናትና አጠባበቅ ምዝገባና ቁጥጥር በወጣው አዋጅ የተሰጠው ሥልጣንና ተግባር ሳይኖር ሌሎች የአስተዳደሩ አካላትን ጭምር በማሳሳት ሕጋዊ ፈቃድ ያለውን ፕሮጀክት ማስቆሙ አግባብ አለመሆኑን አስታውቋል፡፡  

  የራስ አበበ አረጋይ ቤት የሚገኘው በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ከካዛንቺስ ወደ ሲግናል በሚወስደው መንገድ ከዓደዋ ድልድይ ከፍ ብሎ ከሚገኘው፣ የኢትዮጵያ ሴቶች አደባባይ ፊት ለፊት ነው፡፡ ከ70 ዓመት በፊት በ1,800 ካሬ ሜትር ቦታ የተገነባው የራስ አበበ መኖርያ ቤትን ቤተሰቦቻቸው ለአትሌት ቀነኒሳ በቀለ፣ ቀነኒሳ ደግሞ ለአክሰስ ሪል ስቴት ሸጦታል፡፡ በመጨረሻ አክሰስ ሪል ስቴት እንደሸጠው ታውቋል፡፡ ሙለር ሪል ስቴት ይህንን ይዞታ በፍትሕ ሚኒስቴር የሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ጽሕፈት ቤት በ2003 ዓ.ም. በተመዘገበ የግዥ ውል የራሱ ሀብት እንዳደረገው ይናገራል፡፡  

  በዚህ መሠረትም ሙለር ሪል ስቴት የግዥ ውሉን ለአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ በማቅረብ ይዞታው በሕጋዊ መንገድ በስሙ እንዲዛወር፣ በ2004 ዓ.ም. የይዞታ ማረጋገጫ ከወሰደ በኋላ የመኖርያ አፓርታማ ሕንፃ ለመገንባት ለየካ ክፍለ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት የፕላን ስምምነት ጠይቆ 20 ፎቅ ያለው ሕንፃ መሥራት እንደሚችል እንደተፈቀደለት አስታውቋል፡፡

  የፕላን ስምምነት መረጃ ከተሰጠ በኋላ ዲዛይንና ጥናት ተሠርቶ ለአዲስ አበባ ከተማ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን በማቅረብ ባለ 19 ፎቅ አፓርታማ ለመገንባት የሚያስችል ፈቃድ ማግኘቱንም ጠቁሟል፡፡

  የግንባታ ፈቃድ ከተሰጠው በኋላ ግንባታውን ለመጀመር ቅድመ ሁኔታን ለማሟላት በይዞታቸው ላይ የሚገኘውን ቤት ለማፍረስ ፈቃድ እንዲሰጠው ጠይቆ፣ ከየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ጽሕፈት ቤት በይዞታው ላይ የሚገኘውን ቤት ለማፍረስ የግንባታ ማፍረሻ ፈቃድ ማግኘቱን አስረድቷል፡፡

  በመቀጠልም ግንባታ ለመጀመር የሚያስችለውን ፈቃድ ከከተማው የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን በማግኘት፣ ቤቱን በማፍረስ አራት ሜትር ያህል ከቆፈረ በኋላ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከሚመለከታቸው መዋቅሮች ጋር በመተባበር ግንባታውን አስቁሟል፡፡

  ቢሮው ግንባታውን ያስቆመው መኖርያ ቤቱ እስኪፈርስ ድረስ የጣሊያን ሬስቶራንት ነበር፡፡ በአምስት ዓመቱ የጣሊያን ወረራ ታላቅ ተጋድሎ የፈጸሙት የታዋቂው አርበኛ ራስ አበበ መኖርያ ቤት በመሆኑና ከተገነባም 70 ዓመታት ያስቆጠረ ስለሆነ፣ አዲስ አበባ ውስጥ ቅርስ ናቸው ተብለው ከተለዩ 440 ታሪካዊ ቤቶች ውስጥ አንዱ ነው በሚል ምክንያት ነው ግንባታው የቆመው፡፡

  ነገር ግን ሙለር ሪል ስቴት ይዞታው ቅርስ ስለመሆኑ አንድም ቦታ አለመመዝገቡን በመጥቀስ፣ ሕጋዊ መንገዶችን በሙሉ በመጠቀም ግንባታ ማካሄድ መጀመሩን አስታውቋል፡፡

  ግንባታ ለማካሄድ የሚያስችሉ ሒደቶችን በማለፍ መኬድ በነበረበት መንገድ ሁሉ ይዞታው ታሪካዊ ቅርስ መሆኑን የሚያመለክት ምንም ዓይነት አጋጣሚ አልነበረም ብሏል፡፡

  የአዲስ አበባ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ገብረ ጻዲቅ ሐጎስ አስተያየት እንዲሰጡበት የተደረገው ጥረት ባይሳካም፣ በከተማው በሚካሄዱ ግንባታዎች ሙሉ ሥልጣን ያለው የአዲስ አበባ ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መለስ አለቃ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ይዞታው ቅርስ ነው የሚል ቅሬታ ቀርቧል፡፡

  ‹‹ጉዳዩን አጣርተን ውሳኔ እስክንሰጥ ድረስ ግንባታው በዕግድ ይቆያል፤›› ሲሉ አቶ መለስ ገልጸዋል፡፡ ሙለር ሪል ስቴት በዚህ ቦታ ላይ 70 ሜትር ርዝመት ያለው ባለ 20 ፎቅ አፓርታማ ለመመገንባት ፈቃድ ወስዶ ቁፋሮ ጀምሮ ነበር፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የአገሪቱ ባንኮች ካፒታል 199.1 ቢሊዮን ብር ደረሰ

  ከታክስ በኋላ 50 ቢሊዮን ብር ማትረፋቸውን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ የአገሪቱ...

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...