[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ወዳጃቸው ይደውልላቸዋል]
- ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት ነህ ወዳጄ?
- ሰሞኑን እኮ አላንቀሳቅስ አላችሁን፡፡
- እንዴት አላንቀሳቅስ አላችሁን ስትል?
- ቢዝነሱ ተቆላልፏል፤ ከተማውም ተቆላልፏል፡፡
- ማነው የቆላለፈው?
- ከተማው ውስጥ የሉም እንዴ?
- ስልኬ ላይ መስሎኝ የደወልክልኝ?
- ታዲያ ይኼው በመሪዎቹ ስብሰባ ምንም ሥራ መሥራት አልቻልንም፡፡
- ሰውዬ ስብሰባው እኮ ለአገሪቷ በጣም ወሳኝ ስብሰባ ነው፡፡
- ምኑ ነው ወሳኝነቱ?
- ከዚህ ስብሰባ አገሪቷ ብዙ ነው የምትጠቀመው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ከድሮ ጀምሮ የስብሰባው ፋይዳ አይታየኝም፡፡
- ምን ሆነሃል ሰውዬ?
- ሕዝቡ ከዚህ ስብሰባ ያተረፈው አንድና አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡
- ምንድነው?
- መንገላታት፡፡
- አየህ ችግራችሁ እኮ ይኼ ነው፡፡
- እንዴት?
- በዚህ ስብሰባ ምን ያህል የአገሪቷ ገጽታ እንደሚገነባ ተረስቶ የራስህን መንገላታት ነው የምታየው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ሰው ምን እንደሚል አያውቁም?
- ምን ይላል?
- ለስብሰባው የሚመጡ የአፍሪካ መሪዎች ተዝናንተው እንጂ ምንም ሥራ ሠርተው አይደለም የሚሄዱት፡፡
- ምን እያልክ ነው?
- መሪዎች እዚህ ሲመጡ ሰክረውና ጨፍረው ነው የሚሄዱት፡፡
- ምን?
- እንዲያውም የከተማውን ኮረዶች አማግጠው ነው የሚሄዱት፡፡
- ይኼ ተራ አሉባልታ ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እሱን ይተውትና ከስብሰባው ምን አተረፍን?
- እ. . .
- እስኪ አንድ ጥያቄ ልጠይቅዎት፡፡
- ምንድነው?
- የስብሰባው ዋነኛ አጀንዳ ምንድን ነበር?
- ሙስናን መዋጋት፡፡
- ኪኪኪ. . .
- ምን ያስቅሃል?
- ጽድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ አሉ፡፡
- ምን ለማለት ፈልገህ ነው?
- እኮ የአፍሪካ መሪዎች ናቸው ሙስናን የሚዋጉት?
- ምን ያንሳቸዋል?
- አኅጉሪቷን ጨለማ እንድትሆን ካደረጉት ዋነኛ ምክንያቶች መካከል አንዱ መሪዎቿ የተዘፈቁበት ሙስና መስሎኝ፡፡
- ለዚያ አይደል እንዴ ሙስናን መዋጋት ያስፈለጋቸው?
- ሌባ እንዴት ነው ፖሊስ የሚሆነው?
- የምታወራው አልገባኝም፡፡
- ዋነኛ ሙሰኞቹ ሙስናን እንዋጋለን ሲሉ ገርሞኝ ነዋ፡፡
- ምን ችግር አለው?
- ይኼ እንዴት ሊሆን ይችላል?
- ተሃድሶ አድርገው ነዋ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ይኼን ዲስኩርዎን እንዳይጀምሩ፡፡
- የምን ዲስኩር ነው?
- ተሃድሶ ምናምን እያሉ ነዋ፡፡
- ስማ ሙስና እኮ ዋነኛ ጠላታችን ነው፡፡
- ጀመሩ በቃ፡፡
- እውነቴን ነው ስለዚህ አጥብቀን መዋጋት አለብን፡፡
- ለማንኛውም መሪዎቹ የተሰበሰቡት ሙስናን ለመዋጋት አይመስለኝም፡፡
- ታዲያ ለምንድነው?
- ሙስናን ለማስፋፋት!
[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ባለሀብት ደወለላቸው]
- ዜናውን ሰሙ ክቡር ሚኒስትር?
- የትኛውን ዜና?
- ይኼን ዜና ካልሰሙማ የሉም ማለት ነው?
- ስማ እኔ በጣም ብዙ ሥራ ስላለብኝ ዜና እየመረጥኩ ነው የምሰማው፣ በዚያ ላይ ፌክ ኒውስ ስለበዛ እሱንም እየተዋጋሁ ነው፡፡
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር ስለፌክ ኒውስ በእርግጥ ያውቃሉ?
- ኢሕአዴግ መንግሥት ጨቋኝ ነው የሚል ለእኔ ፌክ ኒውስ ነው፡፡
- እ. . .
- አዎ ኢትዮጵያ ልትፈርስ ነው ምናምን እያሉ የጥፋት ኃይሎች የሚያስወሩት ሁሉ ለእኔ ፌክ ኒውስ ነው፡፡
- ለእርስዎ እውነተኛ ዜና ደግ ደጉን የሚያወራ ብቻ ነው?
- ምን ነካህ መጥፎ ዜና የሚያወራ ሰውዬውም ፌክ ነው፣ ዜናውም ፌክ ነው፡፡
- አገሪቷ ውስጥ ግን ምንም ጥሩ ነገር የለም፡፡
- አንተም ፌክ ነህ ማለት ነው?
- ለማንኛውም ዛሬ የደወልኩት መፈታቱን ልነግርዎት ነው፡፡
- ተያዘ ማለትህ ነው ነው?
- ማን?
- ጾሙ፡፡
- ኧረ እኔ ስለጾም አይደለም የማወራው፡፡
- ስለማን ነው ታዲያ?
- ስለባለሀብቱ፡፡
- እኔ አላምንም፣ እኔ አላምንም፡፡
- እውነት ነው ተፈቷል ዜናውን አላነበቡም?
- ምን ላይ ነው የወጣው?
- ሮይተርስ በሉ፣ ኒውዮርክ ታይስም በሉ ያልወጣበት ሚዲያ አለ እንዴ?
- እና ወዳጃችን ተፈታ ነው የምትለኝ?
- እኔ ስለወዳጃችን አይደለም ያወራሁት፡፡
- ታዲያ ስለማን ነው?
- ዋናው የሳዑዲ ቢሊየነር፡፡
- እሱ ተፈታ አልተፈታ ለእኔ ምን ይፈይዳል?
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- እሱ ቤት አልገዛልኝ፣ ወይ አያሳክመኝ ምን ያደርግልኛል?
- ዶሚኖ ኢፌክት አለዋ፡፡
- ምን እያልክ ነው?
- የእኛም ወዳጅ ሊፈቱ ይችላሉ እያሉ ነው፡፡
- ምን ያህል እርግጠኛ ነህ?
- ሰሞኑን ይገባሉ እየተባለ ነው፡፡
- ስማ ባለፈው ይፈታሉ ብላችሁኝ ኤርፖርት ድረስ አበባ አስታቅፋችሁ ላካችሁኝ፡፡
- ልክ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የስንት ሰው መሳለቂያ እንዳደረጋችሁኝ ታስታውሳለህ አይደል?
- አሁን ግን እርግጥ ነው እየተባለ ነው፡፡
- በምን አወቅክህ?
- ይኸው ሁላችሁም አንድ ዓይነት ሙሉ ልብስ አሰፉ ተብለን አሰፍተናል፡፡
- ሌላስ?
- በቃ የሚያርፉበትም ቤት ቀለም እየተቀባ ነው፡፡
- ፌክ ኒውስ እንዳይሆን?
- ፌክማ ከሆነ ማመላለሳችንን እንቀጥላለን፡፡
- ምኑን?
- ስንቁን!
[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሯቸው ውስጥ አንድ ጋዜጠኛ ጥያቄ ጠይቋቸው በጣም ተናደዋል]
- እንዴት ነው እንዲህ ዓይነት ጥያቄ የምትጠይቀኝ?
- ክቡር ሚኒስትር የመጣሁት እኮ ልጠይቅዎት ነው፡፡
- ቢሆንስ እንዴት እንደዚህ ዓይነት ጥያቄ ትጠይቀኛለህ?
- እንዴት ነው የማልጠይቅዎት?
- ደግሞ እንደዚህ ነው የምትመልስልኝ?
- ክቡር ሚኒስትር ይኼ እኮ ሥራዬ ነው፡፡
- ታዲያ እኔ ምን አገባኝ?
- ክቡር ሚኒስትር የተቀመጡበት ቦታ እኮ የሕዝብ ቢሮ ነው ስለዚህ ተጠያቂነት አለብዎት፡፡
- እንዲህ የልብ ልብ የሰጠህ ማነው?
- በድንፋታና በዛቻማ ድሮ ቀረ፡፡
- ምን?
- አሁን በአገሪቷ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ እየሆነ ነው፡፡
- አልገባኝም?
- ሕዝቡና አመራሮቹ ተራርቀዋል፡፡
- እንዴት?
- ሕዝቡ አመራሮቹን የትና የት ጥሏቸው ሄዷል፡፡
- በምንድነው ጥሏቸው የሄደው?
- በአመለካከቱ፡፡
- ስማ እኛ እኮ ለዚች አገር ደማችንን አፍስሰን አጥንታችንን ከስክሰናል፡፡
- ክቡር ሚኒስትር አገሪቷ የእናንተ ብቻ አይደለችም፡፡
- ምን እያልክ ነው?
- ኢትዮጵያ የሁላችንም ናት፡፡
- ታዲያ እኛ መቼ የግላችን አደረግናት?
- ይኸው ችግሩ የመጣው በእኛው ስለሆነ መፍትሔውም ከእኛ ብቻ ነው ትላላችሁ፡፡
- አጠፋን እንዴ?
- ነገርኩዎት እኮ አገሪቷ የሁላችንም ስለሆነች መፍትሔውም ከሁሉም ነው መምጣት ያለበት፡፡
- መፍትሔ ካለማ ከማንም ቢመጣ ችግር የለብንም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ተሃድሷችሁ እኮ አልሠራም፡፡
- ለምን ተብሎ?
- ይኸው አሁንም የሰው ሕይወት እየጠፋ ነው፡፡
- ምን ማድረግ ይቻላል?
- ትክክለኛ ሪፎርም ማምጣት ነዋ፡፡
- የአሁኑን ሪፎርም ሕዝቡ አልተቀበለውም?
- የአሁኑማ ፌክ ሪፎርም ነው፡፡
- እ. . .
- በአሮጌ አቁማዷ አዲስ ወይን ጠጅ አይቀመጥ ሲባል አልሰሙም?
- ምን ለማለት ፈልገህ ነው?
- በእናንተ አስተሳሰብ ይኼንን ወጣት መምራት አይቻልም፡፡
- ምን?
- አስተሳሰባችሁን መቀየር አለባችሁ፡፡
- ከምን ወደ ምን?
- ከአናሎግ. . .
- እ. . .
- ወደ ዲጂታል!
[ክቡር ሚኒስትር ከአንድ ደላላ ጋር እያወሩ ነው]
- ባለፈው ያን ኪስ ቦታ አገኘህልኝ አይደል?
- ስንት ተፋልጬ እኮ ነው በእጅዎ ያስገባሁልዎት፡፡
- አሁን ምን ላድርግበት ታዲያ?
- አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
- ሳር ላብቅልበት ወይስ ከብት ላርባበት?
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር ያንን ያሰቡትን ፕሮጀክት ይገንቡበት እንጂ?
- ታዲያ ምን ያህል ገንዘብ እንደሚጠይቀኝ ታውቃለህ አይደል?
- ምን ችግር አለው ከካዝናዎ ማውጣት ነዋ?
- ያን ሁላ ብር ከየት አመጣለሁ?
- ታዲያ ፕሮጀክቱን በጨበጣ ነው የሚገነቡት?
- ተበድሬ ነዋ፡፡
- ከማን ነው የሚበደሩት?
- ከባንኮች ነዋ፡፡
- ከተማ ውስጥ የሉም እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- ምን እያልክ ነው?
- የንግድ እንቅስቃሴው እኮ ቆፈን ይዞታል፡፡
- ምንድነው የምትዘባርቀው?
- ባንኮቹ እንኳን ሊያበድሩ እነሱም ይፈልጋሉ፡፡
- ምንድነው የሚፈልጉት?
- የሚያበድራቸው፡፡
- እና ገንዘቡን የሚያበድረኝ አላገኝም?
- ምናልባት አራጣ ይሞክሩ፡፡
- እሱንማ አላደርገውም፡፡
- እንግዲያው በዚህ ወቅት እንኳን የሚበደር ገንዘብ. . .
- እ. . .
- የሚሰረቅም የለም!