Friday, August 19, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  መደማመጥ ጠፍቶ መተራመስ አያዋጣም!

  ‹‹የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል››፣ ‹‹ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባበታል››፣ ‹‹በሽታውን የደበቀ መድኃኒት አይገኝለትም፣ ‹‹ሰዶ ማሳደድ ካማረህ ዶሮህን በቆቅ ለውጥ››፣ ‹‹ውኃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው››፣ ‹‹ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል››፣ ወዘተ. ዕድሜ ጠገብ ምሳሌያዊ አባባሎች ለተለያዩ ጉዳዮች የሚጠቀሱ ጠቃሚ ምክሮችን የያዙ ጽንሰ ሐሳቦች ናቸው፡፡ ከግለሰባዊ የዕለት ተዕለት ስንክሳሮች በመውጣት በግዙፍ አገራዊ ዘርፈ ብዙ ምህዋር ውስጥ ስንቃኛቸው፣ ለሚያጋጥሙ ውስብስብ ችግሮችም ሆነ መልካም አጋሚዎች መሠረታዊ የሆነ ጭብጥ ያስይዛሉ፡፡ በተለይ አገራችን ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ ቆም ብለን ራሳችንን እንድንመረምር ይጋብዙናል፡፡ እንደሚታወቀው ችግሮችን ከሥር መሠረቱ ፈልቅቆ ማወቅ ለመፍትሔ ግማሽ መንገድ ያግዛል፡፡ ዘመኑ ካበረከተው ዕውቀትና ቴክኖሎጂ በተጨማሪ አገር በቀል ዕውቀቶችንና ምስክሮችን ማከል ደግሞ፣ ሰከን ብሎ ራስን ለመመርመርና ወደ ቀልብ ለመመለስ ይረዳል፡፡ በዚህ ጊዜ በዚህች ታሪካዊት አገር ውስጥ ላጋጠሙ በርካታ ችግሮች አንዱና ዋናው ምክንያት አለመደማመጥ ነው፡፡ ፖለቲከኞች እርስ በርስ አይደማመጡም፡፡ መንግሥት ሕዝብን አያዳምጥም፡፡ መደማመጥ በመጥፋቱ ብቻ አገር ትተራመሳለች፣ የሰው ሕይወት እንደ አልባሌ ዕቃ ይቀጠፋል፡፡

  ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ላለፉት 26 ዓመታት በላይ በሥልጣን ላይ ሆኖ ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የገባበትን እሰጥ አገባ አስተካክሎ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ምኅዳር መክፈት አቅቶት፣ አሁን ደግሞ በውስጡ በተፈጠረ ሽኩቻ ምክንያት እየተናጠ ነው፡፡ የኢሕአዴግ አራቱ አባል ድርጅቶች እንደ ወትሮው አንድ ገጽ ላይ መሆን አቅቷቸው በተፈጠረ ውስጣዊ ትንቅንቅ ሳቢያ የበርካታ ዜጎች ሕይወት አልፏ፣ አካል ጎድሏል፣ የአገር አንጡራ ሀብት ወድሟል፡፡ የአራቱ ድርጅቶች ሊቃነ መናብርትም ይህንን አሳዛኝ ድርጊት በማመን የተሻለ ዓውድ ለመፍጠር በቅርቡ ቃል ቢገቡም፣ በተለያዩ ምክንያቶች ግጭቶች እየተቀሰቀሱ ንፁኃን እየሞቱ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ የማይታወቁ ብሔር ተኮር ግጭቶች እየተቀሰቀሱ ወገኖቻችን በማንነታቸው እየተለዩ ጥቃት ሲፈጸምባቸው፣ ንብረታቸው ሲዘረፍና ሲወድም፣ እንዲሁም ከኖሩበት ቀዬ ሲሰደዱ ዓይተናል፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ይፈጸማሉ ተብለው የማይታሰቡና የጨዋውንና የአስተዋዩን ሕዝብ የጋራ እሴቶች የሚንዱ አሳፋሪ ድርጊቶች ብዙዎችን አንገት አስደፍተዋል፡፡ መደማመጥ ሲያቅት ውጤቱ ጥፋት እንደሆነ አለመገንዘብ ለበለጠ ውድቀት ይዳርጋል፡፡ እየሆነ ያለውም ይህ ነው፡፡

  አለመደማመጥ አንድነትን ያናጋል፣ መተማመን ያጠፋል፣ ጥርጣሬን እየፈጠረ ጥላቻን ያስፋፋል፣ አነስተኛ ወይም መለስተኛ ቅራኔን የማይታረቅ ያደርጋል፣ አላስፈላጊ ፉክክር እያጧጧፈ ለሰማላዊና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መደረግ ያለበትን ትግል ያኮላሻል፣ ለታሪካዊ ጠላቶችና ለተላላኪዎቻቸው ምቹ መደላድል ይፈጥራል፣ የአገርንና የሕዝብን ህልውና አደጋ ውስጥ ይከታል፡፡ አለመደማመጥ ሥልጡን ግንኙነቶችን በማወክ አገሪቱን የጉልበተኞች መጫወቻ ያደርጋታል፡፡ ሥርዓተ አልበኝነት ሲነግሥ ደግሞ የሕግ የበላይነት አይኖርም፡፡ በየሥርቻው የሚፈጠሩ ትንንሽ ቡድኖች በጎበዝ አለቆቻቸው አማካይነት መንጎማለል ሲጀምሩ፣ አገር በነውጠኛ ኮርማዎች የሚሸበር በረት ትሆናለች፡፡ እዚህም እዚያም ጊዜ እየጠበቁ የሚፈነዱ ሁከቶችንና ግጭቶችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ መፍታት ያቃተው መነጋገርና መደማመጥ ባለመቻሉ ነው፡፡ አገር ያጋጠማት ፅኑ ደዌ መዳን የሚችለው ትክክለኛው መድኃኒት ሲገኝ ብቻ ነው፡፡ መድኃኒቱን ለማግኘት ደግሞ መግባባት ያስፈልጋል፡፡ መግባባት የሚቻለው በምንም ዓይነት ሁኔታ ሳይወሻሹ እርግጥ እርግጡን መነጋገር ሲቻል ነው፡፡ በሰከነ መንገድ መነጋገር ለመደማመጥ ያግዛል፡፡ በሽታን ደብቆ ያልሆነ ፉክክር ውስጥ መግባት ውጤቱ ተያይዞ መጥፋት ነው፡፡

  ከአገር ህልውና በላይ ምንም ነገር የለም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ ከአገር በላይ ሆኖ አያውቅም፣ አይሆንምም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጣዊ ሕመም ፈውስ የሚያገኘው አገር በትክክለኛው ጎዳና ላይ ስትሆን ብቻ ነው፡፡ ኢሕአዴግ እንደ ግንባር፣ አራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች እንደ ተናጠል ፓርቲ ቆም ብለው ማሰብ ያለባቸው የእነሱ ህልውና ከአገር እንደማይበልጥ ነው፡፡ አገር ከገባችበት ቀውስ እንድትወጣ ከፈለጉ የጀመሩትን አጉል ፉክክርና ልፊያ አቁመው፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚጠቅም የፖለቲካ ምኅዳር እንዲከፈት መሠረት ያኑሩ፡፡ በገቡት ቃል መሠረት አሁንም በእስር ላይ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችንና አባላትን ይፍቱ፡፡ በአገሪቱ ሁለንተናዊ ጉዳዮች ያገባናል የሚሉ ግለሰቦችም ሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰላማዊውና ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ትግል ተሳትፎ እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታዎችን ይፍጠሩ፡፡ ሕዝቡ ላቀረበላቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች በቅደም ተከተል ምላሽ እየሰጡ፣ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ያድርጉ፡፡ በሕዝብ የበላይነትና የሥልጣን ባለቤትነት በማመን ለነፃና ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሚረዱ ተግባራትን ያከናውኑ፡፡ በዚህ መሠረት የውስጥ ችግራቸውን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ይፍቱ፡፡ ይህ ይሆን ዘንድ ደግሞ እርስ በርስ ይደማመጡ፡፡ መደማመጥ መፍትሔ መሆኑን ይመኑ፡፡

  ከኢሕአዴግ ውጪ በተለያዩ ጎራዎች የተሠለፉ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ ስብስቦች ወይም ግለሰቦች ከአጉል አተካራና ከተለመደው አሰልቺ አዙሪት ውስጥ መውጣት አለባቸው፡፡ የዘመናት ወይም የዓመታት ቂምና ጥላቻ እየሰበኩ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የማይጠቅሙ አሉባልታዎችና ትርክቶች ውስጥ ከመዘፈቅ፣ አገሪቱና ሕዝቧ ይህንን አስቸጋሪ ወቅት አልፈው የተሻለ ጊዜ እንዲመጣ ያግዙ፡፡ ግማሽ ክፍለ ዘመን ያስቆጠረው የእልህና የግትርነት ፖለቲካ ያተረፈው እስር፣ እንግልት፣ ሞትና ስደት መሆኑን ከግንዛቤ በማስገባት ለሁሉም እኩል የሆነች ዴሞክራሲያዊት አገር እንድትፈጠር የበኩላቸውን ይወጡ፡፡ አገርን ከውድቀት መታደግና ወደሚፈለገው አቅጣጫ መውሰድ ያኮራል እንጂ አያሳፍርም፡፡ ከኢሕአዴግ ጋር ያላቸው ቅራኔ የማይታረቅ ነው ቢሉ እንኳ ቅድሚያ ለአገር መስጠት አለባቸው፡፡ እግረ መንገዱንም በዚህ በሠለጠነ ዘመን የማይታረቅ ምንም ነገር አለመኖሩን ይወቁ፡፡ ይህ ወቅት ከጥላቻ በመውጣት ሰከን ማለት ይጠይቃል፡፡ በዕድሜ የበሰሉት ወጣቶችን እያረጋጉ፣ በትምህርት የገፉት ወጣቶችን እየገሩ አገርንና ሕዝብን መታደግ ሲገባ ለዕልቂትና ለውድመት የሚዳርጉ ቀረርቶዎችና ሽለላዎች ማሰማት እርባና የለውም፡፡ ይህ ዓይነቱ ጊዜ ያለፈበት ድርጊት አገርን ሲያወድምና ሕዝብን መከራ ውስጥ ሲከት ነው የሚታወቀው፡፡ ከሶማሊያ እስከ ሶሪያ ምን እንደተከናወነ ማስታወስ ይጠቅማል፡፡ ስለዚህ ለመነጋገርና ለመደማመጥ ዝግጁ መሆን ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው አማራጭ አይሠራም፡፡ ተሞክሮም ውጤት አላመጣም፡፡

  የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላማዊ ነው፡፡ ከምንም ነገር በላይ አጥብቆ የሚፈልገው ልጆቹ በሰላም ወጥተው እንዲገቡለት ነው፡፡ ትምህርት መማር የሚቻለው ሰላም ሲኖር ነው፡፡ ማረስ፣ መነገድ፣ መጓዝ፣ መውጣትና መውረድ የሚቻለው አገር ሰላም ሲኖራት ብቻ ነው፡፡ ይህ ጨዋና አስተዋይ ሕዝብ ውስጥ ግጭት በመቀስቀስ ዕልቂትና ውድመት መፈጸም ጤነኝነት አይደለም፡፡ የመላው ሕዝባችንን ታሪካዊ የጋራ እሴቶችን የሚጋፉ አሳዛኝ ድርጊቶች በፍጥነት ቆመው ዴሞክራሲ ይስፈን፡፡ ሕዝብ በነፃነት ይኑር፡፡ በመረጠው መንግሥት ይተዳደር፡፡ ለጠብ፣ ለግጭትና ለጥፋት የሚዳርጉ አላስፈላጊ ድርጊቶች ይወገዱ፡፡ ለሕዝብ ፈቃድ መገዛት ሲቻል ሰላም፣ ዴሞክራሲና ብልፅግና ዕውን ይሆናሉ፡፡ ልማቱ የጋራ ሲሆን ውድመት አይኖርም፡፡ እርስ በርስ በብሔር መጋጨት አይሞከርም፡፡ ታሪካዊ ጠላቶችና ተላላኪዎቻቸው መግቢያ ቀዳዳ አያገኙም፡፡ በሞኝነት በሚፈጸሙ ድርጊቶች ሳቢያ ሕይወት አይጠፋም፡፡ የአገር ሀብት አይወድምም፡፡ በመከባበርና በመተሳሰብ አገሪቱንና ሕዝቡን ታላቅ ደረጃ ላይ ማድረስ ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያዊነት ይለመልማል፡፡ ያንዣበበው የሥጋት ደመና ይገፈፋል፡፡ ዕድሜ ጠገብ ምሳሌዎቻችንን ምርኩዝ በማድረግ መደጋገፍ ይቻላል፡፡ ይህ ይሆን ዘንድ ግን ለመደማመጥ ዕድል ይሰጥ፡፡ መደማመጥ ጠፍቶ መተራመስ አያዋጣም!

   

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...

  በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል የተጀመረው የድርድር ሒደት አሳታፊ እንዲሆን ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት፣  በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት...

  አዲስ አበባና ኦሮሚያ ወሰን ለማካለል ተስማሙ

  ኮዬ ፈጬ፣ ቱሉዲምቱ፣ ጀሞ ቁጥር 2 ወደ ኦሮሚያ ለቡ፣ ፉሪና...

  ከጉምሩክ ውጪ ፍተሻ ተፈቅዶላቸው የነበሩ አስመጪዎች ገደብ ተጣለባቸው

  የጉምሩክ ኮሚሽን ወደ አገር ውስጥ የሚገቡና የሚወጡ ዕቃዎችን ከጉምሩክ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  መንግስት 8 የስኳር ፋብሪካዎችን ለጨረታ አቀረበ

  መንግስት ስኳር ኢንተርፕራይዞችን ወደግል ለማዛወር በወጣው ጨረታ ባለሐብቶች እንዲሳተፉ...

  የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ኃይሎች ላይ ጥቃት አልፈጸምኩም አለ

  የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ...

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ኢትዮጵያን የአፍሪካ ጭራ አናድርጋት!

  ኢትዮጵያ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በግብርና፣ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በቴክኖሎጂና በመሳሰሉት የልማት መስኮች አንገቷን ቀና የምታደርግባቸው እንቅስቃሴዎች እየታዩ መሆናቸው ያበረታታል፡፡ ሰሞኑን በኢትዮጵያ የነፃ ንግድ ቀጣና...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁና የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጨው ሁለተኛው ተርባይን ሥራ መጀመሩ፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የፈጠረው ደስታ ቃላት ከሚገልጹት...

  የሥጋት ደመና ተወግዶ ሰላም ይስፈን!

  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደቡብ የአገሪቱ ክፍል ክልል ለመሆን የፈለጉ የተለያዩ ዞኖች እየተሰባሰቡ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ እያቀረቡ ናቸው፡፡ ለብቻችን ክልል መሆን አለብን የሚሉ ዞኖችም...