Sunday, August 14, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናበእነ አቶ መላኩ ፈንታ መዝገብ በሙስና የተከሰሱት አቶ ከተማ ከበደ ለፍርድ ተቀጠሩ

  በእነ አቶ መላኩ ፈንታ መዝገብ በሙስና የተከሰሱት አቶ ከተማ ከበደ ለፍርድ ተቀጠሩ

  ቀን:

  በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል በመዝገብ ቁጥር 131452 ከእነ አቶ መላኩ ፈንታ ጋር በ2006 ዓ.ም. ክስ ተመሥርቶባቸው ሲከራከሩ የከረሙት፣ የኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከፍተኛ ባለድርሻና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ከተማ ከበደ ለፍርድ ተቀጠሩ፡፡

  ድርጅቱና ሥራ አስኪያጁ ላለፉት አምስት ዓመታት ሲያደርጉት የነበረው ክርክር የተጠናቀቀው፣ ዓርብ ጥር 25 ቀን 2010 ዓ.ም ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ተከሳሾቹ በመከላከያ ምስክርነት ላቀረቧቸው ምስክር መስቀለኛ ጥያቄ አቅርቦ ካጠናቀቀ በኋላ ነው፡፡

  ዓቃቤ ሕግ ለምስክሩ ባቀረበላቸው መስቀለኛ ጥያቄ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በተቋቋመበት አዋጅ ቁጥር 669/2002 አንቀጽ 5(5) እና 18 መሠረት የመንግሥት፣ የሕዝባዊ ድርጅቶችንና የግል ድርጅቶችን የመመርመር ሥልጣን እንደተሰጠው ስለማወቃቸው ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ምስክሩ አቶ አማረ ላቀው በሰጡት ምላሽ እንዳስረዱት፣ ዋና ኦዲተር መመርመር የሚችለው የመንግሥትን ገቢ፣ ፕሮጀክቶችንና በጀት ብቻ ነው፡፡ ግብርና ታክስን የመመርመር ሥልጣን እንዳልተሰጠው ገልጸዋል፡፡ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ በውጭ አገር በተደረገ የንግድ ትርዒት ላይ ተገቢ ያልሆነ ወጪ ስለማውጣታቸውና ለምን በወጪ እንዳስያዙ ስለማወቃቸው ምስክሩ ተጠይቀው፣ ሥራ አስኪያጁ ለንግድ ትርዒት ወደ ጀርመን በሄዱበት ወቅት ለጉዞና ለውሎ አበል ያወጧቸው ወጪዎች በሰነድ የተደገፉ መሆናቸውን አስረድተው፣ ሰነዶቹም ለውስጥና ለውጭ ኦዲተሮች ቀርበው ተቀባይነት ያገኙ መሆኑን አክለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንም እንደተቀበላቸው ጠቁመዋል፡፡ የመከላከያ ምስክሩ ታኅሳስ 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ሲመሰክሩ ይዘውት ስለቀረቡት ሰነድ ሕገወጥነት ዓቃቤ ሕግ ሲጠይቃቸው፣ በተደናገረ ሁኔታ ምላሽ የሰጡ ቢሆንም፣ በድጋሚ ጥር 25 ቀን 2010 ዓ.ም. በሰጡት ምስክርነት፣ ይዘውት የነበረው ሰነድ በአዲሱ አዋጅ መሸጋገሪያ አንቀጽ ላይ የቀድሞው አዋጅ ተፈጻሚ እንደሚሆን በመደንገጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

  መነሻ የሆኑትን የገቢዎችና ጉምሩክ መመርያና ማንዋሎች በሚመለከት አስረድተው፣ በኦዲተር ጄነራል ተቋም የተሰጠው አስተያየት ከባለሥልጣኑ መመርያና ማኑዋል ጋር የማይጣጣም መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ኬኬ ድርጅት ከውጭ ያስገባቸውንና ቀረጥ ያልተከፈለባቸውን ዕቃዎች ለድርጅቱ ሠራተኞች ስለመስጠቱ እንደሚያውቁ ዓቃቤ ሕግ ለምስክሩ ላቀረበላቸው ጥያቄ፣ ድርጅቱ በጉድለት ዋስትና ከውጭ የገቡ ዕቃዎችን ለድርጅቱ ደንበኞች በገባው ኃላፊነት መሠረት በነፃ የሰጠ መሆኑን፣ የተተኩና የተበላሹ ንብረቶችን መጋዘን ድረስ ሄደው እንዳላዩና ማየትም እንደማይጠበቅባቸው አስረድተዋል፡፡ ዋና ኦዲተርም በመጋዘን ንብረቶች እንዳልተገኙ አስተያየት አለመስጠቱንም አክለዋል፡፡

  ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ለምርመራው ከሦስተኛ ወገን ሰነዶችን ማግኘቱን ቢገልጽም፣ ከባንክ የወለድን መጠን የሚገልጽ ማስረጃ እንጂ ግብር ከፋዩ የሰወረውና የደበቀው ሰነድ ማግኘቱን አለመግለጹን ጠቁመው፣ ከሦስተኛ ወገን ተገኘ የተባለው ሰነድ የተሳሳተ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

  የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ሙስና ተፈጽሟል ብሎ ክስ ከመሠረተ በኋላ፣ የጄነራል ኦዲተርን የምርመራ ሥራ መጠየቁም ሕጋዊ አለመሆኑን አክለዋል፡፡ ምክንያታቸው ሲያስረዱ ደግሞ ራሱ ፀረ ሙስና ኮሚሽን የመመርመር ሥልጣን መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ጉዳዩ የግብርና ታክስ በመሆኑ፣ ዋና ኦዲተር ባልተሰጠው ሥልጣን መመርመሩ አግባብ አለመሆኑንም ገልጸዋል፡፡

  የድርጅቱ ባለድርሻዎች ትርፍ ሳይከፋፈሉ ብድር መውሰዳቸው ሆን ተብሎ ታክስና ግብር ላለመክፈል ታስቦ መሆኑን ስለማወቃቸው የተጠየቁት ምስክሩ፣ ከኩባንያው ትርፍ ላይ ብድር መውሰዳቸው ጉዳት እንደማያስከትል አስረድተዋል፡፡ የትርፍ ክፍፍል አለመደረጉ ለኩባንያው ካፒታል ዕድገት የሚውልና የመንግሥትን ገቢ የሚያሳድግ በመሆኑ፣ የሚያደርሰው ጉዳት እንደሌለ አስረድተዋል፡፡ በጀርመን አገር ተደርጓል ስለተባለው የንግድ ትርዒት ማረጋገጫ እንዳላቸው ከዓቃቤ ሕግ ጥያቄ የቀረበላቸው ምስክሩ፣ ለኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከቀረቡ ሰነዶች ማረጋገጣቸውን አስረድተዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ሌላው ለምስክሩ ያቀረበው ጥያቄ ታኅሳስ 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ‹‹ዋና ኦዲተር ሥልጣን የለውም›› ብለው  የሰጡት ምስክርነት ሥነ ምግባር የጎደለው የምስክርነት ቃል መሆኑን ገልጾ፣ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ደብዳቤ እንደ ጻፈ ሲናገሩ፣ የኬኬና የሥራ አስኪያጁ ጠበቆች ተቃውሞ አቅርበዋል፡፡

  ጠበቆቹ ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት ተቃውሞ፣ ምስክርነቱ ሳይጠናቀቅ የሌላን አካል ጥያቄ መጠየቅ እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡ ጥያቄው መነሳቱ በራሱ ምስክሩን የሚያሸማቅቅ፣ የሚያስፈራራና ራሳቸውን እንዲወነጅሉ የሚያስገድድ መሆኑንም አክለዋል፡፡ ዓቃቤ ሕጉ በምስክርነት ባቀረቧቸው አንድ ምስክር ላይ ጠበቆች፣ ‹‹ጉትጎታ›› የሚል ቃል ተጠቅመው ‹‹ምስክሬን ተዳፍረውብኛል፤›› በማለት ያቀረቡት ጥያቄ በፍርድ ቤቱ ተቀባይነት ማግኘቱንም አስታውሰዋል፡፡ በእነሱ ደንበኞች የመከላከያ ምስክር ላይ ዓቃቤ ሕጉ ‹‹የሥነ ምግባር ግድፈት ፈጽመዋል፤›› ማለት እንደማይችሉ ጠበቆቹ አቤቱታ አሰምተዋል፡፡

  ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ በሰጠው ብይን እንደገለጸው፣ አንድ ምስክር ለፍርድ ቤት የሚሰጠው ቃል በራሱ በፍርድ ቤት እንጂ በሌላ አካል ተጠያቂነትን አያስከትልም፡፡ ምስክሩ ራሳቸውን እንዲወነጅሉ የቀረበው ጥያቄ ተገቢነት እንደሌለው ገልጾ፣ የዓቃቤ ሕግን ጥያቄ ውድቅ አድርጎታል፡፡

  በመጨረሻም የመከላከያ ምስክሮች ተሰምተው በመጠናቀቃቸው ተከሳሾችና ዓቃቤ ሕግ፣ የክርክር ማቆሚያቸውን እስከ የካቲት 30 ቀን 2010 ዓ.ም. እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ ፍርድ ለመስጠት ለመጋቢት 17 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡  

   

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...