[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸው ጋ ደወሉ]
- ደስ ብሎኛል፤ እንኳን ደስ አለዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ተገኘ ደግሞ?
- አሸነፍን እኮ፡፡
- እናንተ ማን ናችሁ?
- ሰማያዊዎች፡፡
- ምን?
- እኛ ሰማያዊዎች አሸነፍን፡፡
- ምርጫው ገና አይደል እንዴ?
- አይደለም አይደለም፡፡
- ደግሞ የኢሕአዴግ ባርኔጣ አድርገህ ለካ ሰማያዊ ነበርክልኝ?
- ምን አሉኝ?
- ሰማያዊ ፓርቲ ገባህ?
- እኔ አልገባሁም፤ እርስዎ ግን አልገባዎትም፡፡
- ምኑ ነው ያልገባኝ?
- የማወራው ነገር፡፡
- እኮ ምንድነው እያወራህ ያለኸው?
- ቼልሲ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ አነሳው፡፡
- ታዲያ ሰማያዊዎቹ አሸነፍን ለምን አልክ?
- የቼልሲ ሌላኛው ስሙ ነዋ፡፡
- ምን አልከኝ?
- የቼልሲ ክለብ ሌላኛው ስሙ እኮ ሰማያዊዎቹ ነው፡፡ እርስዎም ስለሚደግፉት ነው እንኳን ደስ አለዎት ያልኩዎት፡፡
- እንኳን ስሙን አወቅኩት እንጂ፣ ከዛሬ ጀምሮ አልደግፈውም፡፡
- ለምን?
- ዓይኔ እያየ ሰማያዊን ልደግፍ?
- እነሱ እኮ አሸናፊዎች ናቸው?
- ቢሆኑም ከዚህ በኋላ የማንቸስተር ደጋፊ ነኝ፡፡
- የማንቸስተር ዩናይትድ?
- አዎን፣ የእነሱ ሌላኛው ስም ማን ነበር?
- ቀያዮቹ ሰይጣኖች፡፡
- በቃ የእነሱ ነኝ፡፡
- ለስማቸው ብለው ከሆነ ከእርስዎ ጋር የሚሄደው የአርሰናል ስም ነው፡፡
- የእነሱ ስም ምንድነው?
- መድፈኞቹ፡፡
- እንዲያውም የመድፈኞቹ ደጋፊ ነኝ፡፡
- አሁን ከግብርዎት ጋር የሚሄድ ስም መረጡ፡፡
- አንተ ወሬኛ አሁን በአፋጣኝ ቢሮ ና፡፡
- እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
[አማካሪያቸው ቢሯቸው ገባ]
- ምን ዓይነት ሸሚዝ ነው ያደረግከው?
- ባለፈው ከጣሊያን እርስዎ ነዎት እኮ ያመጡልኝ፡፡
- እኮ ቀለሙ ምን ዓይነት ነው?
- እኔ እንጃ ክቡር ሚኒስትር፣ ምን ዓይነት ነው የሚባለው?
- ውኃ ሰማያዊ እኮ ነው፡፡
- ወደዱት ክቡር ሚኒስትር?
- እኔ ሰማያዊን ልወድ?
- ብዙ ሰው ግን እንደሚወደው ነግሮኛል፡፡
- ሰማያዊን?
- አዎ ሰማያዊን?
- አንተ ይኼ በሽታ ቆይቶብሃል ማለት ነው?
- የቱ በሽታ?
- የሰማያዊ በሽታ፡፡
- ኧረ ክቡር ሚኒስትር፣ እኔ እኮ ስለሸሚዜ ነው እያወራሁ ያለሁት፡፡
- ለማንኛውም ያንን ሪፖርት ምን አደረግከው?
- ክቡር ሚኒስትር እያጠናቀኩት ስለሆነ ባፋጣኝ ጨርሼ አመጣልዎታለሁ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊያቸው ጋር ሄዱ]
- ምን እያደረግሽ ነው አንቺ?
- ኢንተርኔት እየተጠቀምኩ፡፡
- እኮ የምን ዌብ ሳይት ነው ይኼ?
- ፌስቡክ ነው፡፡
- ቀለሙን ዓይተሽዋል?
- አዎን ክቡር ሚኒስትር፣ ዓይን ይስባል አይደል?
- ዓይንሽ ይጥፋ፡፡
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- ከዛሬ ጅምሮ ፌስቡክ ስትጠቀሚ እንዳላይሽ፡፡
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር፣ ከዘመዶቼ ጋር የምንገናኝበት እኮ ነው?
- እንዳትጠቀሚ አልኩሽ፣ እንዳትጠቀሚ፡፡
- ኧረ እባክዎት ክቡር ሚኒስትር?
- መጠቀም የምትችይው አንድ ነገር ካደረግሽ ብቻ ነው፡፡
- ምን ካደረግኩ?
- ቀለሙን መቀየር ከቻልሽ?
- እሱንማ እኔ መቀየር አልችልም፡፡
- በይ ቶሎ ዝጊው፡፡
[ጸሐፊያቸው የፌስቡክ ድረ ገጹን ስተዘጋው፣ የትዊተር ገጽ ኮምፒዩተሯ ላይ መጣ]
- ይኼ ደግሞ ምንድነው?
- ቲዊተር፡፡
- እሱም ቀለሙ ሰማያዊ ነው?
- አዎን ክቡር ሚኒስትር፣ ምን ችግር አለው?
- ከባድ ችግር አለው፡፡
- የምን ችግር?
- በመንግሥት ኮምፒዩተር ሰማያዊ ድረ ገጽ መጠቀም አትችይም፡፡
- ታዲያ ምን ልጠቀም?
- ቫይበር፡፡
- ለምን?
- እሱ ወይን ጠጅ ነዋ፡፡
- ወይ ጣጣ፡፡
- ምን ዓይነት ሻርፕ ነው ደግሞ ያደረግሽው?
- ባለፈው እርስዎ ከውጭ ያመጡልኝ ነው፡፡
- ቀለሙን ነው የጠየቅኩሽ?
- ሰማያዊ ነዋ፡፡
- እኔ ጠፋሁ!
- ሰማያዊ እኮ ተወዳጅ ነው፡፡
- ምን አልሽ አንቺ?
- ሰማያዊ ተወዳጅ ቀለም ነው፡፡
- ተወዳጅማ አይደለም፡፡
- ኧረ ክቡር ሚኒስትር በየቡቲኩና በየልብስ መሸጫ ቤቶች እኮ ሰማያዊ ልብሶች ተመራጭ ናቸው፡፡
- ቡቲኮቹ የሚሸጡት ሰማያዊ ልብስ ነው?
- አዎና፡፡
- ኪራይ ሰብሳቢ ቡቲኮች ናቸው ማለት ነው?
- ኪራይ ሰብሳቢዎች ስለሆኑ ሳይሆን፣ ሰማያዊ ተመራጭ ቀለም ስለሆነ ነው፡፡
- ሰማያዊማ የኪራይ ሰብሳቢዎች ቀለም ነው፡፡
- ዛሬ ተነስቶቦታል፡፡
- የቢሮ ወንበሮችም ሰማያዊ ናቸው?
- ሰማያዊ ያልሆነ ምን ነገር አለ?
- በይ በአፋጣኝ አሁኑኑ እንዲቀየሩ፡፡
- በምን ዓይነት ቀለም?
- በወይን ጠጅ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ውኃ ጠይቀው ስለነበር ተላላኪያቸው ይዛላቸው ገባች]
- ምንድነው አንቺ?
- ውኃ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እኮ ምን ዓይነት ውኃ?
- የታሸገ ውኃ፡፡
- ቀለሙን ነው የጠየቅኩሽ፡፡
- እሱማ ሰማያዊ ነው፡፡
- ሌላ ቀለም የለም?
- ሰማያዊ ያልሆነ ውኃ የለም፡፡
- ይኼን መልሰሽ የቧንቧ ውኃ አምጪልኝ፡፡
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- እንዲያውም ከዛሬ ጀምሮ ምንም ውኃ እንዳይገዛ፣ ሁላችንም የቧንቧ ነው የምንጠጣው፡፡
- የቧንቧ ውኃ እኮ ጥሩ አይደለም፣ በዚያ ላይ ለእንግዶች ምን ይቀርባል?
- እኮ ምን አማራጭ አለን?
- ምናልባት ወተት?
- እንዲያውም ከዛሬ ጀምሮ ለእናንተ የቧንቧ ውኃ ጠጡ፤ ለእንግዳ ደግሞ ወተት ይገዛ፡፡
- የወተቱን ወጪ ግን እንችለዋለን?
- በቃ ላም ይገዛ፡፡
[የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ያዘዙትን ሪፖርት ይዞ ቢሯቸው ገባ]
- ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር ፕሪንተሬ ስለተበላሸብኝ በዚያ ላይም መብራት ስለጠፋ ሪፖርቱን በእጄ ጽፌ መጥቻለሁ፡፡ እንኩ ይመልከቱት፡፡
- ይኼንማ አልቀበልም፡፡
- ለምን ክቡር ሚኒስትር?
- በምንድነው የተጻፈው?
- በእስክሪብቶ አልኩዎት እኮ፡፡
- እኮ በምን ዓይነት እስክሪብቶ?
- በሰማያዊ ነዋ፡፡
- በሰማያዊ የተጻፈ ነገር አልቀበልም፡፡
- ታዲያ በምን ልጻፈው?
- ስትፈልግ በአረንጓዴ፣ ስትፈልግ በቢጫ፣ ስትፈልግ በቀይ ጻፈው፡፡
- ሪፖርቱን በባንዲራ ቀለም ልጻፈው?
- ብቻ በመረጥከው ቀለም ጻፈው፡፡
- የእኔማ ምርጫ ሰማያዊ ነው፡፡
- ሰማያዊ የእኛ ቀለም አይደለም፡፡
- ታዲያ በቢጫ ቀለም ልጻፈው?
- ቢጫን ለምን መረጥከው?
- የፓርቲያችን ቀለም ነዋ፡፡
- እንዴት ሆኖ?
- ያው ምልክታችን ንብ ነው፡፡ ንብ ደግሞ ማር ታመርታለች፡፡ የማር ቀለም ደግሞ ቢጫ ነው፡፡
- በቃ በቢጫ ጻፈው፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ወዲያው የዕቃ ግዢ ኃላፊው ጋ ደወሉ]
- አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በአስቸኳይ ቢሮ ቢጫ እስክሪብቶ ይዘህ ና፡፡
- ኧረ ቢጫ የሚባል እስክሪብቶ የለም፡፡
- አሁኑኑ ይገዛ፡፡
- ገበያ ላይ እንዲህ ዓይነት ቀለም የለም፡፡
- ይታዘዝ፡፡
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር ባለፈው ሳምንት እኮ ሚሊዮኖች አውጥተን ሰማያዊ እስክሪብቶ ነው የገዛነው?
- እነሱ ተቃጥለው ቢጫ ይታዘዝ፡፡
- በቢጫ የሚጻፍ ጽሑፍ እኮ አይነበብም፡፡
- ታዲያ በምን የሚጻፍ ነው የሚነበበው?
- በሰማያዊ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ስልኩን ዘግተው ከአማካሪያቸው ጋር ወሬያቸውን ቀጠሉ]
- በቢጫ የሚጻፍ አይነበብም እንዴ?
- በቢጫ የሚጻፍማ በደንብ አይነበብም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ታዲያ በምን የሚጻፍ ነው በደንብ የሚነበበው?
- በሰማያዊ ነዋ፡፡
- በቀይ መጻፍ አንችልም?
- ቀይ ለማረም ነው የሚመቸው፡፡
- በቢጫ የተጻፈ በቀይ ይታረማል?
- በቢጫ የተጻፈማ በቀይም፣ በጥቁርም፣ በሰማያዊም ይታረማል፡፡
- እኔ በሕይወት እያለሁማ፣ በቢጫ የተጻፈ በሰማያዊ አይታረምም፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኪናቸው ሲሄዱ የመሥሪያ ቤቱን አትክልተኛ ተመለከቱትና ጠጋ ብለው ማውራት ጀመሩ]
- ምንድነው የለበስከው አንተ?
- ቱታ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ዓይነት ቱታ ነው የለበስከው?
- ጥቁር ሰማያዊ፡፡
- ማን ነው የገዛልህ?
- መሥሪያ ቤታችን ነዋ፡፡
- በል ቶሎ አውልቅና ሌላ ልበስ፡፡
- ሌላ ምን ዓይነት?
- ቢጫ፡፡
- ሰማያዊ ግን አሪፍ ነው፡፡
- ለምን?
- ቆሻሻ አይዝም፡፡
- ቢጫስ?
- ቢጫማ ወዲያው ብዙ ቆሻሻ ይሸከማል፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ከሾፌራቸው ጋር ወደ ስብሰባ እየሄዱ ነው]
- ክቡር ሚኒስትር ይኼ ጥርት ያለ ሰማያዊ ሰማይ ደስ አይልም?
- ምን ዓይነት ሰማይ አልከኝ?
- ሰማያዊ፡፡
- እኔ ደመናማ ሰማይ ነው ደስ የሚለኝ፡፡
- እንዴ ከቡር ሚኒስትር ፀሐይ በጣም ስለሚወዱ አይደል እንዴ የመጀመሪያ ልጅዎትን ፀሐይነሽ ያልዋት?
- አሁን ሐሳቤን ቀይሬ ደመናና ዝናብ መውደድ ጀምሬያለሁ፡፡
- ስለዚህ ቀጣዩን ልጅዎትን ዝናቡ ነው የሚሉት ማለት ነው?
- ከዚህ በኋላ ከወለድኩ እንደዚያ ማለቴ አይቀርም፡፡
- ደመናማ ነገር ግን ከጨለማ ጋር ስለሚያያዝ ብዙ አይወደድም፡፡
- ምን አልከኝ?
- ሰማያዊ ሰማይ ከብሩህ ተስፋ ጋር ስለሚያያዝ ተወዳጅና ተመራጭ ነው፡፡
- ተወዳጅና ተመራጭ ማን ነው?
- ሰማያዊ ሰማይ ነዋ፡፡
[የክቡር ሚኒስትሩ ሾፌር የተከለከለ ቦታ ላይ ስለቆመ የትራፊክ ፖሊስ መጣ]
- የተከለከለ ቦታ ላይ ነው የቆማችሁት፡፡
- ምን አልከኝ?
- ውይ ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር እርስዎ ነዎት እንዴ?
- ደግሞ ምን ዓይነት ልብስ ነው የለበስከው?
- የትራፊክ የደንብ ልብስ ነዋ፡፡
- ቀለሙ ምን ዓይነት ነው ያልኩህ?
- ውኃ ሰማያዊና ጥቁር ሰማያዊ ነዋ፡፡
- ከሰማያዊ ውጪ ሌላ ነገር አታውቁም እንዴ?
- ሰማያዊ ምን ችግር አለው?
- በመንግሥት በጀት ሰማያዊ ነገር መገዛት የለበትም፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ቤታቸው ሊገቡ ሲሉ በራቸው ላይ የቆመውን ፌዴራል ፖሊስ ተመለከቱት]
- ና እስቲ አንተ?
- አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ዓይነት ልብስ ነው ያደረከው?
- የፖሊስ የደንብ ልብስ ነዋ፡፡
- ቀለሙን ነው የጠየቅኩህ?
- ሰማያዊ፡፡
- አሁኑኑ ገብተህ ቀይረው፡፡
- ለምን ክቡር ሚኒስትር?
- ማንም የመንግሥት ሠራተኛ ሰማያዊ ነገር መልበስ አይችልም፡፡
- እርስዎ የመንግሥት ሠራተኛ አይደሉም እንዴ?
- ነኝ እንጂ፡፡
- ያደረጉት ከረባት ምን ዓይነት ነው?
- ሰማያዊ!