Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ኪንና ባህልየእውነትና ግነት ትግል በሲትኮም

  የእውነትና ግነት ትግል በሲትኮም

  ቀን:

  ዘሩ ሞላ (ጥላሁን ጉግሳ) እጅግ ያስደሰተውን ዜና ለቤተሰቡ ያወራል፡፡ ሰዎች ምግብ እንዲቀንሱ ጨጓራቸውን ማስጠበብ የሚቻልበት ቴክኖሎጂ መፈጠሩን ሰምቶ ነበር በሐሴት የተሞላው፡፡ ገንዘብ ቆጣቢው አባወራ የቤቱ ሠራተኛ ትርፌ (ሰብለ ተፈራ) ‹‹በልክ እንድትበላ ጨጓራዋ ይውጣ፣ ይጠበብ ወይስ ይጠር?›› የሚል ስብሰባ ይጠራል፡፡ አማወራዋ አዛለች (ማክዳ ኃይሌ)፣ ልጆቻቸው ርስቴ (ሜላት ተስፋዬ)፣ በዛብህ (ፈቃዱ ፋሲል)፣ ይበቃል (አሸናፊ ማህሌት)፣ ማፊ (ገሊላ ርእሶም)፣  ጥበቃው እከ (ንብረት ገላው) እና ሠራተኛዋ ሻሼ (ንፁህ ኃይሌ) ይወያያሉ፡፡

  በአንድ ኮንዶሚኒየም ጊቢ የሚኖሩት ጎረቤታሞች ሀዊ (ማህሌት ሹመቴ)፣ ቤቢ (ዘሪሁን አስማማው) እና ናትናኤል (ዮሴፍ ፈቃደ)፣ አቡዬ (ኤልሳቤጥ ጌታቸው) አዲስ በከፈተችው ካፌ ውስጥ ተሰባስበው የሳራ (ኤደን ሽመልስ) የወንድ ጓደኛ ለልደቷ ምን ሊሰጣት እንደሚችል ይገምታሉ፡፡ ፋብሪካ፣ ቤት ወይስ መኪና ይሆን እያሉ ያሰላስላሉ፡፡ የወንድ ጓደኛዋ ስጦታ ግን ታናሽ እህቱ ለአንድ ቀን አብራት እንድትውል ማድረግ ነበር፡፡ ብልኋ ታዳጊ ሳራን መዝና ‹‹ስልቹ፣ ውሸታም፣ ሥራ ፈትና በራስዋ የማትተማመን›› በማለት ትገልጻታለች፡፡ ጎረቤታሞቹን በዓይነ ቁራኛ የሚከታተላቸው ምንዳዬ (ደረጄ ኃይሌ) ሳራ ታዳጊዋ ከታዘበችው የከፋ ባህሪ እንዳላት ይናገራል፡፡

  የተቀነጨቡት በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት (ኢቢሲ)ና የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ (ኢቢኤኮ) ላይ ከሚተላለፉት ‹‹ጎረቤታሞቹ›› እና ‹‹ቤቶች›› ሲትኮሞች ነው፡፡ ለጥቂት ጊዜ በቴሌቪዥን ተላልፈው የተቋረጡ ሲትኮሞች ቢኖሩም ሁለቱ እስካሁን ዘልቀዋል፡፡ በሲችዌሽን ኮሜዲ (ሲትኮም) ዘርፍ የሚጠቀሱት ‹‹ቤቶች››ና ‹‹ጎረቤታሞቹ›› የሚያጠነጥኑባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ምን ያህል የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያንፀባርቃሉ? በተመልካች ዘንድ የማዝናናት ወይም የማስተማር ዓላማቸውን በማሳካት ረገድ እንዴት ይመዘናሉ? የሚሉ ጥያቄዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡

  እንደባለሙያዎች ገለጻ፣ ሲትኮም ወጣ ያለ ማንነት ያላቸው ገፀ ባህሪያት በሚገጥሟቸው ሁናቴዎች አስቂኝ ድባብ ይፈጥራል፡፡ ገፀ ባህሪያቱ ማንነታቸውን ሳይለቁ በየጊዜው የተለያየ ሁኔታ ውስጥ ይገባሉ፡፡ የሲትኮሙን ታሪክ ፍሰት ተከትሎ በአንድ ክፍል የሚነሱ ጉዳዮች በዛው ክፍል ተደምድመው፣ በሌላ ክፍል ገፀ ባህሪያቱ ወደ አዲስ ሁናቴ ይሸጋገራሉ፡፡ በሁኔታዎች እያሳቁ ልዩ ልዩ ጉዳዮችን በመዳሰስም ዘርፉ ይጠቀሳል፡፡

  ስሜ ይቅር ብሎ ሐሳቡን ያካፈለን ወጣት በግል ተቋም ፊልም ሥራ ይማራል፡፡ በሲትኮሞቹ ከአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ኑሮ በመጻረር ጥያቄ የሚያስነሱ ገፀ ባህሪያት አሉ ይላል፡፡ እንቅልፍ እየጣለው በአሠሪው የሚቀሰቀስ ዘበኛ ወይም ከቤተሰቦቻቸው ጋር ያለመጠን ተቀራርበው የሚወያዩ ወጣቶች የታማኝነት ጥያቄ ያስነሳሉ፡፡ ቢሆንም እንደ ጥበብ ሥራ በዕውን የሚታየውን ብቻ ከማንፀባረቅ በተቃራኒው ‹‹እንዲህ ቢሆንስ›› የሚል ድባብ መፍጠራቸው መልካም ነው ይላል፡፡

  ‹‹ቤቶች›› ለሥራቸው ተገቢ ቦታ የማይሰጣቸው የቤት ሠራተኞች እንደማንኛውም ሰው ሐዘንና ደስታ የሚፈራረቅባቸው፣ ሰዋዊ ፍላጎት ያላቸው እንደሆኑ ያሳያል፡፡ ለዚህ ምሳሌ የሚጠቅሰው ትርፌና ሻሼ እከን በፍቅር ለማማለል የሚያደርጉትን ጥረት ነው፡፡ በሌላ በኩል ወጣቶች የሚቀረፁበት መንገድ ሊታሰብበት ይገባል ይላል፡፡ በሁለቱም ሲትኮሞች ኃላፊነት የመጥላትና ነገሮችን ያለማገናዘብ ባህሪ ያላቸው ወጣቶች መጉላታቸውን ይተቻል፡፡ ‹‹የእኛ አገር ቀለም ያላቸው ሲትኮሞች በብዛት መሠራት አለባቸው፤ አሁን ያሉት በመጠኑም ቢሆን ከማሳቅ በተጨማሪ እያንዳንዱ ሰው ራሱን እንዲፈትሽ የሚያሳስቡ ናቸው፤›› ይላል፡፡

  ጥላሁን ጉግሳ የ‹‹ቤቶች›› መሪ ተዋናይና ፕሮዲውሰር ነው፡፡ ሲትኮሙ አሁን ባለው ቅርፅ አሰናድቶ ለመቅረብ ዓመታት እንደወሰደ ይናገራል፡፡ የ‹‹ቤቶች›› 100ኛ ክፍል በቅርቡ አየር ላይ ይውላል፡፡ መቼቱን በአንድ መኖሪያ ቤት ያደረገው ‹‹ቤቶች››› አራት ልጆች፣ ሁለት ሠራተኞችና አንድ ጥበቃ ባለው ቤተሰብ ያተኩራል፡፡ ገፀ ባህሪያቱ በተናጠል ወይም በጋራ የሚገጥማቸውን ያስቃኛል፡፡ ጥላሁን እንደሚለው፣ ለሲትኮሙ ግብዓት የሚሆኑ ጽሑፎች በተለያዩ ግለሰቦች ስለሚዘጋጁ የሚዳሰሱት ርዕሰ ጉዳዮች ስብጥር አላቸው፡፡

  እንደሚናገረው፣ በሲትኮሙ የሚስተናገዱ ጽሑፎች ቀዳሚ መስፈርት ማዝናናት ቢሆንም፣ ማሳቅን ብቻ ዓላማ ያደረጉ ሳይሆን ቁም ነገር አዘል መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ‹‹ቤቶች›› ካተኮረባቸው ጉዳዮች መካከል ልዩ ልዩ ማኅበራዊ ችግሮች ይገኙበታል፡፡ የመብራት፣ የውኃ፣ የኔትወርክ መቆራረጥና መሰል የአገሪቱ ሳንካዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ችግሮቹ ሲዳሰሱ መፍትሔ እንደሚያመላክቱ ያምናል፡፡

  ‹‹አብዛኛው ተመልካች ቁስሉ እንዲነካለት ይፈልጋል፤›› የሚለው ጥላሁን፣ ከዚህ ጎን ለጎን የእያንዳንዱን ሰው ኃላፊነት እንደሚጠቁሙ ይናገራል፡፡ ሲትኮሙ የወጣቶችን ሥነ ምግባር የመቅረፅ ዓላማ እንዳለውም ይገልጻል፡፡ ‹‹ወጣቶችን በጥሩ መንገድ መምራት ከተሸከምናቸው ኃላፊነቶች አንዱ ነው፤›› በማለት ያስረዳል፡፡

  ‹‹ቤቶች›› በአገሪቱ ያለውን ተጨባጭ እውነታ እንደሚያንጸባርቅ ጥላሁን ይናገራል፡፡ ታሪኩ በነባራዊ ሁኔታ ላይ ከመመሥረቱ ባሻገር ገፀ ባህሪያቱ በገሀዱ ዓለም የሚገኙ ናቸው ይላል፡፡ ብዙዎች የቤት ሠራተኞቹ ትርፌና ሻሼ የቀረቡበት መንገድ ላይ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ እንደ ጥላሁን ገለጻ፣ ‹‹ቤቶች›› በየቤታችን ያሉ ሠራተኞችን መብት ምን ያህል ጠብቀንላቸዋል? ሲል ያጠይቃል፡፡ በሲትኮሙ በሚታየው መጠን መብት ሲቸራቸውና ከአሰሪዎቻቸው ጋር ሲቀራረቡ ባይታይም፣ የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት ፈር መያዝ ይገባዋል ከሚል የተነሳ ነው፡፡ ሐሳቡን ከግምት የሚያስገቡ በተቃራኒው ተቃውመው ‹‹ሠራተኞችን እያበላሻችሁ ነው፤›› የሚሉም እንዳሉ ተናግሯል፡፡

  ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ሀመልማል ደሳለኝ በግል ሥራ ትተዳደራለች፡፡ ሲትኮሞቹ የግድ ቀልድ ወይም ቁም ነገር ብቻ መሆን የለባቸውም የምትለው ሀመልማል፣ ‹‹አዘጋጆቹ ወደ አንዱ ለማዘንበል ጥረት የሚያደርጉ ይመስለኛል፤›› ትላለች፡፡ በቀልድ እያዋዙ አንዳች መልዕክት የሚያስተላልፉ ቢሆኑ ትመርጣለች፡፡ ሲትኮሞቹን ወደው የሚከታተሉ ተመልካቾች ማፍራት መቻላቸው ዘርፉ በአገሪቱ እንደተለመደ ያሳያል ትላለች፡፡

  በእሷ እይታ ሁለቱም መነሻቸውን በማኅበረሰቡ ሕይወት ላይ አድርገው አንገብጋቢ ጉዳዮችን ያነሳሉ፡፡ አልፎ አልፎ ትርጉም አልባ የሆነ ጉዳይ ሲነሳና ከመጠን በላይ የተጋነኑ ገፀ ባህሪያት አድራጎት ይረብሻታል፡፡ በሌላ ተመልካች ላይም ተፅዕኖ እንዳያሳድር ያሠጋል ትላለች፡፡ ሌላው ለቀልድ ግብዓት የሚሆኑ ጉዳዮች መረጣ ነው፡፡ ‹‹ብዙሃኑን የሚያስቀይሙ አነጋገሮች አንዳንዴም ስድቦች እንደ ቀልድ ይቀርባሉ፤ ይህ በእኛ አገር ዐውድ ተቀባይነት የለውም፤›› ትላለች፡፡

  ብሩክ አየለ የ‹‹ጎረቤታሞቹ›› ፕሮዲውሰርና የድምጽ ባለሙያ ነው፡፡ መነሻ ሀሳቡ አዘጋጆቹ በሚኖሩበት ኮንዶሚንየምና በሌሎችም ያስተዋሉት አኗኗር እንደሆነ ይገልጻል፡፡ በአንድ የኮንዶሚኒየም ቅጥር ግቢ የሚኖሩ አምስት ወጣት ጎረቤታሞችን ታሪክ ያትታል፡፡ 31 ክፍሎች ቀርበው የመጀመሪያው ሲዝን ተጠናቋል፡፡

  ሲትኮሙ በሚያጠነጥንበት የዕድሜ ክልል የሚገኙና መሰል ኑሮ ያላቸው ግለሰቦች ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታ እንደሚያሳይ ይናገራል፡፡ ገፀ ባህሪያቱ ፈጠራና ለሲትኮም የሚሆን ግነት ታክሎባቸው የቀረቡ ናቸው፡፡ አስተያየት ሰጪዎች ከሚያነሱት ገፀ ባህሪ ምንዳዬ አንዱ ነው፡፡ ነዋሪዎቹን የሚቆጣጠርበት መንገድ ከእውነታው የራቀ ነው ቢባልም፣ ብሩክ ‹‹በአንዳንድ ኮንዶሚኒየም ካለው ጥብቅ ቁጥጥር የመነጨ ሐሳብ ነው፤›› ይላል፡፡

  እሱ እንደሚለው፣ በ‹‹ጎረቤታሞቹ›› እንደ ሌሎች ሲትኮሞች ሁኔታዎችን ፈጥሮ ማሳቅ እንዳለ ሆኖ የተለያዩ መልዕክቶችም ይተላለፋሉ፡፡ የሚያምንበትን ነገር ከማድረግ ወደኋላ የማይለው ምንዳዬን እንደምሳሌ ይጠቅሳል፡፡ ገፀ ባህሪያቱ አንዳቸው ከሌላቸው የተለየ አቋም ስላላቸው እንደየተመልካቹ አተያይ የሚያስተላልፉት ነገር አለ፡፡

  ‹‹የሀዊ ቤተሰቦች ሀብታም ቢሆኑም ራሷን ለመቻል ትጣጣራለች፡፡ ሳራ በተቃራኒው ከወንዶች ገንዘብ ማግኘትን ዓላማ ያደረገች ወጣት ናት፡፡ ሌሎችም ገፀ ባህሪያት በየፈርጁ ተስለዋል፤›› ይላል፡፡ ታሪኩ ዘመን አመጣሽ የወጣቱን አኗኗር እንደሚያሳይና በገፀ ባህሪያቱ ዕድሜ የሚገኙ ተመልካቾችን የበለጠ እንደሚስብ ይናገራል፡፡

  በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጥበባት ኮሌጅ፣ የቴአትር ትምህርት ቤት መምህር ዳንኤል ስለሺ፣ የተለያየ ባህሪ የተላበሱ ገፀ ባህሪያት እንደየፀባያቸው ወይም ከማንነታቸው የሚቃረን ሁኔታ ውስጥ ሲገቡ ሲትኮም ይፈጠራል ይላል፡፡

  የ‹‹ጎረቤታሞቹ›› ገፀ ባህሪያት ማንነት የሚፈለገውን ያህል አልተገለጸም ይላል፡፡ ገፀ ባህሪያቱ ለተመልካች ቅርብ እንዲሆኑ በጥልቀት መቀረፅ እንዳለባቸው ያስረዳል፡፡ ተመልካች ገፀ ባህሪያቱን ከራሱ ጋር ካላዋሀዳቸው ታሪኩን የመከታተል ፍላጎት አይኖረውም፡፡ የማኅበረሰቡ ነባራዊ ሁኔታ የፈጠራቸው መሆናቸውን ለተመልካች ማሳየት አለባቸው ይላል፡፡ መምህሩ ‹‹ሰው ከገፀ ባህሪያቱ ጋር ተዋህዶ በአንክሮ መከታተል ከጀመረ በኋላ የትኛውንም ጉዳይ መዳሰስ ይቻላል፤›› ይላል፡፡

  የ‹‹ቤቶች›› የመጀመሪያዎቹ ክፍሎች የትኩረት አቅጣጫ በማኅበረሰቡ ሰዋዊ ግንኙነት የሚፈጠሩ ክስተቶች ነበሩ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ውስንነት ላይ ያተኮሩና መተቸትና የመሳሰሉት ጉዳዮች ያጎላሉ፡፡ ገፀ ባህሪያቱ በጥልቀት ስለተገለጹ ማንኛውም የማኅበረሰብ ክፍል ከራሱ ወይም በአቅራቢያው ካለ ሰው ጋር ለማዛመድ አይቸግረውም፡፡ ይህም ታሪኩን ለመከታተል ያስችላል ይላል፡፡ ‹‹የኅብረተሰቡን የዘወትር መስተጋብር ያንፀባርቃል፤ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ሒሶች ላይም ያተኮረ ነው፤›› በማለት ይገልጻል፡፡

  እንደ መምህሩ ገለጻ፣ ሲትኮም የተለያየ የማኅበረሰብ ክፍልን የሚወክሉ ገፀ ባህሪያት ይዞ ዘርፈ ብዙ ፅንሰ ሐሳቦችን መዳሰስ መቻል አለበት፡፡ ሲትኮም በየክፍሉ የተለያዩ ሁኔታዎችን የመዳሰስ ነፃነት የሚሰጥ ዘርፍ በመሆኑ በዚህ መንገድ ጥቅም ላይ ሊውል ይገባል፡፡ አሁን በቴሌቪዥን የሚቀርቡት ሁለቱ ሲትኮሞች የሚጎሏቸው ነገሮች ቢኖሩም ለዘርፉ መንገድ ጠርገዋል ይላል፡፡

  ቶማስ አዲሴ የሥነ ሰብ (አንትሮፖሎጂ) ጥናት ባለሙያ ነው፡፡ ሁለቱ ሲትኮሞች የየራሳቸው አድናቂ እንዳላቸው ይናገራል፡፡ ሲትኮም በቅርብ ስለተጀመረ መስተካከል ያለባቸው ብዙ ነገሮች ቢኖሩም፣ በቴሌቪዥን ከሚታዩ ድራማዎች የተለየ አማራጭ ይዘው ቀርበዋል፡፡ ‹‹ጎረቤታሞቹ›› ወጣቶችን የበለጠ እንደሚያዝናና ያምናል፡፡ ‹‹ቤቶች›› ለገጠሪቷ ኢትዮጵያ እንዲሁም ለከተማ ነዋሪዎች ተመሳሳይ ስሜት ይፈጥራል፡፡ ሁሉንም ተመልካች ያማከሉ ሁኔታዎች ከኅብረተሰቡ ጥሩ ምላሽ ያገኛሉ ይላል፡፡

  ‹‹ሲትኮሞቹ ሁሉንም ሰው ያዝናናሉ ማለት አይቻልም፤ ቀልዶቹ የሚያስቋቸው ምንም ስሜት የማይሰጧቸውም አሉ፤›› ይላል ቶማስ፡፡ እሱን ያዝናኑት ያልወደዳቸውም ክፍሎች አሉ፡፡ መልዕክት አዘል ቢሆኑም እንኳን ከአስተማሪነታቸው ይልቅ ቀለል ያለ ስሜት መፍጠራቸው እንደሚጎላ ይገልጻል፡፡ ቀዳሚ ዓላማቸው ማዝናናት እስከሆነ ድረስ የተመልካችን ስሜት ገዢ መሆን አለባቸው፡፡ አንዳንድ ክፍሎች ውጪ አገር ከተሠሩ ሲትኮሞች እንደተቀዱና ኦሪጅናል ታሪክ ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ጠቁሟል፡፡

  ተጀምረው ከተቋረጡ ሲትኮሞች በአማራ ቲቪ ይተላለፍ የነበረው አንዱ ነው፡፡ የዘለቁት ‹‹ቤቶች››ና ‹‹ጎረቤታሞቹ›› ናቸው ለማለት ይቻላል፡፡ ዘርፉ ለምን በጥቂት ባለሙያዎች ተወሰነ የሚል ጥያቄ አንስተናል፡፡ በሁናቴዎች እያሳቁ ልዩ ልዩ ርዕሰ ጉዳዮችን ማንሳት ከባድ እንደሆነና የጽሑፍ፣ የዝግጅትና የትወና ሥራው ከሌሎች ዘርፎች አንጻር አስቸጋሪ መሆኑን ጥላሁንና ብሩክ ይስማሙበታል፡፡

  ብሩክ ፕሮፌሽናል ባለሙያዎችን የሚያሠለጥን ተቋም አለመኖሩን እንደ ተግዳሮት ይጠቅሳል፡፡ ደረጃቸውን የጠበቁና የዘውጉን መስፈርት የሚያሟሉ ሲትኮሞች የሚበዙት የተማሩ ባለሙያዎች ሲበራከቱ ነው ይላል፡፡ ጥላሁን ‹‹ቤቶች›› በተከታታይነት መተላለፉ በዘርፉ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ያምናል፡፡ ብሩክ በበኩሉ ‹‹ጎረቤታሞቹ››ን ተከትለው ለሚመጡ ሲትኮሞች ተሞክሮው መማሪያ እንደሚሆን ይናገራል፡፡ ወደ ዘርፉ የሚቀላቀሉ ባለሙያዎች ሲበራከቱ የተሻሉ ሥራዎች እንደሚፈጠሩ ያምናል፡፡

  በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል ለሁለተኛ ዲግሪ ማሟያ 2006 ዓ.ም. “A Study on Audience Sense Making of Media Tests: Betoch Drama in Focus” በሚል በመሠረት ታጀበ የተሠራው ጥናት ተመልካቾች ‹‹ቤቶችን›› የሚገነዘቡበትን መንገድ ይዳስሳል፡፡ ጥናቱ እንደሚያሳየው፣ ሲትኮሙ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን በሚያዝናና መልኩ ያቀርባል፡፡ ለመዝናናት ወይም አንዳች ትምህርት ለመቅሰም የሚመለከቱት በተለያየ የዕድሜ ክልልና ሙያ ያሉ ሰዎችን ጥናቱ ይጠቅሳል፡፡ በማጠቃለያው ሲትኮም በጅማሮ ያለ መሆኑን ጠቁሞ ለዘርፉ የሚጠቅሙ ጥናቶች መሥራት እንዳለባቸው ያመለክታል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...