ምርጫውን ተጠቅመው ሰላም ለማወክ የሚንቀሳቀሱ አካላትን መንግሥት የሚታገስበት ምክንያት እንደሌለና ችግር ከተፈጠረም ከአቅም በላይ ሊሆን እንደማይችል፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ሬድዋን ሁሴን አስታወቁ፡፡
ሚኒስትሩ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ግንቦት 6 ቀን 2007 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ አጠቃላይ የቅድመ ምርጫ ዝግጅት ከጥቃቅን ችግሮች ባሻገር ሰላማዊ እንደነበር ባለፈው ሳምንት ከምሁራንና ከፓርቲዎች ጋር በተደረገ ውይይት መረጋገጡን ገልጸዋል፡፡
ቀጣዩ ምዕራፍም ተመሳሳይና ሰፋ ያለ ተሳትፎ የሚደረግበትና ምርጫው በአጠቃላይ እጅግ ሰላማዊ ሆኖ ይጠናቀቃል የሚል እምነት መያዙን ተናግረዋል፡፡
በዚህም መሠረት ሁከትም ሆነ ችግር ለመፍጠር የሚያስችል ምክንያት አለመኖሩን፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ሆኑ ገዥው ፓርቲ በጋራ ባካሄዱት ግምገማ ከሞላ ጎደል ማረጋገጣቸውን ጠቅሰዋል፡፡
‹‹ይህ ማለት ግን ምርጫውን ተጠቅመው ሰላም ለማወክ የሚንቀሳቀሱ አካላት አይኖሩም ማለት አይደለም፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ‹‹ይህንን የሚሸከም የሕዝብ ትከሻ የለም፡፡ በመንግሥት በኩልም ለፀጥታ ኃይሎች ሥልጠናና የቁሳቁስ ዝግጅት የተደረገ በመሆኑ ችግር ከተፈጠረ ከአቅም በላይ ሊሆን እንደማይችል መንግሥት እርግጠኛ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ለፀጥታ ኃይሉ በቅርቡ የተሰጠው ሥልጠናና የአቅም ግንባታ ማዳበሪያ የተከናወነው የተለየ ሥጋት በመኖሩ እንዳልሆነም አስታውቀዋል፡፡ ከምርጫ 97 በኋላ የተደረገ ቀጣይነት ያለው የአቅም ግንባታ ለፀጥታ ኃይሉ መስጠት መደበኛ ተግባር መሆኑን ጠቅሰው፣ ከቁጥጥር ውጪ የሚወጣ ነገር አይኖርም ብለዋል፡፡ የአቅም ግንባታ ሥራውም ከምርጫ በኋላ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
የግንቦት ሰባት ዋና ጸሐፊ የነበሩትና በኢትዮጵያ የደኅንነት ኃይል የመን ሰንዓ አውሮፕላን ማረፊያ በቁጥጥር ሥር የዋሉት የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ ከአዲስ አበባ አዳማ የሚወስደውን የፍጥነት መንገድ ሲጐበኙ የሚያሳይ ፎቶግራፍ በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ ገጾች መታየቱን አስመልክቶ የተጠየቁት አቶ ሬድዋን፣ ‹‹ምሥሉን አይቼዋለሁ፡፡ ነገር ግን ዝርዝር መረጃ አልጠየቅኩም፡፡ በመሆኑም በጉዳዩ ላይ የምሰጠው መረጃ የለም፤›› ብለዋል፡፡