[ክቡር ሚኒስትሩ ከሾፌራቸው ጋር እያወሩ ነው]
- ምንድነው አንተ ይኼ?
- አዲሱ መኪና ነዋ፡፡
- የሰው መኪና አትያዝ አላልኩህም?
- ይኼ የሰው መኪና አይደለም፡፡
- አንተ የእኔ ሾፌር ብቻ ነህ፡፡
- እሱንማ አውቃለሁ፡፡
- ታዲያ ይኼ የማን መኪና ነው?
- የእርስዎ መኪና ነዋ፡፡
- ሰውዬ በጠዋቱ ጠጥተህ ነው እንዴ የመጣኸው?
- በዚህ በጠዋት ምን እጠጣለሁ ብለው ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ታዲያ እንደዚህ ዓይነት መኪና የእርስዎ ነው ስትለኝ ትንሽ አታፍርም?
- ስለሆነ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ስለሆነ ነው ማለት ምን ማለት ነው?
- ባለፈው የወጣውን መመርያ ረሱት እንዴ?
- እኔ እያንዳንዱን የሚወጣውን መመርያ እንዴት ላስታውስ እችላለሁ?
- የመንግሥት ባለሥልጣናት ቪ8 መኪናቸውን ለፊልድ ብቻ ይጠቀሙበት የሚለውን መመርያ ነዋ፡፡
- ምን እያልከኝ ነው ታዲያ?
- በመመርያው መሠረት ከተማው ውስጥ የሚያንቀሳቅስዎት መኪና አገር ውስጥ የተገጣጠመ ነዋ፡፡
- ምን?
- እውነቴን ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እየቀለድክ ነው እንጂ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ይቺን አገር እያጠፋት ያለው ቀልድና ቀልደኞች ናቸው፡፡
- አሁን የማታውቀውን ፖለቲካ ለመፈትፈት ባትሞክር ጥሩ ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ፖለቲከኛ ባልሆንም ከፖለቲካ ግን ማምለጥ እንደማልችል አውቃለሁ፡፡
- ምን እያልክ ነው?
- በቃ የሁሉም ሰው ሕይወት ከፖለቲካ ጋር የተገናኘ ነው፡፡
- እሺ የእኛ የፖለቲካ ፈላስፋ?
- እየተፈላሰፍኩ ሳይሆን እውነታውን ነው የነገርኩዎት፡፡
- አሁን እሱን ተወውና ቪ8ቴን በአስቸኳይ አምጣልኝ፡፡
- አይ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምነው?
- እሱ ቀርቶ ሌላ ዘፈን መጥቶ ሲባል አልሰሙም?
- ምን እያልክ ነው?
- ቪ8 ቀርቶ ሌላ ከቻይና መጥቷል ተብሏል፡፡
- ሰውዬ ቅኔ ዝረፍልኝ አላልኩህም እኮ?
- ያው ለጨዋታ ብዬ ነው፡፡
- አሁን ቪ8ቴን አምጣልኝ፡፡
- ቪ8ቱማ ከፊልድ ውጪ አይቻልም ስልዎት፡፡
- ማነው የከለከለው?
- መመርያው ነዋ፡፡
- እኔ አይደለሁ እንዴ አለቃህ?
- ክቡር ሚኒስትር ከመመርያ ውጪ ብሠራ ስለምጠየቅ፣ ከፈለጉ ራስዎ ቪ8ቱን መያዝ ይችላሉ፡፡
- ይቺን ይወዳል ሰውዬው?
- ክቡር ሚኒስትር ለከተማ ይቺ ናት መኪናዎ፡፡
- ይኼማ ሊሆን አይችልም፡፡
- ቪ8 ለፊልድ ብቻ ነው፡፡
- በቃ ፊልድ እንውጣ?
- እሱንም ማድረግ አንችልም፡፡
- ለምን?
- ከአዲስ አበባ ውጪ መንገዶች ስለተዘጋጉ መውጣት አንችልም፡፡
- አሁን ምን እንደማደርግ አውቃለሁ፡፡
- ምን ሊያደርጉ ነው?
- የሥራ ባልደረቦቼ ጋ ደውዬ አስተባብራለሁ፡፡
- ምንድነው የሚያስተባብሩት?
- መውጣት አለብን ብዬ ነዋ የማስተባብረው፡፡
- ምን?
- ሰላማዊ ሠልፍ!
[ለክቡር ሚኒስትሩ ከውጭ ዳያስፖራ ወዳጃቸው ይደውልላቸዋል]
- እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
- ሰላም ነኝ አንተ እንዴት ነህ?
- አገሪቷ ውስጥ ምንድነው የምሰማው?
- ምን ሰማህ ደግሞ?
- አገር ሰላም ነው?
- ሁሉ ነገር ሰላም ነው፡፡
- ኧረ እኔ የሰማሁት ነገር ደግሞ ሌላ ነው፡፡
- ምን ሰማህ ደግሞ?
- አሁን አንድ ወዳጄ ከአገር ቤት ደውሎልኝ ነበር፡፡
- ምን አለህ?
- ተቃውሞው እንደ አዲስ አገርሽቶ ነገሩ ያስፈራል እያለኝ ነው፡፡
- ይኼ የፀረ ሰላም ኃይሎች ወሬ ነው፡፡
- ኧረ ክቡር ሚኒስትር ይኼንን ነገር ይተው፡፡
- ምኑን?
- ሕዝብን ፀረ ሰላም የምትሉት ነገር ነዋ፡፡
- እንዴት?
- ሕዝብን እንዴት ፀረ ሰላም ትላላችሁ?
- አሁን ምክር ልትመክረኝ ነው የደወልከው?
- ኧረ እንደው የአገሪቷ ሁኔታም ሲያሳስበኝ ነው የደወልኩት፡፡
- ምንም አያሳስብህ ስልህ?
- በነገራችን ላይ ሰሞኑን በሶሻል ሚዲያ ያየሁት ነገር አስገርሞኛል፡፡
- ምን ዓይተህ ነው?
- አንዳንዴ መንግሥት የሚሠራው ሥራ ያስቃል፡፡
- ምኑ ነው የሚያስቀው?
- ባለፈው የጉለሌ ኮሙዩኒኬሽን የለጠፈውን መረጃ ዓይተውታል?
- ምን ላይ?
- ፌስቡክ ላይ ነዋ፡፡
- ፌስቡክ የወሬኞችና የውሸታሞች ቦታ ስለሆነ አልጠቀምበትም፡፡
- በአሁን ጊዜማ ፌስቡክን መጠቀም አለብዎት፡፡
- ለምን?
- በርካታ መረጃዎች ያገኙበታላ፡፡
- እኔ መረጃ የሚሰጠኝ መቼ ጠፋ?
- ለማንኛውም የጉለሌ ኮሙዩኒኬሽን የለጠፈው ግን በሳቅ ነው ያፈነዳኝ፡፡
- ምን ብሎ ለጥፎ ነው?
- በጉለሌ ክፍለ ከተማ ላሉ ነዋሪዎች ሥልጠና መስጠቱን ነዋ የለጠፈው፡፡
- ሥልጠና መስጠት ምን ችግር አለው?
- እሱ አይደለም ቁም ነገሩ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምንድነው ቁም ነገሩ ታዲያ?
- ሥልጠናው ስለኒዮሊብራሊዝም መሆኑ ነዋ፡፡
- ታዲያ ምን ችግር አለው?
- የሥልጠናው ርዕሰ ‹‹ኒዮሊብራሊዝም ሸሸ ወይስ አፈገፈገ?›› የሚል ነበር፡፡
- ምን ችግር አለው ታዲያ?
- ክቡር ሚኒስትር አሁን እነትዬ ብርቄና እትዬ አስካለ ኒዮሊብራሊዝም ቢሸሽ ወይም ቢያፈገፍግ አይደለም ፈርጥጦ ቢጠፋ ምን አገባቸው?
- አንተ ራስህ የኒዮሊብራሊዝም አመለካከት ነው ያለህ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር አሁን እትዬ ስርጉት ስለኒዮሊብራሊዝም ያውቃሉ ብለው ይገምታሉ?
- አንተ ሕዝባችንን ስለምትንቀው ነው፡፡
- እንዲያው ሕዝቡን የምትንቁትማ እናንተ ናችሁ፡፡
- እንዴት?
- ሕዝቡ የሚጠይቀው ሌላ እናንተ የምታወሩት ሌላ፡፡
- ምን እያልክ ነው?
- አሁን ፋብሪካ የሚቃጠለውና መንገድ የሚዘጋው ኒዮሊበራሊዝም በመሸሹ ወይስ በማፈግፈጉ ነው?
- ምን?
- ክቡር ሚኒስትር ይኼ ሕዝብ በጣም እየታዘባችሁ ነው፡፡
- አንተ ውጭ ስለምትኖር የዚህን አገር ሕዝብ ብዙም አታውቀውም፡፡
- ለነገሩ እኔ ፎቶዎቹንም ሳይ የሥልጠናው ዋናው ነገር ኒዮሊብራሊዝም አለመሆኑ ገብቶኛል፡፡
- የሥልጠናው ዋናው ነገር ምንድነው ታዲያ?
- አበሉ!
[የክቡር ሚኒስትሩ የቀድሞ ወዳጅ ይደውሉላቸዋል]
- ክቡር ሚኒስትር እዚህ አገር ላይ ምንድነው እየተካሄደ ነው ያለው?
- ሰው ያለዚህ ጥያቄ የለውም እንዴ?
- በዚህ ወቅት ሌላ ጥያቄ እንዴት ይጠየቃል?
- ምን እያልክ ነው?
- ሰላም ናፈቀን እኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እኛም እንደ ሕዝብ ሰላም ፈላጊዎች ነን፡፡
- እውነት ክቡር ሚኒስትር?
- የሚሠራው እኮ አገር ሰላም ሲሆን ነው፡፡
- የሚሰረቀው ማለትዎ ነው?
- ብንከባበር አይሻልም?
- መከባበር ያለብዎትማ ከሕዝቡ ጋር ነው፡፡
- ምን ማለት ነው?
- የሕዝብ ጥያቄ በአግባቡ ይመለስ፡፡
- መቼ ነው እኛ የሕዝብ ጥያቄ አንመልስም ያልነው?
- ከ27 ዓመት በላይ ሊሆናችሁ ነው፡፡
- ከዚህ በላይ እንዴት ይመለስ?
- ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- እስረኛ እየለቀቅን ነው፡፡
- የሕዝቡ ጥያቄ እሱ ብቻ አይደለም፡፡
- እኔ የሕዝቡ ጥያቄ ምንም ሊገባኝ አልቻለም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ፍላጎት ስለሌላችሁ እንጂ ጠፍቷችሁ አይመስለኝም፡፡
- ሰውዬ ምን እያልክ ነው?
- እናንተ ራስ ወዳድ ሆናችሁ ኪሳችሁን ማደለብ ስለምትፈልጉ እንጂ የሕዝቡ ጥያቄ ቀላል ነው፡፡
- ከዚህ በላይ ምን እንደሚደረግ አይገባኝም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ከእኔ በላይ የሚያውቅልህ የለም የሚለው አካሄድ አያዋጣችሁም፡፡
- አሁን ምንድነው ጥፋታችን?
- ያለአዋቂ ሳሚ ምን ይለቀልቃል ሲባል አልሰሙም?
- ልትሞልጨኝ ነው እንዴ የደወልከው?
- እኔማ የአገሪቷ ሁኔታ አስጨንቆኝ ነው፡፡
- ምንም አትጨነቅ፡፡
- ለነገሩ እኔ ከድሮም ጀምሮ አውቅዎታለሁ፡፡
- አውቅዎታለሁ ስትል?
- ያው በልጅነታችን ካርታ ስንጫወት ያስታውሳሉ፡፡
- ሁሌም እኔ እንደ በላሁዋችሁ ነበር፡፡
- አሁንም እየተጫወቱ ያሉ ነው የመሰለኝ፡፡
- ምን?
- ቁማር!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከሌሎች ባለሥልጣናት ጋር የፓርቲ ስብሰባ አድርገው ሊጨርሱ ነው]
- ክቡር ሚኒስትር በማጠቃለያው ምን ይላሉ?
- አሁን ባፋጠኝ የሕዝቡን ጥያቄ መመለስ አለብን፡፡
- እንዴት ማለት?
- ከበርካታ ሰዎች ጋር አውርቼ የነገሩኝ አንድ ዓይነት ነገር ነው፡፡
- ምንድነው እሱ?
- እስረኛ መፍታት ችግሩን አይፈታም፡፡
- ታዲያ ሌላ ምን ይደረግ?
- ሌላው የሕዝቡ ጥያቄ ይሰማ፡፡
[ሌላኛው ባለሥልጣን መናገር ጀመሩ]
- እኔም ክቡር ሚኒስትሩ ያሉትን ሐሳብ እደግፋለሁ፡፡
- የትኛውን?
- የሕዝቡ ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡
- እሱማ ትክክል ነው፡፡
- ስለዚህ እስከ ታች ድረስ ያለው ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡
- ሁላችንም ተስማምተናል፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ የስብሰባው መጠናቀቅን አስመልክቶ ምን መደረግ እንዳለበት ሐሳብ ማሰባሰብ ጀመሩ]
- እንግዲህ ስብሰባችንን ጨርሰናል፡፡
- ምን ይደረግ ይላሉ ክቡር ሚኒስትር?
- ትንሽ ብንዝናና ጥሩ ነው፡፡
- እንግዲያው እኔ አንድ ሐሳብ አለኝ፡፡
- ምድነው እሱ?
- አንድ ብላክ ሌብል አወርዳለሁ፡፡
[ሌላኛው ባለሥልጣን ማውራት ጀመሩ]
- እኔ ጎልድ ሌብል አወርዳለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በጣም ደስ ይላል፡፡
[ሌላኛው ባለሥልጣን በተራቸው ተናገሩ]
- እኔ ብሉ ሌብል አወርዳለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ይኼ ደግሞ ጫን ያለ ነው፡፡
- እርስዎ ምን ያወርዳሉ ክቡር ሚኒስትር?
- ራሴን፡፡
- ከምን?
- ከሥልጣን!