Tuesday, August 9, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ይድረስ ለሪፖርተርአዲስ የፓርላማ ሕንፃ መገንባት ያስፈለገው ለቅንጦት አይደለም!

  አዲስ የፓርላማ ሕንፃ መገንባት ያስፈለገው ለቅንጦት አይደለም!

  ቀን:

  ሪፖርተር ጋዜጣ እሑድ ጥር 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ባወጣው ዕትም ቅጽ 23፣ ቁጥር 1854፣ ገጽ 50 ላይ በታተመው ‹ይድረስ ለሪፖርተር› ዓምድ ሥር በላይ የተባሉ ግለሰብ  ‹‹የፓርላማ ሕንፃውን መቀየር ለምን አስፈለገ?›› በሚል ርዕስ የሰጡትን አጭር ትችት አዘል አስተያየት ጋዜጣው አስነብቧል፡፡

   የግለሰቡ ጽሑፍ መነሻ፣ አዲስ የፓርላማ ሕንፃ መገንባት ስላስፈለገበት ምክንያት ሲሆን፣ የእንግሊዝ ፓርላማ ሕንፃን በአብነት በመውሰድ፣ አዲስ መገንባት ሳያስፈልግ አሁን ባለው የፓርላማ ሕንፃ መቀጠል አለብን የሚል መልዕክት ያለው ነው።

  አሁን ያለው የፓርላማ ሕንፃ ከ80 ዓመታት በላይ ያስቆጠረና ኪነ ሕንፃውም ኢትዮዽያ በአፍሪካ ቀዳሚ የፓርላማ ታሪክ እንዳላት ታሪካዊ ማሳያና መገለጫ ነው፡፡ ሕንፃው ከአሥር ዓመት በፊት ታሪካዊ ቅርስነቱ ተጠብቆ መጠነኛ ጥገና ተደርጎለታል፡፡ ባለፉት ዓመታት የመንግሥት የልማት አቅጣጫ ማኅበራዊ ችግሮችን ፈጥኖ መፈታት ላይ ያተኮረ በመሆኑ፣ የወቀቱን ፍላጎት ጋር አመቺና ደረጃውን የጠበቀ አዲስ የፓርላማ ሕንፃ  ሳይገነባ ቆይቷል። ዘግይቷል።

  ፓርላማው በንጉሡ ዘመነ መንግሥት የንጉሡን አማካሪዎች የሆኑትን የሕግ መወሰኛንና የሕግ መምርያ ምክር ቤቶች የያዘ ነበር፡፡ ምክር ቤቶቹ እያንዳንዳቸው 56 አባላት ያሏቸው ሲሆን፣ የየራሳቸው ሰባት ኮሚቴዎችን ነበሯቸው። በ1948 ዓ.ም. ሕገ መንግሥቱ ሲሻሻል የሕግ መምርያ ምክር ቤት አባላት በቀጥታ ሕዝብ እንዲመርጥ ተደርጎ፣ 125 የሕግ መምርያና 250 የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት ተመርጠዋል።

  አሁን በምንገኝበት ዘመናዊ የአስተዳደር ሥርዓት ውስጥ፣ የፌዴራሉ መንግሥት ሁለት ምክር ቤቶች አሉት፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 547 አባላት ሲኖሩት ሙያዊ ድጋፍና አስተዳደራዊ አገልግሎት የሚሰጥ ጽሕፈት ቤት በሥሩ አደራጅቷል። የምክር ቤቱና የጽሕፈት ቤቱ አደረጃጀቶች በአስፈጻሚ ተቋማት በሚደረጉ ለውጦችና ነባራዊ ሁኔታዎች አንፃር እየተቃኙ በየጊዜው የአደረጃጀት ለውጥ እየተደረገባቸው የመጡ ናቸው። የቋሚ ኮሚቴዎች ቁጥር በየጊዜው እያደገ ከዘጠኝ ወደ 20 ከፍ ብሏል፡፡

  የምክር ቤቱ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ቁጥር ከነበረበት በሦስት እጥፍ አድጎ ከ400 በላይ ሆኗል። በአሁን ወቅት በፓርላማው ሕንፃና በሥላሴ ሕንፃ ያሉ ቢሮዎች ለምክር ቤቱ ማኅበረሰብ በቂ ባለመሆናቸው ሳቢያ፣ የምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት የአርበኞች ሕንፃን በመከራየት ጊዜያዊ መፍትሔ ለመውሰድ ተገዷል።

  የምክር ቤቱን የክትትልና የቁጥጥር ተግባር በዋናነት የሚያከናውኑት የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች ናቸው፡፡ በቁጥር 20 ሲሆኑ፣ እያንዳንዳቸው ከ15 አስከ 25 የሚደርሱ አባላትና የየራሳቸው ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች አላቸው። የቢሮና የስብሰባ አዳራሽ እጥረቶች  አሉባቸው፣ ቋሚ ኮሚቴዎች የአስፈጻሚ የመንግሥት ተቋማትን ዕቅድና የአፈጻጸም ሪፖርት የሚገመግሙት በፈለጉት ቀንና ሰዓት ሳይሆን፣ የአዳራሽ አገልግሎት ወረፋ በማስያዝ ነው፡፡ ይኼም በአሁን ወቅት በሚያከናውኑት የክትትልና ቁጥጥር ሥራ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ ይገኛል።

  የፓርላማ ወዳጅነት ቡድኖች በቢሮ ዕጦት ተግባራቸውን በሚፈለገው መንገድ እየተወጡ አይደለም። በቀጣይ የአብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት ሲሻሻል የምክር ቤት አባላት ቁጥር በ110 አባላት ይጨምራል፡፡ በምክር ቤቱ ጉባዔ አዳራሽ ተጨማሪ ወንበር ለማከል ምንም ቦታ የሌለውና ታሪካዊ በመሆኑም የማስፋት ሥራ ሊሠራ አይችልም።

  ሌላው ጉዳይ የፓርላማው ሥራ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማጠናከር አለበት፡፡ ምክር ቤቱ ዘመኑ የፈጠራቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም አሠራሩን ማዘመንና ሥራዎቹንም ለዓለም አቀፉ ኅብረሰተሰብ ማሳወቅና ማስተዋወቅ ይኖርበታል፡፡ እንደ ሌሎች አገሮችም ፓርላማው የራሱ የቴሌቪዥን ጣቢያ ሊኖረው ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ በቂ፣ ምቹና ዘመናዊ ሕንፃ መገንባት ያስፈልጋል። አዲስ ፓርላማ መገንባት ያስፈለው ለቅንጦ ሳይሆን፣ ከላይ በተጠቀሱ ምክንያቶች እንደሆነ አስተያየት ሰጪውም ሆነ አንባቢ እንዲገነዘቡ  እንፈልጋለን፡፡ 

  ‹‹በአገራችን የመሠረተ ልማት ችግር እያለብን፣ የሥራ አጥ ቁጥር ከፍተኛ በሆነበት አዲስ የፓርላማ ሕንፃ መገንባት ለምን አስፈለገ?›› የሚለው የግለሰቡ አስተያየት፣ ባለፉት ጊዜያት የሕንፃ ፕሮጀክቱ በታሰበው ጊዜ እንዳይጀመር ለመጓተቱ ምክንያት ነው፡፡ ነገር ግን ምክር ቤቱ አሁን ባለው ሁኔታ የቢሮና የስብሰባ አዳራሽ ችግሮች እንዳሉበት መቀጠል አለበት ወይ? ከወቅታዊ ፍላጎቶችና ነባራዊ ሁኔታዎች አንፃር አሁን ባለው ሕንፃ መቀጠል ይቻላል? የሚሉትንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ሚዛናዊ ሆኖ ማጤን ያስፈልጋል። መነሳት ያለበት ጥያቄ አዲሱ ሕንፃ ግንባታ እንደ ቀድሞው ሕንፃ ከትውልድ ትውልድ መተላለፍ አለበት የሚል እንጂ የአዲስ ፓርላማ ሕንፃ መገንባት አስፈላጊነት ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፡፡ ምክር ቤቱ ሥራ እስከሚያቆም መጠበቅ የለበትም፤ የዘገየ ፕሮጀክት ነው።

  አሁን ያለውን የፓርላማውን ሕንፃ ንጉሥ ተፈሪ ንጉሠ ነገሥት ከመሆናቸው በፊት በራሳቸው ገንዘብ ማሠራታቸውን አስተያየት ሰጪው አያይዘው በጽሑፋቸው ገልጸዋል፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪው ከሆነ አገሪቱ በወቅቱ ኋላ ቀር የምትባልና በከፋ ድህነትና የመሠረተ ልማት ችግር ውስጥ ነበረች፡፡ ስለዚህ በወቅቱ ይኼ ችግር እያለ ንጉሡ የፓርላማውን ሕንፃ ማስገንባታቸው ስህተት ይሆናል ማለት ነው። ኢትዮጵያ ከጥንታዊና ልማዳዊ አመራር ወጥታ ወደ ዘመናዊ አስተዳደር እንድትሻገርና ብሎም በዓለም እንድትታወቅ ማድረግ የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ በመሆኑ፣ ንጉሡ የፓርላማ ሥርዓት ለመዘርጋት ወስነው አሁኑ ያለውን ሕንፃ መገንባት ችለዋል፡፡ ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈም እስከ አሁን ድረስ ሊያገለግል ችሏል።

  አስተያየት ሰጪው አዲስ የፓርላማ ሕንፃ መቀየር የቀድሞውን ታሪካዊ ሕንፃ እንደሚጎዳ ሥጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡ በመሠረቱ አዲስ የፓርላማ ሕንፃ ተገነባ ማለት  የቀድሞ ሕንፃ ይፈርሳል ወይም ጉዳት ይደርስበታል ማለት አይደለም፡፡ ባለፉት ጊዜያትም  ምንም ዓይነት የማስፋፋትም ሆነ ታሪካዊ ቅርስነቱን ሊጎዱ የሚችል ግንባታዎች በሕንፃው ላይ አልተደረገም፡፡ ለአብነት ለመጥቀስ የጉባዔ አዳራሽ መቀመጫዎች ምቹ ባለመሆናቸው እንዲቀየሩ በተደጋጋሚ ቢጠየቅም፣ ታሪካዊ ቅርስነቱን ይጎዳል በሚል እንዲቀየሩ  አልተደረገም። የአዲሱ ሕንፃ ፕሮጀክት ግንባታም በሌላ ሥፍራ የሚከናወን ሲሆን፣ ግንባታው ሲጠናቀቅ፣ የቀድሞ የፓርላማ ሕንፃ በሙዚየምነት ተጠብቆ ለጎብኚዎች ክፍት  ይሆናል። አስተያየት ሰጪውም ሆነ አንባቢ ግንዛቤ እንዲይዝ ይኼን ጽሑፍ አዘጋጀን።

  (የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት

  ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት)

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የአገሪቱ ባንኮች ካፒታል 199.1 ቢሊዮን ብር ደረሰ

  ከታክስ በኋላ 50 ቢሊዮን ብር ማትረፋቸውን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ የአገሪቱ...

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...