Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊየልማት ሰለባዎች

  የልማት ሰለባዎች

  ቀን:

  በከፍተኛ ሁኔታ ግንባታ እየተካሄደባት ባለው አዲስ አበባ ከተማ የፈራረሱ መንደሮች የከተማዋ ገጽታ ከሆኑ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በመልሶ ማልማት ከፈረሱ አካባቢዎች ፊት በር (ለሸራተን አዲስ ግንባታ) እና ካዛንችስ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ ለመንገድና ለኮንዶሚኒየም በተለያዩ አካባቢዎች መንደሮች ተነስተዋል፡፡ ዛሬም በመፍረስ ላይ ያሉና የሚፈርሱበት ቀን የተቆረጠላቸው አካባቢዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ ካዛንችስና አራት ኪሎ በዚህ ረገድ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

  ካዛንችስ ዮርዳኖስ ሆቴል ጀርባ የሚገኘውና በተለምዶ ‹‹ቻይና ሠፈር›› እየተባለ የሚጠራው አካባቢ እንደሚነሳ ለነዋሪዎቹ ከተነገረ አንድ ዓመት መሆኑን ያነጋገርናቸው የመንደሩ ነዋሪዎች ገልጸውልናል፡፡ ለ 30 እና ለ 50 ዓመታት ከኖሩበት ቦታ ለመነሳት፣ ገንዘብን ጨምሮ ሁለንተናዊ ዝግጅት ለማድረግ አንድ ዓመት በቂ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ የሚያነሱ ጥቂት አይደሉም፡፡

  ወ/ሮ ቅድስት በቀለ መዋለ ሕፃናት የምትማርና የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ሕፃናት እናት ነች፡፡ የምትኖረው ቻይና ሠፈር በሚገኘው በባለቤቷ እናት ቤት ሲሆን የባለቤቷ እናት በቤቱ ለ50 ዓመታት ገደማ ኖረዋል፡፡ ቅድስት ቤተሰብ የምታስተዳድረው እዚያው ከከፈተቻት ትንሽ ምግብ ቤት በምታገኘው ገቢ ነው፡፡ አሁን ግን የአካባቢው በልማት መነሳት የኑሮዋ መሠረት የሆነውን ትንሽ ንግድ ስለሚያሳጣት የእኔና የቤተሰቤ ቀጣይ ኑሮ እንዴት ይሆናል? የሚል ፍርሀት ውስጥ እንደገባች ትናገራለች፡፡

  ‹‹የተጨናነቁ መንደሮች፣ ለውጥና ዘመናዊነት›› በሚለው ጥናታቸው ዶ/ር ኤልያስ ይትባረክ፣ የአዲስ አበባ የተጨናነቁ መንደሮች መንገዶች እንዲሁ ከአንድ ጫፍ ሌላ ጫፍ የሚያደርሱ ብቻ ሳይሆኑ ብዙዎች በትንንሽ የንግድ ሥራ ሕይወታቸውን የመሠረቱባቸው እንደሆኑ ያስቀምጣሉ፡፡ ገቢ፣ ማኅበራዊ ግንኙነት በአጠቃላይ ለኗሪዎቹ ሕይወት ያለው እነዚህን የተጨናነቁ መንደሮችና መንገዶቹን በሚያገናኘው ነጥብ ላይ ነው፡፡ ወይዘሮ ቅድስት ከእነዚህ ውስጥ ናት፡፡

  ምንም እንኳን አካባቢው በልማት ተነሽ እንደሆነ ከዓመት በፊት የተነገራቸውና እንደ አማራጭ ኮንዶሚኒየምና የቀበሌ ቤት የቀረበላቸው ቢሆንም ለብዙዎች ሁለቱም አማራጭ ቀላል አይደለም ትላለች፡፡ ‹‹ለኑሮአችን እንኳ ይህ ነው የሚባል ገቢ ለሌለን ሰዎች የኮንዶሚኒየም ክፍያ በጣም ከባድ ነው፡፡ የቀበሌ ቤት ልምረጥ ቢባልም እሱም በቀላሉ አይገኝም፡፡ እንዲያውም አላግባብ የተያዘ ወይም ክፍት የቀበሌ ቤት ጠቁሙ የቀበሌ ቤት ከፈለጋችሁ እየተባለ ነው፤›› ትላለች፡፡ የቀበሌ ቤት ብመርጥም ነገም ከዚያም ከመነሳት ዕጣ አላመልጥም በሚል የውዴታ ግዴታ ምንም እንኳ የኮንዶሚኒየም ክፍያ በኑሮአቸው የማይታሰብ ቢሆንም ኮንዶሚኒየም የመረጡ ብዙ ናቸው፡፡ ወይዘሮ ቅድስትም ከእነዚህ መካከል ነች፡፡ ኮንዶሚኒየም መርጣ ሰሚት ቁጥር ሁለት ባለሁለት መኝታ ቤት ከስድት ወር በፊት ተቀብላለች፡፡ 54,000 ብር ቅድሚያ ክፍያ የከፈለችበት ኮንዶሚኒየም ቤት ግን ሥራው ያላለቀና ሊኖሩበት የማይችሉበት ዓይነት እንደሆነ ገልጻልናለች፡፡ ያላለቀውን ጨርሼ ልግባ እንዳይባል ደግሞ ይህ በብዙዎች አቅም የሚሞከር አይደለም፡፡

  ባይቀጥልም አካባቢው በልማት ይነሳል እንደተባለ ወዲያው ማፍረስ ተጀምሮ እንደነበር ወይዘሮ ቅድስትና ሌሎችም የአካባቢው ነዋሪዎች ይገልጻሉ፡፡ እነሱ እንደገለጹልን ፈረሳው የቆመው የአካባቢው ሰው ተሰባስቦ ኡኡታውን በማሰማቱ ነበር፡፡ በዚህ ድንገተኛ ፈረሳ ሳያስቡት እንደዋዛ ከእንጀራቸው (ከንግድ) የተፈናቀሉና መኖሪያቸውን ያጡም እንዳሉ ይገልጻሉ፡፡

  የ66 ዓመቱ አቶ ግዛው ኃይሌም እዚሁ ቻይና ሠፈር ነዋሪ ናቸው፡፡ የልብ ሕመምተኛ ሲሆኑ የሕክምና ማስረጃቸውን በማቅረብ ዕጣ ውስጥ ሳይገቡ መሬት ላይ እንዲሰጣቸው መጀመሪያ ላይ ጥያቄ ቢያቀርቡም ‹‹መጀመሪያ ዕጣ ውስጥ ይግቡና ዕድልዎት ታይቶ ከዚያ ይወሰናል፤›› በሚል ጥያቄያቸው ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱን ይናገራሉ፡፡ ዕለት በዕለት በሚወሰድ መድኃኒት ሕይወታቸውን ለማቆየት እየታገሉ ያሉት አቶ ግዛው የደረሳቸው ሰሚት ቁጥር ሁለት ሳይት አራተኛ ፎቅ ላይ ነው፡፡ ሕክምና ከሚከታተሉበትና በልብ ሕክምና ከሚጠቀሱ ሆስፒታሎች አንዱ ከሆነው ላንድ ማርክ ሆስፒታል የተሰጣቸውን የሕክምና ማስረጃ አያይዘው ከኅዳር ጀምሮ ለወራት ይመለከታቸዋል ካሏቸው ቢሮዎች ያደረጉት ደጅ ጥናት ምንም ዓይነት ውጤት ሳያስገኝላቸው ቀርቷል፡፡

  ቅድመ ክፍያውን ከዘመድም ከዚያም ከዚያም ብለው ቢከፍሉም ቤታቸው ያልተጠናቀቀ መሆንና ቀጣይ ክፍያ (ወርሃዊ 2250 ብር) ጭንቀት ውስጥ ከትቷቸዋል፡፡ ኮንደሚኒየም ምርጫቸው ሆኖ ሳይሆን ከዚህ አናመልጥም ጊዜ በሄደ ቁጥር ደግሞ ዋጋው ይወደዳል ብለው ነው የወሰኑት፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የጤናቸው ጉዳይ አሳስቧቸዋል፡፡ ‹‹ልማቱ ለአገር ለሕዝብም አይደል እንዴ?›› የሚሉት አቶ ግዛው ከሳይት ኃላፊዎች ጀምሮ፣ ከክፍለ ከተማ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤቶችና ከከተማ አስተዳደሩ ጋር አቤቱታቸውን ይዘው ቀርበዋል፡፡ ስምንት ወር የፈጀው ጥረታቸው ግን እስካሁን ያስገኘው አንዳችም ነገር የለም፡፡ ያላለቀው የቤታቸው ግንባታ ግምት 70,000 ብር ነው፡፡ ሕመማቸውን በሚመለከት የተሰጣቸው ምላሽ በዓይን ከሚታይ የአካል ጉዳት ውጪ እንደሳቸው ላለ ለውስጥ ሕመም መልስ የሚሰጥበት አሠራር አለመኖሩ እንደተገለጸላቸው ይናገራሉ፡፡

  ከተሞችን መልሶ ማልማት በብዙ መልኩ ጠቀሜታው ከፍተኛ እንደሆነ እርግጥ ቢሆንም ይህ መልሶ ማልማት በሚገባ ካልተጠናና በዕቅድ ካልተመራ ነዋሪዎች ላይ ሊያስከትል የሚችለው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ቀላል አይሆንም፡፡ በዚህ ያረጁ ቤቶችን ለማንሳትና ነዋሪዎችን ወደ ተሻሉ ቤቶች ለማስገባት ወይም ቦታዎቹ ለተያዘላቸው የግንባታ ምደባ እንዲተላለፉ በሚደረግ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ሥር የከተማ ልማት ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር አቶ ደመቀ ኃይሌ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ይህ የመልሶ ማልማት ሥራ በደንብ ሊታሰብበትና ሊጠና ይገባል፡፡ የሚነሱ ነዋሪዎች የት ይሂዱ የሚለው ብቻ ሳይሆን በሚሄዱበት ቦታ ሊኖር ስለሚገባቸው የማኅበራዊ አገልገሎቶችም ሊታሰብ ይገባል፤›› የሚሉት አቶ ደመቀ ይህ ሳይሆን ግን የተነሽዎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ደኅንነት እንደሚናጋ ይጠቁማሉ፡፡

  ረዥም ዓመታትን ያስቆጠሩ አካባቢዎችን ማንሳት ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሻ እንደሆነ የሚያሰምሩት አቶ ደመቀ ለተነሽዎች መነገር ያለበት መቼ ነው? መነሳት ያለባቸውስ መቼ ነው? የሚሉት ነገሮች ሁሉ ሊተኮርባቸው እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡ እነዚህ የተጠቀሱ ሁኔታዎች ታስቦባቸውና ከግምት ገብተው እንደሆነ ነዋሪዎች መነሳት ያለባቸው ያስረዳሉ፡፡ ይህ እሳቸው ሊሆን ይገባል የሚሉት ነገር ሲሆን እነዚህ ሁኔታዎች ሳይሟሉ ነዋሪዎች ከመኖሪያቸውና ከንግድ ቦታቸው እየተፈናቀሉ ለመሆኑ ማሳያ የሚሆኑ ኬዞች አሉ፡፡ በካዛንችሱ ቻይና ሠፈር ገፍቶ ባይቀጥልም ቦታው እንደሚነሳ በተገለጸ ማግስት ቤቶችን ማፍረስ መጀመር፣ የዚያው አካባቢ ነዋሪዎች ያልተጠናቀቁና ኤሌክትሪክና ውኃ ያልገባባቸው ቤቶችን እንዲረከቡ መደረግ አቶ ደመቀ መሆን ይገባዋል ከሚሉት በተቃራኒው ነው፡፡

  በሌላ በኩል በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ አካባቢ የ32 በንግድ ላይ የተሰማሩ ነዋሪዎች ለ40 ዓመታት ከሠሩበት ቦታ በመልሶ ማልማት ምክንያት መፈናቀል የአቤቱታቸውም ለስምንት ዓመታት አለመሰማት ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሪፖርተር መዘገቡ ይታወሳል፡፡ ነጋዴዎቹ በአክሲዮን ተደራጅተው ከ40 ዓመት በላይ ሲነግዱ የኖሩበትን ቦታ ለማልማት የጠየቁ ቢሆንም የከተማ አስተዳደሩ ‹‹ነባር አጠቃላይ ነጋዴዎች አክሲዮን›› ለሚባል ማኅበር እነሱ ይሠሩበት የነበረውን ቦታ ጭምር በሊዝ በመውሰዱ ነበር አቤቱታቸውን ያሰሙት፡፡

  ነጋዴዎቹ ሕጋዊ መሆናቸውን የሚገልጹ ማስረጃዎችን በማያያዝ ከወረዳ እስከ ከተማ አስተዳደር ቢሄዱም ያገኙት ምላሽ የለም፡፡ ጉዳያቸውን ወደ ሕዝብ እንባ ጠባቂ የወሰዱ ቢሆንም ይህም መፍትሔ አላስገኘላቸውም፡፡ ዛሬም መፍትሔ ለማግኘት ይመለከታቸዋል የሚሏቸውን የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ደጅ እየጠኑ ነው፡፡

  እየሆነ ያለው መሆን ካለበት የተለየ በመሆኑ ለአቶ ደመቀ ጥያቄ አቅርበን ነበር፡፡ የመልሶ ማልማት ሥራ በተጀመረባቸው ዓመታት ላይ በአጭር ጊዜ ማሳወቅ ነዋሪዎች እንዲነሱ የማድረግ ነገር፣ በበቂ ሁኔታ ግንዛቤ ያለመፍጠር ችግር እንደነበር በማስታወስ አሁን ግን ነገሮች መሻሻላቸውን ይገልጻሉ፡፡ የመልሶ ማልማት በፖሊሲ የሚመራና በፕላን የሚተገበር መሆን የሚጠቀሱ መሻሻሎች ናቸው እሳቸው እንደሚሉት፡፡

  በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሶሺዮሎጂ ዲፓርትመንት መምህር የሆኑት ዶ/ር የራስወርቅ አድማሴ ዛሬም የመልሶ ማልማት እንቅስቃሴ በተጠናና በተቀናጀ ፕላን እየተመራ ነው ለማለት የማያስደፍር ሁኔታ እንዳለ ይገልጻሉ፡፡ በተግባር ካልተተረጐመ በወረቀት ስላለ መመርያ አለ፣ ፕላን አለ አይባልም፤›› ይላሉ፡፡ አቶ ደመቀም አፈጻጸም ላይ የሚታዩ ችግሮች የአቅም ውስንነት ውጤት እንደሆኑ ክፍተቱን ለመሙላት በመልሶ ማልማት የግሉ ዘርፍና ሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ እንደ መፍትሔ የሚጠቁሙት አቅጣጫ ነው፡፡ በመንግሥት ተቋማት በኩል ያለው የአቅም ውስንነትን በሚመለከት እሳቸው ያስቀመጡትና መሰል መፍትሔዎች በተለያዩ ጊዜዎች ተሰንዝረዋል፡፡ በሌላ በኩል የእምቅ ውስንነት ሲነሳ አነስተኛ ገቢ ያላቸውና ለኮንዶሚኒየም መክፈል የማይችሉ ሰዎች ጉዳይ ይነሳል፡፡

  የ65 ዓመቷ አዛውንት ወ/ሮ ፀዳለ ወልደ ፃዲቅ በካዛንችስ ቻይና ሠፈር ነዋሪ ናቸው፡፡ እዚያ ሠፈር ከ30 ዓመታት በላይ ኖረዋል፡፡ በሰኔ አልያም በሐምሌ እንደሚነሱ እንደተገለጸላቸው ነገሩን፡፡ ለሚኖሩባት ጠባብ አንድ ክፍል በወር የሚከፍሉት አምስት ብር ነው፡፡ ኮንዶሚኒየም በእሳቸው አቅም ፈጽሞ የሚታሰብ ባለመሆኑ ከዓመት በፊት አካባቢው እንደሚነሳ ሲገለጽላቸው ምርጫቸው የቀበሌ ቤት መሆኑን አሳውቀው ነበር፡፡ ‹‹የት እወድቅ ይሆን እያልኩ እጨነቃለሁ፡፡ እድር ይበተናል ከጐረቤት ከዘመድ መለያየት አለ፤›› ይላሉ፡፡

  ከአምስት ዓመታት በፊት ፍል ውኃ ፖሊስ ጋራዥ ጀርባ ያለ መንደር ሲነሳ ኮንዶሚኒየም የመግባት አቅም የለኝም ያሉትና የቀበሌ ቤት ተሰጥቷው ካዛንችስ ቻይና ሠፈር ኑሯቸውን የመሠረቱት የስድስት ልጆች እናት ወ/ሮ አስናቀች ሽመልስ ዛሬም ከዚህ ሠፈር በመልሶ ማልማት እንደገና ሊፈናቀሉ ነው፡፡ ኑሮአቸው ከእጅ ወደ አፍ በመሆኑ ዛሬም ምርጫቸው አንድና አንድ ነው፡፡ የቀበሌ ቤት፡፡ ‹‹ምን አማራጭ አለ የትም መሄድ ነው እንጂ›› የሚሉት ወ/ሮ አስናቀችና የእሳቸው ዓይነት ብዙዎች በመልሶ ማልማት ከቦታ ቦታ መዘዋወር የት ላይ ሊቆም ይችላል? የሚል ጥያቄ እዚህ ላይ ሊነሳ ይችላል፡፡ አቅም ለሌላቸው የቀበሌ ቤት መስጠት እንደ አንድ ጊዜያዊ መፍትሔ ታይቶ ከመልሶ ማልማት ጋር በተያያዘ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን በሚመለከት ምናልባትም አቶ ደመቀ እንዳሉት የግሉን ዘርፍና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን ተሳታፊ ማድረግ ዘላቂ መፍትሔ ሊያመለክት ይችላል የሚል አስተያየት የሚሰነዝሩም አሉ፡፡

  ሰማንያ በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ሕዝብ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ በሚገኙ የተጨናነቁ መንደሮች እንደሚኖርና እነዚህ ቤቶች በሌላ መተካት አልያም ከፍተኛ እድሳት እንደሚያስፈልጋቸው በዩኤን ሀቢታት እ.ኤ.አ. በ2010 ጥናት ተመልክቷል፡፡ በ1967 ዓ.ም. የከተማ መሬትና ትርፍ የግል ቤቶች የመንግሥት መሆኑ መታወጅን ተከትሎ በዚያ ዘመን 60 በመቶ የሚሆነው የአዲስ አበባ ቤት በኪራይ ስር የነበረ ሲሆን ከዚህ 93 በመቶ የሚሆኑት ቤቶች የሚተዳደሩት በቀበሌ ነበር፡፡

  የኢሕአዴግ ሥልጣን መያዝን ተከትሎ በነበሩት ዓመታት የታየው የተጨናነቁ መንደሮችን የማንሳትና የመልሶ ማልማት ዕርምጃ በደርግ ዘመን ከነበረው የብዙዎች የመንግሥት የኪራይ ቤቶችን ተከራይቶ መኖር ወደ ግል ቤት ባለቤትነት ማሸጋገር ከአንድ መስመር ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ የመዞር ያህል ነው፡፡ ጥያቄው በዚህ የአቅጣጫ ለውጥ ውስጥ ይህ ነው የሚባል ገቢ የሌላቸው እንደ ወይዘሮ አስናቀችና ፀዳለ ያሉ ብዙዎች እንዴት ያልፋሉ? የሚለው ይሆናል፡፡

  በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሀሊማ ባድገባ የተጨናነቁ መንደሮች ለኗሪዎቹ ለከተማው ልማትና ገፅታ ሲባል መነሳት አለባቸው ይላሉ፡፡ ይህ የመልሶ ማልማት እንቅስቃሴም በዕቅድ እየተመራ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ከካዛንቺሱ ቻይና ሰፈር የሚነሱ ኗሪዎች ያላለቁ ቤቶች መረከባቸውንና ከጥቂት ቀናት በኋላ ሊነሱ መሆኑን በማስመልከት ጥያቄ አንስተንላቸው ሲመልሱ ‹‹ችግር ያለው ባለ 2 እና 3 ክፍል መኝታ ቤት ኮንደሚኒየም የመረጡ ኗሪዎችን በሚመለከት ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ቤቶች ያሉት ከከተማ ወጣ ባሉና መሠረተ ልማት ባልተሟላላቸው አካባቢዎች ላይ ነው›› ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል ኗሪዎች መቼ እንደሚነሱ በእርግጠኝነት እንደማያውቁ ቢገልጹም ‹‹ወደ ኮንደሚኒየም ግቡ አልተባሉም›› ይላሉ፡፡

  አቅም የሌላቸውና በተደጋጋሚ መንደሮች በልማት በተነሱ ቁጥር እንደ ወይዘሮ አስናቀች ያሉ ከቀበሌ ቤት ወደ ቀበሌ ቤት ለመዘዋወር የሚገደዱ ብዙዎች ችግር በዘላቂነት ሊፈታ የሚችልበት መንገድን በሚመለከት ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ጊዜያዊ መፍትሔው የቀበሌ ቤት መግባት ብቻ እንደሆነ፣ የረዥም ጊዜ መፍትሔ የሚታሰበው በሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ መንግሥት የሚችለውን ሁሉ እየሠራ እንደሆነ የሚናገሩት ወይዘሮ ሀሊማ መንግሥት በቅርቡ ባስተላለፋቸው 35,000 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከሊዝ ሊያገኝ የሚችለውን 7.2 ቢሊዮን ብር ማጣቱን መንግሥት ምን ድረስ እየሄደ እንደሆነ በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡   

  በአዲስ አበባ መልሶ ማልማት ፕሮግራም ከተጀመረ 10 ዓመታት በላይ ተቆጥሯል፡፡     

  ምሕረት አስቻለው እና ጥበበሥላሴ ጥጋቡ

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...

  ሰበበኞች!

  ዛሬ የምንጓዘው ከሜክሲኮ ወደ አየር ጤና ነው፡፡ ዛሬም፣ ነገም...