Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናተቃዋሚ ፓርቲዎች በአባላቶቻቸው መገደል መንግሥትን እየወቀሱ ነው

  ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአባላቶቻቸው መገደል መንግሥትን እየወቀሱ ነው

  ቀን:

  –  መንግሥት የፓርቲዎቹን መግለጫ ውድቅ አድርጓል

  በአንድ ቀን ልዩነት የአረና/መድረክ እና የሰማያዊ ፓርቲ አባላት በተለያዩ ሥፍራዎች ተገድለው በመገኘታቸው ምክንያት ሰማያዊ ፓርቲና አረና/መድረክ በመንግሥት ላይ ወቀሳ አቀረቡ፡፡

  ሰኔ 8 ቀን 2007 ዓ.ም. በአማራ ክልል በምሥራቅ ጎጃም ዞን በደብረ ማርቆስ ከተማ አቶ ሳሙኤል አወቀ የተባሉ የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩ ሲገደሉ፣ በማግሥቱ አቶ ታደስ አብረሃ የተባሉ የአረና/መድረክ አባል በትግራይ ክልል ምዕራብ ዞን ማይካድራ ከተማ  መገደላቸውን ሁለቱም ፓርቲዎች አስታውቀዋል፡፡

  አረና/መድረክ ባወጣው መግለጫ አባሉ በምዕራብ ትግራይ ዞን የድርጅቱ ጉዳይ ኃላፊ ሆነው በ2007 ምርጫ ወቅት፣ የፓርቲውን ሥራ በማደራጀትና በማንቀሳቀስ ከፍተኛ ሚና ሲጫወቱ የቆዩ መሆናቸውን፣ ሰኔ 9 ቀን 2007 ዓ.ም. ከምሽቱ 3፡00 ሰዓት ለጊዜው ባልታወቁና ቤታቸው በመጡ ሦስት ሰዎች ግድያ እንደተፈጸመባቸው አስታውቋል፡፡

  ፓርቲው የገዳዮቹን ማንነት አለመታወቁን በጠቆመበት መግለጫ፣ ሟች አባሉ ከግድያው ቀደም ብሎ በመንግሥት የፀጥታ ሠራተኞች ወከባና ማስፈራርያ ይደርስባቸው እንደነበር ጠቁሟል፡፡

  ‹‹ለጉዳተኛው የሕክምና ዕርዳታ እንዲደረግላቸው ለማስተባበርና ወንጀለኞችም ለመከታተልና ለማስያዝ የተደረገው ሙከራ በፖሊሶች አለመተባበር›› ሳይሳካ መቅረቱን በመግለጫው አረና/መድረክ አስታውቋል፡፡

  በተመሳሳይም ሰማያዊ ፓርቲ አቶ ሳሙኤል የተባሉ አባሉ ከመገደላቸው በፊት፣ በደኅንነት ሠራተኞችና በአካባቢው ሹሞች የግድያ ማስፈራርያ ይደርሳቸው እንደበር ገልጿል፡፡

  የምሥራቅ ጎጃም ዞን ፖሊስ መምርያ በበኩሉ አቶ ሳሙኤል በሁለት ግለሰቦች መገደላቸውን ገልጾ፣ አንደኛው ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር ውሎ ሲመረመር ግድያውን መፈጸሙን ማመኑን አስታውቋል፡፡

  ነገር ግን የፖሊስን መግለጫ ሙሉ በመሉ ውድቅ ያደረገው ሰማያዊ ፓርቲ፣ ‹‹የሰማዕታት ደም ይጮሃል፣ ይጣራል›› በሚል ርዕስ ሰኔ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹ይህ ሥርዓት በሕግም፣ በሞራልም ኢትዮጵያን የማስተዳዳር ብቃት የለውም፡፡ ወንጀለኞችን ለፍርድ ይቅረቡ እያልን አናላዝንም፣ ወንጀለኞቹ የመንግሥት አካላት ናቸውና፤›› ሲል መንግሥትን ምንም ዓይነት ፍትሕ እንደማይጠብቅም ገልጿል፡፡

  እንዲሁም አረና/መድረክ በበኩሉ በትግራይ ክልል ከ17 በላይ አባላት ጨምሮ በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ ክልሎች በአባላት ላይ እስራት፣ ግርፋትና ግድያ እየተፈጸመባቸው መሆኑን በመግለጫው አስፍሯል፡፡

  መንግሥት በበኩሉ ክሶቹን ውድቅ በማድረግ ተገደሉ በተባሉት ሰዎች እጁ እንደሌለበት ገልጾ፣ ትችቶቹ ሁሉ እውነትነት የሌላቸው መሆኑን አስታውቋል፡፡

  በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሽመልስ ከማል፣ ‹‹ሁለቱም የተቃዋሚዎች አባላት በግለሰቦች መገደላቸውንና ጉዳዮችን ይዞ ለፍርድ ለማቅረብ ፖሊስ ምርመራውን ቀጥሏል፡፡ መንግሥት እንደሚያምነው የሁለቱ ዜጎች መገደል ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ይዘት የለውም፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

  በተለይ የሰማያዊ ፓርቲ አባል ግድያ አሳዛኝ እንደሆነ፣ ሟች ከቀድሞ ደንበኞቹ ጋር በተፈጠረው አለመግባባት መገደሉን ፖሊስ አረጋግጧል  ካሉ በኋላ፣ አቶ ታደሰ በማይታወቁ ሰዎች ከመገደላቸውና ፖሊስ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ከማወቃቸው ውጪ፣ ገና መረጃው እንዳልደረሳቸው አቶ ሽመልስ ገልጸዋል፡፡

  ከዚህ በተጨማሪ የአረና/መድረክ አባልን ግድያ በተመለከተ የትግራይ ክልል የፀጥታና የደኅንነት ቢሮን ምላሽ ለማግኘት ሪፖርተር ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም፣ ኃላፊዎችን በስብሰባ ምክንያት ለማግኘት ባለመቻሉ አስተያየታቸውን ማካተት አልተቻለም፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...

  ሰበበኞች!

  ዛሬ የምንጓዘው ከሜክሲኮ ወደ አየር ጤና ነው፡፡ ዛሬም፣ ነገም...