Sunday, August 14, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ጎብኚዎች የሚያኖሯት የቱሪስት መናኸሪያዋ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ታሪኳ ከብዙ ሺሕ ዓመታት በላይ ወደ ኋላ ይሳባል፡፡ አንዴ ግሪኮች ሌላ ጊዜ ሮማውያን ተፈራርቀው ገዝተዋታል፡፡ የጥንቱ የሮም ባዛንታይን ስርወ መንግሥት ትልቅ አሻራውን ያሳረፈባት ቱርክ፣ እንደውም በንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ዘመን ከሮም ቀጥላ በዓለም ሁለተኛዋ የንግሥናው ከተማ እንድትሆን በማሰብ የገነባት ቆስጥንጥንያ ወይም የዛሬዋን ኢስታንቡል ጨምሮ የኤፌሶን ከተማ በዘመኗ የገነነች የብዙ ታሪክ መገኛ ናት፡፡ ከቆስጠንጢኖስ ባሻገር ታላቁ እስክንድር ግዛቱን ያፈረጠመባት፣ የሮማን የበላይነትና የግዛት ታላቅነት ያሳየባት የጥነቷ ቱርክ፣ የቅድመ ታሪክ ዳራዎቿ አናቶሊያ የሚል ስያሜ እንደነበራት ይተርካሉ፡፡ ይኸው የቀደመ ታሪኳ ሚሊዮኖች አገርና አኅጉር አቋርጠው፣ ባህር ተሻግረው ለማየት የሚጋፉባት አገር ሆና እንድትገኝ አስችሏታል፡፡

  ከዋና ከተማዋ ማለትም መንግሥታዊ መቀመጫዋ ከሆነችው የአንካራ ከተማ ውጭ፣ በርካቶች የቱርክ ከተሞች በቱሪስቶች እንደተጨናነቁ ይከርማሉ፡፡ በተለይ በበጋው ወራት የውጭ አገር ጎብኝዎች ብቻም ሳይሆኑ የአገሬው ከበርቴዎች ነቅለው ለመዝናናትም ሆነ ለመጎብኘት የሚመርጧቸው ታሪካዊና በተፈጥሮ የታደሉ ውብ ሥፍራዎችን በጉያዋ ሸሽጋለች፡፡

  የጥንት የሰው ልጅ የሥልጣኔ፣ የአኗኗር፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊና መሰል ክንውኖችን ትናንት የተፈጸሙ እስኪመስሉ ድረስ በቱርክ በአግባቡ ተጠብቀውና ታድሰው ዘመን ተሻግረው ዛሬም ድረስ ይኖራሉ፡፡ ይጎበኛሉ፡፡ በእየሩሳሌም የኢየሱስ ክርስቶስ ታሪኮች ጎልተው ይተረካሉ፡፡ ከውልደቱ እስከ አሟሟቱ፣ እስከ እርገቱ ያሉት ታሪኮች በእየሩሳሌምና በዙሪያ ገቧ ጎልተው ይጠቀሳሉ፡፡ ቱርክ የሐዋርያት ታሪክ በተለይ ደግሞ የቅዱስ ጳውሎስ ታሪክ ይነገርባታል፡፡ እርግጥ ድንግል ማርያም እንደጎበኘቻትና ‹‹የድንግል ማርያም ቤት›› እየተባለች የምትጠራ ቤተ ክርስቲያንም በቱርክ ከሚጎበኙ አበይት የታሪክ ሥፍራዎች ውስጥ ትካተታለች፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች የጻፈው መልዕክት በመጽሐፍ ቅዱስ አማኞች ዘንድ የሚታወቅ ነው፡፡ የዚህ ታሪክ መገኛ የሆነችው ኤፌሶን ከተማ ዛሬም ስለጥንቱ ከፍርስራሾቿ ብዙ የምትናገረው፣ የምትዘክረው ቅሪት ይዛለች፡፡ በኢስታንቡል ከተማ ደግሞ ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ገላትያ ሰዎች በሚል የከተበው መልዕክት ሲታወስ፣ በኢስታንቡል የቆየው የከተመው ክፍልም የገላትያ መንገድ፣ ገላትያ አደባባይ፣ የገላትያ ምኩራብ አሁንም ድረስ ይታወሳሉ፡፡ ቅዱሱ መጽሐፍም ስለገላትያና ስለነዋሪዎቿ ከትቧል፡፡

  የዛሬዋ ቱርክ የጥንቷን ገላትያ፣ ጋላታሳራይ በሚል መጠሪያ የምትዘክራት ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ የእግር ኳስ ክለቦቿ ከሆኑት አንዱ ጋላታሳራይ በኢስታንቡል ይገኛል፡፡ በዓመት ከ37 ሚሊዮን በላይ ቱሪስቶች የሚጎበኟትና ከአሥር ዋና ዋና የቱሪስት መዳረሻ አገሮች ተርታ የምትሰለፈው ቱርክ፣ በጥንቱ መጠሪያዋ ታናሿ እስያ ወይም አናቶሊያ ተብላም የምትታወቅ ሲሆን፣ የአውሮፓና የእስያ መገናኛ ማዕከል ትመስላለች፡፡ በአንድ ጫፏ ከቡልጋሪያ፣ ከጆርጂያ፣ ከአርሜንያ፣ ከግሪክ፣ ከሩስያ፣ ከአዘርባጃንና ከሌሎች የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች ስትጎዳኝ፣ በሌላኛው ጎኗ ደግሞ ከሶሪያ፣ ከኢራቅ፣ ከኢራንና ከሌሎችም አገሮች ጋር ትዋሰናለች፡፡

  የአሁኗን ወይም ዘመናዊዋን ቱርክ የመሠረቱትና የቱርክ መሥራች የሚባሉት . ሙስጣፋ ከማል አታቱርክ ብዙ የሚነገርላቸው ሰው ናቸው፡፡ ቱርክ እ.ኤ.አ. ከ1453 እስከ 1923 በዘለቀው የኦቶማን ቱርክ አገዛዝ ሥር የቆየችውን ቱርክ በመቀየርና ዘመናዊቷን ቱርክ ሪፐብሊክ መንግሥት በመገንባት ያደረጉት አስተዋጽኦ ይነገርላቸዋል፡፡ አውሮፓዊ ገጽታ አላብሰዋታል ይባልላቸዋል፡፡ የመጀመርያው የቱርክ ፕሬዚዳንት በመሆንም በሕገ መንግሥት የምትመራ፣ ሃይማኖትና መንግሥት የተለያዩባት አገር ለመሆን በቅታለች፡፡ የአታተሩክ ኃውልቶችና ምስሎች በቱርኮች መገበያያ ገንዘብ ሊራ እንዲሁም በየአደባባዮቻቸው ታትሞ ይታያል፡፡

  ጥንታዊቷ ኤፌሶን

    ጎብኝዎች የሚጋፉባቸው፣ ሰው አልባ በራሪ መሣሪያዎችንና ዘመናይ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የተለያዩ የጥንት ፍርስራሾን ከሚቀርጹባቸው ታሪካዊ ሥፍራዎች መካከል፣ ኤፌሶን ትጠቀሳለች፡፡ የጥንቷ ኤፌሶን ከተማ፣ ከኢስታንቡል 392 ኪሎ ሜትር ርቃ፣ ከሪዞርት ከተማዋ ቦድሩም የሁለት ሰዓት የመኪና ጉዞ በኋላ የሚደረስባት ከተማ ናት፡፡ ሴልሹክ በምትባለው ግዛት ድንበርተኛ ሆና በኢዝሚር ግዛት ፈንጠር ብላ የምትገኘው ኤፌሶን፣ ከክስርቶስ ልደት በፊት ከ6000 ዓመታት በላይ የቆየ ታሪክ ያላት ከተማ ናት፡፡

  እንደ አብዛኞቹ የቱርክ ከተሞች በወንዝ ዳርቻ ላይ የተመሠረተችው ኤፌሶን፣ አጂያን የተባለው ወንዝ ዙሪያዋን ከቧታል፡፡ በኤፌሶን ከተማ ዳርቻዎች ከሚታየው የተንጣለለ ባህር ባሻገር፣ የወይራ ዛፍ ባህር ዓይን እስኪታክተው ድረስ ቢታይ ማለቂያ የለውም፡፡ በአውሮፓ የወይራ ዘይት ወደ ውጭ በመላክም ቱርክ ስማቸው ከሚነሳ አገሮች ተርታ ትሰለፋለች፡፡ ከቦድሩምና ከኢስታንቡል በተጨማሪም አንታሊያ ከተማ የሪዞርት ከተማ በመሆን ለቱሪስቶች የተመቸች ናት፡፡ በየቱሪስት መዳረሻዎች የሚታየው ጽዳት፣ አቀባበል፣ የሚቀርቡት አገልግሎቶች በሙሉ ቱርክን በአሥርት የሚቆጠሩ ሚሊዮኖች ቢጎበኟት እንደማይዘባት የሚመሰክሩ ናቸው፡፡

  በበዶሩም ከሚጎበኙ የጥንቷ ቱርክ ቅሪቶች መካከል የውኃ ውስጥ አርኪዎሎጂ ውጤቶችን የሚያሳየው ሙዘየም የሚገኝበት፣ ቦድሩም የውኃ ውስጥ የአርኪዎሎጂ ሙዚየም ይገኝበታል፡፡ ሙዚየሙ በጥንታዊው የቦድሩም ግንብ (ካስል) ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ የዚህ ግንብ ግንባታ በቅዱስ ጂዬን ጊዜ የቱርክና የሮማ መሳፍንት አማካይነት እ.ኤ.አ. ከ1406 እስከ 1522 ባለው ጊዜ ውስጥ መገንባቱ ይነገርለታል፡፡ የጨረቃ ቅርጽ ያለው ይህ የቦድሩም ግንብ እ.ኤ.አ. በ1964 በተደረገ አሰሳ የተገኘ ሲሆን፣ በውስጡ በርካታ የጥንት መርኮችን፣ የጥንት ጠርሙስ ሥራዎችን፣ የተለያዩ መጠጥ ማዓይነቶችና ማስቀመጫና ዘመናት ያስቆጠሩ የእርሻ ዘር ማኖሪያ የሸክላ ውጤቶች ይገኙበታል፡፡ ግንቡ በዋናነት የተገነባው በጥንታውያኑ የመስቀሉ ጦርነት አዝማቾች ሲሆን፣ ዓላማውም ወደ ኢየሩሳሌም የሚደረጉ የባህር ላይ የንግድ እንቅስቃሴዎችን የባህር ላይ ወንበዴዎችን ለመከላከል ታስቦ እንደነበር ታሪኩ ይዘክራል፡፡

  ወዲህ ወደ ኢስታንቡል ከተማ ሲመጣ ደግሞ ‹‹ሃጊያ ሶፊያ›› እየተባለ የሚጠራው ሙዚየም የከተማዋ ትልቅ ቅርስ ነው፡፡ በስድስተኛው ክፍለ ዘመን መገንባቱ የሚነገርለት ሃጊያ ሶፊያ መጀመሪያ ለቤተ ክርስቲያንነት የተገነባ ትልቅ ቤተመቅደስ ነበር፡፡ ሦስት ጊዜ ፈርሶ እንደገና የተገነባ ሲሆን፣ በሦስተኛው ግንባታ ግዙፍ ተደርጎ የተገነባ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ መቅደስ ከመሆኑም ባሻገር፣ ንጉሥ ሰሎሞን ከገነባው ቤተ መቅደስ የበለጠ እንዲሆን ተብሎ 161 ምሰሶዎች እንዲኖሩት ተደርጎ ታንጿል፡፡ ይህ ቤተ መቅደስ በኋለኛው ዘመን በኦቶማን ቱርኮች ወደ መስጂድነት ተቀይሮ የእስልምና ዕምነት ተከታዮች ሲገለገሉበት ቆይቷል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1935 ወዲህ ግን በሙዚየምነት ለዓለም ቱሪስቶች መናኸሪያ ሆኖ ይገኛል፡፡ ሮማውያኑ ከገነቡት በኋላ ‹‹የዕውቀት ቤተ መቅደስ›› የሚል ዓይነት ስያሜ እንደሰጡትና በዚያው ስያሜው ዛሬም ድረስ ይጠራበታል፡፡ ጥቂት ሜትሮች ከሃጊያ ሶፊያ ርቆ የሚገኘው ታላቁ መስጂድ ሱልጣን አህመድ የሚባል ሲሆን፣ በቅጥል ስሙ ሰማያዊው መስጂድ ‹‹ዘ ብሉ ሞስክ›› የሚል መጠሪያ አትርፏል፡፡ በግዙፍነቱና በትልቅነቱም ከሃጊያ ሶፊያ የሚፎካከር ቤተ አምልኮ ነው፡፡

  ታላቁ ‹‹ግራንድ ባዛር››

  በኢስታንቡል በርካታ ዓይን የሚስቡ ታሪካዊ ሥፍራዎችና መስህቦች ቢኖሩም፣ በወፍበረር ቅኝት ሁሉን ማዳረስ ይከብዳል፡፡  ይህም ሆኖ በኢስታንቡል መሐል ከተማ የተንሰራፋው ታላቁ ግራንድ ባዛር እ.ኤ.አ. በ1453 የተገነባ ነው፡፡ ስፋቱ 200 ሺሕ ካሬ ሜትር የሆነው ግራንድ ባዛር ከአራት ሺሕ በላይ መደብሮች የተገጠገጡበት የግብይት መናኸሪያ ነው፡፡ እጅግ ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ ዙሪያ ገባውን አዳርሶ ለመውጣት አንድ ቀንም የማይበቃው ጥንታዊ የገበያ ሥፍራ ሲሆንም አሁንም ድረስ በሚገባ እያገለገለ ይገኛል፡፡ በርበሬ፣ ዕርድና ሌላውም ቅመማቅመም፣ ወርቅ፣ ብርና አልማዝን ጨምሮ ከባህላዊ አልባሳትና ቁሳቁሶች እስከ ዘመናዊ መገልገያዎች የታጨቁበት ግራንድ ባዛር፣ በቱሪስቶች የሚጣበብ ትልቅ የገበያ መናኸሪያ ነው፡፡ በየመደብሮቹ ከተገጠገጡት ዕቃዎችና ከሚነግዱት ነጋዴዎች ባሻገር፣ በየጥጋጥጉ በክንዳቸውና በጉያቸው ልዩ ልዩ ሸቀጦችን ታቅፈው የሚሸቅጡ ተባራሪ ነጋዴዎችም የግራንድ ባዛር ተጋሪዎች ናቸው፡፡ የዋህ የመሰላቸውንና አትኩሮቱን ወደ እነሱ የሳበ ጎብኝ ያገኙ ጊዜ መላቀቂያ የላቸውም፡፡ ትክት እስኪለው ድረስ ልቡን አጥፍተው ያላሰበውን እንዲገዛ ይወተውቱታል፡፡ በግራንድ ባዛር ሌላው አስገራሚ ነገር የዋጋ ድርድር ነው፡፡ ልክ እንደመርካቶ ዋጋ በግምት ነው፡፡ ዋጋ እንኳ የተለጠፈባቸው ዕቃዎች ላይ ድርድር ይደረጋል፡፡ ሃምሳ ዶላር የተባለውን ዕቃ ተከራክረው በአሥር ወይም በአሥራ አምስት ዶላር ሸምተው ይወጣሉ፡፡ ግራንድ ባዛር የሁሉም ዓይነት ገበያ ነው፡፡

  ከገበያውም ከጥንታዊና ታሪካዊ ቦታዎች ጉብኝት የተነሳ ድካም የተሰማው ኪሱ ሞላ ያለ ጎብኝ፣ የባህር ላይ ሽርሽር ለማድረግ የሚያስችሉ የባህር ላይ ታክሲዎች አሉለት፡፡ በጀልባ ታክሲዎች ተሳፍሮ ከአውሮፓዋ ኢስታንቡል ከሦስት ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ወደ እስያው ኢስታንቡል በማምራት ውድ ከሆኑት ቪላ ቤቶች መደዳ፣ ከሚገኙ ውብ ሬስቶራንቶች ራቱን ይመገባል፡፡ ወደ እስያው የኢስታንቡል ክፍል የሚያቀና ሰው ምራማራ (እምነበደር) ባህርን እየቀዘፈ፣ የአውሮፓና የእስያ መገናኛቸው ከሆነው ከትልቁ የቦስፎረስ ድልድይ ሥር ቀዝቃዛውን አየር እየማገ ያልፋል፡፡ ሲመለስም የቦስፎረስ  ድልድይ በቀለም መብራቶች ተሸቆጥቁጦ ዓይኑን ያጥበረብረዋል፡፡ 

   

   

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች