Thursday, August 11, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ኢትዮጵያ ዋስትና ያለው ሰላምና ዴሞክራሲ ይገባታል!

  ለአገራችን ኢትዮጵያ ሰላምና ዴሞክራሲን ከመመኘት በላይ፣ ለተግባራዊነቱ ርብርብ የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ ዋስትና ያለው ሰላምና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ቅንነት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ቅንነት በመነጋገር፣ በመደራደርና የጋራ ውሳኔ ላይ በመድረስ ሰፊውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያማከለ መግባባት ለመፍጠር ማገዝ አለበት፡፡ ምንም እንኳ ፖለቲካ በባህሪው ከቅንነት በላይ ውስብስብና መሰናክሎች የበዙበት የሥልጣን ፍትጊያ ቢኖርበትም፣ ለሕዝብ ደኅንነትና ለአገር ህልውና ሲባል በሰጥቶ መቀበል መርህ መመራት አለበት፡፡ የፖለቲከኞች የመጨረሻ ግብ ሥልጣን ቢሆንም፣ የሥልጣኑ ሉዓላዊ ባለቤት ሕዝብ መሆኑን ከልብ ማመን ተገቢ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩ የሚኮራበት ትልቁ እሴቱ ችግሮቹን በማስተዋልና በአርቆ አሳቢነት የመፍታት ፀጋው ነው፡፡ በአራቱም ማዕዘናት የሚገኘውን ጨዋና አስተዋይ ሕዝብ የሚመጥን በሳል የፖለቲካ ውሳኔ ላይ በመድረስ፣ አገሪቱን ከገጠማት ፈተና መታደግም ሆነ ሕዝብን ከጭንቀት መገላገል የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡ ዋስትና ያለው ሰላምና ዴሞክራሲም የሚሰፍነው በዚህ መሠረት ለመሥራት መንቀሳቀስ ሲቻል ብቻ ነው፡፡

  ይህች ታሪካዊ አገር መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆማ ልጆቿን በምትማፀንበት በዚህ ወሳኝ ጊዜ፣ ከግለሰባዊና ቡድናዊ ፍላጎቶች በመላቀቅ አገርን መታደግ ያስፈልጋል፡፡ ጥልቅ የአገር ፍቅር ስሜት ያላቸው ኢትዮጵያዊያን አገራቸው ሰላም እንዲሰፍንባት፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባባትና ለሁሉም ልጆቿ እኩል እናት እንድትሆን ከቃል በላይ ተግባር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከሥልጣን በላይ አገርና ሕዝብን ማስቀደም ተገቢ ነው፡፡ የወጣቱን ትውልድ ተስፋ የሚያለመልሙና የተጀመሩ የልማትና የዕድገት ጉዞዎችን የሚያስቀጥሉ ታሪካዊ ዕርምጃዎች መወሰድ አለባቸው፡፡ ይህች አገር ልጆቿ በነፃነት አንገታቸውን ቀና አድርገው የሚራመዱባትና ከገባችበት ቀውስ ውስጥ ጎትተው የሚያወጧት እንድትሆን፣ በኢትዮጵያዊ ጨዋነትና አስተዋይነት ፀጋ በመመራት በአንድነት መቆም  ተገቢ ነው፡፡ የፈለገውን ያህል ልዩነት ቢኖር እንኳን፣ ልዩነቱን ለማስተናገድ የሚረዳ አማካይ በመፍጠር መነጋገርና መደራደር የዴሞክራቶች የተለመደ ተግባር ነው፡፡ ማዶ ለማዶ ቆሞ መፋጠጥ ወይም ጥርስ እየተነካከሱ ለፀብ መጋበዝ ጊዜ ያለፈበት ነው፡፡ ሰላምና ዴሞክራሲ ዕውን የሚሆኑት በዴሞክራቶች ስለሆነ፣ በዚህ ቁመና ላይ መገኘት የማይታለፍ የወቅቱ ጥያቄ ነው፡፡

  በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠረው የእልህና የግትርነት በሽታ አገርን እንዳሳመመ መቀጠል የለበትም፡፡ በተለይ በዚህ አሳሳቢና ውሉ በማይታወቅ ጊዜ በለመዱት መንገድ መቀጠል የማይሞከር መሆኑን መተማመን ይገባል፡፡ ከአገር ህልውና በላይ ምንም ነገር ሊኖር አይችልም፡፡ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ተተኪውን ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሰየም ዝግጅት እያደረገ ባለበት በዚህ ወቅት፣ ከምንም ነገር በላይ አገርና ሕዝብን ማሰብ አለበት፡፡ ኢሕአዴግ በውስጥ የሚያደርገውን ፍጭት አጠናቆ አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሰይም፣ አገሪቱ ባለፉት ሦስት ዓመታት የገጠማትን ፈተና ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ለዘላቂ ሰላምና ዴሞክራሲ የሚበጀውን ሁሉ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ አዲሱ ተሿሚ የኢትዮጵያን ሕዝብ በእኩል የሚያይ፣ ለአገር አንድነት ተግቶ የሚሠራ፣ ብልሹ አሠራሮችንና ፀረ ዴሞክራሲ ድርጊቶችን አምርሮ የሚታገልና ለወደፊቷ ዴሞክራሲያዊት አገር ፅኑ መሠረት የሚያስቀምጥ ብልህና አርቆ አሳቢ ቢሆን ጥቅሙ ለአገር ነው፡፡ ሁሉንም ሰው በአንድ ጊዜ ማስደሰት ባይቻልም፣ ቢያንስ የጋራ መግባባት በመፍጠር ለልማትና ለዕድገት የሚያነሳሳ ተተኪ ማግኘት ጥቅሙ ለአገርና ለሕዝብ ነው፡፡ ሕዝባዊነት በተግባር የሚረጋገጠውም በዚህ መንገድ ነው፡፡

  አገሪቱ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ገብታ ያ ሁሉ ሞትና ውድመት ያጋጠመው መንግሥት ሕዝብን ባለማዳመጡ ምክንያት ነው፡፡ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወደ ሌላ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተሸጋገርነውም ቀውሱ ተባብሶ አጥፊነቱ በመጨመሩ ነው፡፡ ቀውሱ ለአገሪቱ ገጽታም ሆነ ህልውና አይጠቅምም፡፡ ለሕዝብ ሕይወትና ንብረትም ሥጋት ነው፡፡ በዚህ ዓይነቱ ሁኔታ ውስጥ መቆየት ራስን በራስ ከማጥፋት አይተናነስም፡፡ ቀውሱ እንዲያበቃና አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ፖለቲካዊ መፍትሔ ያስፈልጋል፡፡ በዚህም መሠረት የሕግ የበላይነትን በማስፈን ዘለቄታ ያለው ሰላምና ዴሞክራሲ ማምጣት ይቻላል፡፡ ይህ ይሆን ዘንድ ደግሞ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለአገርና ለሕዝብ ማሰብ ይገባል፡፡ የሥልጣን ሽግግሩ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ከአጉል ገመድ ጉተታ መውጣት የግድ ነው፡፡ አሁን ወቅቱ ለአገር ምን ይበጃል በማለት የሚነጋገሩበት እንጂ፣ ‹እኛና እነሱ› እየተባባሉ በመቃቃር ሰላምን ማደፍረስ አይደለም፡፡ መረር ቢል እንኳን ተጨባጩን እውነታ በመረዳት ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ሸብረክ ማለት ተገቢ ነው፣ ያስከብራል፡፡

  በዚህ ወሳኝና ታሪካዊ ወቅት በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ ማኅበራት ወይም ግለሰቦች ማጤን ያለባቸው፣ አገርን ከድጡ ወደ ማጡ የሚከቱ ሽኩቻዎች ላይ ከማተኮር ይልቅ ዋስትና ያለው ሰላምና ዴሞክራሲያዊ ምዕራፍ እንዲፈጠር ዕገዛ ማድረግ ጠቃሚ መሆኑን ነው፡፡ የአገር ጉዳይ የጋራ መሆኑ እስከታመነ ድረስ ከቧልትና ወንዝ ከማያሻግር ስላቅ መላቀቅ ይገባል፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያዎችም ሆነ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን አማካይነት በአገር ጉዳይ የሚነጋገሩ ወገኖችም፣ ከጎራ ፖለቲካ አሠላለፍና ቡድንተኝነት በመላቀቅ ለአገርና ለሕዝብ ጥቅም ማሰብ አለባቸው፡፡ አገር ከጠባብ ቡድናዊ አመለካከትና መሳሳብ በላይ መሆኗን ማመን ተገቢ ነው፡፡ የወደፊቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ንጣፍ በአግባቡ እንዲጀመርና የሕዝብ ተስፋ እንዲለመልም፣ ከማያስፈልጉ ውዝግቦችና እሰጥ አገባዎች መታቀብ የሚጠቅመው ለአገር ነው፡፡ እስካሁን የተመጣበት መንገድ የፈየደው ከሌለ፣ የባሰ ችግር ለመፍጠር መሯሯጡ ማንንም አይጠቅምም፡፡ ለአገርም አይበጅም፡፡ አሁን የሚፈለገው ኢትዮጵያን ከገባችበት አጣብቂኝ በማውጣት ዋስትና ላለው ሰላምና ዴሞክራሲ ማዘጋጀት ብቻ ነው፡፡

  ይህ ጨዋ፣ ኩሩና አስተዋይ ሕዝብ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ብልፅግና ያስፈልገዋል፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት፣ በነፃነት የፈለገበት ሥፍራ የመኖርና ሀብት የማፍራት መብት፣ በነፃነት የፈለገውን የመምረጥ መብት፣ በሕግ ፊት እኩል የመሆን መብት፣ በአገር ሁለንተናዊ ጉዳዮች የመሳተፍ መብት፣ ወዘተ. የሚገኝበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው ልዩነትን አስታርቆ መነጋገርና መደራደር ሲቻል ብቻ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ከቤተሰብ እስከ አገር ድረስ ለጋራ ጉዳይ መነጋገርና መደራደር የሚቻልበት ባህል መፍጠር ይቻላል፡፡ ጨዋውና አስተዋዩ ሕዝብ ዘመናትን የተሻገረውና አገርን ከትውልድ ወደ ትውልድ እያቀባበለ የኖረው በዚህ መሠረት ነው፡፡ ሕዝቡ በክፉና በደግ ጊዜያት ተከባብሮና ተስማምቶ በፍቅር የዘለቀው ለትውልዶች አርዓያነት ባለው ተምሳሌቱ ነው፡፡ ይህንን ተምሳሌት አስከብሮ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታዋ መመለስ የግድ ነው፡፡ ኢሕአዴግም ሆነ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች ሰላምን ማስቀደም አለባቸው፡፡ ዴሞክራሲ የህልውና ጉዳይ መሆኑን ማመን የግድ ይላል፡፡ የፖለቲካ  ቀውስ ውስጥ እየገቡ ሕዝብን ማተራመስና አገርን ማመሰቃቀል ፋይዳ የለውም፡፡ ኢትዮጵያ አገራችን ብሩህ ጊዜ ከፊቷ ስላለ ወደ ጨለማ ማፍጠጥ አይገባም፡፡ በዚህ ታሪካዊና ወሳኝ ጊዜ የኢትዮጵያችንን ውድቀት አሰፍስፈው ለሚጠባበቁ ታሪካዊ ጠላቶችም ሆነ፣ በተፈጠረው ቀውስ ምክንያት ግራ ለተጋባው ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ እኛ ኢትዮጵያውያን ከአያትና ከቅድመ አያቶቻችን የተረከብነውን አስተዋይነትና ተምሳሌታዊነት በማሳየት ታሪክ መሥራት ይገባናል፡፡ በአውሮፓ ኮሎኒያሊስት ኃይል ላይ ታላቁን የዓደዋ ድል የተቀዳጀችበት 122ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል ዋዜማ ላይ ያለች ታላቅ አገር ወደ ታላቅነቷ መመለስ አለባት፡፡ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች ታላቅ ተምሳሌት የሆነችው ኢትዮጵያችን በዚህ ዘመን ዋስትና ያለው ሰላምና ዴሞክራሲ ይገባታል መባል አለበት!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

  በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...

  የአገሪቱ ባንኮች ካፒታል 199.1 ቢሊዮን ብር ደረሰ

  ከታክስ በኋላ 50 ቢሊዮን ብር ማትረፋቸውን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ የአገሪቱ...

  የማስተማር ሙያ ሥልጠና ባልወሰዱ መምህራን ላይ አስገዳጅ ውሳኔ ተላለፈ

  ለአሥር ዓመት ሥልጠናውን ያልወሰዱ መምህራን ከመምህርነት ሙያ ይወጣሉ የግል ትምህርት...

  ከሱር ታክስ ነፃ የተደረጉ ምርቶች የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ ተጣለባቸው

  የሚኒስትሮች ምክር ቤት ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ ምርቶች ላይ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት ጀመረ

  ሦስተኛ ዙር ሙሌት በዛሬው ዕለት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ...

  የክላስተር አደረጃጀት ፖለቲካዊ ውዝግብ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይባል የነበረውን አደረጃጀት...

  በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

  በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...

  የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ምሥረታና ተጠባቂ ዕድሎቹ

  ነፃ የንግድ ቀጣናዎች የልዩ ኢኮኖሚ ቀጣናዎች አካል ሲሆኑ፣ በውስጣቸው...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የሥጋት ደመና ተወግዶ ሰላም ይስፈን!

  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደቡብ የአገሪቱ ክፍል ክልል ለመሆን የፈለጉ የተለያዩ ዞኖች እየተሰባሰቡ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ እያቀረቡ ናቸው፡፡ ለብቻችን ክልል መሆን አለብን የሚሉ ዞኖችም...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር ሕዝቦችና ለአፍሪካውያን ነፃነትም ተምሳሌት ናት፡፡ የጥንቶቹ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን የሚያኮራ ተግባር ፈጽመው ያለፉት፣ ከአገራቸው በፊት የሚቀድም...

  የማንም ሥልጣንና ጥቅም ከኢትዮጵያ አይበልጥም!

  የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ፣ የኢትዮጵያን የወደፊት ብሩህ ጊዜ አመላካች ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ይህ የአፍሪካ ታላቅ ግድብ ፕሮጀክት ዕውን...