Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናፕሬዚዳንት ኦባማን ለማነጋገር ጥያቄ ያቀረቡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አልተሳካልንም አሉ

  ፕሬዚዳንት ኦባማን ለማነጋገር ጥያቄ ያቀረቡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አልተሳካልንም አሉ

  ቀን:

  በአምስተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ተሳትፈው የነበሩትና የምርጫውን ውጤት እንደማይቀበሉት የገለጹት ሦስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰኔ 29 ቀን 2007 ዓ.ም. በራስ ሆቴል ሰጥተውት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ከሐምሌ 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ኢትዮጵያን የሚጎበኙት የአማሪካን ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ እንዲያነጋግሯቸው ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት አለማግኘቱን ለሪፖርተር አስታወቁ፡፡

  ጥያቄውን በይፋ አቅርበው የነበሩት ፓርቲዎች የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) እና የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ናቸው፡፡

  የሦስቱ ፓርቲዎች ፕሬዚዳንቶች ሰጥተውት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት፣ ፕሬዚዳንት ኦባማ አግኝተው እንዲያነጋግሯቸውና ወሳኝ ባሏቸው ጉዳዮች ላይ ለፕሬዚዳንቱ ገለጻ ለማድረግና ለመመካከር እንደሚፈልጉ ገልጸው ነበር፡፡

  ይህንን የፓርቲዎቹን ጥያቄ በተመለከተም አዲስ አበባ ለሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲና ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደብዳቤ መጻፋቸውን ያስታወሱ ሲሆን፣ ሆኖም ጥያቄያቸው ምላሽ እንዳላገኘና ምንም ዓይነት ቀጠሮ እንዳልተያዘላቸው አስረድተዋል፡፡

  የኢዴፓ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ፣ ‹‹ፕሬዚዳንቱን በጋራ ለማግኘት ያቀረብነው ጥያቄን በተመለከተ ምንም የተሰጠ መልስ የለም፡፡ ነገር ግን በተናጠል ፕሬዚዳንቱ በአፍሪካ ኅብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ የሚያደርጉትን ንግግር እንድንታደም ኤምባሲው ጥሪ ልኮልናል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

  ጉዳዩን በተመለከተ ኤምባሲውን ማብራሪያ መጠየቃቸውን የገለጹት ዶ/ር ጫኔ፣ ‹‹ከፕሬዚዳንቱ ጋር ቀጠሮ ማስያዝ ከእነርሱ ቁጥጥርና ኃላፊነት ውጪ እንደሆነና በሌላ አካል እየተመራ ነው፤›› የሚል ምላሽ ማግኘታቸውን አብራርተዋል፡፡

  ‹‹ምንም እንኳን ፕሬዚዳንቱን አግኝቶ የመነጋገርና የመወያየት ጥያቄያችን ባይሳካም፣ የተለያዩ ጥያቄዎችን ያካተተው ደብዳቤ ግን ለፕሬዚዳንቱ መድረሱን አረጋግጠናል፤›› ብለዋል፡፡

  በተመሳሳይ የመኢአድ ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መሐሪ ‹‹ፕሬዚዳንቱ በአፍሪካ ኅብረት በሚያደርጉት ንግግር ላይ እንድንገኝ የሚገልጽ ደብዳቤ ከመላክ ባለፈ፣ ከፕሬዚዳንቱ ጋር ለመወያየት ላቀረብነው ጥያቄ ምንም ዓይነት የተሰጠ ምላሽ የለም፤›› በማለት ጥያቄያቸው ተቀባይነት አለማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

  የኢራፓ ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮም በጋራ ፕሬዚዳንቱን የማግኘትና የመወያየት ጥያቄ እስከ ዓርብ ሐምሌ 17 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ ምላሽ አለማግኘቱን ገልጸው፣ ‹‹ሦስት ፓርቲዎች በጋራ በመሆን ያቀረብነው የአነጋግሩን ጥያቄ ምላሹን እየጠበቅን ነው፤›› በማለት ፕሬዚዳንቱን የማግኘት ተስፋ ሊኖር እንደሚችል እምነታቸውን አስረድተዋል፡፡

  እነዚህ ሦስት ፓርቲዎች በጋራ ለመሥራት ከተስማሙባቸው ጉዳዮች መካከል ጋዜጣዊ መግለጫዎችንና የተቃውሞ ሠልፎችን በጋራ የመጥራትና የማዘጋጀት ተጠቃሽ እንደሆነ ቀደም ሲል ማስታወቃቸውን መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...

  ሰበበኞች!

  ዛሬ የምንጓዘው ከሜክሲኮ ወደ አየር ጤና ነው፡፡ ዛሬም፣ ነገም...