Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  የንግዱ ማኅበረሰብ ከሕግ አውጪዎች ጋር የመከረበት የአፍሪካና የዓረቡ ዓለም ፎረም

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  በአፍሪካና በዓረቡ ዓለም መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት ለማስፋት ብቻም ሳይሆን ከሦስት እስከ አምስት እጥፍ ለማሳደግ ይረዳሉ የተባሉ የመፍትሔ ሐሳቦችን ለማቅረብ ጭምር በዓረቡ ዓለምና አፍሪካ አገሮች የሕግ አውጪዎችና በንግዱ ማኅበረሰብ መካከል ውይይት ሲደረግ ጥቂት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ይኸው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ፎረም ተካሂዷል፡፡

  አፍሪካና የዓረቡ ዓለም ከታሪካቸውም በላይ እጅግ የቀረበ የመልከዓ ምድራዊ ግንኙነት ቢኖራቸውም፣ በሁለቱ ሕዝቦችና መንግሥታት መካከል እንደ ጥንቱ የሲራራ ንግድ ወይም ‹‹ትራንስ ሰሃራ›› የንግድ መስመር ያለውን ዓይነት ግንኙነት ዳግመኛ ሳይመሠርቱ ረጀም ዘመናትን አሳልፈዋል፡፡ ትራንስ ሰሃራ የተባለው የንግድ መስመር እ.ኤ.አ. በዘጠኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአፍሪካና በዓረቡ ዓለም መካከል ይካሄድ የነበረውን የሽቶና እንደ ወርቅ፣ ነሐስ፣ ብርና የመሳሰሉ የከበሩ ማዕድናት ግብይት፣ የዝሆን ጥርስ፣ የዱር እንስሳት ቆዳ፣ የባርያ ንግድ የመሳሰሉት የንግድ እንቅስቃሴዎች ይቀላጠፉበት የነበረው ዘመን ያፈጀና ታሪካዊ ሆኖ በሰነዶች ለትውስታ የቀረ ሆኗል፡፡

   እንደ ጥንቱም ባይሆን ድንበር አልፎ፣ ወንዝ ተሻግሮ የሚካሄድ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነትን ለማዳበር የመከረው የአፍሪካና የዓረቡ ዓለም ፎረም፣ የንግድ ማኅበረሰቡ በሕግ አውጪዎች ዘንድ ሊታወቁለት ስለሚፈልጋቸው ችግሮቹ፣ የሕግ አውጪዎችም የንግድ ማኅበረሰቡ ሊያከብሩለት ስለሚገቡ ጉዳዮች ሲመርክር አራተኛው ዙር ላይ ደርሷል፡፡ በፓን አፍሪካ ንግድ ምክር ቤትና ኢንዱስትሪ እንዲሁም በአፍሪካና በዓረቡ ዓለም ሴኔቶች፣ ሹራና አቻ ምክር ቤቶች ማኅበር በትብብር የተዘጋጀው ፎረም፣ በአዲስ አበባ ከሐምሌ 25 እስከ 26 ቀን 2007 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ሲካሄድ፣ በአፍሪካና በዓረብ አገሮች መካከል ስላለው የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት መምከር ዓላማው ነበር፡፡

  ሁለቱ አካባቢዎች ካላቸው ቅርበት አኳያ በንግድና ኢንቨስትመንት ተራርቀው ቆይተዋል፡፡ በአንፃሩ ከሩቅ ምሥራቅና አጎራባች አካባቢዎች፣ ከካሪቢያንና ከፓስፊክ አገሮች ሳይቀር እየመጡ በአፍሪካ ኢንቨስት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ዓረቦች አፍሪካን ለምን ራቋት? ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጡት የአፍሪካና የዓረቡ ዓለም ሴኔቶች፣ ሹራና አቻ ምክር ቤቶች ዋና ጸሐፊ አቶ አብዱልዋሴ ዩሱፍ አሊ ናቸው፡፡ አቶ አብዱልዋሴ ዩሱፍ፣ የአፍሪካና የዓረቡን ዓለም ሕግ አውጪዎችን የሚወክለውንና እ.ኤ.አ. በ2002 በሞሮኮ ተመሥርቶ በየመን ሰነዓ ዋና የመሥሪያ ቤቱን መገኛ ያደረገውን ማኅበር በዋና ጸሐፊነት ከኢትዮጵያ ተወክለው እንዲመሩት የተመረጡት እ.ኤ.አ. በ2011 ነበር፡፡

  አቶ አብዱልዋሴ እንዳብራሩት፣ በአፍሪካና በዓረብ አገሮች መካከል በንግድና ኢንቨስትመንት መስክ ጠንካራ ግንኙነት ሳይመሠረት ከቆየባቸው ምክንያቶች መካከል በአፍሪካ ቀጣና ለዓመታት የዘለቁት የሰላምና ፀጥታ ችግሮች ይጠቀሳሉ፡፡ በመሆኑም በንግድና በኢንቨስትመንት ለመጣመርና የጠበቀ ግንኙነት ለመመሥረት በቅድሚያ የጋራ መተማመን መፈጠር እንደነበረበት አቶ አብዱልዋሴ ይዘክራሉ፡፡

  ‹‹በመጀመሪያ በሁለቱ አካባቢዎች መካከል የጋራ መተማመንን መፍጠር ያፈልጋል፡፡ የጋራ መተማመን ከሌለ ችግሮች ይኖራሉ፡፡ ሌላው የሁለቱን አካባቢዎች ባለሥልጣናት አብሮ በመሥራት የሚያገኙትን ጠቀሜታ እንዲገነቡ ማድረግን ይጠይቃል፡፡ እስካሁን በርካታ ነገሮች ተከናውነዋል፡፡ በቂ ግን አይደሉም፡፡ በርካታ ሀብቶች አሉን፡፡ የሰው ኃይል፣ የተፈጥሮ ሀብቶችና የነዳጅ ክምችት በተለይ በመካከለኛው ምሥራቅ ይገኛል፡፡ ስለዚህ ሁለቱን አካባቢዎች ይበልጥ እንዲቀራረቡ ማድረግ መዋቅራዊ ለውጥ በማምጣት ፈጣን ልማት ለማስመዝገብ  ያስችላል፡፡››

  በቀደሙት ዓመታት የዓረብ አገሮች በአፍሪካ ያለው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ያስፈራቸው እንደነበርና ከአፍሪካ አገሮች ጋር በንግድና በኢንቨስትመንት ለመተሳሰር ሥጋት እንደነበረባቸው አቶ አብዱልዋሴ ጠቁመዋል፡፡ በአፍሪካ የነበረው ዴሞክራሲያዊ ሒደት ለዓረቡ ዓለም ኢንቨስተሮች የልብ ልብ የሚሰጥ እንዳልነበር ገልጸዋል፡፡ በአፍሪካ የነበረው ፖለቲካዊ አመራር በአሁኑ ወቅት ፀጥታና ሰላም በአፍሪካ እንዲሰፍን የሚያስችሉ ሥራዎች በመሠራታቸው ለውጦች ታይተዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን በመሠረተ ልማት ግንባታ ዘርፍ የሚታዩ ድክመቶች ሊሻሻሉ እንደሚገባና ሙስናም ትኩረት እንዲሰጠው ዋና ጸሐፊው አብራርተዋል፡፡ ሙስና ዋናው ጋሬጣ በመሆኑ ኢንቨስተሮች እንዳይመጡ እንቅፋት በመሆኑ አፍሪካውያን በዚህ ዘርፍ እንዲበረቱ፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቶችን እንዲያስፋፉ፣ ሰላምና ፀጥታ እንዲያሰፍኑ የዓረቡ አገሮች ፍላጎት መሆኑም ተገልጿል፡፡

  ይህም ሆኖ ግን በአፍሪካ እየታየ ያለው ኢኮኖሚያዊ ለውጥና የሌሎች አገሮች ኢንቨስተሮች መብዛት የዓረቡን ዓለም ባለሀብቶችም ወደ አፍሪካ እንዲመለከቱ በር ከፍቷል፡፡ ይህም ሆኖ ቀርቦ መተዋወቅና መግባባት ንግድን በሁለት ጎኑ ለማስፋፋት ያስቻላል የሚሉት አቶ አብዱልዋሴ፣ ‹‹ስንተዋወቅ፣ መተማመንን እናመጣለን፡፡ መተማመን ደግሞ ውስጥን ከፍቶ በሙሉ ልብ ገንዘብን በማምጣት ኢንቨስት ለማድረግ ያበቃል፤›› ያሉት ዋና ጸሐፊው፣ በአፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ወይም በዓረቡ ዓለም ይህ እየተፈጠረ መምጣቱን ይገልጻሉ፡፡

  በመሆኑም የንግድ ማኅበረሰቡ ከሕግ አውጪዎች ጋር እንዲመክሩ ያስፈለገው፣ ሕግ አውጪዎች ለሕግ አስፈጻሚው የመንግሥት አካል ቅርብ በመሆናቸው በንግድና በኢንቨስትመንት መስክ የሚገጥሟቸው ችግሮች ምን እንደሆኑ በቅርበት እንዲያውቁላቸው ለማስቻል ሲባል በሁለቱ ወገኖች መካከል ምክክር ሲደረግ መቆየቱን አብራርተዋል፡፡

  የዓረቡ ዓለም ኢኮኖሚያዊ ሀብት (ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ) 2.3 ትሪሊዮን ዶላር መድረሱን የገለጹት የፓን አፍሪካ ንግድ ምክር ቤትና ኢንዱስትሪ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ክቡር ገና ናቸው፡፡ አቶ ክቡር ለፎረሙ እንዳስታወቁት፣ በአፍሪካ ያለው ሰፊ መሬት አፍሪካን አልፎ የዓረቡን ዓለም ሊመግብ የሚችል ትልቅ ሀብት ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ከአፍሪካ ወደ ዓረብ አገሮች የሚላኩ ሸቀጦች መጠን እንዲጨምር ለማገዝ የአፍሪካ መንግሥታት ከመሠረተ ልማት ማስፋፋት ባሻገር ደንቦችና መመርያዎቻቸውን ማሻሻል እንደሚጠበቅባቸው አስታውቀዋል፡፡ በአፍሪካ አኅጉር አቀፍ ነፃ የንግድ አካባቢ ለመፍጠር የሚደረገው እንቅስቃሴ የንግድ ታሪፍን መቀነስ ብቻም ሳይሆን ለንግዱ ማኅበረሰብ ተወዳዳሪነትን የሚጨምርለት ሥርዓት በመሆኑ፣ ለዚህ ስምምነት ተግባራዊነት ተቋማቸው እንደሚሠራ አቶ ክቡር ተናግረዋል፡፡ የዓረብ አገሮች በአፍሪካ በመሠረተ ልማት ግንባታ፣ በቴክኖሎጂ፣ በታዳሽ ኃይሎች ግንባታ ዘርፍ በአፍሪካ ኢንቨስት ቢያደርጉ ለሁለቱም ወገን ትልቅ ትርጉም ያለው ጥቅም እንደሚገኝ አሳስበዋል፡፡

  የፈረንሳይ ልማት ኤጀንሲ ባልደረባ ሚሁብ ሜዞሃጂ የተባሉ ጸሐፊ፣ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮችና በዓረቡ ዓለም መካከል በጥንቱ ጊዜ የነበረው ጥብቅ የንግድ ግንኙነት፣ በቅኝ ግዛት ዘመን ሊዳከም መቻሉን ይጠቅሳሉ፡፡ በጸሐፊው ሐተታ መሠረት ምንም እንኳ ድህረ ቅኝ ግዛት አፍሪካና ዓረቦች የላላውን የንግድ ግንኙነት ለማጠበቅ ቢሞክሩም ይህ ነው የሚባል መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጣ የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ፣ ባህላዊና መተባበር ላይ የተመሠረተ ግንኙነትና የንግድ ልውውጥ መፍጠር ሳይቻላቸው ቆይተዋል፡፡ በዓረብ አገሮች ዘንድ በምግብ ነክ ምርቶች ጋር በተያያዘ አፍሪካን የገበያ ምንጭ የማድረግ ፍላጎት እየገፋና እየጎላ የመጣው እ.ኤ.አ. ለ2008 የዓለም የኢኮኖሚ ቀውስ ማግሥት እንደሆነ የሚገልጹም አሉ፡፡ በኢትዮጵያ ሳዑዲ ስታርን ጨምሮ ጥቂት የዓረብ ኩባንያዎች በእርሻ መስክ ተሰማርተው፣ ያመረቱትን ምርት ወደ አገሮቻቸው ለመላክ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ ይህም ቢባል ግን በአፍሪካና በዓረብ አገሮች መካከል ያለው ሁለትዮሽ የግብርና ውጤቶች ንግድ ከሦስት ከመቶ ብዙም ፈቅ እንደማይል ሜዞሃጂ በጽሑፋቸው አስፍረዋል፡፡ ይህ መሆኑ በጸሐፊው እምነት በሁለቱ ወገኖች መካከል የላላ የንግድ ግንኙነት መኖሩን ያሳያል፡፡

  ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ20 በላይ የአፍሪካና የአገሮች የመሠረቱት ማኅበር፣ በሁለቱ ዓለማት መካከል መልካም ግንኙነትን ይፈጥራሉ በሚላቸው ጉዳዮች ላይ እየመከረ ከአሥር ዓመታት በላይ ዘልቋል፡፡ ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ በአዲስ አበባም ከንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ጋር በንግድ ግንኙነት መስኮችና በኢንቨስትመንት መስኮች የመከረበት መድረክ፣ አፍሪካንና የዓረቡን ዓለም ለማቀራረብ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

   

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች