[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን ቢሮ አስጠሩት]
- ፈለጉኝ ክቡር ሚኒስትር?
- የቀረው ጉዳይ ላይ እንድንነጋገር ብዬ ነው፡፡
- የምን የቀረ ጉዳይ?
- የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ላይ የቀረ ነገር ካለ ብዬ ነው፡፡
- ኧረ በፈጠርዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ሆነሃል?
- አሁንስ ይህ ጉዳይ እጅ እጅ ነው ያለኝ፡፡
- ለምን?
- አሁንም ቴሌቪዥን ላይ መክፈቻ ዜና እኮ የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ነው፡፡
- ታዲያ ምን ችግር አለው? ወሳኝ ጉዳይ እኮ ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር አሁን ወደ ኖርማል ሥራችን የምንመለስበት ጊዜ ነው፡፡
- አትሳሳት ይኼም ቢሆን እኮ የሥራችን አካል ነው፡፡
- ቢሆንም በቃን፤ አሁን ወደ ሌላ ሥራ መሸጋገር አለብን፡፡
- ለማንኛውም ጥሩ ሥራ የሠራን ይመስለኛል፡፡
- እኔ ግን አንድ ቅር ያለኝ ነገር ነበር፡፡
- ምንድን ነው ቅር ያለህ?
- ሰሞኑን ዩቲዩብ ላይ ያየሁት ቪዲዮ ነበር፡፡
- ምን ላይ? ደግሞ እሱ ምንድን ነው ዴኤስቲቪ ላይ ያለ ፕሮግራም ነው?
- አይደለም ኢንተርኔት ላይ ቪዲዮ ማሠራጫ ቻናል ነው፡፡
- ሥራ ትተህ ኢንተርኔት ላይ ነው የምትውልልኝ አይደል?
- ክቡር ሚኒስትር ይኼም እኮ የሥራዬ አካል ነው፡፡
- እሱን ግምገማ ላይ ታወራለህ፤ ለመሆኑ ምንድነው ያየኸው?
- አላገጠችብን አይደል እንዴ?
- ማን?
- ይህቺ የሩዝ ስም ያላት የአሜሪካ ባለሥልጣን ናታ፡፡
- ምን ብላ?
- ስለምርጫው ተጠይቃ የፌዝ ሳቅ ነው የሳቀችብን፡፡
- የፌዝ መሆኑን በምን አወቅክ?
- ታዲያ የምን ሳቅ ነው የሳቀችው?
- የአድናቆት ነዋ፡፡
- እንዴት ሆኖ?
- አሜሪካን ረዳናት እኮ፡፡
- እንዴት ሆኖ?
- የአሜሪካ ወዳጅ የሆኑትን እነ ሳዑዲ ዓረቢያን አስብ፡፡
- ምን ሆኑ እነሱ?
- አሜሪካ ከእነሱ ጋር ባላት ወዳጅነት ሁሌም ትተቻለች፡፡
- ለምን?
- እነሱ ምርጫ አካሂደው አያውቁማ፡፡
- እ…
- እና ሁሌ በዚህ ጉዳይ አሜሪካ አንገቷን እንደደፋች ነው፡፡
- በዚህ ጉዳይማ አሜሪካ ሁሌም ትተቻለች፡፡
- እኛ ግን ምርጫ አካሂደን ሙሉ ለሙሉ ማሸነፍ እንደሚቻል አስመስክረናል፡፡
- ለዚያ ነው ፕሬዚዳንቱ ‘ዴሞክራቲካሊ ኢሌክትድ’ ብለው ያሉት፡፡
- እንዴታ?
- ኋላ ላይ ግን ዴሞክራሲ ማለት ምርጫ ማካሄድ ብቻ አይደለም ብለው እኮ ጐሸም አደረጉን፡፡
- ሰውዬ፣ አሁን እኛ ከአሜሪካ ጋር ዓለምን የምንመራበት ወቅት ነው፡፡
- ማን እኛ?
- አዎና፡፡
- እንዴት ሆኖ?
- አሜሪካ ዓለምን ትመራለች፤ እኛ ደግሞ አፍሪካን እንመራለን፡፡
- ምን?
- ለዚህ ነው ሕዝቡን ማብቃት አለብን የምልህ፡፡
- በምን?
- ዛሬ አንድ የክፍለ ከተማ አስተዳዳሪ መሆኑን አትይ፣ ነገ የአንድ የአፍሪካ አገር ከተማ ከንቲባ ሊሆን ይችላል፡፡
- የምርዎትን ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ስቀልድ ታውቀኛለህ?
- እንግዲህ ምኞት አይከለከሉም፡፡
- ምኞት ሳይሆን እውን አድርጌ አሳይሃለሁ፡፡
- ይሁንልዎት፡፡
- ለመሆኑም ያንን ዶክመንት አነበብከው?
- አንብቤዋለሁ ግን ጥቂት ይቀረኛል፡፡
- ምን ያህል ፐርሰንት አንብበኸዋል?
- 99.6 ፐርሰንት፡፡
- ተመልሰንማ ወደ ኋላ አንሄድም፤ 100 ፐርሰንት ካላነበብከው መወያየት አንችልም፡፡
- እሺ፡፡
[ክቡር ሚኒስትር ቤታቸው ሲገቡ ሚስታቸው ዘንጠው ሊወጡ ሲሉ አገኟቸው]
- አንቺ እንደዚህ ሱፐር ሞዴል መስለሽ ወዴት ልትሄጂ ነው?
- ያን ፕሮጀክታችንን የደረሰበት ለመመልከት ነው የምሄደው፡፡
- በግል መኪናሽ?
- እህሳ?
- ወቅቱን ረሳሽው እንዴ?
- የምን ወቅት ነው የምታወራው?
- ወቅቱ እኮ የግምገማ ወቅት ነው፡፡
- ቢሆንስ?
- ሻሽ አስረሽ በመንቀሳቀሻሽ ጊዜ እንደዚሁ ተዘንጦ?
- የአንተ ሚስት መሆኔን ረሳኸው እንዴ?
- ለምንድን ነው ሹፌሩ የማይወስድሽ?
- ፕሮጀክቱን ሰው ማወቅ የለበትም ብዬ ነዋ፡፡
- በዚህ ወቅት በመኪና መንቀሳቀሱ ዓይን ውስጥ ነው የሚያስገባሽ፡፡
- በምን ልሂድ ታዲያ?
- በኮንትራት ታክሲ፡፡
- ምነው ያለመጠን ፈራህ?
- የዘንድሮን ግምገማ ካለፍን ከዚያ ማንም አያቆመንም፡፡
- ማን ማንን ይገመግማል ብለህ ነው? አሁን ያልተጨማለቀ ይገኛል ብለህ ነው?
- ቢሆንም መጠንቀቁ አይከፋም፡፡
- ከተገመገምክም ያው መላውን ታውቀዋለህ፡፡
- ምንድነው መላው?
- ጨከን ብለህ ማልቀስ ነው፡፡
- እ…
- ኢሕአዴግ እኮ ሆደ ቡቡ ነው፡፡
- እንዴት?
- ስትገመገም ካለቀስክ፣ ወዲያው መለስ ይልልሃል፡፡
- ለነገሩ እውነትሽን ነው፣ ግን ያው ወንድ ሆኖ ማልቀስ ይከብዳል ብዬ ነው፡፡
- ለግምገማው ብለህ ጾታህን መቀየር አሰብክ?
- ቢቻልማ ደስ ይለኝ ነበር፡፡
- በቃ ዝም ብላችሁ እኩልነት ትላላችሁ እንጂ፣ ሴቶች አልቃሽ ወንዶች አስለቃሽ ናቸው ብለህ ነው አሁንም የምታስበው?
- እንደሱ ማለቴ አይደለም፡፡
- ለማንኛውም እንደዚህ ከፈራህ እኔ ከነልጆቹ ለምን ወጣ አልልም፡፡
- እኔስ?
- አንተማ ግምገማህን ተወጣ፡፡
- የአንበሳ ጥርስ ውስጥ ብቻዬን ከታችሁኝ ልትሄዱ?
- ታዲያ ሁላችንም እንግባ?
- ለማንኛውም ጥንቃቄ አይለይሽ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ሕንፃቸውን የሚሠራላቸው ኮንትራክተር ጋ ደወሉ]
- አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በዚህ ዓይነት ሌላ ሥራም ልሰጥህ አልችልም፡፡
- ለምን?
- አሁን እኮ ሕንፃዬ አልቆ መከራያ ጊዜው ነበር፡፡
- ምን ላድርግ ክቡር ሚኒስትር?
- እንዴት ምን ላድርግ ትላለህ? ጥፋቱማ የአንተው ነው፡፡
- የምን ጥፋት?
- ሕንፃውን መጨረስ አልቻልክም፡፡
- ሌላም ሥራዎች እንዳሉኝ እንዳይረሱ፡፡
- ስግብግብ ስለሆንክ እኮ ነው ሁሉንም ካልሠራሁ የምትለው?
- ክቡር ሚኒስትር እውነቱን ንገረኝ ካሉ ችግሩ እናንተው ናችሁ፡፡
- እንዴት?
- ራሳችሁ ያወጣችኋቸው መመርያዎች የማያሠሩ ናቸው፡፡
- መመርያዎቹ ባያሠሩህም እኔ እያስፈቀድኩልህ አይደል እንዴ?
- ክቡር ሚኒስትር እንደነገርኩዎት እኔ የምሠራው የእርስዎን ሕንፃ ብቻ አይደለም፡፡
- የእኔን ሕንፃ ብትጨርስ ኖሮ ሌላም ሁለት ቪላዎች ነበሩኝ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እኔ መቼ ሥራ አጣሁ?
- ታዲያ ምንድነው ያጣኸው?
- የሚያሠራ መመርያ፡፡
- ለማንኛውም ተጠንቀቅ፡፡
- ስለምኑ?
- ስለዚህ ሕንፃ ለሰዎች አታውራ፡፡
- ለምን?
- ወቅቱ የግምገማ ነው፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ አንድ ወዳጃቸው ቀብር ከሾፌራቸው ጋር እየሄዱ ነው]
- ክቡር ሚኒስትር እኔ ግን ትንሽ አንገሽግሾኛል፡፡
- ምኑ?
- እኔ የተቀጠርኩት ሽንኩርትና ድንች ላመላልስ ነው?
- ምን ማለት ፈልገህ ነው?
- እኔ አሸዋና ብረት ልገዛም የተቀጠርኩ አይመስለኝም፡፡
- ስላቀረብኩህ ነው?
- ክቡር ሚኒስትር እኔ የእርስዎ ሾፌር ነኝ፡፡
- እኮ ለቤቴ ቅርብ ስላደረኩህ ነው ይህ ሁላ ወቀሳ?
- ቅርብ በመሆኔ ሥራውን እንድጠላው ነው የተደረግኩት፡፡
- ለምንድነው የጠላኸው?
- ይኸው ቅዳሜ የለ፣ እሑድ የለ፣ ሕይወቴ ሥራ ብቻ ሆነ፡፡
- አገሪቱ እኮ በሥራ ነው የምትለወጠው፡፡
- እኔ ሥራ ብቻ ነው እንጂ የተረፈኝ ለውጡን አላየሁትም፡፡
- አይዞህ ቅርብ ነው ጊዜው፡፡
- በተግባር ካላየሁት ወሬ ብቻ ምን ያደርግልኛል?
- ምን አልክ አንተ?
- እኔ ስለምቀርብዎት መጀመሪያ ልንገርዎት ብዬ ነው እንጂ ሌላ ሰውም ሲማረር ሰምቻለሁ፡፡
- ማነው ሌላው ሰው?
- አትክልተኛችን ነዋ፡፡
- ደግሞ እሱ ምናለ?
- እኔ የመሥሪያ ቤቱ አትክልተኛ እንጂ የሚኒስትሩ አትክልተኛ አይደለሁም ሲል ሰምቼዋለሁ፡፡
- ከፍዬው አይደል እንዴ የሚሠራው?
- ከሥራ ያባርሩኛል ብዬ ፈርቼ ነው እንጂ ክፍያው ኪሳራ ነው እያለ ነበር፡፡
- ምን?
- ምናልባትም ግምገማ ስለደረሰ መጠንቀቁ አይከፋም ብዬ ነው፡፡
- የሰማኸው ነገር አለ እንዴ?
- በርካታ ሰው በዚህኛው ግምገማ ምንም የሚደበቅ ነገር የለም እየተባለ ሲወራ ሰምቼያለሁ፡፡
- ጉድ ፈልቷል በለኛ?
- ምን ያልፈላ ነገር አለ?
- ወይ ጣጣ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ቀብሩ ላይ ከሌላ ሚኒስትር ጋር ተገናኙ]
- አስመሳይ ሰው ነህ ልበል?
- ለምን ክቡር ሚኒስትር?
- እንደዚህ የሚያንሰቀስቅህ ምንድነው?
- ወዳጃችን እኮ ጥሩ ሰው ነበር፡፡
- ጥሩ ሰው?
- አዎና፡፡
- ለማን? ለአንተ ወይስ ለአገር?
- ለአገር ነው እንጂ እኔ እንደዚህ ዓይነት ነገር ደስ እንደማይለኝ ያውቃሉ፡፡
- እሱን እንኳን ተወው፡፡
- እንዴት?
- መስመር ላይ እስክንገናኝ ነው፡፡
- ያው እንግዲህ ሰሞኑን ግምገማ ላይ እንገናኛለን፡፡
- እ…
- እርስዎ ግን ከመቼ ጀምሮ ነው እንደዚህ ጨካኝ የሆኑት?
- የምን ጭካኔ ነው?
- አንድ ዘለላ እንባ እንኳን የለዎትም?
- ኧረ እየቆጠብኩት ነው፡፡
- ለምንድን ነው የሚቆጥቡት?
- ለግምገማ!