Thursday, August 11, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ክቡር ሚኒስትሩ ከሚስታቸው ጋር ቤታቸው እያወሩ ነው

  [ክቡር ሚኒስትሩ ከሌላ ሚኒስትር ጓደኛቸው ጋር እያወሩ ነው]

  • እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
  • ሰላም ነህ?
  • ይኼ መቼም በጣም ከባድ ሳምንት ነው?
  • በጣም ወሳኝ ሳምንት እንጂ?
  • በዚህ ሳምንት ነው አይደል የሚታወቀው?
  • አሸናፊው የሁለተኛነት ቦታውን ይይዘዋል፡፡
  • አሸናፊው ሊቀመንበር አይሆንም እያሉኝ ነው?
  • ስለምንድነው የምታወራው?
  • ስለወሳኙ ጉዳይ ነዋ፡፡
  • ስለማንቸስተርና ሊቨርፑል ጨዋታ?
  • ምን አሉኝ ክቡር ሚኒስትር?
  • በጣም ወሳኝ ጨዋታ ነው፡፡
  • እየቀለዱ ነው ክቡር ሚኒስትር?
  • ስማ በማንቸስተር መቼም ቀልጄ አላውቅም፡፡
  • በዚህ ወሳኝ ወቅት የሚያስቡት ስለእግር ኳስ ነው?
  • ሌላ ስለምን ላስብ?
  • ስለአገሪቷ ቀውስና የፖለቲካ ጉዳይ ነዋ፡፡
  • እሱ ምን ያሳስባል ብለህ ነው?
  • እንዴት አያሳስብም ክቡር ሚኒስትር?
  • ስለእሱ አታስብ፡፡
  • ለምን አላስብም?
  • ጥርሳችንን የነቀልንበት ነው፡፡
  • ምኑን?
  • ፖለቲካውን፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር ከእኛ አልፎ ሌሎች አገሮችን እያሳሰበ ነው እኮ?
  • ደግሞ ማንን አሳሰበ?
  • ይኸው የአሜሪካ፣ የሩሲያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ዲፕሎማቶች በዚህ ሳምንት ይመጣሉ አይደል እንዴ?
  • ታዲያ እኛ ሁሌም እንግዳ ተቀባዮች ነን፡፡
  • የሚመጡት ግን የአገራችን ሁኔታ አሳስቧቸው ነው እኮ?
  • ኧረ ምንም የሚያሳስብ ነገር የለም፡፡
  • አገሪቷ እኮ በቋፍ ላይ ነው ያለችው ክቡር ሚኒስትር?
  • ሊጠራ ሲል ይደፈርሳል ሲባል አልሰማህም?
  • ኧረ ክቡር ሚኒስትር ደፍርሶ ቀርቶብን ነው እኮ ሌሎች ሊያማክሩን የሚመጡት፡፡
  • በእኛ ጉዳይ ማንም ገብቶ ሊፈተፍት አይችልም፡፡
  • ዲፕሎማቶቹ ታዲያ ለምንድነው የሚመጡት?
  • የአገራችን ዕድገት አስጎምዥቷቸው ነዋ፡፡
  • ተው እንጂ ክቡር ሚኒስትር?
  • ስማ በብጥብጥ ውስጥ ራሱ በ11 በመቶ እያደገች ያለች ብቸኛ አገር መሆኗን አታውቅም?
  • ይኼን ሌላ ሰው እንዳይሰማዎት?
  • እውነት እኮ አያሳፍረኝም፡፡
  • ለማንኛውም የእኛ አቋም ምንድነው?
  • ልማቱን ማስቀጠል ነዋ፡፡
  • እኔ ያልኩዎት ሩሲያም ሆነ አሜሪካ የራሳቸው የሆነ ፍላጎት ይኖራቸዋል፡፡
  • ታዲያ ምን ችግር አለው?
  • የሁለቱ አገሮች ፍላጎት የተለያየ ሊሆን ይችላል ብዬ ነው፡፡
  • አየህ ሁለቱንም እሺ ማለት አይቻልም፡፡
  • አውቃለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ሁለቱንም ደግሞ እምቢ ማለት አይቻልም፡፡
  • ታዲያ ምን እናደርጋለን?
  • ብቸኛው ዕድላችን መጣል ነው፡፡
  • ምንድነው የምንጥለው?
  • ዕጣ!

  [ክቡር ሚኒስትሩ ሾፌራቸውን አስጠርተው እያዋሩት ነው]

  • አቤት ክቡር ሚኒስትር?
  • ሠፈራችሁ እንዴት ነው?
  • ሰሞኑንማ ነፍስና ሥጋዬ እየተላቀቀች ነው፡፡
  • ለምን?
  • ያው ስገባና ስወጣ ተሳቅቄ ነው የምንቀሳቀሰው፡፡
  • ችግር አለ ማለት ነው?
  • የከተማ ዳር ስለሆነ ቤቴ ምንም እንቅስቃሴ የለም፡፡
  • እሱን ለማወቅ ነው እኔም የጠየቅኩህ?
  • ባንክ አይሉ ሱቆች ሁሉም ተዘግተው ነበር፡፡
  • ታዲያ አልተቸገርክም?
  • ምን ማድረግ እችላለሁ?
  • ወደ ከተማ ለምን አትገባም?
  • ኪራዩ አልቀመስ ብሎኝ ነዋ፡፡
  • ለካ እሱም አለ፡፡
  • ከቻሉማ እርስዎ ጋ ብሆን ደስ ይለኛል፡፡
  • እሱን አስብበታለሁ፣ አሁን የፈለግኩህ ለሌላ ጉዳይ ነው፡፡
  • ምን ልታዘዝ?
  • ወረቀትና እስኪርቢቶ አምጣ፡፡
  • እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • የምትጽፈውን ነገር ገዝተህ ትመጣለህ፡፡
  • አስቤዛ ሊያስገዙኝ ነው?
  • አሁን ዝም ብለህ ጻፍ፡፡
  • ይቀጥሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • በመጀመርያ አንድ አይሱዙ ሙሉ ውኃ ግዛ፡፡
  • እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
  • ምነው?
  • ውኃ ማከፋፈል ሊጀምሩ ነው እንዴ?
  • እሱን ማን ጠየቀህ?
  • ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ሁለተኛ ሁለት አይሱዙ ጤፍ ትገዛለህ፡፡
  • ወፍጮ ቤት ሊከፍቱ መሆን አለበት?
  • ሰውዬ ያልተጠየቅከውን ለምን ታወራለህ?
  • ውይ ይቅርታ፡፡
  • የነገርኩህን ጻፍክ?
  • በሚገባ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ሌላ ሁለት አይሱዙ ዘይት፡፡
  • እ. . .
  • ይኼ የጭቃውን አይደለም እኔ የምፈልገው፣ ሰን ፍላወር ነው፡፡
  • እሺ፡፡
  • 20 ካርቶን ሳሙና፡፡
  • የሚከፍቱት ሱፐር ማርኬት ነው ማለት ነው?
  • ለምን ያልተጠየቅከውን ትዘባርቃለህ?
  • ይቅርታ ይቅርታ፡፡
  • ሁለት አይሱዙ ስኳርም እፈልጋለሁ፡፡
  • አሁን ኬክ ቤት መሆኑ ገባኝ፡፡
  • ዝም ማለት አትችልም እንዴ?
  • ጓጉቼ እኮ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ለማንኛውም አሥር ኩንታል በርበሬም ግዛልኝ፡፡
  • ምነው በርበሬዋን አሳነሷት?
  • ሁሉም ነገር አቃጣይ ነው ብዬ ነዋ፡፡
  • እሱስ ልክ ብለዋል፡፡
  • ለማንኛውም እነዚህን ግዛና ሌላውን እጨምርልሃለሁ፡፡
  • ጥያቄ ግን አለኝ ክቡር ሚኒስትር?
  • የምን ጥያቄ?
  • እነዚህ ሁሉ ዕቃዎች ለምንድነው የሚገዙት?
  • ከሰሞኑ ያሰብኩት ነገር አለ፡፡
  • ምንድነው ያሰቡት?
  • መመነን!

  [ክቡር ሚኒስትሩ አገር ውስጥ ኢንቨስት ካደረጉ የውጭ ባለሀብት ጋር እያወሩ ነው]

  • ክቡር ሚኒስትር እኛ ጠቅልለን ልንወጣ ነው፡፡
  • ምን ሆናችሁ?
  • አገሪቷ እኮ በየጊዜው እየባሰባት ነው፡፡
  • ከቁጥጥር ውጭ የሚወጣ ነገር አይኖርም፡፡
  • እንዲህ እያሉን ሦስት ዓመታት ተቆጠሩ እኮ?
  • በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሁሉን ነገር እንፈታዋለን፡፡
  • ከብጥብጡ ባለፈ ሌላ ወሳኝ ጥያቄያችን ሊመለስ አልቻለም፡፡
  • የትኛው ጥያቄያችሁ?
  • ይኸው የሠራንበትን ገንዘብ መቼ አገኘን?
  • እስካሁን አልተከፈላችሁም እንዴ?
  • በብር ቢከፈለን ለእኛ ምን ይጠቅመናል?
  • እሱማ የአገሪቱ ችግር መሆኑን ታውቃላችሁ?
  • ክቡር ሚኒስትር በዶላር ካልቀየርነው ለእኛ ምን ይጠቅመናል?
  • ትንሽ ታገሱን ይስተካከላል፡፡
  • አሁን በጣም ተማረናል፡፡
  • እዚህ አገር እንደ ንጉሥ አይደል እንዴ የተያዛችሁት?
  • ገንዘባችንን ወደ አገራችን በዶላር ቀይረን መላክ አልቻልንም፡፡
  • ሁላችንም እኮ የዶላር እጥረት አለብን፡፡ እኔም በጣም ዶላር እፈልጋለሁ፡፡
  • ለማንኛውም በቅርቡ እኛም እንወስናለን፡፡
  • ምንድነው የምትወስኑት?
  • ጠቅልለን ለመውጣት ነዋ፡፡
  • ይኼማ አይደረግም፡፡
  • ታዲያ ያለ ዶላር እንዴት እንሠራለን?
  • በቅርቡ መፍትሔ ይገኝለታል፡፡
  • ምን ዓይነት መፍትሔ?
  • ለማተም አስበናል፡፡
  • ምን ጋዜጣ ነው?
  • ኧረ አይደለም፡፡
  • ምንድነው የምታትሙት ታዲያ?
  • ዶላር!

  [ክቡር ሚኒስትሩ ከሚስታቸው ጋር ቤታቸው እያወሩ ነው]

  • ቁጭ ብለህ ቲቪ ታይልኛለህ አይደል?
  • ምን ላድርግ ታዲያ?
  • አገሪቷን ግን ወዴት እየወሰዳችኋት ነው?
  • ወደ አደጉ አገሮች ተርታ ነዋ፡፡
  • ቀልዱን ለጊዜው ተወው፡፡
  • የምን ቀልድ ነው?
  • አገሪቷ እንዴት እየታመሰች መሆኗን ረሳኸው?
  • ከታገሽ ሁሉን ነገር ታይዋለሽ፡፡
  • ምኑን ነው የማየው? ስማ በዚህ ብጥብጥ ምክንያት ሁሉ እንቅስቃሴ እንደቆመ ረሳኸው?
  • ማን ነው ያቆመው?
  • ለነገሩ አንተ በበቂ ሁኔታ ስለዘረፍክ እሱ አይታወቅህም፡፡
  • ሴትዮ አንቺም የሌባ ተባባሪ መሆንሽን አትርሺ?
  • ምን ላድርግ አማራጭ ስለሌለኝ ነው፡፡
  • ለማንኛውም እኛ ዘላቂ ዕድገትና ሰላም ለማምጣት ተግተን እየሠራን ነው፡፡
  • ያድርግላችሁ ሌላ ምን ይባላል?
  • እውነቴን ነው፡፡
  • ቅድም አስጨፍረህ አስጨፍረኸኝ በአንዴ ደስታዬ ላይ ውኃ ቸለስክበት፡፡
  • ምን ሆንሽ?
  • እኔማ አዲስ ኮሚሽን ተቀብለህ አካውንቴ ውስጥ የከተትክልኝ መስሎኝ ነበር፡፡
  • የምን ኮሚሽን ነው?
  • ቅድም ሁለቱ የባንክ አካውንቶቼ ውስጥ ያለውን ገንዘብ ደምረህ ላክልኝ ብየህ ቢሊየነር አድርገኸኝ ነበር፡፡
  • ስደምር ተሳስቼ ይሆናላ፡፡
  • እኔማ የሒሳብ ችሎታህ እንዲዳብር እያፈላለግኩልህ ነው፡፡
  • ምን?
  • ስኮላርሽፕ!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

  በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...

  የአገሪቱ ባንኮች ካፒታል 199.1 ቢሊዮን ብር ደረሰ

  ከታክስ በኋላ 50 ቢሊዮን ብር ማትረፋቸውን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ የአገሪቱ...

  የማስተማር ሙያ ሥልጠና ባልወሰዱ መምህራን ላይ አስገዳጅ ውሳኔ ተላለፈ

  ለአሥር ዓመት ሥልጠናውን ያልወሰዱ መምህራን ከመምህርነት ሙያ ይወጣሉ የግል ትምህርት...

  ከሱር ታክስ ነፃ የተደረጉ ምርቶች የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ ተጣለባቸው

  የሚኒስትሮች ምክር ቤት ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ ምርቶች ላይ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት ጀመረ

  ሦስተኛ ዙር ሙሌት በዛሬው ዕለት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ...

  የክላስተር አደረጃጀት ፖለቲካዊ ውዝግብ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይባል የነበረውን አደረጃጀት...

  በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

  በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...

  የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ምሥረታና ተጠባቂ ዕድሎቹ

  ነፃ የንግድ ቀጣናዎች የልዩ ኢኮኖሚ ቀጣናዎች አካል ሲሆኑ፣ በውስጣቸው...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  [ክቡር ሚኒስትሩ የሥራ አጥነት ችግሮችን የመፍታት ተልዕኮ የተሰጠው ተቋም በዋና ጽሕፈት ቤቱ ሕንፃና ቢሮዎች ላይ ያደረገውን ዕድሳት መርቀው በመክፈት ጉብኝት እያደረጉ ነው]

  እጅግ ውብ ዕድሳት ያደረጋችሁት! በእውነቱ በጣም ድንቅ ነው፡፡ አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር። በጣም ድንቅ ነው። ዕድሳቱን ያከናወነው ድርጅት ጥሩ ልምድ ያለው ይመስላል? ተቋራጩ ማን እንደሆነ አልነገርኩዎትም እንዴ? የትኛው ተቋራጭ...

  [ክቡር ሚኒስትሩ በስንዴ የተሸፈኑ ሰፋፊ እርሻዎች ያሉበትን ሁኔታ ለመገምገም ከስንዴ ምርት ድጋፍና ክትትል ኮሚቴ ሰብሳቢ ጋር እየመከሩ ነው] 

  ክቡር ሚኒስትር እንደነገርክዎት በሁሉም ስንዴ አብቃይ አካባቢዎቻችን ያሉ አርሶ አደሮች ጥሪያችንን ተቀብለው መሬታቸውን በኩታ ገጠም አርሰው በስንዴ ዘር ሸፍነዋል። በጣም ጥሩ ዜና ነው። በጣም እንጂ። የሚገርምዎት...

  [ክቡር ሚኒስትሩ የሚመሩት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ አጀንዳ አድርጎ በያዘው ወቅታዊ የፀጥታና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ ትኩረት በመስጠት ቢጀመርም በስተመጨረሻ አጀንዳውን ስቶ ስለ መዋደድ እየተጨቃጨቀ...

  በዛሬው መደበኛው መድረካችን አጀንዳ የተለመደው የፀጥታና ደኅንነት ጉዳይ ይሆናል። ሌላ አጀንዳ የምታስይዙት አጀንዳ ከሌለ በቀር ማለቴ ነው። ክቡር ሚኒስትር... እሺ ...ቀጥል አመሰግናለሁ ክቡር ሚኒስትር። መደበኛ አጀንዳው እንደተጠበቀ...