[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚስታቸው ጋር ስለትንሹ ልጃቸው ጉዳይ እየተወያዩ ነው]
- ሰማህ አይደል ጉድህን?
- የምን ጉድ ነው?
- የትንሹ ልጅህን ጉድ ነዋ፡፡
- ደሞ የምን ጉድ ነው?
- ጀምሮልሃል፡፡
- ምን? ትምህርት?
- ሱስ ይዞታል፡፡
- የምን ሱስ?
- የምን ሱስ እንድልህ ነው የምትጠብቀኝ?
- የአብዮታዊ ዴሞክራሲ?
- እሱ ይሻለው ነበር፡፡
- ታዲያ የምን ሱስ ነው የያዘው?
- የሲጋራ፡፡
- ምን?
- ይኸውልህ ክፍሉ ያገኘሁት የሮዝማን ፓኬት፡፡
- ጭራሽ ሮዝማን ነው የሚያጨሰው?
- ምን እንዲያጨስ ፈልገህ ነበር?
- እኛ ሌት ተቀን ኢምፖርት ሰብስቲትዩሽን ላይ እየሠራን፡፡
- ምንድን ነው የምትቀባጥረው?
- የአገር ውስጥ ሲጋራ እያለ የውጭ ሲጋራ?
- ትቀልዳለህ ልበል?
- እሱ ነው እንጂ እየቀለደ ያለው፡፡
- ኧረ ሰውዬ ሰው ጉድ እንዳይልህ?
- እሱን ነው እንጂ ጉድ የሚለው እኔማ ምን አደረኩ?
- ሌላ ልጨምርልህ?
- ጨምሪልኝ፡፡
- ጫትም ጀምሮልሃል፡፡
- አይደረግም?
- ተደርጓል ስልህ፡፡
- ልጁ ምን ነክቶታል?
- እስቲ አንተ ጠይቀው፡፡
- አገሪቷን የውጭ ምንዛሪ እያሳጣልኝ ነዋ?
- አልገባኝም፡፡
- ኤክስፖርት የሚደረግ ምርትን እዚሁ አገር ውስጥ እየተጠቀመበት ነው እኮ?
- ጤነኛ ነህ ግን?
- ጤነኛ ያልሆነውማ እሱ እኮ ነው፡፡
- ምንድን ነው የምትዘባርቀው?
- ልጁ ለአገር ማሰብ አቁሟል ማለት ነው?
- አንተ ደግሞ ለልጅህ ማሰብ አቁመሃል ማለት ነው፡፡
- ለአገሬ ካሰብኩ እኮ ለልጄም አሰብኩ ማለት ነው፡፡
- ለዛ ነዋ የምትቦጠቡጣት?
- ታዲያ በአንዴ በልቼ ልጨርሳት?
- ለማንኛውም ውጤቱን ተመልከተው፡፡
- የምን ውጤት ነው?
- የክረምት ትምህርቱ ፈተና ነው፡፡
- ስንት ነው ያመጣው?
- ዘጠኝ ከሃምሳ፡፡
- አይደረግም?
- ተደርጐማ እያየኸው ነው፡፡
- አገሪቱ በሁለት ዲጂት እያደገች የእኔው ጉድ ነጠላ አኃዝ ውጤት ያመጣል፡፡
- እውነትም ጤና የለህም፡፡
- በቃ ዛሬ ማታ መቀመጥ አለብን፡፡
- ምንድን ነው የምንቀመጠው?
- ግምገማ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ከአማካሪያቸው ጋር እያወሩ ነው]
- እንኳን ደስ አለዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለምኑ?
- ለሹመቱ ነዋ፡፡
- ተሾምኩ እንዴ?
- ያው የሥራ አስፈጻሚው ውስጥ ገቡ አይደል እንዴ?
- ታዲያ እሱ ሹመት ነው?
- ለነገሩ ስጦታ ነው ብለው ነው?
- ምን ማለት ፈልገህ ነው?
- ያው በጣም ተገምግመው ስለነበሩ …
- ይባረራሉ ብለህ አስበህ ነበር?
- እህሳ፡፡
- እና ለዛ ነው ስጦታ ነው ያልከኝ?
- ትክክል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እባክህ ይኼን ጨዋታ በሚገባ አውቀዋለሁ፡፡
- የቱን ጨዋታ?
- የግምገማ ጨዋታውን፡፡
- ለነገሩ ከሃያ ዓመታት በላይ ተጫወቱት አይደል?
- ስለዚህ ጨዋታውን ለእኛ ተወው፡፡
- እኔ የምለው ተዋችሁት እንዴ?
- ምኑን?
- መተካካቱን፡፡
- ለጥቂት እኮ ነው የተረፍኩት፡፡
- እንዴት?
- እኛን ቄስ እግዚአብሔር ዕድሜ ይስጣቸው፡፡
- አልገባኝም?
- ይህ መገፋፋት እንጂ መተካካት አይደለም ብለው እኮ ነው ስበው የመለሱኝ፡፡
- እንጂ ተተክተው ነበር?
- ለጥቂት ነው የተረፍኩት ስልህ፡፡
- ለወጣቶቹ ግን ለምን አይለቁም?
- ለቀን የት እንሂድ?
- ኧረ ክቡር ሚኒስትር ይህ እንዴት ያስጨንቅዎታል?
- እንዴት አያስጨንቀኝ?
- ቢያንስ ጥሩ አባት መሆን ይችላሉ፡፡
- ይኸው አሁንስ ቢሆን የዘጠና ሚሊዮን ሕዝብ አባት አይደለሁ እንዴ?
- ለነገሩ ይኼ የሁላችሁም ፖለቲከኞች ችግር ነው፡፡
- እንዴት?
- ተቃዋሚዎቹም ቢሆኑስ ከጥቂቶቹ በስተቀር ሁሉም ሥልጣናቸውን መቼ መልቀቅ ይፈልጋሉ?
- እኛ እስረኛ ከለቀቅን አይበቃንም እንዴ?
- ብቻ ክቡር ሚኒስትር ይኼን መተካካት ያስቡበት፡፡
- ይኸው አንተ ወጣት ሆነህ ከእኔ ጋር እየሠራህ አይደል እንዴ?
- ወጣቱ ሥልጣን ላይ መውጣት አለበት፡፡
- ሥልጣን ላይ ካልወጣ አገር ማገልገል አይችልም?
- እናንተስ ከሥልጣን ወርዳችሁ አገር ማገልገል አትችሉም?
- ይኼ መገፋፋት ነው፡፡
- የለም መተካካት ነው፡፡
[የክቡር ሚኒስትሩ ወዳጅ ባለሀብት ደወለላቸው]
- በሰላም ጨረሳችሁ ክቡር ሚኒስትር?
- የማያልቅ ነገር የለም ያው አለቀ፡፡
- ሳይጨርሳችሁ መጨረሳችሁ መልካም ነው፡፡
- እንዴት ማለት?
- ያው አደገኛ ግምገማ መሆኑን ሰምቻለሁ፡፡
- አደገኛ ብቻ? ዋናው መትረፋችን ነው፡፡
- ግምገማ ብቻ ምንም ጥቅም የለውም፡፡
- እንዴት ማለት?
- ከፍተኛ ችግር ነዋ ያለው፡፡
- የምን ችግር?
- የመልካም አስተዳደር፣ የፍትሕ፣ የሙስና ኧረ ስንቱ፡፡
- እኛም የተገማገምነው እሱ ላይ ነው፡፡
- እርስዎም ክፉኛ እንደተገመገሙ ሰምቻለሁ፡፡
- አዎን ተገምግሜያለሁ፡፡
- እና ምን ወሰኑ?
- ያው ለመለወጥ ወስኛለሁ፡፡
- አይ ጥሩ ነው፡፡
- ስለዚህ ከአንተ ጋርም ያለኝ ግንኙነት መቀነስ አለበት፡፡
- ይሻላል?
- ያው ለውጡ ከዚህ ነው የሚጀምረው፡፡
- ያፅናልዎት፡፡
- አሜን!
[የክቡር ሚኒስትሩ ወዳጅ ሌላ ሚኒስትር ደወሉ]
- ተረፉ ክቡር ሚኒስትር?
- ከምኑ?
- ከመዓቱ፡፡
- ይኸው ቆሜ እሄዳለሁ፡፡
- ቀጣዩስ ምንድን ነው?
- ሹመት ነዋ፡፡
- ሽረቱንም መጠበቅ ጥሩ ይመስለኛል፡፡
- የሰማኸው ነገር አለ እንዴ?
- የሚወራውማ ብዙ ነው፡፡
- እኮ ምን ሰማህ?
- ሊቀየሩ ይችላሉ?
- ወዴት?
- ወደ ሌላ መሥሪያ ቤት፡፡
- ለምን?
- ያው በግምገማው ምክንያት ነዋ፡፡
- ይኼማ ሊደረግ አይችልም፡፡
- ለምን?
- የመሥሪያ ቤቱ ራዕይስ?
- የሚመጣው ሰው ያስቀጥለዋላ፡፡
- በሕይወት እያለሁ ሌላ ሰው ሊያስቀጥለው?
- ምን ችግር አለው?
- ራዕዩንማ እኔ ነኝ ማስቀጠል ያለብኝ፡፡
- ተፈርቶ እኮ ነው፡፡
- ምንድን ነው የተፈራው?
- ራዕዩን እንዳያቋርጡት፡፡
- ሂሴን ዋጥኩ አይደል እንዴ ከዚህ በላይ ምንድን ነው የምትፈልጉት?
- ሂስዎትን እንዲያወራርዱት ነዋ፡፡
- በምንድን ነው የማወራርደው?
- ከሥልጣን በመውረድ ነዋ፡፡
- ኧረ ይቀየርልኝ፡፡
- በምን?
- በውኃ እንዳወራርደው፡፡
- ሳይዋረዱ መውረድ ነው የሚሻለው እባክዎት፡፡
- ከየት?
- ከሥልጣን!
[ክቡር ሚኒስትሩ ቤት ሲገቡ ልጃቸውን መገምገም ጀመሩ]
- ምንድን ነው የምሰማው?
- ምን ሰማህ አባዬ?
- ሱስ ይዞሃል አሉ፡፡
- የምን ሱስ?
- የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አልልህ የሲጋራ ነዋ፡፡
- እ…
- ብለህ ብለህ የአገር ውስጥ እያለልህ የውጭ ሲጋራ?
- ምን?
- በዛ ላይ የኒዮሊብራሎቹን ሲጋራ ታጨስልኛለህ?
- ምንድን ነው የምታወራው አባዬ?
- ኢምፖርት ሰብስቲትዩሽን ላይ እየደከምን ጉድ ትሠራን?
- ኧረ አልገባኝም?
- ከዚያም አልፎ ኤክስፖርት የሚደረግ ምርት ለአገር ውስጥ ፍጆታ እያዋልክልኝ ነው?
- የምን ኤክስፖርት የሚደረግ ምርት ነው?
- ጫት ነዋ፡፡
- እ…
- ይህ አልበቃ ብሎህ የነጠላ አኃዝ ውጤት ማስመዝገብ ጨምረሃል፡፡
- የምን ነጠላ አኃዝ ነው?
- በፈተና ያመጣኸው ውጤት ነው፡፡
- ከብዶኝ ነዋ፡፡
- ቢከብድህስ እንዴት ነጠላ አኃዝ ውጤት ታመጣለህ?
- ምን ላድርግ ታዲያ?
- ምን እየተደረግክ እንደሆነ ታውቃለህ?
- አላውቅም፡፡
- እየተገመገምክ ነው፡፡
- በምን?
- በኪራይ ሰብሳቢነት!
- ልክ እንደ አንተ?