Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ከቡና ኢንቨስትመንት ወደ ታሸገ ውኃ ምርት

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ከ16 ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ ያልተመደና ለአገሬው እንግዳ የነበረው የታሸገ ውኃ ምርት ወደ ገበያ ሲገባ ብዙዎችን አነጋግሮ ነበር፡፡ በወቅቱ በአቶ ኤርሚያስ አመልጋ ባለቤትነት በአፔክስ ኩባንያ ሥር መመረት የጀመረው ‹‹ሐይላንድ›› የሚል መጠሪያ ያለው የታሸገ ውኃ ተመርቶ ለገበያ ሲቀርብ ነገሩን እንደ ቅንጦት የተመለከቱ ብዙዎች ነበሩ፡፡ በዚያን ጊዜ አንድ ሊትር የታሸገ ውኃ የችርቻሮ ዋጋው ከመጀመርያው ባለጋዝ ውኃ ምርት ከሆነው ከአምቦ ውኃም በላይ ሆኖ አምስት ብር ይሸጥ ነበር፡፡ አንድ ሊትር ውኃ በዚያን ያህል ዋጋ ገዝቶ ለመጠቀም እንዴት ይቻላል? የሚል ጥያቄም ማስነሳቱ ይታወሳል፡፡ በተለይ ለአንድ ሊትር ውኃ ዋጋ የተቆረጠለት አምስት ብር አብዛኛው የከተማ ነዋሪ ለባንቧ ውኃ በወር የሚከፍለው ነው በሚልም የታሸገ ውኃን በአምስት ብር መግዛት ከባድ ስለሚሆን የአቶ ኤርሚያስ እንግዳ ቢዝነስ እንደማይቀጥል እምነት የነበራቸውም ነበሩ፡፡ ሆኖም ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኖ ሐይላንድ ገበያውን ያዘ፡፡ ገበያ ሳያጣ ቀጠለ፡፡ የሐይላንድ የደራ ገበያን የተመለከቱ  ሌሎች የታሸገ ውኃ ማምረቻ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ ገቡ፡፡

  በሐይላንድ ውኃ አንድ ብሎ የጀመረው የታሸገ ውኃ ማምረቻዎች ቁጥር አሁንም እያደገ ቢመጣም፣ ያለውን የገበያ ፍላጎት አላሟላም እየተባለ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዙሪያ የተጀመረው የታሸገ የውኃ ምርት አሁን ሁሉንም ክልሎች ማዳረስ ችሏል፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱትም በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች  የታሸገ ውኃ ማምረቻዎች ቁጥር ከ30 በላይ ስያሜ ያላቸው የታሸገ ውኃ ምርቶች ለገበያ እያቀረቡ ነው፡፡ ይሁንና በዚህ ቢዝነስ ውስጥ በተለያዩ ስያሜዎች የሚጠሩ የታሸጉ ውኃዎች ያሉ ቢሆንም፣ አብዛኛው ሸማች የታሸገ ውኃ ለመግዛት ሲፈልግ ሌሎችን ምርቶች ስም በቀጥታ ከመግለጽ ይልቅ ‹‹ሐይላንድ አለ?›› ማለት ይቀናዋል፡፡ ይህ የሆነው የታሸገ ውኃ ምርት ሐይላንድ ፈር ቀዳጅ በመሆኑ እንደሆነ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ ዛሬ ሐይላንድ የለም፡፡ በታሸገ ውኃ ምርትና ገበያ ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶችና የንግድ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው በዚህ ዘርፍ ለመግባት እየተንቀሳቀሱ ወይም ፈቃድ የወሰዱ ከ20 በላይ ኩባንያዎች መኖራቸውን ነው፡፡ በቅርቡም ወደ ስድስት የሚሆኑ አዳዲስ የታሸገ ውኃ ማምረቻዎች ወደ ሥራ ይገባሉ እየተባለ ነው፡፡

  ከነዚህ ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው አባሃዋ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል  ኩባንያ ነው፡፡ ኩባንያው ‹‹ዋን›› የሚል መጠሪያ የሰጠውን የታሸገ ውኃ ምርት በከፍተኛ ደረጃ ለማምረት ዝግጅት ማጠናቀቁንም ባለፈው ቅዳሜ ይፋ አድርጓል፡፡ በቡና ዝግጅትና ላኪነት የሚታወቀው አቡሃዋ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ በአሁኑ ወቅት የታሸገ ውኃ ፋብሪካ ግንባታውን በማጠናቀቁ ከሁለት ሳምንት በኋላ ዋን የተባለውን የታሸገ ውኃ ለገበያ እንደሚያቀርብ የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ አቶ እንየው ዘለቀ ገልጸዋል፡፡

  እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ ኩባንያቸው ወደዚህ ኢንቨስትመንት የገባው በዘርፉ ያለውን አዋጭነት በጥናት በማረጋገጡ ነው፡፡ ለታሸገ ውኃ ማምረቻ ፋብሪካው ግንባታና ለማሽነሪ ተከላ 150 ሚሊዮን ብር እንዲሁም ለጥሬ ዕቃ ግዥ ደግሞ ወደ 50 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል፡፡ በፊንፊኔ ዙሪያ ሰበታ ልዩ ዞን ሞግሌ የተባለውን ተራራ ተጠግቶ የተገነባው ይህ ፋብሪካ በቀን 14 ሺሕ ባለ 600 ሚሊ ሊትር የታሸገ ውኃ የማምረት አቅም ያለው ነው ተብሏል፡፡ 

  ለአባሃዋ የታሸገ ውኃ ለማምረት የሚያስችለውን የአዋጭነት ጥናት ያጠናው ኤችኤን ኢንጂነሪንግ ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሔኖክ ነጋሽ እንደገለጹት፣ የታሸገ ውኃ ምርት አዋጭ መሆኑን አረጋግጠናል፡፡

   በገበያው ውስጥ በርካታ የታሸገ ውኃ ማምረቻዎች እያሉ በዚህ ቢዝነስ መግባት እንዴት አዋጭ ይሆናል የሚል ጥያቄ የተነሳ ቢሆንም፣ አቶ ሔኖክም ሆኑ የአባሃዋ የሥራ ኃላፊዎች ገበያው ችግር የሌለው መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

  በአሁኑ ወቅት በርካታ የውኃ ማምረቻዎች ቢኖሩም አሁንም ገበያው አልተነካም ይላሉ፡፡ እንደ አቶ ሔኖክ፣ ገለጻ በድርጅታቸው ጥናት መሠረትም የታሸገ ውኃ ገበያ ወደፊት እያደገ የሚሄድ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በምርት ሥራ ላይ ወደ 32 ፋብሪካዎች ያሉ ሲሆን፣ ከአምስት ዓመት በፊት ግን 15 ብቻ እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡ በቅርቡም ወደ ስድስት አዳዲስ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ ይገባሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው ይላሉ፡፡ በጥቅሉ የታሸገ ውኃ ለማምረት ፈቃድ የወሰዱና ግንባታ ላይ ያሉ ከ20 በላይ የውኃ ፋብሪካዎች ይኖራሉ ተብለው እንደሚጠበቅም መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህም የታሸገ ውኃ ማምረቻዎችን ቁጥር በቅርቡ ወደ 60 ያደርሳል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ ወደፊትም በዚህ ዘርፍ የሚገቡ እንደሚኖሩ የሚገመት ሲሆን፣ ገበያው ሰፊ በመሆኑ አንዳንዶች ወደ ማስፋፊያ ሥራ እየገቡ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

  የታሸገ ውኃ ፋብሪካ ቢበዛም ገበያው እንዳለ የኩባንያው ጥናት እንዳረጋገጠ የሚገልጹት  አቶ ሔኖክ ገበያው የማያቋረጥ ዕድገት እያሳየ የሚቀጥል ነው ይላሉ፡፡ ባለፉት አሥር ዓመታት የታየው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ብዙዎችን የታሸገ ውኃ ለመግዛት አቅም የፈጠረላቸውና ወደፊትም የታሸገ ውኃ ፍላጎት እየጨመረ እንደሚሄድ ያሳያል፡፡ በተለይ የከተማ ነዋሪዎች ቁጥር በየዓመቱ አራት በመቶ እያደገ የሚሄድ ስለሚሆን ለታሸገ ውኃ ገበያ ምቹ መሆኑንም አቶ ሔኖክ አስረድተዋል፡፡

   በኩባንያቸው ጥናት መሠረት በ2025 በኢትዮጵያ የታሸገ ውኃ ፍጆታም ከ6.69 ሚሊዮን ሔክቶ ሊትር የሚደርስ መሆኑንም ያሳያል፡፡ የታሸገ ውኃ ምርት ዕድገት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገሮችም በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን ገልጸው፣ ውኃን ከዚህ ቀደም ከምንጠቀምበት በተለየ ጥቅም ላይ የማዋል ልምዱ በማደጉ የታሸገ ውኃ ፍላጎት እያደገ ሊመጣ ችሏል ብለዋል፡፡

  ጥናቶች እንደሚያለክቱት እ.ኤ.አ. በ2015 በጀት ዓመት የታሸጉ ውኃዎች ምርት 214 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል፡፡ ትራንስፓረንሲ ማርኬት ሪሰርች የተባለው ተቋም ጥናት ደግሞ እ.ኤ.አ. በ2020 የታሸገ ውኃ ምርት ሽያጭ ከ279.6 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ይተነብያል፡፡ የሚሸጠው የውኃ መጠንም 465.12 ቢሊዮን ሊትር እንደሚደርስ ግምቱን አስቀምጧል፡፡

  እንደ ትራንስፓረንሲ ማርኬት ሪሰርች መረጃ እ.ኤ.አ. በ2013 የታሸገ ውኃ ምርት ሽያጭ መጠን 157.27 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር አስታውሰው፣ ይህ የሽያጭ መጠን በየዓመቱ 8.7 በመቶ እያደገ ይሄዳል፡፡ የሚሸጠው የውኃ መጠንም በ8.3 በመቶ ያድጋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2011 ላይ ዓመታዊ ሽያጩ 181.61 ቢሊዮን ሊትር ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ2012 ደግሞ 288 ቢሊዮን ሊትር ነበር፡፡ በኢትዮጵያም የታሸገ ውኃ ምርት እያደገ መምጣቱ በግልጽ የሚታይም ነው ተብሏል፡፡

  በኢትዮጵያ የሚመረተው የታሸገ ውኃ ምርት ለአገር ውስጥ ፍጆታ ብቻ  ሳይሆን ለውጭ ገበያ ሊቀርብ የሚችል በመሆኑ፣ የዋን ውኃ ዕቅድም የጥራት ደረጃና ክምችት ያለ በመሆኑ ውኃው በተለይ በምሥራቅ አፍሪካ ገበያ እንዲገባ የሚያስችል ቅድመ በጀት አድርጓል ተብሏል፡፡ ይህ ምክንያታዊ መሆኑን የገለጹት አቶ ሔኖክ፣ የታሸገ ውኃ ለማምረት ኢትዮጵያ ከሌሎች የምሥራቅ አፍሪካና ከኮሜሳ አባል አገሮች የተሻለ ተፈጥሮ ስላላት ነው ይላሉ፡፡

  የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ አቶ እንየው እንደገለጹትም፣ ኩባንያቸው የሚያመርተውን የታሸገ ውኃ ‹‹ዋን›› ውኃ የሚል መጠሪያ የተሰጠው በውጭ ገበያ በቀላሉ ለመግባት እንዲቻል በማሰብ ጭምር ነው፡፡ በአካባቢው አገሮችም እንደ ኢትዮጵያ የታሸገ ውኃ ማምረቻ ፋብሪካ ያላቸው አገሮች ሊኖሩ ቢችሉም፣ በኢትዮጵያ የተሻለ ዕድል መኖሩን ይጠቅሳሉ፡፡ የዚህን ያህል የታሸገ ውኃ ማምረቻዎች መስፋፋት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በተለያየ መንገድ የሚገለጽ ነው፡፡ ያነጋገርናቸው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት፣ የታሸገ ውኃ ቢዝነስ አዋጭ ስለመሆኑ እየታየ ነው፡፡ ዘርፉ ከሌሎች ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች በተሻለ ትርፍ የሚያስገኘ መሆኑ ቢዝነሱ የብዙዎችን ቀልብ እየሳበ በመምጣቱ ነው፡፡

  የአብዛኛው የንግድ ኅብረተሰብ በቶሎ ትርፍ የሚያስገኝ ዘርፍ ላይ የመሰማራት ባህል ማዳበሩን የሚያሳይ ነው የሚል አስተያየትም አክለዋል፡፡ በአንፃሩ ግን የእነዚህ ፋብሪካዎች መስፋፋት አሁን ባለው ደረጃ ከዚህ ቀደም ከውጭ ይገባ የነበረው የታሸገ ውኃ ከውጭ እንዳይገባ ማድረግ ችለዋል፡፡ ከ15 ዓመታት በፊት ግን የታሸገ ውኃ ከውጭ ይገባ ስለነበር ይህንን በአገር ውስጥ በማምረት ምርቱን መተካቱ ትርጉም የሚሰጥ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳለውም ይነገራሉ፡፡ ለሥራ ዕድል ፈጠራም ይረዳል፤ ለውኃ የሚከፈለው ቀረጥም ከፍተኛ በመሆኑ ለግብር ዕድገት የራሱ አስተዋጽኦ ስለሚኖረው በተለይ ማምረቻዎቹ የወጪ ንግድን ትኩረት ካደረጉ ዘርፎች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የጎላ እንደሚሆን ጠቅሰዋል፡፡

  እንደ አባሃዋ የሥራ ኃላፊዎችም በዚህ መሰማራታቸው የተለያዩ ጠቀሜታዎችን ያስገኛል፡፡ በተለይ አዳዲስ አሠራሮችን ይዘው እንደሚቀርቡና ለውጭ ገበያ ሊቀርብ በሚችል ደረጃ ወደ ምርት የሚገቡ በመሆናቸው የውጭ ገበያውንም እንደሚያሳኩ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም የምርቱን የጥራት ደረጃ ማረጋገጫ ለማግኘት ተዘጋጅተዋል፡፡ 13 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የተገነባው የዋን ውኃ ማምረቻ ለ166 ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሏል፡፡

  ውኃው የጥራት ደረጃ ለታሸገ ውኃ ምርት ተስማሚና በቂ ክምችት ያለበት ሥራ የተመረጠ በመሆኑ፣ በሰከንድ 15 ሊትር ውኃ የሚገኝበት አካባቢ ነው፡፡ ውኃው ከፍተኛ ክምችት ስላለውም ተጨማሪ ማስፋፊያ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ጥናት ተግባራዊ ሲሆን፣ የዋን የታሸገ ውኃ ምርትን በከፍተኛ ደረጃ ያሳድጋል ተብሏል፡፡

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች