[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ ቢሯቸው ገባች]
- እንኳን አደረስዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለምኑ?
- ለዘመን መለወጫው ነዋ፡፡
- አንቺ ኪራይ ሰብሳቢ ሆነሻል ልበል?
- የምን ኪራይ ስብሰባ አመጡ?
- ዘመኑ ለምን ሲባል ነው የሚለወጠው?
- መለወጥ ስላለበት ነዋ፡፡
- ዘመኑማ አይለወጥም፡፡
- ለምን አይለወጥም?
- ዘመኑ የእኛ ነው፤ አይለወጥም አልኩሽ፡፡
- ኧረ እኔ እንደሱ ማለቴ አይደለም፡፡
- ታዲያ ምን ማለትሽ ነው?
- እኔ ለአዲሱ ዓመት እንኳን አደረሰዎት ለማለት ፈልጌ ነው፡፡
- ገና አይደለን እንዴ?
- እሱማ ገና ነን ግን የእርስዎ ስጦታዎች አስታውሰውኝ ነው፡፡
- ምኑን ነው ያስታወሱሽ?
- አዲሱን ዓመት ነዋ፡፡
- የምን ስጦታ ነው?
- የአዲስ ዓመት ስጦታው እኮ እየጐረፈልዎት ነው፡፡
- ምን መጥቶልኝ ነው?
- ይኸው የፖስት ካርድና የካላንደር መዓት እየጎረፈ ነው፡፡
- ያ ነው ስጦታው?
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር ስጦታ አይናቅም፡፡
- በይ እኔ የማስቀምጥበትም ቦታ ስለሌለኝ ለሠራተኛው አከፋፍይልኝ፡፡
- ምኑን?
- ስጦታውን፡፡
- ሁሉንም?
- አዎን አልኩሽ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ተለውጠዋል ልበል?
- ታዲያ ዘመኑ ብቻ ነው የሚለወጠው?
- እና የመጡትን ኬኮች፣ መጠጦችንም ለሠራተኛው ላከፋፍለው?
- እሱን ማን አለሽ?
- ታዲያ ምኑን ነው ያሉኝ?
- የኪራይ ሰብሳቢዎቹን ስጦታ ነው ያልኩሽ፡፡
- የትኛው ነው የኪራይ ሰብሳቢዎቹ ስጦታ?
- ይኼ ፖስት ካርድና ካላንደር ነዋ፡፡
- ሌላውንስ?
- ሌላውንማ በአስቸኳይ ወደ ቤቴ ላኪልኝ፡፡
- የተለወጡ መስሎኝ?
- ዘመኑ ከተለወጠ ይበቃል፡፡
- ይህን ሁሉ ኬክ ወደ ቤት ልላከው?
- ስንት ኬክ መጥቶ ነው?
- እስካሁን አሥር መጥቷል፡፡
- አዎ ሁሉንም ላኪው፡፡
- ኬክ ቤት ሊከፍቱ ነው እንዴ?
- ያልተጠየቅሽውን ለምን ታወሪያለሽ?
- ትንሽ ቢያካፍሉን ብዬ እኮ ነው?
- እኔ ማካፈል አልወድም፡፡
- ምንድነው የሚወዱት?
- መደመርና ማባዛት፡፡
- ካላካፈሉ ግን ኋላ ላይ መቀነስዎት አይቀርም፡፡
- ማን ነው ያለው?
- መርሁ እንደዚያ ነው፡፡
- ቀስ ብለሽ ሥልጣንህንም አካፍል ልትይኝ ነው?
- መጨመር ከፈለጉ ማካፈል አለብዎት፡፡
- ከሥልጣኔ ማካፈል የምፈልገው ጭንቀቴን ብቻ ነው፡፡
- እንግዲያውስ የሚበዛልዎትም እሱ ይሆናል፡፡
- ምኑ?
- ጭንቀቱ፡፡
[የክቡር ሚኒስትሩ ጓደኛ ሚኒስትር ደወለላቸው]
- እንኳን አደረስዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንኳን አደረሰህ፡፡
- የበዓሉ ዋዜማ እንዴት ነው?
- እኔ ጋ በዓሉ ከአሁኑ እየደመቀ ነው፡፡
- እንዴት?
- ይኸው የአገር ስጦታ እየጐረፈልኝ ነው፡፡
- የምን ስጦታ?
- የበዓሉ ነዋ፡፡
- እኮ ምን መጣልዎት?
- እስካሁን እንኳን አሥር ኬክ መጥቷል፡፡
- ሌላስ?
- መጠጦችም ብትል ቢሮዬን ሞልተውታል፡፡
- ሌላስ?
- በጐችስ ብትል፡፡
- ለዚያ ነው የበግ ድምፅ የሚሰማኝ?
- አምስት ሙክቶች የመሥሪያ ቤቴ ግቢ ውስጥ ቆመዋል፡፡
- መሥሪያ ቤት መሆኑ ቀርቷላ፡፡
- ታዲያ ምንድነው?
- የበጐች ጉሮኖ ሆኗላ፡፡
- ቀልደኛ ሆነሃል ልበል?
- እርስዎ ነዎት እንጂ ቀልደኛ፡፡
- እንዴት?
- ትንሽ እግዚአብሔርን እንኳን አይፈሩም?
- ምን አልከኝ?
- ሌላው ቢቀር ግምገማውን አይፈሩም፡፡
- የምን ግምገማ? አለቀ አይደል እንዴ?
- ክቡር ሚኒስትር ምን ያህል እንደተገመገሙ ያውቃሉ አይደል እንዴ?
- ግምገማውማ ከባድ ነው፡፡
- ታዲያ ተመልሰው እዚያው?
- ወድጄ አይደለም፡፡
- ማን አስገደድዎት?
- ግምገማ ራሱ፡፡
- እንዴት?
- ግምገማው በጣም ጐድቶኛል፡፡
- እና?
- ማገገም ያስፈልገኛል፡፡
- በምን?
- በእነዚህ ስጦታዎች፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ብቻ ይጠንቀቁ፡፡
- ከምን?
- ሳያገግሙ ዳግም እንዳይገመገሙ፡፡
[የክቡር ሚኒስትሩ ወዳጅ ዳያስፖራ ደወለላቸው]
- እንኳን አደረስዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንኳን አደረሰህ ወዳጄ፡፡
- እንዴት ነው በዓሉ?
- ይኸው እዚህ ሞቅ ሞቅ እያለ ነው አንተስ ጋ እንዴት ነው?
- እዚህ እኛ ጋ ሥራ ነው፡፡
- ዕረፍት አትወጣም እንዴ? አንተ እኮ ሀብታም ነህ?
- ክቡር ሚኒስትር ዝም ብሎ እኮ ሀብታም አይኮንም፡፡
- እንዴት?
- ያለዕረፍት ስለምንሠራ ነው ሀብታም የሆነው፡፡
- እኛም እኮ ይኼን ባህል ለማምጣት ነው እየሠራን ያለነው፡፡
- አገር ቤትማ ብዙ በዓላት ናቸው ያሉት፡፡
- ተው ተው የሕዝቡን ሃይማኖት መንካት አይፈቀድም፡፡
- ኧረ እኔ መቼ እሱን ወጣኝ?
- ታዲያ የምን በዓል ነው የምትለው?
- የመንግሥት በዓል ነዋ፡፡
- መንግሥት ይሠራል እንጂ በዓል አያከብርም፡፡
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር አንዴ የባንዲራ፣ አንዴ የብሔር ብሔረሰብ፣ አንዴ የፍትሕ እያላችሁ ስታከብሩ አይደል እንዴ የምውትሉት?
- እ…
- እንደ እኔ እንደ እኔ ግን የፍትሕን ቀን ከማክበር ፍትሕን ማስፈን ይሻላል፡፡
- እሱማ ልክ ነው፡፡
- ለማንኛውም ዛሬ የደወልኩት ለሌላ ጉዳይ ነው፡፡
- ለምንድነው?
- የበዓል ስጦታ ለመላክ፡፡
- የአንተን ውለታ በምን እንደምከፍለው አላውቅም፡፡
- አያስቡ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ላክልኝ ታዲያ?
- የዚህን ዓመት የልጅዎን ትምህርት ቤት ክፍያ እኔ ነኝ የምከፍለው፡፡
- አይበዛብህም?
- ለእርስዎ ይኼ ሲያንስብዎት ነው፡፡
- እንዲያው አሁን አሁን እኮ እየፈራን መጣን፡፡
- ምንድነው የሚፈሩት?
- አሁን ይኼንንም ሙስና ይሉታል፡፡
- ይኼማ ሙስና አይደለም፡፡
- ታዲያ ምንድነው?
- የዓመት በዓል ስጦታ፡፡
- ታዲያ እኔስ ምን የዓመት በዓል ስጦታ ልስጥህ?
- ክቡር ሚኒስትር እርስዎማ ብዙ የሚሰጡኝ ነገር አለ፡፡
- እኮ ንገረኛ?
- ያው ፕሮጀክቴን በዚህ በአዲሱ ዓመት ልጀምረው አስቤያለሁ፡፡
- ምን ላድርግ ታዲያ?
- ያው የመሬቱን ነገር ያስቡበት?
- እሱ በአንድ ስልክ የሚያልቅ ነገር ነው፡፡
- ማሽኖቹም በቅርቡ ይገባሉ፡፡
- ታዲያ ምን ያስፈልጋል?
- ያው የታክሱን ጉዳይ ብዬ ነው፡፡
- አንተ እኮ የልማት አጋር ነህ፡፡
- አመሰግናለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ከሾፌራቸው ጋር ወደ ቤት እየሄዱ ነው]
- ሁሉንም ስጦታዎች ቤት አደረስካቸው?
- አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ምንድነው ያደረስከው?
- አሥር ኬክ፣ አምስት በግና በርካታ መጠጦች፡፡
- ለመሆኑ በዓል እንዴት ነው?
- የምን በዓል?
- አዲስ ዓመት ነዋ፡፡
- እኔ እኮ በዓል ማክበር ካቆምኩ ቆየሁ፡፡
- ለምን? ፈረንጅ ነህ እንዴ?
- ይኼ ኑሮ ውድነት አይደለም ፈረንጅ ገና ሌላ ነገር ያደርገኛል፡፡
- እና አታከብርም?
- ክቡር ሚኒስትር በዓል ማክበር ትቼ ሰዎችን ማክበር ጀምሬያለሁ፡፡
- ለነገሩ ሰው ማክበር ጥሩ ነው፡፡
- ቤት ድግስ አለብዎት እንዴ?
- የለብኝም፤ ምነው ጠየቅከኝ?
- አይ ያ ሁሉ በግ፣ ኬክና መጠጥ ብዬ ነው፡፡
- ለበዓል ነው፡፡
- ይህ ሁሉ ለበዓል?
- ወዳጆቼ ስጦታ ሰጥተውኝ ነው፡፡
- እኔ ግን የሁለቱ ልዩነት አይገባኝም፡፡
- የምንና የምን?
- የስጦታና የሙስና!
[ክቡር ሚኒስትሩ ቤት ገብተው ከሚስታቸው ጋር ማውራት ጀመሩ]
- የበዓል ዝግጅቱ እንግዲህ ከወዲሁ ይጀመር፡፡
- ይኼ ሁሉ በግ ምንድነው?
- ስጦታ ተሰጥቶኝ ነው፡፡
- የምን ስጦታ?
- የበዓል ነዋ፡፡
- ታዲያ ምን ልናደርገው ነው?
- አንዱን በግ ለቀይ ወጥ ሌላውን ላልጫ እያልሽ ሁሉንም ሥሪልኝ፡፡
- አንተ ግን ይበላልሃል?
- ለምን አይበላልኝም?
- የሙስና በግ ነዋ፡፡
- አትሳሳቺ የስጦታ በግ ነው፡፡
- ለመሆኑ አንድ ለአምስት አደረጃጀቱን በዚህም ተገበራችሁት ማለት ነው?
- በምኑ?
- አምስት በግ…
- እ…
- ለአንድ ባለሥልጣን!
- ወሬ አለብሽ፡፡
- ሰው በአዲስ ዓመት ይለወጣል አንተ ግን እዚያው፡፡
- ተለውጬ አይደል እንዴ ስጦታ ይዤ የመጣሁት?
- ለነገሩ ተለውጠሃል፡፡
- እኮ ምኔ ነው የተለወጠው?
- የሙስና ሥልትህ!