Monday, August 8, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች 5.5 ቢሊዮን ብር ዓረቦን ሰበሰቡ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  – 2.31 ቢሊዮን ብር ለካሳ ክፍያ አውለዋል

  በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ያሉ 17 የግልና የመንግሥት የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በ2007 በጀት ዓመት፣ ከ5.55 ቢሊዮን ብር በላይ ዓረቦን (ፕሪምየም) ሲሰበስቡ፣ ከታክስ በኋላም ከ823 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማግኘታቸው ተጠቆመ፡፡

  የበጀት ዓመቱ ኦዲት ያልተደረገው የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ ዓመታዊ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በበጀት ዓመቱ ያሰባሰቡት ዓረቦን መጠን ካለፈው በጀት ዓመት በ600 ሚሊዮን ብር ብልጫ አለው፡፡ ይሁንና የተመዘገበው ዕድገት አነስተኛ እንደሆነ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢንሹራንስ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ አሥራ ሰባቱም የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ባለፈው ዓመት ከሰጡት የመድን ሽፋን ማሰባሰብ የቻሉት 4.9 ቢሊዮን ብር እንደነበር ይታወሳል፡፡ በበጀት ዓመቱ ከተሰበሰበው ጠቅላላ ዓረቦን ገቢ ውስጥ 16 የግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በጠቅላላው 3.4 ቢሊዮን ብር፣ መንግሥታዊው  የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ደግሞ 2.1 ቢሊዮን ብር ማሰባሰብ ችለዋል፡፡

  ይህም በግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎችና በኢትዮጵያ መድን ድርጅት መካከል ያለው የገበያ ድርሻ ልዩነት እየሰፋ መምጣቱን ያመለክታል፡፡ በ2006 በጀት ዓመት ሁሉም የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አሰባስበው የነበረው 4.9 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ሁለት ቢሊዮን ብር፣ የግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ደግሞ 2.9 ቢሊዮን ብር ማሰባሰብ ችለው እንደነበር ይታወሳል፡፡

  በበጀት ዓመቱ የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ያሰባሰቡት የዓረቦን መጠን ወደ 500 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ጭማሪ ሲያሳዩ፣ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ደግሞ የዓረቦን መጠኑን ማሳደግ የቻለው በ114 ሚሊዮን ብር ነው፡፡

  ከተለያዩ ኩባንያዎች የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፣ የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ በጥቅል ካሰባሰቡት ዓረቦን ውስጥ 5.24 ቢሊዮን ብር ሕይወት ነክ ካልሆነ የመድን ሽፋን፣ ቀሪው 315.04 ሚሊዮን ብር ደግሞ ከሕይወት ኢንሹራንስ የመድን ሽፋን የተገኘ ነው፡፡ አምና ከተሰበሰበው 4.9 ቢሊዮን ብር ከሚሆነው ዓረቦን ውስጥ ሕይወት ነክ ካልሆነው የኢንሹራንስ ዘርፍ ማሰባሰብ የተቻለው 4.65 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ለሕይወት ኢንሹራንስ መድን ሽፋን የተሰበሰበው ደግሞ 373.87 ሚሊዮን ብር እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

  በኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉት የሁሉም ኩባንያዎች በ2007 ዓ.ም. ከታክስ በፊት ያገኙት ትርፍ 823.6 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ከአምናው ጋር ሲነፃፀር 85 ሚሊዮን ብር አካባቢ ብልጫ አለው፡፡ አምና ከታክስ በኋላ አግኝተውት የነበረው ትርፍ 739.3 ሚሊዮን ብር እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

  ይህ የትርፍ መጠን በቀጥታ ከኢንሹራንስ አገልግሎት ጋር የተያያዘ ብቻ ሳይሆን፣ ኩባንያዎቹ በተለያዩ ኢንቨስትመንቶቻቸው በዓመቱ ውስጥ ያገኙትን ትርፍ የሚያካትት ነው፡፡ በበጀት ዓመቱ የተገኘው የትርፍ መጠንም ሆነ የተሰበሰበው የዓረቦን መጠን ዕድገት ግን አነስተኛ የሚባል እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

  መረጃዎች እንደሚያስረዱት ከሆነ በበጀት ዓመቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ የከፈሉት የካሳ መጠን ደግሞ 2.31 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ አምና በተመሳሳይ ወቅት ለካሳ ከተከፈለው 2.06 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የዘንድሮ ለካሳ ክፍያ የዋለው ብልጫ አሳይቷል፡፡ ሆኖም በበጀት ዓመቱ ከተሰበሰበው ዓረቦን አንፃር የዘንድሮ ካሳ ክፍያ ካለፈው የተሻለ እንደሆነ ሪፖርተር ያነጋገራናቸው የኢንሹራንስ ባለሙያዎች አስረድተዋል፡፡ እንደ ባለሙያዎቹ ገለጻ፣ አምና ከተሰበሰበው ዓረቦን 65 በመቶው ካሳ ጥያቄ የቀረበበት ሲሆን ዘንድሮ ግን 63 በመቶ ነው፡፡ ይህም ከተሰበሰበው ዓረቦን አንፃር በሁለት በመቶ የካሳ ክፍያ ጥያቄው መቀነሱን እንደሚያሳይ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡  

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች