በኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ እንቅስቃሴ ውስጥ የራሱን የአጻጻፍ ዘዬና አሻራ እያሳረፈ እንደሆነ የሚነገርለት አዳም ረታ ‹‹አፍ›› በሚል ርዕስ ያዘጋጀውና በርሱ አጠራር ‹‹ሥግር ልብወለድ›› ያለውን መጽሐፉን ማክሰኞ መጋቢት 11 ቀን 2010 ዓ.ም. በ11 ሰዓት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ያስመርቃል፡፡ ኢጋ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን እንዳስታወቀው ከሀሳብ አሳታሚ ጋር በመተባበር በተዘጋጀው የ10ኛ መጽሐፉ ሥርዓተ ምረቃ ደራሲው በተገኘበት በመጽሐፉ ላይ የሚደረጉ ምልከታዎች፣ የግጥምና የወግ ሥራዎች፣ ከመጽሐፉ የተቀነጨቡ ኮርኳሪ ንባቦችና ሌሎች ኪነጥበባዊ ዝግጅቶች ይቀርባሉ፡፡ አዳም ረታ ከዚህ ቀደም ዘጠኝ ሥራዎቹን ማለትም፡- ማህሌት፣ ግራጫ ቃጭሎች፣ አለንጋና ምስር፣ እቴሜቴ የሎሚ ሽታ፣ ከሰማይ የወረደ ፍርፍር፣ ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ፣ ህማማትና በገና፣ መረቅ፣ የስንብት ቀለማት ማሳተሙ ይታወሳል፡፡