Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናየፓርላማ ተመራጩ አምባሳደር ዶ/ር አዲስ ዓለም ባሌማ የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው...

  የፓርላማ ተመራጩ አምባሳደር ዶ/ር አዲስ ዓለም ባሌማ የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ተሾሙ

  ቀን:

  የትግራይ ክልል ምክር ቤት የሕወሓት ሊቀመንበር አቶ ኣባይ ወልዱ የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት ሆነው እንዲቀጥሉ ሲወሰን፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነው የተመረጡት አምባሳደር ዶ/ር አዲስ ዓለም ባሌማን ምክትላቸው አድርጎ ሾሟል፡፡

  የትግራይ ክልል ምክር ቤት ከመስከረም 14 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ቀናት ባካሄደው የመጀመሪያው መደበኛ ስብሰባ፣ የክልሉ ገዥ ፓርቲ ሕወሓት ባቀረበው ሐሳብ መሠረት አምባሳደር ዶ/ር አዲስ ዓለም ባሌማ ምክትል ፕሬዚዳንትና የከተማ ልማት፣ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ እንዲሆኑ ወስኗል፡፡ በተጨማሪም የቀድሞ የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ በየነ ምክሩና ወ/ሮ አዜብ መስፍን ትእምትን እንዲመሩ ወስኗል፡፡

  እንዲሁም ቀደም ሲል የክልሉ ዕቅድና የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ ዳንኤል አሰፋ የመቐለ ከተማ ከንቲባ ሆነው እንዲሠሩ ሐሳብ የቀረበ ሲሆን፣ በከተማው ምክር ቤት እንደሚፀድቅ ይጠበቃል፡፡ ቦታው ላይ የነበሩት አቶ ተወልደ ብርሃን ተስፋ ዓለም በበኩላቸው የደቡብ ዞን አስተዳዳሪ ሆነው ተሹመዋል፡፡ እንዲሁም ምክር ቤቱ በአዲስ አበባ የሕወሓት ጽሕፈት ቤት አደረጃጀት ኃላፊ የነበሩትን አቶ ብርሃነ ገብረ ኢየሱስ የመቐለ ከተማ ምክትል ከንቲባ አድርጎ መሾሙን ለማወቅ ተችሏል፡፡

  የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፣ በቅርቡ በሕወሓት 12ኛ ጉባዔ በመተካካት በተሸኙት በአቶ ቴድሮስ ሐጎስ ምትክ የቀድሞ የውኃ ሀብት ልማት ኃላፊ አቶ ዓለም ገብረ ዋህድ ተሹመዋል፡፡ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔርን ዳግም የፓርቲው ጽሕፈት ቤት የፕሮፓጋንዳና አደረጃጀት ኃላፊ አድርጎ ድርጅቱ ሾሟል፡፡

  የፕሬዚዳንቱ የአቶ ኣባይ ወልዱ ባለቤት ወ/ሮ ትርፏ ኪዳነ ማርያም የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ አባልና የክልሉ ሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊ የነበሩ ሲሆን፣ በድርጅቱ 12ኛ ጉባዔ ለማዕከላዊ ኮሚቴ ሳይመረጡ መቅረታቸው ይታወሳል፡፡ በመሆኑም በምትካቸው ወ/ሮ አረጋሽ በየነ ተሹመዋል፡፡

  ምክር ቤቱ ወ/ሮ ቅዱስን ነጋ የትግራይ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ፣ አቶ ኪሮስ ቢተው የክልሉ እርሻና ገጠር ልማት ቢሮ፣ አቶ ሐዱሽ ዘነበ የፀጥታና አስተዳደር ቢሮ፣ አቶ ጎበዛይ ወልደ አረጋይ የትምህርት ቢሮ እንዲሁም አቶ ጎይቶም ይብራህ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠናና ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች ሆነው በነበሩበት እንዲቀጥሉ ወስኗል፡፡ እንዲሁም ምክር ቤቱ በአቶ ዳንኤል አሰፋ ምትክ አቶ ብርሃነ ፀጋይ የዕቅድና ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አድርጎ የሾመ ሲሆን፣ አቶ ገብረ መስቀል ታረቀ በአቶ ዓለም ገብረ ዋህድ ምትክ የክልሉ የውኃ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ ልዑል ካህሳይ የክልሉ የፍትሕ ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ ዳዊት ኃይለ ደግሞ የቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አድርጎ ሾሟል፡፡

  በተጨማሪም አቶ ሩፋኤል ሽፈረ ምክትል አፈ ጉባዔ፣ አቶ ኃይለ አሰፋ የእርሻና ገጠር ልማት ሁለተኛ ኃላፊ፣ አቶ ሐጎስ ጎደፋይ የጤና ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ ተስፋይ ገብረ ኪሮስ የኮንስትራክሽን መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ፣ እንዲሁም ዶ/ር ገብረ ሕይወት ገብረ እግዚአብሔር የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ ሆነው ተሹመዋል፡፡

  በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ባለፈው ዓመት በተካሄደው አምስተኛው ዙር ምርጫ ሕወሓት ሁሉንም ወንበሮች መቆጣጠሩ አይዘነጋም፡፡ በምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ዶ/ር አዲስ ዓለምን ጨምሮ አምስት የድርጅቱ አመራሮች ከፌደራል ወደ ክልሉ በመውሰድ በከፍተኛ የሥልጣን እርከን ያስቀመጠ ሲሆን፣ በፓርቲው ጉባዔ እንደተገመገመው በክልሉ የተንሰራፋውን ሥርዓተ አልበኝነት፣ የፍትሕ እጦት፣ አድርባይነትንና ሙስናን ለመታገል ታስቦ እንደሆነ ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በምክር ቤቱ ፊት ባደረጉት ንግግር በክልሉ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን፣ ኪራይ ሰብሳቢዎችን ለመታገልና ማኅበራዊ ለውጥ ለማምጣት ጠንክረው እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል፡፡

  በምርጫው የሕዝብ ተወካዮች አባል ሆነው ምክር ቤት የተመረጡት አምባሳደር ዶ/ር አዲስ ዓለም የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው መመረጥ ጥያቄ ያስነሳ ሲሆን፣ ምንም ዓይነት የሕግ ጥሰት እንደሌለበት አንድ የምክር ቤቱ ኃላፊ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በዜጎች የጋራ ጉዳይ ላይ ተመርኩዘው የተመረጡበትን የምርጫ ክልል ነዋሪዎች እንደሚወክሉ ሲታሰብ፣ የክልል ምክር ቤት አባላት ደግሞ ለክልሉ መብትና ጥቅም እንደሚቆሙ የፌዴራል የመንግሥት መዋቅር መሠረታዊ ሐሳቦች ያሳያሉ፡፡ ከዚህ አንፃር የዶ/ር አዲስ ዓለም የክልል ኃላፊ መሆን በፓርላማ የሚኖራቸው ሚና ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ እንደሚኖረው አስተያየት ሰጪዎች እየገለጹ ነው፡፡ ለአብነትም ያህል ሁለቱም ምክር ቤቶች በተመሳሳይ ወቅት ስብሰባ ሲያካሂዱ የትኛውን ሊመርጡ ነው ሲሉ አስተያየት ሰጪዎቹ ይጠይቃሉ፡፡ ዜጎች በምርጫው ወቅት ድምፅ የሚሰጡትም የትኛው ግለሰብ በየትኛው ምክር ቤት ጥቅሜን ያስከብራል ብለው ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ለኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች አዲስ አይደለም፡፡ ባለፈው ዓመት የፓርላማ አባል የነበሩት አቶ ሙክታር ከድር የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሆነው ሟቹን አቶ ዓለማየሁ አቶምሳን መተካታቸው አይዘነጋም፡፡

    

   

                                                  

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...