Sunday, August 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  የግል ባንኮች የተከፈለ ካፒታላቸውን ሁለት ቢሊዮን ብር እንዲያደርሱ ተወሰነ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  – በየዓመቱ ቅርንጫፎቻቸውንና የሚሰጡትን ብድር በ30 በመቶ አሳድጉ ተብለዋል

  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የግል ባንኮች የሚገዙበትን ጥብቅ መመርያ ባወጠ በቀናት ልዩነት፣ የተከፈለ ካፒታላቸውን ሁለት ቢሊዮን ብር ማድረስ እንዳለባቸው የሚያስገነዝብ ሰርኩላር አስተላለፈ፡፡

  ከአንድ ሳምንት በፊት የወጣው ጥብቅ የተባለው የብሔራዊ ባንክ መመርያ፣ በባንኮች አካባቢ የፈጠረው አነጋጋሪነት ሳይበርድ አዲስ የወጣው የብሔራዊ ባንክ ሰርኩላር ተጨማሪ ሆኗል፡፡

  የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ ብሔራዊ ባንክ ያወጣው ሰርኩላር በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ሁሉም የግል ባንኮች የተከፈለ ካፒታላቸውን ሁለት ቢሊዮን ብር ማድረስ የሚጠበቅባቸው መሆኑን የሚያስገነዝብ ብቻ አይደለም፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን ሁሉም የግል ባንኮች ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው ያላቸውን ሌሎች ክንውኖች ያካተተ ጭምር ነው፡፡

  ሰርኩላሩ ሁሉም የግል ባንኮች የ2007 በጀት ዓመት አፈጻጸማቸውን መነሻ በማድረግ በየዓመቱ የብድር መጠናቸውንና ቅርንጫፎቻቸውን በ30 በመቶ እንዲያሳድጉ በማስገንዘብ፣ የአምስት ዓመታት ዕቅዶቻቸውንም በዚህ መሠረት ቃኝተው ማቅረብ እንደሚኖርባቸው ያሳስባል፡፡ በዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ ሁሉም ባንኮች ምን ያህል ኤጀንት ባንኪንግ ሊኖራቸው እንደሚገባና ሌሎች ሊፈጽሟቸው ይገባሉ የተባሉ ክንውኖች በዝርዝር የተቀመጡበት ነው ተብሏል፡፡

  ከአንድ ሳምንት በፊት ከወጣው ‹የኮርፖሬት ገቨርናንስ› መመርያ ጋር ተያይዞ እንዲሠራ የሚፈለገው የባንኮች ስትራቴጂና በአምስት ዓመታት ሊደርሱበት ይገባል የተባለው አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ሰርኩላር አስጨናቂ መሆኑን፣ አንዳንድ የባንክ የሥራ ኃላፊዎች ይገልጻሉ፡፡

  በተለይ ካፒታላቸውን ሁለት ቢሊዮን ብር ማድረስ አለባችሁ የሚለው የብሔራዊ ባንክን ትዕዛዝን ለማሟላት አስቸጋሪ እንደሚሆንባቸውና ብዙዎቹን የግል ባንኮች እንደሚፈትን ከወዲሁ ሥጋት እንደገባቸው ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የባንክ ኃላፊዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት ባንኮች የተከፈለ ካፒታላችሁን 500 ሚሊዮን ብር አድርሱ የሚለውን መመርያ ለመፈጸም አብዛኛዎቹ ባንኮች የገጠማቸው ፈተና ቀላል እንዳልነበረም ያስታውሳሉ፡፡

  የተከፈለ ካፒታላቸው 500 ሚሊዮን ብር እንዲሆን የሚያዘውን መመርያ ማሟላት ያልቻሉ እንዳሉ እየታወቀ፣ እንደገና ሁለት ቢሊዮን ብር አድርሱ መባሉ እንዳሳሰባቸው የገለጹ አሉ፡፡ ብሔራዊ ባንክ የተከፈለ ካፒታል መጠንን ማሳደጉ የሚጠበቅ ቢሆንም፣ መጠኑ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ይሆናል ብለው እንዳልጠበቁም ሪፖርተር ያነጋገራቸው የባንክ የሥራ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡

  በአሁኑ ወቅት ከ16 የግል ባንኮች ሁለቱ የተከፈለ ካፒታላቸውን 500 ሚሊዮን ያላደረሱ ሲሆን፣ ቀሪዎቹም የተከፈለ ካፒታላቸው ከሁለት ቢሊዮን ብር በታች ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የተከፈለ ካፒታሉን 1.9 ቢሊዮን ብር ያደረሰው አዋሽ ባንክ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ 15 ባንኮች የተከፈለ ካፒታላቸው ከዚህ በታች ነው፡፡

  ሪፖርተር ያነጋገራቸው የባንክ ባለሙያዎች ይህ የካፒታል ዕድገት ትልልቅ ለሚባሉት ባንኮች ብዙም የማያስቸግራቸው ቢሆንም፣ በተለይ የተከፈለ ካፒታላቸው ከአንድ ቢሊዮን ብር በታች የሆነ አብዛኞቹ ባንኮች ላይ ጫና ማሳደሩ አይቀርም ይላሉ፡፡

  እንደ ምንጮች ገለጻ ከሆነ ብሔራዊ ባንክ ባለፈው ሳምንት ከባንክ ፕሬዚዳንቶች ጋር አድርጎት በነበረው ውይይት ላይ የካፒታል ማሳደጉ ጉዳይ በቃል ተገልጾላቸዋል፡፡ በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ካፒታላቸውን ሁለት ቢሊዮን ያላደረሱ ባንኮች እንደ ብቸኛ አማራጭ ሊወሰድ የታሰበው መፍትሔ እንዲዋሀዱ ማድረግ እንደሆነም በውይይቱ ላይ እንደተጠቀሰ፣ ከምንጮች መረዳት ተችሏል፡፡

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች