Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  የባንክና የኢንሹራንስ ባለአክሲዮኖችን ዜግነት የሚቆጣጠር መመርያ ወጣ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  በአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት (ባንክና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች) ውስጥ አክሲዮን የገዙ ባለአክሲዮኖችና ኩባንያዎች ዜግነት ኢትዮጵያዊ መሆን አለመሆን እንዲለዩ፣ ኢትዮጵያዊ ሆነው ካልተገኙ ለብሔራዊ ባንክ ወይም ለሕግ አስከባሪዎች እንዲያሳውቁ ባንኮችንና የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን የሚያስገድድ መመርያ ወጣ፡፡

  እ.ኤ.አ. ከኦክቶበር 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆነውና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ተፈርሞ የወጣው መመርያ፣ የባንክና የኢንሹራንስ ኩባንያ ኃላፊዎች የባለአክሲዮኖቻቸው ዜግነት ኢትዮጵያዊ መሆን ያለመሆኑን በመመርያው መሠረት ካላረጋገጡ፣ ዕርምጃ የሚወስድ መሆኑን የሚያስጠነቅቅ ነው፡፡

  የአክሲዮን የትርፍ ክፍፍልም ሆነ የአክሲዮን ዝውውር ሲደረግ ባለአክሲዮኑ ኢትዮጵያዊ መሆኑን የማረጋገጥ ኃላፊነት ያለባቸው ሲሆን፣ ባለአክሲዮኑ በሚያቀርበው መረጃ ኢትዮጵያዊ ያለመሆኑ ከተረጋገጠ የትርፍ ክፍፍልም ሆነ የአክሲዮን ዝውውር እንዳይካሄድ መመርያው ያዛል፡፡ ኢትዮጵያዊ አለመሆኑ የተረጋገጠበትን ባለአክሲዮንን የሚመለከት መረጃ ለብሔራዊ ባንክና ለፖሊስ እንዲያሳውቁም መመርያው ታዟል፡፡

  በአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ባለአክሲዮን የሆኑ ግለሰቦችና ኩባንያዎች ዜግነት እንደገና እንዲጣራና ለመቆጣጠር ያስችላል የተባለው በመመርያ፣ ከዚህ በኋላ የአክሲዮን ትርፍ ክፍፍል ሲደረግ ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ማረጋገጥ እንደሚገባቸው የሚያስገነዝብ ነው፡፡

  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለባንክና ለኢንሹራንስ ኩባንያዎች ያሠራጨው ይህ መመርያ፣ ኢትዮጵያዊ ላልሆነ ባለአክሲዮን የትርፍ ክፍፍል ሲያደርጉና ባለአክሲዮኑ የውጭ ዜግነት እንዳለው እያወቁ ለፖሊስና ለብሔራዊ ባንክ ካላሳወቁ ዕርምጃ እንደሚወስድባቸው አስታውቋል፡፡

  አክሲዮኖችን በመሸጥ ወይም በማስተላለፍ ወቅት ባለአክሲዮኖች ኢትዮጵያዊ ዜግነት እንዳላቸው ሕጋዊ ማረጋገጫ ሰነዶችን ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ በወኪል አማካይነት የሚፈጸም ከሆነም ወካይ ባለአክሲዮኑ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለው መሆኑን የሚያረጋግጡ ሕጋዊ ሰነዶችን ቅጂ በወኪሉ በኩል ሲቀርቡ፣ የሕጋዊ ማስረጃዎቹ ቅጂ መሆናቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነትም በፋይናንስ ተቋማቱ ላይ ተጥሏል፡፡

  አንድ ባለአክሲዮን የማስተማመኛ ሰነድ ላይ ሲፈርም ከመሸጡ ወይም ከማስተላለፉ አስቀድሞ የሚተላለፍለት ወይም የሚሸጥለት ሰው ኢትዮጵያዊ ዜጋ መሆኑን፣ ወይም ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያዊያን ዜጐች ባለቤትነት ሥር መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚኖርባቸው መመርያው ያስገነዝባል፡፡

  የትርፍ ክፍፍል ክፍያ በሚፈጸምበት ወቅትም መረጋገጥ ይኖርባቸዋል ብሎ በመመርያው ከተቀመጡት ውስጥ፣ በአካል የቀረቡ ባለአክሲዮኖች ሕጋዊና የአገልግሎት ጊዜው ያላለቀ ወይም የታደሰ የቀበሌ መታወቂያ፣ ፓስፖርት፣ የመንጃ ፈቃድ ወይም ኢትዮጵያዊ ዜግነታቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ሲያቀርቡ ብቻ መስተናገድ እንደሚገባቸውም ተካቷል፡፡

  ኢትዮጵያዊ ዜግነት ሊያረጋግጡ የሚችሉበት የታደሰ የቀበሌ መታወቂያ፣ ፓስፖርት፣ የመንጃ ፈቃድ ወይም ሥልጣን በተሰጠው ሌላ አካል የተሰጡ ሰነዶችን ቅጂ ካቀረቡ በኋላ፣ የቀረቡት ቅጂ ሰነዶች እውነተኛ፣ የተረጋገጡና ተገቢ ሕጋዊ ሰነዶች መሆናቸውን ለማረጋገጥ በመተማመኛ ሰነድ ላይ ሊፈርሙ እንደሚገባም ያስገድዳል፡፡

  መመርያው በጥብቅ ያስቀመጠው ሌላው ነጥብ ደግሞ ባንኮች ወይም የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ባለአክሲዮኑ ኢትዮጵያዊ ዜግነት የሌለው መሆኑን ካረጋገጡ፣ የትርፍ ክፍፍል ክፍያዎችን በከፊልም ሆነ በአጠቃላይ፣ እንዲሁም የአክሲዮን ይዞታዎችን በማንኛውም ሁኔታ ከማስተላለፍ እንዲቆጠቡም የሚያሳስብ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ጉዳይ ካጋጠማቸው ተያያዥነት ካላቸው ሰነዶች ጋር በማያያዝ በጽሑፍ ለብሔራዊ ባንክና ለፖሊስ ጉዳዩ ከታወቀበት ቀን ጀምሮ ባሉት አምስት የሥራ ቀናት ውስጥ ሊያሳውቁ ይገባል፡፡

  ከትርፍ ክፍፍል፣ ከሽያጭ፣ ወይም ከመተላለፍ የታገደው አክሲዮኖችን የተመለከተ ዝርዝር መረጃ ለብሔራዊ ባንክ እንዲቀርብ መመርያው ያዛል፡፡ ይህም መረጃ ቢያንስ የበጀት ዓመቱ ከተጠናቀቀ ጀምሮ የፋይናንስ ተቋማቱ እስከ ዘጠኝ ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ ለብሔራዊ ባንክ ማሳወቅ ይኖርባቸዋል፡፡

  ይህንን የብሔራዊ ባንክ መመርያ የተላለፈ ማናቸውም ባንክ ሆነ የኢንሹራንስ ኩባንያ፣ በባንክና ኢንሹራንስ ሥራዎች አዋጅ በተቀመጡት አንቀጾች መሠረት ቅጣት እንደሚጣልበት በመመርያው ውስጥ ተካቷል፡፡

  በዚሁ መመርያ በተለይ የዳይሬክተሮች ቦርድ በማንኛውም ወቅት የኩባንያዎቻቸው ባለአክሲዮኖች ዜግነት ኢትዮጵያዊ መሆኑን፣ ድርጅቶቹም ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን ዜጎች ባለቤትነት ሥር መሆናቸውን የሚያረጋግጥ የአሠራር ዘዴ በሥራ ላይ የማዋል ግዴታ ጥሎባቸዋል፡፡ የቦርድ አባላቱ የመቆጣጠሪያ ዘዴያቸውን ሥራ ላይ ማዋላቸውንም ለብሔራዊ ባንክ ማሳወቅና የዚህንም የአሠራር ዘዴ፣ ተግባራዊነትና አፈጻጸም በመቆጣጠር ማረጋገጥ አለባቸው፡፡

  ብሔራዊ ባንክ ይህንን መመርያ ያወጣው የፋይናንስ ተቋማቱ ባለቤትነት ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለው ብቻ እንዲሆንና ተቋማቱም በሙሉ በኢትዮጵያዊያን ዜጐች ባለቤትነት ተቋቁመው እንዲመሩ ሕጉ የሚደነግግ በመሆኑ ነው ተብሏል፡፡ የፋይናንስ ተቋማቱ በኢትዮጵያዊያን ወይም ድርጅቶች ባለቤትነት ሥር መዋላቸውን ተከታትሎ ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት፣ ይህ የቁጥጥር ዘዴ በሥራ ላይ መዋሉም ተገልጿል፡፡

  አክሲዮን ሲገዙ ኢትዮጵያዊ የነበሩና ከዚያ በኋላ ዜግነታቸውን የቀየሩ ባለአክሲዮኖች፣ አክሲዮናቸውን እንዲያስተላልፉ ወይም እንዲሸጡ እንደሚያስገድዳቸው ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ የውጭ ዜግነት ያለው እንዳይገባ የማይፈቀድለት በመሆኑ ምክንያት፣ መመርያው የመጣው እንዲህ ያለውን ክፍተት ለመድፈን እንደሆነ እየተገለጸ ነው፡፡ ይሁንና አክሲዮን ሲገዛ ኢትዮጵያዊ የነበረ ሰው ዜግነቱን ሲቀይር ምን መደረግ አለበት የሚለው ጉዳይ አነጋጋሪ ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች