Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊምንም ገቢ የሌላቸው 200 ሺሕ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በሴፍቲኔት ፕሮግራም ሊታቀፉ ነው

  ምንም ገቢ የሌላቸው 200 ሺሕ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በሴፍቲኔት ፕሮግራም ሊታቀፉ ነው

  ቀን:

  በአዲስ አበባ ለሚገኙ ምንም ገቢ ለሌላቸው 200 ሺሕ ድሆች የሴፍቲኔት ፕሮግራም ተዘጋጀ፡፡ በዚህ ፕሮግራም የሚታቀፉ ዜጐች የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ ከመሆናቸውም በተጨማሪ፣ በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ ይደረጋል ተብሏል፡፡ ይህ ፕሮግራም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በአምስት ዓመት ውስጥ በሚተገብረው ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተፈጻሚ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡

  በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተዘጋጅቶ ለውይይት በቀረበው የትራንስፎርሜሽን ረቂቅ ዕቅድ ላይ እንደተጠቀሰው፣ በከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ፣ አቅመ ደካሞች ደግሞ ክብካቤ ማዕከላት እንዲገቡ ይደረጋል፡፡

  በዚህ ፕሮግራም የሚስተናገዱ ዜጐች ምንም ገቢ የሌላቸውና ጎዳና ላይ የወደቁ ሲሆኑ፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አጠራር ‹‹የደሃ ደሃ›› የሆኑ ናቸው፡፡

  ለእነዚህ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በሴፍቲኔት ፕሮግራም ታቅፈው የመኖሪያ ቤት ባለቤት እንዲሆኑና የተለያዩ ሥልጠናዎች እንዲሰጣቸው ተደርጎ የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ማድረግን ያካትታል፡፡

  በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ እየተደረጉ ካሉት አራት የመኖሪያ ቤት ፕሮግራሞች በተጨማሪ፣ አምስት አዳዲስ የመኖሪያ ቤት ፕሮግራሞች በመቀረፅ ላይ እንደሚገኙ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኢያሱ ማርቆስ በቅርቡ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማም በቅርቡ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በሚቀረፁት የመኖሪያ ቤት ፕሮግራሞች ምንም ገቢ የሌላቸው ነዋሪዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡

  መንግሥት እስካሁን በገጠሩ የአገሪቱ ክፍል እንጂ በከተሞች ደረጃ የሴፍቲኔት ፕሮጀክት አልጀመረም፡፡ በፌዴራል መንግሥት ደረጃ በትላልቅ ከተሞች ይህንን የሴፍቲኔት ፕሮግራም ለመጀመር የሚያስችል ዕቅድ ተነድፏል፡፡ ዕቅዱን የነደፈው በአዲሱ አጠራር የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ነው፡፡

  ሚኒስቴሩ ይህንን ፕሮጀክት ከመንግሥትና ከዓለም ባንክ በሚያገኘው ድጋፍ የሚያካሂድ ሲሆን፣ ፕሮግራሙ 300 ሚሊዮን ዶላር እንደሚፈልግ ተገልጿል፡፡

  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማኅበራዊ ችግሮችን በተለይም ምንም ገቢ ለሌላቸውና ጐዳና ላይ ለወደቁ ዜጐች በአነስተኛ ደረጃ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

  ከንቲባ ድሪባ ያቀረቡት የ2007 ዓ.ም. በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ ውሎና አዳራቸው ጐዳና ላይ የሆኑ 4,151 ዜጐች በኮንስትራክሽን፣ በኦቶሞቲቭ፣ በእርሻና በተለያዩ ዘርፎች ሥልጠና ተሰጥቷቸው ወደ ሥራ እንዲሰማሩ ተደርጓል፡፡ በበጀት ዓመቱ የመጨረሻ ወራትም 7,500 ዜጐች ከጎዳና እንዲነሱ ተደርጎ ወደሚሠለጥኑበት ቦታ ተልከዋል፡፡

  ከዚህ በተጨማሪ 600 የሚሆኑ አረጋውያንና ሴቶች ከጎዳና ተነስተው በአዲስ አበባ በሚገኙ የተለያዩ ክብካቤ ማዕከላት መግባታቸውን የከንቲባው ሪፖርት ያመለክታል፡፡

  በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ግን በሴፍቲኔት ፕሮግራም 200 ሺሕ ዜጐችን ከድህነት ለማውጣት የታቀደ ሲሆን፣ ከንቲባ ድሪባ እነዚህ ዜጐች የልማቱ ተጨማሪ አቅም እንዲሆኑ ይደረጋል ብለዋል፡፡ 

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ኃይሎች ላይ ጥቃት አልፈጸምኩም አለ

  የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ...

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...