Monday, August 15, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊየድለላው ሠንሠለት

  የድለላው ሠንሠለት

  ቀን:

  ድለላ ወይም ደላላ ሲባል ከሥራ፣ ከሙያ ጋር ብቻ ሳይሆን ብዙ ጊዜ ካለመታመን ከቃል አባይነት ጋርም ሲያያዝ ይስተዋላል፡፡ ከዚህ ሲያልፍም እንደ ስድብ ሁሉ ይሆናል፡፡ ድለላ በተለይም ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ባለበት በአሁኑ ወቅት ብዙዎች በቀጥታም ይሁን ባየ በሰማ የሚንቀሳቀሱበት ዘርፍ መሆኑን የሚጠቁሙ አሉ፡፡ በቋሚነት እንጀራዬ ብለው ቤተሰብ የሚያስተዳድሩበትም ብዙዎች ናቸው፡፡

  ይህ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ያለበት፣ ብዙዎች የሚንቀሳቀሱበትና ከፍተኛ ገንዘብ የሚሽከረከርበት ዘርፍ በተለያየ መንገድ መልኩ እየተቀያየረ ይገኛል፡፡ በተለያየ ምክንያት የቢሮ ሠራተኛው፣ ጥበቃው፣ ሾፌሩና ሌላ ሌላው በድለላ ሥራ ውስጥ ተሳታፊ መሆንና የድለላ ኢንተርኔትን መሠረት እያደረገ መምጣት የወቅቱ የድለላ ዋነኛ ገጽታዎች መሆናቸውን ያነጋገርናቸው ይገልጻሉ፡፡

  በሌላ በኩል መሀል ከተማ ላይ በመልሶ ማልማት የቤት ሽያጭ በጣም በመቀዛቀዙ መሀል ከተማ ላይ ያሉ ደላሎች በቤት ኪራይ እንዲወሰኑ፤ እንዲሁም ከከተማ ወጣ ባሉና የቤት ሽያጭ በከፍተኛ ሁኔታ በሚካሔድባቸው እንደ ሲኤምሲ፣ ለገጣፎ፣ ለቡና በመሰሉት አካባቢ ከሚገኙ ደላሎች ጋር መተሳሰር እንዲፈጥሩ የግድ ያለበት ሁኔታም አለ፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ በድለላ ሥራ የተሰማሩት እነማን ናቸው? ምን ያህል ገንዘብ ይንቀሳቀሳልና የግብር ጉዳይ ጥያቄ የሚሆኑ ናቸው፡፡

  ቤትና መጋዘን በመሸጥ እንዲሁም በማከራየት ሥራ ላይ የተሰማራው ኢትዮ ብሮከርስ ባለቤት አቶ ካሌብ ዮሐንስ በአብዛኛው የድለላ ሥራውን የሚሠራው ኢንተርኔትን መሠረት በማድረግ የራሱን ድረ ገጽ ከፍቶ እንዲሁም፣ በማስታወቂያና የተለያዩ ማኅበራዊ ድረ ገጾችን በመጠቀም በመሆኑ ባየ በሰማ የብዙዎች ድለላ ላይ መሰማራት ተፅዕኖ እንዳላደረገበት ይናገራል፡፡ ኢንተርኔት ተጠቃሚው አነስተኛ በመሆኑና ማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይም የሚሳተፈው ሰው ቁጥር እንዲሁ በመሆኑ እንጂ ኢንተርኔት ለድለላ ሥራቸው አደጋ የሚሆንበት መንገድም እንዳለ ይናገራል፡፡ ይህም ሰዎች ቤት ለመግዛት፣ ለመሸጥ አልያም ለማከራየት ቢፈልጉ በቀጥታ እንደ buy & sale ወይም what’s happening in Addis Ababa? ባሉ ድረ ገጾች መለጠፍ መጀመራቸው፤ መከራየት መግዛት የፈለጉ ሰዎችም እንዲሁ ማድረጋቸው ነው፡፡ ከ15 ዓመት በላይ በሥራው መቆየቱን የሚናገረው አቶ ካሌብ ይህ አካሔድ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ለሥራቸው ፈተና መሆን መጀመሩ እንደማይቀር ሥጋት አለው፡፡  

  ዋና መገኛውን ሰሜን ሆቴል አካባቢ አድርጐ ቤት በማከራየትና በመሸጥ ድለላ የተሰማራው አቶ ፀጋዘአብ ገብረ እግዚአብሔር በድለላ ሥራ ከዘጠኝ ዓመት በላይ ቆይቷል፡፡ ከተማ ውስጥ ከጦር ኃይሎችና ቃሊቲ አካባቢ በስተቀር በሌሎች አካባቢዎች የድለላ ሥራውን የሚሠራው ሌሎች አካባቢዎች ላይ ከሚገኙ ደላሎች ጋር በመተሳሰር እንደሆነ ይናገራል፡፡

  ‹‹ሠፈሮች በመልሶ ማልማት እየተነሡ ባሉበት በዚህ ወቅት እንደ እኔ ያሉ የከተማ ደላሎች በቤት ሽያጭ ሊጠቀሙ አይችሉም፡፡ ሰዎች የሚገዙት አዳዲስ ሰፈር እየሔዱ ነው፡፡›› የሚለው አቶ ፀጋዘአብ የከተማ ቤት ሽያጭ በመቀዛቀዙ የከተማው ደላላ መጐዳቱን ይገልጻል፡፡ በሦስትና በአራት ወር በመልሶ ማልማት አይነሱም በተባሉ አካባቢዎች ላይ ቤት ለማሻሻጥ ጫፍ ላይ ሲደረስም ምንም እንኳ ሽያጩን ለማጽናት መረጃ ፍለጋ ወደ ከተማ አስተዳደሩ ጐራ የሚሉ ቢሆንም ሙሉ መረጃ ስለማያገኙ በመጨረሻ እንደሚፋረስባቸው ያስረዳል፡፡

  በኑሮ ውድነት ያገኘውን ሠርቶ ገንዘብ ለማግኘት ሁሉ ሰው አየር በአየር ድለላ ውስጥ በገባበት በዚህ ወቅት ከድለላ የሚገኝ ጥቅም አስቸጋሪ እየሆነ መሆኑን፤ በአንድ ሥራ ውስጥ አሥር፣ አሥራ አምስት ሰው መኖሩን ይናገራል፡፡ ‹‹ለሁለት ወይም ለሦስት የሚሠራ ሥራ በጣም ጥቂት ነው፡፡ ለካርድ መሙያ ቤት ሽያጭም ከሆነ ሁለት ሦስት ሺሕ ብር ባገኝ ብለን ነው የምንገባው›› በማለት ይገልጻል፡፡ ሥራው እንኳንስ እንደተገለጸው ባየና በሰማ ብዙ ሰው ገብቶበት ብዙ ድካም ያለውና ከብዙ ልፋት በኋላ ሊሳካ ላይሳካ የሚችል መሆኑ በጣም አስቸጋሪ እንደሚያደርገው ያመለክታል፡፡ ‹‹ጫማ ያልቃል ስልክ ያልቃል በሌላ በኩል ደግሞ ደላላ ነው ተብሎ የከበረ ይታያል›› በማለት የሥራውን ፈታኝነት ለማስረዳት ይሞክራል፡፡  

  የአቶ ፀጋዘአብን ሀሳብ የሚጋራው የኢትዮ ብሮከርሱ አቶ ካሌብ ‹‹የኤምባስው ጥበቃ፣ የቢሮ ፀሐፊና ሾፌር ሁሉ በድለላ ውስጥ ይገባሉ›› ይላል፡፡ ምንም እንኳ ለእነዚህ ጣልቃ ገብ ደላሎች መክፈል ግዴታ ባይሆንበትም ነገሮችን ለማቅለል ሲል የድርሻቸውን የሚሰጥበት አጋጣሚ አለ፡፡ ገዥና ሻጭን በቀጥታ ስለሚያገኝ ለእሱ ይህ ብዙ ችግር ባይሆንም ለትንንሽና ሕጋዊ ደላሎች ተፅዕኖው ከባድ እንደሆነ ይገልጻል፡፡

  ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ የንግድ ድርጅት (ድለላም ይሠራል) ሥራ አስኪያጅ ‹‹እኔም አለሁበት ብሎ የሚገባ ብዙ ነው›› ሲሉ ሁኔታውን ይገልጹታል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንድ ሥራ ላይ የብዙ ደላሎች መገኘት እየተለመደ ነው፡፡ ገዥ ወይም ሻጭ ይዞ የመጣ ሰው መጨረሻ የሚደርሰውን ኮሚሽን ታሳቢ በማድረግ በሥራው ስንት ሰው አለበት ብሎ ሁሉ ይጠይቃል፡፡

  የቤት ኪራይ፣ የቤትም ይሁን የመኪና ሽያጭ ከተማ ውስጥ እንዲንር ዓይነተኛ ሚና የሚጫወቱት ደላሎች ናቸው የሚል አስተያየት በስፋት ይሰነዘራል፡፡ እንደሚባለው ደላሎች እራሳቸው ያስገቡትን ተከራይ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የተሻለ የሚከፍል ሌላ ተከራይ በማምጣት ባለቤቶችን አሳምነው የቀደመውን ተከራይ ያስወጣሉ፡፡ ቤት ሽያጭ ላይም ባለቤት በዚህ ይሸጥ ሲል አይ ይሔን ያህል ያወጣል ብለው ዋጋ በመስቀል ኮሚሽናቸውንም ይሰቅላሉ፡፡ ከዚህም ባለፈ የማይሆነውን ይሆናል የሌለውን አለ ብሎ ማከራየትና መሸጥ የተለመደ የሥራው ባህሪይ ይመስላል፡፡ ባገኙት ክፍተት በእንደልላለን ስም የሚያጭበረብሩም ጥቂት አይባሉም፡፡

  አቶ ካሌብ በእነሱ ደረጃ የደላላ ዋጋ የማናር ነገር እንደሌለ ነገር ግን በዝቅተኛ ደረጃ፣ በኮንዶሚኒየም ቤት ኪራይና ሽያጭ ዋጋ መናር ደላሎች ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸው በተለያየ መንገድ ማስተዋሉን ይናገራል፡፡ በእነሱ ደረጃ እንዴት ደላሎች ዋጋ የማናር ሚና እንደማይኖራቸው ለአቶ ካሌብ ጥያቄ አቅርበን መልሳቸው ‹‹ለምሳሌ እኛ ጋር የሚሸጥ ሰው ቢመጣ ዋጋ ጠይቀነው የማይሆን ከሆነ የሚሸጠው ነገር እንደማያወጣ እንነግረዋለን፡፡ ገዥ ሲመጣም ፍላጐቱን ጠይቀን በጀቱን እንጠይቀዋለን፡፡ ሥራውን የምንጀምረው ይህን አረጋግጠን ነው›› የሚል ነበር፡፡

  የውጭ አገር ዜጐች ለመኖሪያ ቤትም ይሁን ለቢሮ ቤት ቢገዙ ወይም ቢከራዩ በጀታቸውን ሲጠየቁ በግልጽ ሲናገሩ ኢትዮጵያዊያን ለመናገር አለመፍቀዳቸውን እንደ አንድ ችግር ያነሳል፡፡ ‹‹በጀቴ አንድ ሚሊዮን ብር ነው ብሎ በአምስት ሚሊዮን የሚገዛ አለ›› በማለት ለማስረዳት ይሞክራል፡፡ በተቃራኒው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት ድለላን ጨምሮ አጠቃላይ ንግድ የሚሠራው ድርጅት ሥራ አስኪያጅ በየትኛውም ደረጃ ከተማ ውስጥ እየተንቀሳቀሰ ያለ ደላላ የተለያዩ ነገሮችን የሽያጭ ዋጋ እንዲንር እያደረገ መሆኑ አጠራጣሪ አይደለም ይላሉ፡፡

  ደላሎች በራሳቸው ብቻ ሳይሆን ከባለቤት ጋር በመመሳጠር እንደሆነ ዋጋ የሚያንሩት የሚናገረው አቶ ካሌብ ከዚህ በላይ ከሸጥክ ተጠቀም ብለው ደላላ ዋጋ እንዲወስን የሚተውም ዋጋ በማናር ሚናቸው የጐላ እንደሆነ ያምናል፡፡

  አቶ ፀጋ ዘአብ ደግሞ ነገሩን ከሥነ ምግባር ጋር ያያይዘዋል፡፡ ለምሳሌ የተሻለ የሚከፍል ሲገኝ ባለቤትን አሳምኖ ቀድሞ ያከራዩትን ማስወጣትን ብዙ ጊዜ የሚያደርጉት እንደ እሱ ድለላ ሥራዬ ብሎ እንጀራቸው ያደረጉ ሳይሆን ዘርፉ ክፍት በመሆኑ በተባራሪ የሚገቡት ናቸው ብሎ ያምናል፡፡ እንደ አቶ ካሌብ ሁሉ ደላላ ሳይጠብቁም ራሳቸው ዋጋ በማጣራት ተከራይን አስወጥተው የተሻለ ከፋይ ለማስገባት የሚንቀሳቀሱ ባለቤቶች መኖራቸውን ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹የቤት ኪራይንም ሆነ ሽያጭ ዋጋን ያናረው ደላላ ብቻ ሳይሆን ባለቤትም ነው›› ይላል፡፡

  አቶ ፀጋ ዘአብ በቤት ሽያጭ የተከፈለውን ከፍተኛው ክፍያ ሰላሳ ሺሕ ብር መሆኑን ሲናገር አቶ ካሌብ ይህን በግልጽ መናገር አይፈልግም፡፡ በሌላ በኩል አቶ ካሌብ ከሽያጭ ሁለት ከመቶ ሲያገኙ ከኪራይ ግን የዓመት ከተከፈለ የአንድ ወር፣ የስድስት ወር ቢከፈል ደግሞ የግማሽ ወር ክፍያ የሚሆነውን ያህል ከሁለቱም ወገን እንደሚወስዱ ይገልጻል፡፡ በቤት ኪራይ ብዙ ደላሎች ከሁለቱም ወገን አሥር በመቶ መውሰዳቸው የተለመደ ቢሆንም እነ አቶ ካሌብ ይህን አይከተሉም፡፡ በውጭ አገር በአብዛኛው ኮሚሽን የሚታሰበው ከባለቤቶች በመሆኑ የውጭ አገር ዜጐች ኮሚሽን ለመክፈል ፍቃደኛ የማይሆኑበት አጋጣሚ መኖሩን አቶ ካሌብ ይጠቅሳል፡፡ ምንም እንኳ በቤት ሽያጭ በከፍተኛ በዝቅተኛ ደረጃ ድለላም የኮሚሽን አከፋፈል (ሁለት በመቶ) አንድ ዓይነት ቢሆንም ኪራይ ላይ ወጥነት አለመኖሩ ይታያል፡፡

  ብዙዎች በሚሳተፉበት አንድ ሽያጭ ወይም ግዥ ምንም ዓይነት የድላለ ፈቃድ የሌላቸው እጅ ይበዛል፡፡ አቶ ካሌብ እንደሚገምተው ከሰማንያ በመቶ በላይ የሚሆነው በድለላ የተሰማራ ሕጋዊ አይደለም፡፡ አቶ ፀጋ ዘአብም ማን ሕጋዊ ነው አይደለም ማለት በማይቻልበት ሁኔታ በጋራ ሁሉ እንደሚሠራ ይጠቁማል፡፡

  ሕጋዊ ባለመሆናቸው ብዙ ደላሎች በቤት ሽያጭ ሥራ ውል እንደማይዋዋሉ፤ ይልቁንም በእምነት እንደሚሠሩ የገለጹልን አሉ፡፡ ይህን በማወቅ ማግኘት የሚገባቸውን ሁለት በመቶ ኮሚሽን አንድ የሚያደርጉ ከናካቴውም የሚከለክሉ መኖራቸውንም ይናገራሉ፡፡

  ከዓመታት በፊት ሕገወጥ ደላሎች ተደራጅተው ወደ ሕጋዊው መስመር እንዲገቡ የተደረገ ጥረት ቢኖርም ዛሬም ሥራው በአብዛኛው ያለው ሕጋዊ ባልሆኑት እጅ እንደሆነ ያነጋገርናቸው ይገልጻሉ፡፡ ይህ ደግሞ ተገልጋዮችን ለተለያየ ችግር ሲያጋልጥ ምንም እንኳ ትልቅ ገንዘብ እየተንቀሳቀሰ ቢሆን ተገቢው ግብር እንዳይገኝ ማድረጉ ግልጽ ነው፡፡ ሕጋዊ ያልሆኑት ወደ ሕጋዊነት መስመር እንዲገቡ የሚያደርግ ሥርዓት መዘርጋት እንዳለበት ያነጋገርናቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡                 

  ምናልባትም አቶ ፀጋ ዘአብ እንደገመተው የኑሮ ውድነት የጫነባቸውን ሸክም ለማቅለል የብዙዎች ባገኙት ክፍተት ድለላ ውስጥ መግባት ለሽያጭ ወይም ለግዥ እንኳ ባይሆን ለሥራ ወይም ለሌላ የግል ጉዳይ የሚፈላለጉ ሰዎችን ማገናኘትን ጨምሮ ብዙ ነገሮች የግድ ድለላና ደላላ የነካቸው እንዲሆኑ እያደረገ ያለ ይመስላል፡፡

        

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...