በወቅቶች የታጀበው አጀንዳ
ዘንድሮ ከተበረከቱ ጥበብ ነክ ሥራዎች መካከል በአቶ ፈለቀ ደነቀ የተዘጋጀው አጀንዳ ይጠቀሳል፡፡ የኢትዮጵያውያንን ዘመን አቆጣጠር ተመርኩዞ የተዘጋጀው አጀንዳ የቀናት፣ ሳምንታት፣ ወራት እንዲሁም ወቅቶችን (ክረምት፣ መፀው፣ በጋ፣ ፀደይ) ስያሜ፣ አመጣጥ እንዲሁም ሌሎችም መረጃዎች ያካተተ ነው፡፡ አቶ ፈለቀ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በአግባቡ ታውቆ ጥቅም ላይ እንዲውል ለማስቻል አጀንዳውን አዘጋጅተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ያሏት እምቅ ሀብቶች በአግባቡ ጥቅም ላይ አለመዋላቸው ዘወትር እንደሚያስቆጫቸው ይናገራሉ፡፡ ከሀብቶቹ አንዱ የሆነውን ዕድሜ ጠገብ የዘመን አቆጣጠርም ብዙዎች በዕለት ከዕለት ሕይወታቸው ሲጠቀሙበት ማየት ምኞታቸው ነው፡፡ አክሱምና ላሊበላን ከመሰሉ ግዙፍ ቅርሶች ባልተናነሰ የዘመን አቆጣጠሩ መታወቁ አገሪቷን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ይገልጻሉ፡፡
አቶ ፈለቀ ለ20 ዓመታት በኢትዮጵያ ካርታ ድርጅት የካርታ ንድፍ ሥራ የሠሩ ሲሆን፣ አሁን በግላቸው የፎቶግራፍና ግራፊክስ ዲዛይን ሥራዎች ይሠራሉ፡፡ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሊሴ ገብረማርያም የተከታተሉ ሲሆን፣ የካርታ ሥራን በፈረንሳይና ኔዘርላንድስ አጥንተዋል፡፡ ሙያቸው ከኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር ቀመር ጋር ባይያያዝም፣ በንባብ ላይ ተመርኩዘው አጀንዳውን እንዳዘጋጁም ያስረዳሉ፡፡
የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ሥራ ላይ ካልዋለ እየተዘነጋ እንደሚሄድ የሚናገሩት አቶ ፈለቀ፣ አጀንዳው የሥራ ዕቅድን ከማስፈር በተጨማሪ ስለቀን አቆጣጠር ግንዛቤ ማስጨበጡ ጠቃሚ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ አዘጋጁ በሚቀጥሉት ዓመታትም መሰል አጀንዳዎች የማሰናዳት ዕቅድ ያላቸው ሲሆን፣ ቅዳሜ ጥቅምት 6 ቀን በኢሠማኮ አዳራሽ በይፋ የተመረቀው አጀንዳው በ75 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡
* * *
ኮንሰርት
ዝግጅት፡- ግርማ ይፍራሸዋ ‹‹ማይ ስትሮንግ ዊል›› በሚል ለሚለቀው አዲስ አልበም ማስመረቂያ የክላሲካል ሙዚቃ ኮንሰርት ተዘጋጅቷል፡፡
ቀን፡- ጥቅምት 12 ቀን 2008 ዓ.ም.
ሰዓት፡- 12 ሰዓት
ቦታ፡- ሸራተን አዲስ
የመጽሐፍ ምርቃት
ዝግጅት፡- የትዕግስት ዓለምነህ ‹‹ዕልልታና ሙሾ›› የተሰኘ የግጥም መድበል ይመረቃል
ቀን፡- ጥቅምት 15
ሰዓት፡- 1፡30
ቦታ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር