Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  አንበሳ ባንክ ዓመታዊ ትርፉን ከእጥፍ በላይ አሳደገ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  – የተበላሸ የብር መጠኑ 2.9 በመቶ ደርሷል

  አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ አክሲዮን ማኅበር ከአንድ ዓመት በፊት አሽቆልቁሎ የነበረውን ዓመታዊ የትርፍ መጠኑን ከእጥፍ በላይ ማሳደጉን አስታወቀ፡፡

  የባንኩ የ2007 በጀት ዓመት የፋይናንስ ሪፖርቱ እንደሚያመለክተው፣ ባንኩ ከታክስ በፊት 275.6 ሚሊዮን ብር ማትረፍ ሲችል፣ ይህም ባለፈው በጀት ዓመት ከታክስ በፊት ካስመዘገበው የ127.2 ሚሊዮን ብር የ117 በመቶ ብልጫ አለው፡፡

  ባንኩ በበጀት ዓመቱ ያገኘው የተጣራ ትርፍ 151 ሚሊዮን ብር ሲደርስ፣ ለመንግሥት የከፈለው የትርፍ ግብር ደግሞ 74.8 ሚሊዮን ብር መሆኑ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡ ባንኩ የቀረውን 50 ሚሊዮን ብርም በመጠባበቂያነት እንደያዘው አስታውቋል፡፡ ባንኩ ባለፈው በጀት ዓመት ከታክስ በኋላ ያስመዘገበው ትርፍ 72 ሚሊዮን ብር መሆኑን አስታውቆ፣ በዚህ በጀት ዓመት የተገኘው ትርፍ ከፍተኛ ነው ብሏል፡፡ ከአክሲዮን ድርሻ የሚገኘው የባንኩ ትርፍም 10.63 ብር ሲደርስ፣ ይህም በ81 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡

  በባንኩ ሪፖርት መሠረት በ2007 በጀት ዓመት ከታክስ በኋላ የተመዘገበው ትርፍ ከባለፈው ዓመት ጋር በንጽጽር ሲቀመጥ ከ108 በመቶ ብልጫ አለው፡፡ ባንኩ በ2004 ዓ.ም. 104 ሚሊዮን ብር፣ በ2005 ዓ.ም. ደግሞ 150 ሚሊዮን ብር ማትረፉ ይታወሳል፡፡

  በትርፍ ግኝቱ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የባንክ አገልግሎቶች አመርቂ ውጤት መመዝገቡን የባንኩ ሪፖርት አመልክቷል፡፡ ከእነዚህም መካከል ባንኩ በበጀት ዓመቱ ያገኘው የገቢ መጠን በ83 በመቶ መጨመሩ አንዱ ነው፡፡ የባንኩ አጠቃላይ ገቢ 663.6 ሚሊዮን ብር ሲደርስ፣ በ2006 በጀት ዓመት አግኝቶት የነበረው ግን 363 ሚሊዮን ብር መሆኑ ይታወሳል፡፡

  ባንኩ በበጀት ዓመቱ የሰጠው ብድር 83.7 በመቶ ያደገ ሲሆን፣ እስከ ሰኔ 2007 መጨረሻ ድረስ የሰጠው ብድር 2.83 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ አምና በተመሳሳይ ወቅት ሰጥቶ የነበረው የብድር ክምችት መጠን 1.54 ቢሊዮን ብር እንደነበር አስታውሷል፡፡ ከተሰጠው ብድር ውስጥ ለኢምፖርት፣ ለኤክስፖርት፣ ለአገር ውስጥ ንግድና አገልግሎቶች ሥራ ማስኬጃ  የተሰጠው የብድር መጠን ከፍተኛውን ድርሻ ሲይዝ፣ ለኮንስትራክሽንና ሕንፃ ግንባታ፣ ለማኑፋክቸሪንግ፣ ለሆቴልና ቱሪዝም፣ ለግብርናና ለሌሎች ዘርፎች የተሰጡ ብድሮችም ጉልህ ስፍራ ነበራቸው ተብሏል፡፡

  ይህ በእንዲህ እንዳለ የባንኩ የተበላሸ የብድር መጠን ግን ከቀዳሚው ዓመት በልጦ ተገኝቷል፡፡ ባንኩ በ2006 በጀት ዓመት የተበላሸ የብድር መጠኑ 2.1 በመቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በ2007 በጀት ዓመት ግን የተበላሸ የብድር መጠኑ ወደ 2.9 በመቶ ሊያድግ ችሏል፡፡ ይህ አፈጻጸም ብሔራዊ ባንክ የተበላሸ የብድር መጠን ከአምስት በመቶ መብለጥ እንደሌለበት ካወጣው መመርያ አንፃር ሲታይ ባንኩ በእጅጉ በተሻለ ደረጃ ላይ መገኘቱንና በዚህ ዙሪያ የተሠራው ሥራ እጅግ አበረታች እንደነበረ ያመላክታል ሲል በሪፖርቱ ገልጿል፡፡ ይኸውም ብድር አሰጣጥና አሰባሰብ ሒደቱ ጤነኛ እንደሆነ የሚያመለክትም ነው ብሏል፡፡ ባንኩ በ2005 በጀት ዓመት የተበላሸ የብድር መጠኑ 1.1 በመቶ እንደነበርም ይታወሳል፡፡

  ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂን በተመለከተም ባንኩ ከጅምሩ ቅርንጫፎቹን በኔትዎርክ በማስተሳሰር ወደ ሥራ የገባ መሆኑን የሚገልጸው የባንኩ ሪፖርት፣ በዚህ ረገድ አቅሙን ይበልጥ በማጎልበት የካርድ ክፍያና ሌሎች አገልግሎቶችን በስፋት ለመስጠት የሚያስችለውን ዝግጅት በማጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስተባባሪነት እየተዘረጋ ያለውን ‹‹ኢት-ስዊች›› የገንዘብ ዝውውር መረብ ዝርጋታ ሥራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ወደ አገልግሎት ሲገባ ባንኩ የተሟላ የካርድ ክፍያ አገልግሎት መስጠት የሚጀምር መሆኑንም ገልጿል፡፡ 

  በአሁኑ ወቅት ‹‹ሄሎ ካሽ›› በመባል የሚታወቀው የሞባይልና ኤጄንት ባንኪንግ አገልግሎትም በብሔራዊ ባንክ ፍቃድና ዕውቅና አግኝቶ ሙሉ በሙሉ ወደ ትግበራ ገብቷል፡፡ የሞባይልና ኤጄንት ባንኪንግ አገልግሎቶችን የባንኩ ቅርንጫፎች በሌሉበት የአገሪቱ አካባቢ የሚገኙ ደንበኞች ሞባይሎቻቸውንና የኤጀንት ባንኪንግ ወኪሎቻችንን በመጠቀም ማንኛውም የሐዋላ፣ የቁጠባ ተቀማጭ ገንዘብና ከተቀማጭ ገንዘብ ወጪ የማድረግ አገልግሎት ለማግኘት ስለሚያስችላቸው የተደራሽነት አድማሱን በይበልጥ ያሰፋዋል ተብሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪም ደንበኞች በባንኩ ያላቸውን የሒሳብ እንቅስቃሴ አስመልክቶ መረጃ የሚሰጥ የአጭር የስልክ መልዕክት አገልግሎት መስጠት እንደጀመረም አስታውሷል፡፡ ባንኩ በአሁኑ ወቅት ከ90 በላይ ቅርንጫፎች አሉት፡፡

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች