Thursday, August 11, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊእስራኤል-የተቃርኖዎች ምድር ፪

  እስራኤል-የተቃርኖዎች ምድር ፪

  ቀን:

  ነፍስ አድን ሩጫ

  ጋይ ራፓፖርት ይባላል፡፡ አሁን የሚኖርበት ነቲቭ ሃአሻ ከተወለደበት ኪቡቲ አሥር ኪሎ ሜትር ርቆ ይገኛል፡፡ ‹‹ከዚህ ወደ ጋዛ ስንት ኪሎ ሜትር ነው›› ስንል ጠየቅነው፡፡ ‹‹ዜሮ ኪሎ ሜትር›› አለ፡፡ ጋዜጠኞቹ አላመኑም፡፡ ሁለቱ አገሮች የሚለያዩበትን አንድ ትልቅ ግንብ አሻግሮ አሳየን፡፡

  የሁለት ልጆች አባት እንደሆነ የሚናገረው ጋይ፣ በአንድ ፋብሪካ ተቀጥሮ ይሠራል፡፡ ‹‹ከጋዛ ይተኮሳል›› የሚለውን ሮኬት ለመከላከል የተሠራና ‹‹ቦንብ ሼል›› እያሉ የሚጠሩትን የሕይወት አድን መጠለያ እያሳየን፤ ‹‹የሚያሳዝነኝ የእኔ አይደለም፡፡ የእኔ ሕይወት በቃ ይኼ ነው፡፡ ከአሁን በኋላ ሌላ ሕይወት ፍለጋ የምባዝንበት ምክንያት የለኝም፡፡ በጦርነት ተወልጄ በጦርነት እሞታለሁ፡፡ የሚያሳዝነኝ የልጆቼ ዕድል ነው፡፡ ጧትና ማታ የሚያስቡት ስለ ትምህርት ሳይሆን ስለ ሮኬት ነው፡፡ የሆነ ኮሽታ በተሰማ ቁጥር ይደነግጣሉ›› ይላል፡፡ እናታቸውም የሚያስጨንቃት ልጆቿን ምን እንደምታለብስ፣ ምን እንደምትመግብ አይደለም፡፡ ሲነጋም የምትሰጣቸው ተስፋ ታጣለች የሚለው ጋይ፤ በጦርነት የተገነባው የልጆቹ ሥነ ልቦና ያሳስበዋል፡፡

  ሁለቱም አገሮች ከሚለያዩበት ግንብ አጠገብ ሌላ የበለጠ ርዝመት ያለው ግንብ ይታያል፡፡ በግድግዳውም ላይ የተለያዩ የሰላም የያዙ አጫጭር ጽሑፎችና የሰላምና የፍቅር ምልክት የያዙ ምስሎች ይታያሉ፡፡ በስፍራው ያገኘናት ሳማሪት ዛሚር፣ ትናንሽ ቅርፆች ከሸክላ እየሠራች ትለጥፋለች፡፡ ‹‹አንድ ቀን በዚህ ምድር ሰላም ይወርዳል ብዬ አምናለሁ፤›› ትላለች፡፡ ፓዝ ቱ ፒስ (የሰላም መንገድ) የሚለውን ድርጅት የምትመራው ዛሚር፣ ዓላማዋ የሕዝብ ለሕዝብ ሰላምና ፍቅር ማምጣት ነው፡፡ ወደ አካባቢ የመጣ እንግዳ ሁሉ የሰላም ምኞትን እንዲያስቀምጥ ታደርጋለች፡፡ እኛም ምኞታችንን አስፍረናል፡፡

  የሚለጠፈውን ከግድግዳው ጀርባ ያሉት ፍልስጤማውያን ያዩታል፡፡ እነሱም በተለያየ መንገድ የፍቅርና የሰላም መልዕክት ይልካሉ፡፡ ‹‹ሁለቱም ሕዝቦች በዚሁ ግንብ ልብ ለልብ ይገናኙ ይሆን?›› የጋዜጠኞቹ ጥያቄ ነው፡፡ ሕዝቦቹ በዚሁ ትልቅ ግንብ እንዲለዩ የተደረገው፣ ኦስሎ ስምምነት እየተባለ በሚጠራ ድርድር መሠረት ሲሆን፣ በስምምነቱ ጋዛ ውስጥ የነበሩት እስራኤላውያን ከተማዋን ጠቅልለው እንዲወጡ ተደርጓል፡፡ ለሁለቱም ሕዝቦች የመጨረሻ ዕልባት ያስገኛል ተብሎ የቀረበው ስምምነት ግን፣ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ አልሆነም፡፡ አሁንም በየቀኑ የሚሰማው ግድያና ጠለፋ፣ ኦስሎ ስምምነት ከተደረገ ከ20 ዓመታት በኋላ ስምምነቱ በፍልስጤማውያኑ ዘንድ ተቃውሞ ስለገጠመውና ዕውቅና ስለተነፈገው ነው፡፡

  በተለይ አሁን ሥልጣን ላይ ባለው የሃማስ ድርጅት የሚመራው የፍልስጤም መንግሥት፣ እስራኤል ለምትባል አገር መኖር ዕውቅና አይሰጥም፡፡ የእስራኤል ምድር የፍልስጤም ይዞታ፣ አይሁዶች ወረው በጉልበት የያዙት መሬት መሆኑን ነው የሚያምኑት፡፡ ዓረቦችም አንድ ቀን ነፃ እናወጣዋለን የሚሉት ምድር ነው፡፡

  ጋዛ ድንበር አካባቢ ተዘዋውረን በጎበኘናቸው መንደሮች የሚነገሩ ታሪኮች በአብዛኛው ተመሳሳይ ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ቤት ቢያንስ አንድ የሮኬት ጥይት የማይበሳው ክፍል ያለው ሲሆን፣ በትምህርት ቤቶች፣ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ በካፌዎችና ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ሁሉ ሰፋ ሰፋ ያሉ የነፍስ አድን መጠለያ ተመልክተናል፡፡ እንዲሁም በእያንዳንዱ መንደር በርከት ያሉ የማስጠንቀቂያ ደውሎች አሉ፡፡ ከጋዛ የሚተኮሰው ሮኬት ከተተኮሰበት ቅፅበት ጀምሮ የአንቡላንስ ድምፅ የሚያሰማ ደወል ነው፡፡

  ቴልአቪቭና ኢየሩሳሌም ያሉ ነዋሪዎችም የደወል ድምፅ ከተሰማ ጊዜ ጀምሮ ሮኬቱ መሬት ላይ እስኪወድቅ ወደ ማምለጫ ስፍራ ለማምራት የአንድ ደቂቃ ዕድል አላቸው፡፡ ጋዛ ድንበር አካባቢ ላሉት ግን የ15 ሰከንዶች ዕድል ነው ያላቸው፡፡ ዘወትር ተሸብረው መኖር ልማዳቸው ነው፡፡ አንድ ሌሊት ሰላም ያለው እንቅልፍ እንደሌላቸውም ያገኘናቸው ነግረውናል፡፡

  ኑሯቸው በሕይወት አድን ሩጫ የተጠመደ መሆኑን የሚናገሩት ነዋሪዎቹ፣ ሮኬቱም ከሚያደርሰው ጉዳት በላይ የሚያሳስባቸው በታዳጊዎቹ ላይ የሚፈጥረው የሥነ ልቦና ጭንቀት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

  ለጋዛ ቅርብ በሆኑ መንደሮች የሚገኙ ነዋሪዎች፣ ሕይወታቸው ሁሌም ድንገት በሚተኮስ ቦንብ አጠገብ ያለች መስሎ ይሰማቸዋል፡፡ በእርግጥ የነዋሪዎቹ ሕይወት ተመልክቼ ሳበቃ ከ20 ዓመታት በላይ ወደኋላ መልሶ የወሰደኝ ትዝታ ነበር፡፡

  በልጅነቴ ያየሁት ነው፡፡ የሕውሓት ታጋዮች እየገፉ ሲሄዱ የደርግ ወታደሮች ሕዝቡን ባገኙበት አጋጣሚ መግደልና ማሰር ተያይዘውት ነበር፡፡ ከዚህም በላይ ግን በከተሞች ላይ ከአውሮፕላን ይወርድ የነበረውን የቦንብ ድብደባ አልረሳውም፡፡ የ‹‹ጊ›› ቅርፅ ያለው ጉድጓድ እያንዳንዱ እንዲቆፍር ተምሮ ነበር፡፡ የአውሮፕላን ድምፅ በተሰማ ቁጥር ልጆቹን ሰብስቦ ወደዚህ ስፍራ የማይሮጥ አልነበረም፡፡ የጋዛ አጎራባች እስራኤላውያን ኑሮም ከዚህ ጋር ይመሳሰላል፡፡

  ጋይን ጨምሮ ብዙዎቹ ግን መንደሩን ለቀው ለመሄድ ዕቅድ የላቸውም፡፡ ‹‹ቤታችንን ትተን የት እንሄዳለን? አንድ ቀን ከወንድሞቻችን ሰላም እንሆናለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ›› ይላል፡፡

  የኪቡቲ አስተዳደር የፀጥታ ኃላፊን አነጋግረናቸው ነበር፡፡ መጀመርያ ከመነጋገራችን በፊት ሕይወት አድን መጠለያ አካባቢ እንድንሆን ጠየቁን፡፡ ከዚያም ጣብያው ውስጥ የተወንጫፊ ስብርባሪ ክምር እያመላከቱን፤ በቀን ቢያንስ በአማካይ ከአሥር ጊዜ በላይ ሮኬት እንደሚተኮስና ባለፉት 14 ዓመታት ውስጥ 28 ሺሕ ሮኬቶች መወንጨፋቸውን ነገሩን፡፡

  ከዚሁ መንደር ትንሽ ራቅ ብሎ፤ አንድ ወታደራዊ ካምፕ ይገኛል፡፡ አካባቢው እጅግ ሞቃታማ ሲሆን፣ በሰው ሠራሽ ደን የተሸፈነ ነው፡፡ ሌተናል ታማራ ኢፐልባም፣ ኒውዮርክ ተወልዳ ያደገች የአይሁድ ተወላጅ ወጣት ነች፡፡ በፖለቲካል ሳይንስ ሁለተኛ ዲግሪ አጠናቃ ወደ እስራኤል በመመለስ በማገልገል ላይ ትገኛለች፡፡ ታማራ ወታደራዊ ሥልጠና ወስዳ የእስራኤል መከላከያ ኃይል ቃል አቀባይ ነች፡፡ በ20ዎቹ መጀመርያ የምትገኘው ወጣቷ፣ በአንድ ለሰማዕታት ማስታወሻ ከተሠራ አደባባይ ቆማ ስታወራ፣ ራቅ ባሉ ዛፎች ስር ከነትጥቃቸው የተንጋለሉ ወታደሮችን እያመላከተች፤ ‹‹እነዚህ የምታዩዋቸው ወታደሮች ሕዝቡን ለመጠበቅ ነው የተቀመጡት፡፡ አሸባሪዎቹ በምን ሰዓትና የት እንደሚከሰቱ አይታወቅም›› አለች፡፡ ስለመሿለኪያዎቹ (ተነል) ታሪኮች ስታወራ ውስጥ ለውስጥ ካሉት ጉድጓዶች ይዛን የገባች ያህል ነው የተሰማኝ፡፡ ምናልባትም ሕዝቦቹ ላይ ከሚነበበው የተጠቂነት ስሜት ውጪ፣ ማራኪ በሆነ የእንግሊዝኛ ችሎታ ስታወራ ቁጭትም፤ የጀግንነትም ስሜት ይነበብባታል፡፡ ትከሻዋ ላይ ያረፈው የኮረኔልነት ማዕረግ የሚገልፅ መለዮና ወታደራዊ ልብስ፣ ቆፍጣና ተዋጊ ቢያስመስላትም፣ በፈገግታ የታጀበው አወራሯና አገላለፅዋ ደንበኛ ዲፕሎማት ያሰኛታል፡፡ እያንዳንዱ እስራኤላዊ ወታደራዊ ሥልጠና የመውሰድና የሁለት ዓመት አገልግሎት መስጠት ግዴታ ያለበት ቢሆንም፣ እሷ ግን ወታደርነትን እንደምትወደውና እንደማትለቀው በኩራት ነበር የገለጸችልን፡፡

  አንዳንድ ጥያቄ ተቀብላ ማብራርያ የሰጠችን ታማራ፤ የእስራኤል ወታደራዊ ኃይል ሥራ መከላከል እንደሆነ ትናገራለች፡፡ ከጋዛ የሚቃጣባቸው ጥቃት በሁለት መንገድ ነው፡፡ አንዱ በሮኬትና ሚሳኤል የሚወነጨፍ ሲሆን፣ ሁለተኛው መሬት ውስጥ ለውስጥ በሚሠራ መሿለኪያ (ተነል) ናቸው፡፡ ‹‹እንግዲህ ሃማስ ገንዘቡን ኢንቨስት የሚያደርገው በእነዚህ ላይ ነው፡፡ የእኛ ወታደር ሥራ ደግሞ እነዚህ ጥቃቶች ለመከላከል ቀን ተሌት የቴክኖሎጂ ምርምር ማድረግ ነው›› ትላለች፡፡

  መከላከያ ኃይሉ ተወንጫፊ ሮኬት ሲተኮስ ሰማይ ላይ ሳለ የሚያመክን መሳርያ ፈጥሯል፡፡ መሬት ውስጥ ለውስጥ የሚሠራው መተላለፊያ ግን እስከ ሦስት ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸውና 27 ሜትር ጥልቀት ያለው ነው፡፡ ‹‹ከወዴት አካባቢ እንደሚመጡ ማወቅ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ በዚሁ ተሽለኩልከው መጥተው ብዙዎችን ይጠልፋሉ፤ ይገድላሉ ከዚያም ይሰወራሉ›› ትላለች፡፡ ባለፈው ዓመት የእስራኤል መከላከያ ኃይል ጋዛ ውስጥ በመግባት መሿለኪያውን ማግኘትና ማውደም ተችሎ የተወሰነ ዕረፍት እንዳገኙ ትናገራለች፡፡ ከጋዛ ወደ ግብፅና ወደ እስራኤል የተዘረጉ በርካታ መተላለፊያ መስመሮች መኖራቸውን በመጠቆም፣ ‹‹የሚያስቸግረው መተላለፊያዎቹ የሚሠሩት ከመስጊድ ወይም ከትምህርት ቤት ውስጥ በመሆናቸው ለማጥቃት እንቸገራለን›› ትላለች፡፡

  ቃል አቀባይዋ እንዲህ ትበል እንጂ ዓለም አቀፉ ሚዲያ የሚዘግበው ግን በተቃራኒው ነው፡፡ ባለፈው ሐምሌ ወር ላይ ውስጥ ለውስጥ የተሠሩት መተላለፊያ መስመሮች ለማጥቃት የእስራኤል መከላከያ ኃይል ጋዛ ውስጥ ያደረገው የማጥቃት ዘመቻ በተለያዩ አገሮች ወቀሳ ገጥሞታል፡፡ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም ትምህርት ቤትና መስጊድ ላይ ተፈጸመ ያሉትን ጥቃት በማሳየት ትችታቸውን መሰንዘራቸው ይታወሳል፡፡ ለታማራ ግን እግር ለእግር እየተኮሱ ከማጥቃት ውጪ ሌላ አማራጭ የለም፡፡

  ዘመናዊቷ እስራኤል

  እስራኤል ከጥንታዊው ኢየሩሳሌም ጀምሮ ተራሮቿ በሙሉ ታሪካዊ ናቸው፡፡ አንድ መጽሐፍ ቅዱስ ያነበበ ሰው እስራኤልን ባያይም በምናቡ የእስራኤልን ታሪክ ሊዘራው ይችላል፡፡ ይህ ግን የጥንታዊቷ እስራኤል ታሪክ ነው፡፡ ዘመናዊቷ እስራኤል ደግሞ ሌላ ታሪክ እየሠራች ነው፡፡

  በሰሜን ጫፍ ሜዴትራንያን ባህር ዳር ላይ የከተመችው የመንግሥቷ መቀመጫ ቴልአቪቭ፣ እምብዛም ታሪካዊ ዳራ የላትም፡፡ ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎቿ፤ ዘመናዊ መዝናኛ ስፍራዎቿ እንዲሁም ደረጃቸውን የጠበቁ መሠረተ ልማቶችዋ መንገድ፣ የባቡር ሃዲድ ለሰከንድም የማይቋረጥ መብራቷ ለከተማዋ ውበት ሰጥተዋታል፡፡

  በቀንም በሌሊትም ብርሃን ያላት ከተማ በመሆኗም ‹‹የማትተኛ ከተማ›› በማለት ያንቆለጳጵሷታል፡፡ ኢየሩሳሌም የጥንታዊቷ እስራኤል ዋና ማሳያ ስትሆን፣ ቴልአቪቭ ደግሞ ዘመናዊቷን እስራኤል ቁልጭ አድርጋ ታሳያለች፡፡ የበለፀጉ አገሮች ዋና ከተሞች መልክም አላት፡፡

  በእርግጥ የበለፀጉ አገሮች ማሳያ ቴልአቪቭ ከተማ ብቻም አይደለችም፡፡ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚውና በሕዝቡ ገቢ ዕድገት፣ በፖለቲካና የሚዲያ ነፃነት ከበለፀጉ አገሮች እኩል የምትመደብ ነች፡፡ የፖለቲካ ልዩነት ያላቸው ኃይሎች በፍልስጤምና በተያያዥ የደኅንነት ጉዳዮች ላይ እምብዛም ልዩነት ያላቸው አይመስልም፡፡ ሆኖም፣ እጅግ ጥግ የያዘ የፖለቲካ አቋም የሚያራምዱም፣ እንደ እኛ አገር በጠላትነት የሚፈራረጁም አይደሉም፡፡ ከፍተኛ ተቀባይነት አለው ተብሎ የሚታመንበት ገዢው ፓርቲ፣ ሌሎችን አያገልም፡፡ ፓርላማ ውስጥ 40ና ከዚያ በላይ መቀመጫ ያላቸው ተቃዋሚዎች፤ ከአገራቸው ጉዳይ አይገለሉም፡፡ ልዩነታቸው በአብዛኛው በአገር ውስጥ ፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠነ ነው፡፡

  የአገሪቱን ፓርላማ ወክለው እኛን ሊያነጋግሩ የተመደቡልን የፅዮን ፓርቲ (ሌበር ፓርቲ) መሪ ሴት ሲሆኑ፣ ከመካከላችን አንዱ ‹‹ገዢው ፓርቲ እንዴት እርሷ መንግሥትን ወክላ እንድታነጋግረን ወሰነ? በእኛ አገር ቢሆን ዜና ይሆን ነበር›› ብሎ ፈገግ አሰኘን፡፡ እሳቸውም ቢሆኑ፤ ከገዢው መንግሥት ጋር ልዩነት ያላቸው ቢሆንም፣ አገሪቱ ያላትን የደኅንነትና የውጭ የፖለቲካ ግንኙነትና ጫና አስመልክቶ የመንግሥትን አቋም ነበር ያንፀባረቁልን፡፡

  ምድረ በዳ ላይ የበቀለው ‹‹የከበረ ዘር››

  አካባቢው በሙሉ ማለት ይቻላል በተፈጥሮ አሸዋማና ድንጋያማ ሲሆን፣ የግብርና ልማቱ ከድንጋይ ተፈልጦ በተገኘው አፈር ጭምር የሚካሄድ ነው፡፡ እሱም ብቻ አይደለም በእስራኤል ከጫፍ እስከጫፍ የተጓዝንባቸው ቦታዎች በሙሉ ተራሮቹን ጨምሮ በደን የተሸፈኑ ናቸው፡፡

  ናቲቭ አሸራ በመባል የሚታወቀው ጋዛ አካባቢ የሚገኘው አንድ የእርሻ ማሳ ለመጎብኘት ዕድል አግኝተን ነበር፡፡ አቨድያ ካይናራ፣ በዚሁ የግሪን ሐውስ ዘመናዊ እርሻ ቲማቲምና ቃርያ በማምረት ላይ ከተሰማሩት ድርጅቶች መካከል በአንዱ ይሠራሉ፡፡ ሃዝራ ጀነቲክስ በሚባል ኩባንያ የሚሠሩት ካይናራ እጅና እግራችንን ታጥበን እንድንገባ አዘዙን፡፡ ውስጥ ከግባታችን በፊት ‹‹እንግዲህ በዚህ ቅፅበት ምንም እንደማይፈጠር ተስፋ እናደርጋለን፣ ለማናቸውም ግን ድንገት የተተኮሰብን እንደሆነ ድምፅ እንደሰማችሁ በ15 ሰኮንዶች ውስጥ እዚህ ላይ መድረስ አለባችሁ›› አሉን፣ እሳቸውም የነብስ አድን መጠለያ እያሳዩን፡፡

  ፍርሃት ፍርሃት እያለን ግሪን ሐውሱ ውስጥ ገባን፡፡ ቲማቲምና ሌሎች ሰብሎች አሸዋ ላይ በቅሎ ማየት ለማመን ያስቸግራል፡፡ እያንዳንዷ ቲማቲም የራሷ መቆጣጠርያ ደብተር አላት፡፡ እርስ በርስ መራባት አይቻልም፡፡ ተባዕት አካሉ እንዲወገድ ይደረግና በእሱ ቦታ ከሌላ ይመጣለታል፡፡ ‹‹ክሮስ ፖሊኔሽን›› ይሉታል፡፡ በዚህ ምክንያት እጅግ ምርጥ የተባለ ዘር ማግኘት ይቻላል፡፡ በዚህ ምክንያት እስራኤል የምታመርታቸው የግብርና ምርቶች በዓለም ተፈላጊነታቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ የቲማቲም ምርጥ ዘር በግራም እስከ 2000 ዶላር ይሸጣል ብለውናል፡፡ እሳቸው እንዳሉን፣ በዓመት እስከ 300 ኪሎ ግራም ዘር ያመርታሉ፡፡

  እጅግ አስቸጋሪ በሆነው የጋዛ ዙርያ ግብርና ማካሄድ የተመረጠበትን ምክንያት ጠይቀን ነበር፡፡ የቦታው አየር ፀባይ የሚፈለገውን ምርጥ ዘር ለማምረጥ ምቹ ቦታ መሆኑን ነው የነገሩን፡፡ ‹‹ለነገሩ የትስ እንሄዳለን፡፡ ይኼ እኮ ቤታችን ነው፡፡ ሌላ ቦታ የለንም፡፡ አንድ ቀን በመካከላችን ሰላም ይነግሳል የሚል ተስፋ አለን፤›› ብለውናል፡፡ በአገሪቱ የመስኖ አጠቃቀም የላቀ እንደሆነም ነው የተገነዘብነው፡፡

  ‹‹ዕርዳታ ያሰንፋል››

  እስራኤል ግብርና በጣም የምትተማመንበት ዘርፍ ነው፡፡ ምርታቸውም በዓለም በውድነቱ የታወቀ ነው፡፡ የተለያዩ የሥልጠናና የትምህርት ማዕከሎችም አሉዋቸው፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ለሚመጡ ሥልጠና ይሰጣሉ፡፡

  በዚሁ ምድረ በዳ አምርተው ለራሳቸውና ለዓለም ገበያ ማቅረብ በመቻላቸው እየተገረምኩ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን በዝናብ ላይ ጥገኛ የሆነ ግብርና፣ ሰፊ ለም መሬት እና በቂ ውኃ ይዘን ለድርቅና ለረሃብ መጋለጣችን አሳፈረኝ፡፡ አንዱ የአገሪቱ የመንግሥት ኃላፊ ኢትዮጵያን በተመለከተ ለቀረበለት ጥያቄ ሲመልስ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ስለ ረሃብ መስማት ባለተገባ ነበር፡፡ መሬታችሁ ለም ነው፡፡ በቂ ውኃ አላችሁ፡፡ አቀናጅታችሁ መሥራት አቅቷቸዋል የፖሊሲ ችግር ነው›› ነበር ያለው፡፡

  በእርግጥ በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ አንዳንድ የግብርና ፕሮጀክቶች ውስጥ እስራኤል እጅ አልራቀም ነበር፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፤ በጀርመን የትብብር ድርጀት (GIZ) እንዲሁም በዩኤስኤአይዲ አማካይነት ቴክኒካዊ ድጋፍን ይሰጣሉ፡፡

  በዋናነት በአፋር እንዲሁም በትግራይና በአማራ ክልሎች የበርካታ ፕሮጀክቶችን ስም እየጠቀሱ ተሳትፎአቸውን ሲገልጹ ነበር፡፡ እስራኤላውያን ዕርዳታ መስጠት አይወዱም፡፡ በተለይ በጥሬ ገንዘብ ዕርዳታ መስጠት ያሰንፋል የሚል እምነት አላቸው፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባዩ፤ ‹‹ትንሽ አገር ነን፡፡ በገንዘብ መርዳት አንችልም፡፡ ያለንን ዕውቀትና ቴክኖሎጂ ለማካፈል ግን ሁሌም ዝግጁ ነን›› ብለው ነበር፡፡ በእርግጥ በ1970ዎቹ የተመሠረተው ‹‹ማሻብ›› እየተባለ የሚጠራ የዕርዳታ ድርጅት አለ፡፡ የማሻብም ምክትል ኃላፊ ያረጋገጡልን ይህንን ነው፡፡ ሥልጠና በነፃ ይሰጣሉ፣ ወደ ጎበኘነው ማሳ እየወሰዱም ለወራት የተግባር ትምህርት ይሰጣሉ፡፡ በርካታ ኢትዮጵያን የዚህ ሥልጠና ተካፋይ መሆናቸውንም ገልጸውልናል፡፡

  በእርግጥ እስራኤላውያን በሌላም መንገድ ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡ “Save the Child’s Heart” በሚል በአንድ ትልቅ ሆስፒታል (ቴልአቪቭ) የሚገኘው ማዕከል የመክፈል አቅማቸው ደካማ ለሆኑ ቤተሰቦች ልጆችን በነፃ ያክማሉ፡፡ ይኸኛውም ማዕከል፤ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተቋማዊ ግንኙነት እንዳለው ለማወቅ ችለናል፡፡

  በቁጥር በርከት ካሉት የልብ ሕመም ያለባቸውን ልጆቻቸውን ይዘው ሲያሳክሙ ከነበሩት አፍሪካውያን መካከል፣ ጥቂት ኢትዮጵያውያን ተመልክቼያለሁ፡፡ በዚህ ማዕከል ታክመው በመልካም ጤንነት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ምስክርነት የሰጡበት ዘጋቢ ፊልምም ተመልክተናል፡፡

  እስራኤላውያን የሚታወቁት በእርሻ ብቻ አይደለም፡፡ ውኃን በማቆር፣ በአግባቡ በመጠቀም፤ መልሰው በመጠቀምና ከባህር በማጣራት የሚደርስባቸው የለም፡፡ መኮሮት በመባል የሚታወቀው የአገሪቱ የውኃ ልማት ድርጅት፣ ውኃን ባለማባከንና መልሶ በመጠቀም አገሪቱን በዓለም ቀዳሚ ሲያደርጓት፣ 85 በመቶ የአገሪቱ ውኃም መልሶ ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ከተጣራው ውኃ የሚባክነውም ሦስት በመቶ ብቻ ነው፡፡ 1.5 ቢሊዮን ኩቢክ ሜትር ማመንጨት የሚችለው ይኸው ድርጅት ወደ የትኛውም የእስራኤል ምድር ብቁ ውኃ ያቀርባል፡፡ በዚሁ ቀዳሚነቱን ይዟል፡፡ በመሆኑም አገሪቱ ዘንድሮ ዓለም አቀፍ የውኃ ጉባዔና ትርዒት አዘጋጅ ሆና ተመርጣለች፡፡

  ተቃርኖዎቹ

  በኢየሩሳሌም ጥንታዊነት ይደነቃሉ፡፡ በመፅሐፍ ቅዱስ መሠረት ኢየሱስ በእስራኤል በሠራቸው ተዓምራት ምክንያት ተራሮቿ በሙሉ ታሪክ የተሸከሙ ናቸው፡፡ እንደ ኢየሩሳሌምንና ደብረ ታቦር የመሳሰሉትን ጎብኝተን በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቀን ስናበቃ፣ የአገራቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ታሪካዊ ሁኔታዎች በውስጣችን እየተመላለሰ ወደ አገር ቤት መመለስ ግድ ብሎናል፡፡

  እስራኤል ታሪካዊና ጥንታዊ መስህቦቿ በአንድ በኩል፣ አሁን ከየትኛው አገር የሚስተካከል የኢኮኖሚና የአስተሳሰብ ብልፅግና በሌላ በኩል፣ አቀናጅታ መሄድ የቸገራት አይመስልም፡፡

  በአሁኑ ወቅት የዓለም ቅዱስ ቦታ ተብሎ ከሚታወቀው ከታላቁ የንጉሥ ዳዊት ቤተ መንግሥት ጀርባ የፍልስጤም መስጊድ ይገኛል፡፡ አንድ ግንብ ለሁለት የሚጋሩት ሲሆን፣ ከግንቡ ተቃራኒ በኩል የቆመው መስጊድ ደግሞ በፍልስጤማውያን እጅግ ታሪካዊ የሚባል ቦታ ነው፡፡ የታክሲው ሾፌር እንዳለው ‹‹ግጭቱ የትም ቦታ›› ሲሆን፣ የሚጀምረው ከዚሁ ስፍራ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ፍልስጤማውያን ከዚሁ አናት ላይ በመውጣት በተሳላሚዎቹና በአይሁድ ቄሶች ላይ ድንጋይ በመወርወር ጉዳት ያደርሳሉ፡፡ እነዚህን ወርዋሪዎች አነጣጥሮ በተጠንቀቅ የቆመ የጦር መሣሪያ መኖሩን የተመለከትነው በአንድ በኩል ገብተን ተሳልመን ጨርሰን በሌላ በኩል ስንወጣ ነው፡፡ ከታሪካዊው ግንብ በተቃራኒው የቆመው ሌላ ግንብ፣ ቀን ተሌሊት እንዲጠባበቁ አድርጓቸዋል፡፡ ችግራቸው ይኸው ነው፡፡

  በጋባዣችን በአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተያዘው እጅግ የተጨናነቀ ፕሮግራም ውጪ ተንቀሳቀስን የትኛውንም ከተማ መመልከት አልቻልንም፡፡ እስራኤላውያን መሬት ላይ ያለውን እውነታ ራሱ ይናገር የሚል አቋም ያላቸው ይመስል፤ ቁጥቦች ናቸው፡፡ ጠንካራ ጥያቄ እንኳን መስማት የሚፈልጉ አይመስልም፡፡ የመቆጣት ባህሪ አላቸው፡፡ መመለሳችንም እንደመግባታችን አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ በቤን አርዬን ኤርፖርት የማይታመን ቃለ መጠይቅና ፍተሻ ተካሂዶብን ወደ የመጣንበት አቅንተናል፡፡

  የማነ ናግሽ፣ ኢየሩሳሌም እስራኤል

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት ጀመረ

  ሦስተኛ ዙር ሙሌት በዛሬው ዕለት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ...

  የክላስተር አደረጃጀት ፖለቲካዊ ውዝግብ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይባል የነበረውን አደረጃጀት...

  በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

  በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...