Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ተስፋ ያደረጋቸው የውጭ ኩባንያዎችና በእንጭጭ ያስቀሩት ዕቅድ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የጨርቃ ጨርቅና ልብስ ስፌት ኢንዱስትሪው መንግሥት በአፍሪካ በቀላል አምራች ኢንዱስትሪው መስክ ኢትዮጵያን ቀዳሚ ያደርጋሉ ተብሎ ከሚነገርለት መካከል ተመድቧል፡፡ እንደውም ትልቁን ድርሻ ወስዷል፡፡ በመጪው አምስት ዓመት ጊዜ ውስጥም ከዚሁ ከጨርቃ ጨርቅና ስፌት ዘርፍ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ በወጪ ንግድ በኩል እንዲገኝ ታቅዷል፡፡ ከዘርፉ የሚጠበቀው ጠቅላላ ምርት 2.5 ቢሊዮን ዶላር እንደሚገመትም የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ይፋ አድርጓል፡፡

  በዚህ መነሻም ባለፈው ጥቅምት 26 ቀን 2008 ዓ.ም. ስለመጪዎቹ አምስት ዓመታት ግብ እንዲሁም ስላለፉት አምስት ዓመታት አፈጻጸም መንግሥት ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች ስለመንግሥት ዕቅድ፣ ስላልተፈቱላቸው ማነቆዎችና ስለሌሎችም ጥያቄ አንስተዋል፡፡ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ማግኘት ስላልቻሏቸው አገልግሎቶች ጥያቄ ያሰኑም ነበሩ፡፡ 

  ከሁሉ በፊት ያለፉት አምስት ዓመታት እንዴት ታለፉ? የሚለውን መመልከት ተገቢ ይሆናል፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት ማለትም በመጀመርያው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሠረት የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ የድርና ማግ፣ የስፌት ወዘተ. የባህል አልባሳትን ጨምሮ ፋብሪካዎች አምርተው ወደ ውጭ የሚልኩት ምርት በ2007 ዓ.ም. መጨረሻ አንድ ቢሊዮን ዶላር እንዲያስገኝ ይጠበቅ ነበር፡፡ ሆኖም ውጤቱ 98 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ያስገኘ ሆኗል፡፡ 2.5 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ የሚያወጣ ምርት በጠቅላላው ሲጠበቅ ውጤቱ ግን 689 ሚሊዮን ዶላር ብቻ በመሆን የመጀመርያው አምስት ዓመት ዕቅድ ተደምድሟል፡፡ በዚህም ሳያበቃ የፋብሪካዎችን የማምረት አቅም ወደ 90 ከመቶ ለማድረስ ይታሰብ ነበር፡፡ እርግጥ ከአምስት ዓመት በኋላም አሁን ያሉት 130 ፋብሪካዎች በአማካይ እያመረቱ ያሉት ከሙሉ አቅማቸው 35 እስከ 40 ከመቶ ያህሉን ብቻ በመጠቀም ነው፡፡

  በሁለተኛው ምዕራፍ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ያለፉትን አምስት ዓመታት ለመድገም ግድ የሆነበት የጨርቃ ጨርቅና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ባለፉት ዓመታት የወጠናቸው ግቦች ያልተሳኩት ‹‹ከአቅም በላይ ስለተለጠጡ›› ብቻ እንዳልሆነ ይከራከራል፡፡ ዕቅዱ ሲታለም ታሳቢ አድርጓቸው ከነበሩት መካከል በዓለም ላይ ግዙፍ መሆኑ የሚነገርለት የህንድ ኩባንያ በዋቢነት ይጠቀሳል፡፡

  ባለፉት አምስት ዓመታት የታለሙት ዕቅዶች የተለጠጡ ናቸው ከተባለ አሁንም መልሶ ያንኑ ማቀዱ በምን ምንክንያት ነው? በማለት ሪፖርተር ጥያቄ ያረበላቸው የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ለማ ማብራሪያ አላቸው፡፡ እንደ አቶ ስለሺ ማብራሪያ ለዘርፉ ዕቅድ ታሳቢ ከነበሩት ውስጥ አንዱ ኤስቪፒ ቴክስታይል ግሩፕ የተባለው ኩባንያ ነው፡፡ ይህ ኩባንያ በህንድ ያለው አቅም ሲታይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች በጠቅላላ ቢደመሩ እንኳ የኩባንያውን 40 ከመቶ የማይደርሱበት አቅም ያለው ግዙፍ ኩባንያ ነበር፡፡

  በመሆኑም ይህ ኩባንያ ቢያንስ እ.ኤ.አ. ከ2012 ጀምሮ ከመንግሥት ኃላፊዎች ጋር መነጋገር እንደጀመረ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይሁንና ኩባንያው ‹‹በ2003 ዓ.ም. መጨረሻ ወይም በ2004 መጀመርያ ገደማ 400 ሚሊዮን ዶላር የሚያስገኝ ምርት ወደ ውጭ እንደሚልክ ይጠበቅ ነበር፡፡ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መጨረሻ ማለትም በ2007 ዓ.ም. ይኸው ኩባንያ ብቻ 700 ሚሊዮን ዶላር የማስገኘት አቅም እንዳለው አረጋግጠን ነበር፡፡ ይኼ አንዱ ታሳቢ ነው፡፡ ይህንን የመሳሰሉ አራት አምስት አቅም ያላቸው ኩባንያዎችን ብንስብ ዕቅዱን ለማሳካት ብዙም ላይከብደን ይችል ነበር፤›› ያሉት አቶ ስለሺ፣ ለዚህ ኩባንያ በኢትዮጵያ ተደርጎ የማያውቅ ዕድል ተሰጥቶት እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ ‹‹በአገራችን ተደርጎ የማይታወቅ ለጥጥ እርሻ ብቻ 50 ሺሕ ሔክታር መሬት ተሰጥቶታል፡፡ ምክንያቱም የግባችን ማሳኪያም መውደቂያው ይኼው ነው የሚል እምነት ይዘን ስለነበር ነው፤›› በማለት ኩባንያው ከእርሻ መሬት በተጨማሪ በኮምቦልቻ ከተማ ፋብሪካውን እንዲገነባበት የሚያስችለው ተጨማሪ መሬት ተሰጥቶት እንደነበር አቶ ስለሺ ገልጸዋል፡፡ (ሺርቫላባ ፒቲዬ) ኤስቪፒ ግሩፕ ለማምረቻ ፋብሪካ መገንቢያ የተሰጠው ቦታ 50 ሺሕ ሔክታር እንደነበር ሪፖርተርን ጨምሮ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች አምና ዘግበው እንደነበር አይዘነጋም፡፡

  ይሁንና ‹‹ይህ ኩባንያ በ2004 እና በ2005 ዓ.ም. መንኮታኮቱን አረጋገጥን፤›› ያሉት አቶ ስለሺ፣ የኩባንያው መውደቅ የተያያዘው በዓለም በተከሰተው የፋይናንስና የኢኮኖሚ ቀውስ ሳቢያ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በምሥራቅ አውሮፓ ሳይቀር ትልቅ ድርሻ የነበረው ይህ ኩባንያ መውደቁ፣ የአገሪቱን ዕቅድም አብሮ አንኮታኩቶታል በማለት በዚህ ኩባንያ ላይ ጥገኛ በሆነው ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ዕቅድ ላይ የደረሰውን ውድቀት ለማካካስ ከህንድ፣ ከቻይናና ከቱርክ በርካታ ኩባንያዎችን ለማምጣት እንደተቻለ ዋቢ የሚያደርጉትም እነአይካ አዲስ የመሳሰሉትን በመጥቀስ ነው፡፡

  150 ዓመታት ዕድሜ ያለው ኤስቪፒ ግሩፕ ባለፈው ዓመት በኮምቦልቻ የሚገነባው ፋብሪካ በአፍሪካ ግዙፉ የድርና ማግ ፋብሪካ እንደሚሆን መግለጹ አይዘነጋም፡፡ 550 ሚሊዮን ዶላር ወይም ከአሥር ቢሊዮን ብር በላይ ኢንቨስት ያደርግበታል የተባለው የኮምቦልቻ ፋብሪካ፣ በቀን 280 ቶን ድርና ማግ ያመርታል ተብሎ መገለጹም ይታወሳል፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ያበድርኝ በማለቱ ባንኩ ለመጀመርያው ምዕራፍ ግንባታ 23 ሚሊዮን ዶላር ብድር ሊሰጠው ፈቃደኛ መሆኑን እንዳስታወቀ መዘገባችንም የሚታወስ ነው፡፡ ምንም እንኳ አቶ ስለሺ ኩባንያው በ2003 ዓ.ም. መጨረሻ ወይም በ2004 መጀመርያ ላይ 400 ሚሊዮን ዶላር የሚያስገኝ ምርት ወደ ውጭ እልካለሁ ማለቱን ቢጠቅሱም፣ ኩባንያው ግን ይህንን መጠን ይፋ ያደረገው ባለፈው ዓመት እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ግንባታ መጀመሩም እንዲሁ ይፋ የተደረገው አምና እንደነበር ተዘግቧል፡፡

  የህንዱ ኩባንያ እንዲህ ቢዘረርም አሁንም ሌላ ጥያቄ የሚያጭር ነጥብ ይነሳል፡፡ እስካሁን በዘርፉ እየተገኘ ካለው መቶ ሚሊዮን ዶላር የወጪ ንግድ ገቢ ውስጥ 60 ከመቶውን እያስገኘ ያለው የቱርኩ አይካ አዲስ ጨርቃ ጨርቅ መሆኑ አነጋጋሪ ነበር፡፡ ይሁንና አቶ ስለሺ በዚህ አይስማሙም፡፡ ምንም እንኳ አይካ አዲስ በስሙ የተመዘገበለት 60 ከመቶ የኤክስፖርት ድርሻ መያዙ እግርጥ ቢሆንም፣ ለአይካ አዲስ አምራች በመሆን ሠርተው የሚያስረክቡት አሥር ያህል ፋብሪካዎች አብረውት እየሠሩ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡

  የሆነው ሆነና ያለፈው አምስት ዓመት ዕቅድ በሌሎቹ መስኮች እንዳሳየው የላሸቀ አፈጻጸም ሁሉ በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው መስክም ተመሳሳዩን አስመዝግቦ ተደምድሟል፡፡ በዕቅዱ መጨረሻ ዓመት የተገኘው መቶ ሚሊዮን ዶላር ገደማ ሆኗል፡፡ የሚጠበቀው አንድ ቢሊዮን ዶላር እንደነበር ልብ ይሏል፡፡ ምንም እንኳ የህንዱ ኤስቪፒ ግሩፕ ባጋጠመው የፋይናንስ ቀውስ ዳፋ ያቀደውን አለማሳካቱ፣ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪም ችግር ውስጥ ቢጥለው ከዚህ ኩባንያ ውጭ ይጠበቅ የነበረው መጠን እንኳ አለመገኘቱ ግን ሌላው ዘርፉ መመለስ ያለበት ጥያቄ ነው፡፡ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ባወጣው መረጃ መሠረት በአምስቱ ዓመት ዕቅድ መገባደጃ የተገኘው የወጪ ንግድ ገቢ 98 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡

  እርግጥ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ያሰበውን እንዳያሳካ እክል ከሆኑበት ማነቆዎች መካከል የመሬት፣ የኤሌክትሪክ ኃይልና የውኃ አቅርቦት በፍጥነት ለማግኘት አለመቻል፣ ለጥሬ ዕቃም ሆነ ለማሽነሪ ግዥ የሚውል የብድርና የውጭ ምንዛሪ እጦት ኢንስቲትዩቱ የጠቀሳቸው ማነቆዎች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል መንግሥት የቱንም ያህል ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ትኩረት እንደሚሰጥ ቢገለጽም፣ እንደነሲሪላንካና ባንግላዴሽ ያሉ አገሮች ኢትዮጵያ በአግባቡ ሳትጠቀምበት የቆየችውን የዓለም ገበያ ሊቀራመቷትና ከጨዋታ ውጭ ሊያደርጓት እንደሚችሉ ፋብሪካዎች ሥጋት ገብቷቸዋል፡፡

  የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ፋሲል ታደሰ እንዳሳሰቡት፣ በዓለም የጨርቃ ጨርቅ ገበያ ላይ የቻይና ሚና እየተዳከመ መምጣቱን በመመርኮዝ ሁለቱ አገሮች ምርታቸውን በገፍ ለመጨመር መዘጋጀታቸውን የገለጹት አቶ ፋሲል፣ አሁን ያለንን ተፈላጊነትና የገበያ አጋጣሚ ለመጠቀም፣ በመቐለ፣ በባህር ዳር፣ በኮምቦልቻና በድሬዳዋ እየተገነቡ የሚገኙትና በአዲስ አበባ የተገነቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች በቂ አለመሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ መንግሥት ተጨማሪ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን መገንባትና እየተገነቡ ያሉትን በፍጥነት አጠናቆ ሥራ እንዲያስጀምር አቶ ፋሲል አሳስበዋል፡፡ የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ረጅም ጊዜ መውሰዱ አግባብ እንዳልነበረም ጠቅሰዋል፡፡

  በመሠረተ ልማት ማለትም እንደ እሳት አደጋና የሥራ ላይ ደኅንነት ለሠራተኞች አለመሟላት የመሳሰሉ መሠረታዊ ጉዳዮች በቦሌ ለሚ ፓርክ ስለሚታዩ እንደ ዎልማርት ለመሳሰሉት ትልልቅ የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶችን የሚገዙ ኩባንያዎች ምርት እንዲገዟቸው ለማድረግ አለመቻላቸውን የጠቀሱት ኩባንያዎች፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ታደሰ ኃይሌ ምላሽ እንዲጡባቸው ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ መንግሥት በቦሌ ለሚ የመሠረተ ልማቶችን ለማሟላት ያሳየውን መንቀርፈፍ የተቹ ኢንቨስተሮች፣ የአካባቢና የሠራተኞች የሥራ ላይ ደኅንነትና የእሳት አደጋ መቆጣሪያ ሥርዓት በአስቸኳይ እንዲዘረጋና ኤክስፖርት ማድረግ እንዲጀምሩ የሚያስችላቸው ሌላውም መሠረተ ልማት እንዲሟላ ሲጠይቁ ተደምጠዋል፡፡ ከሕንፃ ግንባታ ጀምሮ፣ በኢንዱስትሪ ፓርኩ ስለተገጠሙት መሠረታዊ የሥራና የሠራተኞች እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃና ደኅንነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት እንደ ዎልማርት ካሉ የዓለም ግዙፍ ኩባንያዎች በየሦስት ወሩ ማግኘት እንደሚጠበቅባቸው የገለጹት ፋብሪካዎች፣ በኢንዱስትሪ መንደሩ እንዲህ ያሉት ግዴታዎች እንዲሟሉላቸው ጠይቀዋል፡፡ ከገቢዎችና ከጉምሩክ፣ ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ወጪ የመሳሰሉትም ምላሽ እንዲያገኙ ጥያቄ ቀርቦባቸዋል፡፡

  አቶ ታደሰ ኃይሌና አቶ ስለሺ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የቀድሞውን የሸቀጦች ጅምላ ንግድና አስመጪ ድርጅትን (ጅንአድ) በመተካት ለኢንዱስትሪዎች የሥራ ማስኬጃና የጥሬ ዕቃዎች በማቅረብ እንዲሠራ ተደርጎ እንደ አዲስ በአራት ቢሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመው የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃዎች ልማት ድርጅት የአምራቾችን ችግሮች እንደሚፈታ የሚጠበቅ ተቋም መሆኑም ተነግሮለታል፡፡

   

   

   

   

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች