Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ክቡር ሚኒስትር

  [አንድ ባለጉዳይ ክቡር ሚኒስትሩን ለማግኘት ፈልጐ ቢሯቸው ቢመጣም ጸሐፊያቸው ልታስገባው አልፈለገችም]

  • ለምንድን ነው ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ የማታስገቢኝ?
  • ቀጠሮ አለህ?
  • የለኝም ግን አንገብጋቢ ጉዳይ ነው ያለኝ፡፡
  • ጉዳይማ ማን የሌለው አለ?
  • እኔ እኮ ኢትዮጵያዊ ነኝ፤ በዚያ ላይ እሳቸው እዚህ ያሉት ሕዝቡን ሊያገለግሉ ነው፡፡
  • አውቃለሁ፤ ቀጠሮ ግን ከሌለህ ዝም ብሎ ማግኘት አይቻልም፡፡
  • ዝም ብዬ አይደለም ላገኛቸው የፈለግኩት፣ ትልቅ ጉዳይ ይዤ ነው፡፡
  • የምን ጉዳይ ነው?
  • እኔ ለአገሪቱም ሆነ ለሕዝቡም የሚጠቅም ኢንዱስትሪ ልገነባ በዝግጅት ላይ ነኝ፡፡
  • እሺ ምን ተቸገርክ?
  • ይኸው መሬት ለማግኘት ከዓመት በላይ ነው የፈጀብኝ፡፡
  • መታገስ ነዋ፡፡
  • ምን እያልሽ ነው ልሥራ እንጂ ልዝረፍ አይደለም ያልኩት?
  • ያው ቢሮክራሲውን ታውቀው የለ?
  • ይኸው በየሚዲያውና በየስብሰባው የመልካም አስተዳደር ችግርን እንቀርፋለን እያላችሁ አይደል እንዴ የምትለፍፉት?
  • ችግርህ ይገባኛል፡፡
  • እሱ ምን ይጠቅመኛል አሁን? እኔ የምፈልገው ክቡር ሚኒስትሩን ማናገር ነው፡፡
  • እስቲ ለማንኛውም ጠብቀኝ ላናግራቸው፡፡

  [ጸሐፊያቸው ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ገባች]

  • ባለጉዳይ አለ፡፡
  • የምን ባለጉዳይ?
  • ላናግርዎት እፈልጋለሁ እያለ ነው፡፡
  • ቀጠሮ አለው?
  • የለውም ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ታዲያ ይኼ ኬክ ቤት መሰለው እንዴ ዘው ብሎ የሚገባበት?
  • ተቸግሬያለሁ እያለ ነው፡፡
  • ታዲያ ይኼ ማን ነው ኤንጂኦ ነው ያለው?
  • የመልካም አስተዳደር በደል ደርሶብኛል እያለ ነው፡፡
  • ስንቱ ሕዝብ ተመሳሳይ ችግር እንዳለበት አያውቅም ታዲያ?
  • እኮ እሱንም ያዳምጡት፡፡
  • ሴትዮ የግለሰብ ጉዳይ ማዳመጥ ትቻለሁ፡፡
  • ለምን ክቡር ሚኒስትር?
  • ደላላው በዝቷል፡፡
  • እና ምን ልበለው?
  • አሰናብችው፡፡

  [አንድ ጉዳይ አስፈጻሚ ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ዘው ብሎ ገባ]

  • ሳትደውል እንዴት መጣህ ባክህ?
  • መደወሉ አስተማማኝ አይደለም ብዬ ነው፡፡
  • ለምን? ምን ተፈጠረ?
  • ያው ባለፈው ኃላፊያችሁ ከዚህ ስብሰባ ወጥታችሁ እንደምትደራጁ አውቃለሁ ብለዋል አይደል?
  • እሱማ ብለዋል፡፡
  • በልበ ሙሉነት እንደዚያ ያሉት በስልክ የሚወራውን ስለሚሰሙ ይሆናላ፡፡
  • እዚህም መምጣትህን ግን አልወደድኩትም፡፡
  • ለምን ክቡር ሚኒስትር?
  • አሁን ከአንተ ዓይነት ሰው ጋር መታየት ጥሩ አይደለም፡፡
  • እንደዛ ከዓይኔ አትራቅ እንዳላሉኝ አሁን ከአንተ ጋር መታየት አልፈልግም ይሉኛል?
  • ጊዜው ተቀይሯል፡፡
  • ረሱት እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
  • ምኑን?
  • ያሠራሁልዎትን ቤት፡፡
  • እ…
  • ደመወዝዎት ይሠራው ነበር እንዴ?
  • ምን አልከኝ?
  • ለማንኛውም እኔ በጣም አስፈልግዎታለሁ፡፡
  • እሱንማ አውቃለሁ፡፡
  • ታዲያ ይኼን ካወቁ ለምን እንደዚህ ይላሉ?
  • ፈርቼ ነዋ፡፡
  • ምኑን ነው የሚፈሩት?
  • ባለፈው ያደረግነውን ስብሰባ አላየኸውም?
  • አይቼዋለሁ፡፡
  • ስለድለላ ሲወራ የነበረውን ሰምተሃል አይደል?
  • ክቡር ሚኒስትር ምንም አዲስ አገር እኮ የለውም፡፡
  • እንዴት የለውም?
  • የመልካም አስተዳደር ችግሮች እኮ የነበሩ፣ ያሉና የሚቀጥሉ ናቸው፡፡
  • አሁን ግን ቆርጠን ተነስተናል፡፡
  • ምን ለማድረግ?
  • የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ፡፡
  • ኧረ ስንተዋወቅ አንተናነቅ ክቡር ሚኒስትር?
  • እንዴት?
  • ኢሕአዴግ ያወራል እንጂ መቼ ይተገብራል?
  • እና አንተም አይተገብርም እያልከኝ ነው?
  • እርስዎማ ኢሕአዴግ አይደሉም፡፡
  • እንዴት?
  • እስከዛሬ የሰጥሁዎትን ሁሉንም ፕሮጀክቶች እኮ አስፈጽመዋቸዋል፡፡
  • እሱን እኮ ነው የምልህ፡፡
  • አሁን ግን አንድ ወሳኝ ፕሮጀክት ይዤ መጥቻለሁ፡፡
  • የምን ፕሮጀክት?
  • አንድ የውጭ ባለሀብት እዚህ ኢንቨስት ማድረግ ይፈልጋል፡፡
  • ምን ላይ ነው ኢንቨስት ማድረግ የሚፈለገው?
  • ፋብሪካ ማቋቋም ነው የሚፈልገው፡፡
  • የምን ፋብሪካ?
  • የጁስ ፋብሪካ፡፡
  • ይኼማ የሚበረታታ ነው፡፡
  • ትልቅ መሬት ግን ይፈልጋል፡፡
  • ሌላስ?
  • ኤልሲም መክፈት ይፈልጋል፡፡
  • የምን ኤልሲ?
  • ፍራፍሬ ማስመጫ ነው፡፡
  • አገሪቷ ውስጥ ያለው ፍራፍሬስ?
  • ክቡር ሚኒስትር ጨዋታውን ረሱት እንዴ? ዋናው የተፈለገው ነገር እኮ ኤልሲው ነው፡፡
  • ፍራፍሬ ከአገር ውስጥ ለምን አይገዛም ብንባልስ?
  • ምን ችግር አለው ማስወራት ነዋ?
  • ምንድን ነው የምናስወራው?
  • የአገሪቱ ፍራፍሬ መርዛማነት አለው ብለን ነዋ፡፡
  • አባ መላ ነህ እኮ፡፡
  • ይኼን ካስደረግን ጐረስን ማለት ነው፡፡
  • ምንድን ነው የምንጐርሰው?
  • ከፈለጉም ቤት አሊያም ሕንፃ፡፡
  • አስቸጋሪ ነገር እኮ ነው የምትጠይቀኝ፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር በጐርፍ ስንመታ አልታየዎትም?
  • የኤልኒኖን ጐርፍ ነው የምትለኝ?
  • የለም የለም፣ የብር ጐርፍ ነው እንጂ፡፡
  • ወይ ጣጣ፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር እኛና እናንተ እኮ እንደ ሙቀጫና ዘነዘና ነን፡፡
  • እንዴት?
  • እናንተም ያለ እኛ እኛም ያለ እናንተ ሥራ መሥራት አንችልም፡፡
  • ማን ነው ሙቀጫ? ማን ነው ዘነዘና?
  • እርሱን ለእርስዎ ተውኩት፡፡

  [ክቡር ሚኒስትሩ በመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ የመሥሪያ ቤታቸውን ሠራተኞች ሰብስበዋል]

  • ይህን ስብሰባ የጠራሁት በመሥሪያ ቤታችን ያሉት የመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ መወያየት ስላለብን ነው፡፡ ስለዚህ ዛሬ በግልጽ ያሉትን ችግሮች መወያየት አለብን፡፡ መድረኩ ክፍት ነው፡፡
  • እኔ የምናገረው አለኝ፡፡
  • እሺ ቀጥል፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር ይህ ስብሰባ ቢዘገይም ዛሬ በመደረጉ ደስ ብሎኛል፡፡
  • ወደ ጉዳይህ ግባ፡፡
  • የመልካም አስተዳደር ችግር አንገብጋቢ ሆኗል፡፡
  • ከችግሮቹ መካከል መጥቀስ ትችላለህ?
  • ክቡር ሚኒስትር አንዳንድ ባለሀብቶች ምን እንደሚሠሩ እንኳን ሳይታወቅ ሁሉም ነገር ይሟላላቸዋል፡፡
  • እንዴት ማለት?
  • ሌሎች ደግሞ በትክክል ለአገር የሚጠቅም ፕሮጀክት ይዘው ሲመጡ ዞር ብሎ የሚያያቸው የለም፡፡
  • እኮ ለምን?
  • ሥራ የሚሠራው በድለላ ሆኗል፡፡
  • ምን እያልክ ነው?
  • ከላይ ያሉ አመራሮች ትልልቅ ጉዳዮች በቃል ትዕዛዝ ብቻ እንዲፈጸሙ ያደርጋሉ፡፡
  • እኔን እያልከኝ ነው?
  • እንደዛ ማለቴ አይደለም፡፡
  • ታዲያ ምን እያልክ ነው?
  • የፕሮጀክቶች ጠቀሜታ በግልጽ ሳይታወቅ፣ ከበላይ አመራሮች በሚመጡ ትዕዛዞች ብቻ ጉዳዮች ያልቃሉ፡፡
  • አንድ መታወቅ ያለበት  ጉዳይ አለ፡፡
  • ምን ክቡር ሚኒስትር?
  • መንግሥት ባለሀብቶች እዚህች አገር ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ሌት ተቀን ነው የሚጥረው፡፡
  • እሱማ የታወቀ ነው፡፡
  • ስለዚህ በልፋት የመጡ ባለሀብቶች በቢሮክራሲ ልናሰለቻቸው አይገባም፡፡
  • እዚህ ላይ ግን መጠንቀቅ አለብን፡፡
  • የምን ጥንቃቄ?
  • አንዳንዱ ኢንቨስተር ኪራይ ሰብሳቢ ነው፡፡
  • እንዴት?
  • የቴክኖሎጂ ትራንስፈር ሳይኖርና ምንም ዓይነት እሴት ሳይጨምር የአገሪቷን ሀብት ሊመዘብር ይፈልጋል፡፡
  • ቆይ እነዚህ ኢንቨስተሮች የአንተ ኪስ ውስጥ ገብተዋል?
  • እሱማ አልገቡም፡፡
  • ታዲያ ምን እያልክ ነው?
  • ያው የአገሪቷ ሀብት ሲመዘበር እኮ የእኔም ኪስ በተዘዋዋሪ ተመዘበረ ማለት ነው፡፡
  • ለማንኛውም ባለሀብቶች ላይ እየደረሰ ያለው የመልካም አስተዳደር ችግር መቀረፍ አለበት፡፡

  [ክቡር ሚኒስትሩ ከስብሰባው በኋላ ከአማካሪያቸው ጋር እያወሩ ነው]

  • በል በቃ ሥራችንን በአዲስ መልክ መጀመር አለብን፡፡
  • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
  • ኢንቨስተሮችን ማስከፋት የለብንም፡፡
  • የምንሠራው እኮ ላለማስከፋት ነው፡፡
  • የሚያመጧቸው ፕሮጀክቶች ባፋጣኝ እየታዩ ምላሽ ይሰጣቸው፡፡
  • ያው አንዳንዶቹ እኮ ኪራይ ሰብሳቢዎች ስለሆኑ ነው፡፡
  • ቢሆንም አገሪቱ እነዚህን ባለሀብቶች በጣም ትፈልጋቸዋለች፡፡
  • ያው እንግዲህ የምንሠራው በደንብና በመመርያው መሠረት ነው፡፡
  • እሱ ነው እኮ ችግሩ፡፡
  • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
  • አንዳንድ ደንቦችና መመርያዎቻችን አያበረታቱም፡፡
  • ምኑን?
  • ኪራይ ሰብሳቢዎችን፡፡
  • እሱን ነው የምልዎት፡፡
  • ማለቴ ኢንቨስተሮችን፡፡
  • መጠንቀቅ ግን ያስፈልጋል፡፡
  • ለማንኛውም ሰሞኑን የሚመጡ ኢንቨስተሮች ስላሉ በደንብ ይስተናገዱ፡፡
  • ብቻ ኪራይ ሰብሳቢዎች እንዳይሆኑ?
  • ስለእሱ አታስብ፡፡

  [ክቡር ሚኒስትሩ ጉዳይ አስፈጻሚው ጋ ደወሉ]

  • በቃ ቀጭን ትዕዛዝ አስተላልፌያለሁ፡፡  
  • አንጀት አርስ ነዎት እኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እያወቅከኝ እኔን፡፡
  • በአጋጣሚ ባለሀብቱ ከእኔ ጋር ነበርና እንገናኝ እያለ ነው፡፡
  • እንችላለን፡፡
  • የት እንገናኝ ታዲያ ክቡር ሚኒስትር?
  • ያው እኔ ከፋይቭ ስታር በታች ቦታ መታየት አልፈልግም፡፡
  • ሰው የማይበዛበት ቦታ ብንገናኝ ግን ጥሩ ነው፡፡
  • የቀበሌ መዝናኛ እንገናኝ እያልከኝ ነው?
  • ምን ሰሞኑን የሆቴሎቹን ስታር እኮ አምሰውታል፡፡
  • እኮ የት እንገናኝ?
  • በቃ ባለአንድ ኮከብ ሆቴል እንገናኝ፡፡
  • እኔ ባለአንድ ኮከብ ሆቴል ልገባ?
  • እርስዎ ሲገቡበት እኮ ባለስድስት ኮከብ ይሆናል፡፡
  • እንዴት?
  • ራስዎ ባለአምስት ኮከብ ነዎት፡፡

   

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  አዲስ አበባና ኦሮሚያ ወሰን ለማካለል ተስማሙ

  ኮዬ ፈጬ፣ ቱሉዲምቱ፣ ጀሞ ቁጥር 2 ወደ ኦሮሚያ ለቡ፣ ፉሪና...

  በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል የተጀመረው የድርድር ሒደት አሳታፊ እንዲሆን ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት፣  በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...

  ባንኮች እንዲዋሀዱ እስከ ማስገደድ ሊገባ እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ ጠቆመ

  በአሁኑ ወቅት የባንኮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ችግር የሚሆንና የውጭ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...

  ሰበበኞች!

  ዛሬ የምንጓዘው ከሜክሲኮ ወደ አየር ጤና ነው፡፡ ዛሬም፣ ነገም...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  [ክቡር ሚኒስትሩ ወዳጃቸው ከሆነ አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ጋር ሻይ ቡና እያሉ በኬንያ ስለተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እየተጫወቱ ነው]

  ኬንያ በዚህ ደረጃ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ታደርጋለች ብዬ አላሰብኩም ነበር ክቡር ሚኒስትር። አዎ። ጥሩ ዝግጅት አድርገውበታል። ቢሆንም... ቢሆንም ምን ክቡር ሚኒስትር?  እባክህ ክቡር ሚኒስትር የምትለውን ነገር አቁም። ወዳጅ...

  [ክቡር ሚኒስትሩ የሥራ አጥነት ችግሮችን የመፍታት ተልዕኮ የተሰጠው ተቋም በዋና ጽሕፈት ቤቱ ሕንፃና ቢሮዎች ላይ ያደረገውን ዕድሳት መርቀው በመክፈት ጉብኝት እያደረጉ ነው]

  እጅግ ውብ ዕድሳት ያደረጋችሁት! በእውነቱ በጣም ድንቅ ነው፡፡ አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር። በጣም ድንቅ ነው። ዕድሳቱን ያከናወነው ድርጅት ጥሩ ልምድ ያለው ይመስላል? ተቋራጩ ማን እንደሆነ አልነገርኩዎትም እንዴ? የትኛው ተቋራጭ...

  [ክቡር ሚኒስትሩ በስንዴ የተሸፈኑ ሰፋፊ እርሻዎች ያሉበትን ሁኔታ ለመገምገም ከስንዴ ምርት ድጋፍና ክትትል ኮሚቴ ሰብሳቢ ጋር እየመከሩ ነው] 

  ክቡር ሚኒስትር እንደነገርክዎት በሁሉም ስንዴ አብቃይ አካባቢዎቻችን ያሉ አርሶ አደሮች ጥሪያችንን ተቀብለው መሬታቸውን በኩታ ገጠም አርሰው በስንዴ ዘር ሸፍነዋል። በጣም ጥሩ ዜና ነው። በጣም እንጂ። የሚገርምዎት...