Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  አቢሲኒያ ባንክ የተበላሹ ብድሮቹን ምጣኔ ወደ 2.7 በመቶ አወረደ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  – ከተጣራ ትርፉ 215 ሚሊዮን ብር ለባለአክሲዮኖች እንዲከፋፈል ወሰነ

  አቢሲኒያ ባንክ በ2007 በጀት ዓመት የተበላሹ ብድሮች (NPLs) ምጣኔውን ወደ 2.7 በመቶ ዝቅ ማድረጉን ገለጸ፡፡ በበጀት ዓመቱ ከተገኘው የተጣራ ትርፍ ውስጥ ከ215 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆነውን ለባለአክሲዮኖች እንዲከፋፈል ተወሰነ፡፡

  ባንኩ ባለፈው ቅዳሜ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔው ላይ እንዳስታወቀው በ2006 በጀት ዓመት የባንኩ የተበላሹ ብድሮች ምጣኔ 3.42 በመቶ ነበር፡፡ በ2007 በጀት ዓመት ግን የባንኩን ብድሮች ጤናማ ለማድረግ ባደረገው ጥረት የተበላሹ ብድሮች ምጣኔውን ወደ 2.7 በመቶ ዝቅ አድርጓል፡፡

  በቀደሙት ዓመታት የባንኩ የተበላሹ ብድሮች ምጣኔ ከሌሎች ባንኮች በተለየ ከፍተኛ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ በተለይ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ የተበላሹ ብድሮች ምጣኔውን ዝቅ እያደረገ በመምጣት የባንኩ ብድሮች በበለጠ ጤናማነት የያዘ ሆኗል ተብሏል፡፡

  በቅዳሜው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የባንኩን ዓመታዊ የሥራ ክንውን ሪፖርት ያቀረቡት የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ መሠረት ታዬ እንደገለጹት፣ የባንኩ የተበላሹ ብድሮች ምጣኔ 2.7 በመቶ መድረሱ ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው የአምስት በመቶ ጣራ ጋር ሲነፃፀር ያነሰ ነው፡፡ ይህም የባንኩን ብድሮች ጤናማ ከማድረግ አኳያ እየተደረገ ያለውን ጥረት አመላካች ነውም ብለውታል፡፡

  ባንኩ ለበጀት ዓመቱና ከበጀት ዓመቱ በፊት ከሰጠው ብድሮች ውስጥ 2.44 ቢሊዮን ብር ማሰባሰቡን ገልጿል፡፡

  በ2007 በጀት ዓመት የባንኩ የብድርና ቅድሚያ ክፍያዎች መጠን ወደ 5.99 ቢሊዮን ብር ያደገ ሲሆን፣ ይህም አኃዝ ካለፈው ዓመት ውጤት ጋር ሲነፃፀር የ844 ሚሊዮን ብር ወይም የ16.3 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡

  እንደ ሪፖርቱ ከሆነ ባንኩ በበጀት ዓመቱ ከሰጠው ብድር ውስጥ የአገር ውስጥ ንግድና አገልግሎት 42 በመቶውን በመያዝ ትልቁን ድርሻ ይዟል፡፡ የወጪ ንግድ 20 በመቶ እንዲሁም ለግንባታ የተሰጠው ብድር ደግሞ 15 በመቶ እንደሆነ አቶ መሠረት በሪፖርታቸው ላይ አመልክተዋል፡፡

  በ2007 በጀት ዓመት ባንኩ 1.21 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ያገኘ ሲሆን፣ ይህም ከቀደመው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ19.2 በመቶ ወይም የ194.24 ሚሊዮን ብር ብልጫ አሳይቷል፡፡ ለገቢው መጨመር ከወለድ የተገኘው ገቢ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘ ቢሆንም ከአገልግሎት ክፍያ፣ ከኮሚሽንና ከሌሎች የገቢ ምንጮች የተገኘው ገንዘብም ለጠቅላላ ገቢው መጨመር የራሱ ሚና ነበረው ተብሏል፡፡

  በአንፃሩ ግን የባንኩ የ2007 በጀት ዓመት አጠቃላይ ወጪው በ25.9 በመቶ ጨምሮ 833 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህም ወጪ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ171.8 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳሳየ ሪፖርቱ ያመላክታል፡፡

  የባንኩ ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ ማደግን ተከትሎ ለአስቀማጮች የተከፈለው ወለድ፣ የሠራተኞች የደመወዝ ማስተካከያ መደረግ፣ የቤት ኪራይ መናር፣ የቢሮ መገልገያ ዕቃዎች ዋጋ መጨመርና በበጀት ዓመቱ የበርካታ ቅርንጫፎች መከፈት ለዚህ ለታየው የወጪ ጭማሪ ትልቅ ሚና ነበራቸው ተብሏል፡፡  

  በ2007 በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ የባንኩ ያልተጣራ አጠቃላይ ትርፉ 373.97 ሚሊዮን ብር እንደሆነ የሚያሳየው የባንኩ ሪፖርት፣ ይህ ትርፍ ከ2006 በጀት ዓመት ከተገኘው ጋር ዓመት ሲነፃፀር 22.5 ሚሊዮን ብር ወይም የ6.4 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

  ባንኩ ከአጠቃላይ ትርፉ ላይ የመንግሥት ግብርን ጨምሮ አስፈላጊ ቅናሾችን ካደረገ በኋላ 287.81 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ አግኝቷል ተብሏል፡፡ ከዚህ የተጣራ ትርፍ ላይ 71.95 ሚሊዮን ብር ለሕጋዊ መጠባበቂያና ለዳሬክተሮች ቦርድ አባላት የሚከፈለው ዓመታዊ ክፍያ 423 ሺሕ ብር ከተቀነሰ በኋላ፣ 215.43 ሚሊዮን ብር የባንኩ ባለአክሲዮኖች ባላቸው የተከፈለ የአክሲዮን ድርሻ መጠን እንዲከፋፈል የቀረበው ሐሳብ ከባለአክሲዮኖች ይሁንታ አግኝቷል፡፡

  ይህ የተጣራ ትርፍ ከቀዳሚው ዓመት የ12.85 ሚሊዮን ብር ብልጫ አሳይቷል፡፡ በዚህ መሠረት መቶ ብር ዋጋ ያለው አንድ አክሲዮን ያስገኘው ትርፍ 27.84 ብር ሆኗል፡፡ ይህ የትርፍ ክፍፍል ድርሻ ግን ከቀደሙት ዓመታት ያነሰ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

  በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የባንኩ አጠቃላይ ካፒታል 1.8 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ይህ አኃዝ ካለፈው ዓመት ከታየው ውጤት ጋር ሲነፃፀር የ281.6 ሚሊዮን ብር ወይም የ18.4 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በበጀት ዓመቱ የታየው የተከፈለ ካፒታል መጠንም ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ጊዜ ከነበረው የ196 ሚሊዮን ብር ወይም የ21.2 በመቶ በመጨመር ወደ 1.12 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የባንኩ ሕጋዊ መጠባበቂያ ካፒታል ደግሞ 19 በመቶ በማደግ ወደ 443 ሚሊዮን ብር ከፍ ብሏል፡፡

  በተጠናቀቀው የ2007 በጀት ዓመት የባንኩ አጠቃላይ ሀብት 13.67 ቢሊዮን ብር ደርሶልኛል ያለው አቢሲኒያ ባንክ፣ አጠቃላይ የሀብት መጠኔ የ21.2 ከመቶ ዕድገት አሳይቶኛል ብሏል፡፡

  ባንኩ የኢንተርኔትና የወኪል (ኤጀንት) ባንኪንግ አገልግሎቶችን እንደሚጀምር በዚሁ በዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔው ላይ ያሳወቀ ሲሆን፣ ሌሎች አዳዲስ አገልግሎቶችን እጀምራለሁም ብሏል፡፡

  ሪፖርቱ እንደተጠቀሰው በበጀት ዓመቱ ካጋጠሙ ተግዳሮቶች ውስጥ አንዱ በተለይ ከሰው ኃይል ጋር ተያይዞ ያለው ችግር ይጠቀሳል፡፡ አቶ መሠረት በቀረበው ሪፖርት ላይም፣ ‹‹ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በባንኩ ዘርፍ በተፈጠረው መነቃቃት የሰው ኃይል ፍላጎቱ በእጅጉ ጨምሯል፤›› ብለዋል፡፡ አዳዲስ ተመራቂዎችን መልምሎና አሠልጥኖ ለሥራ ከማብቃት ይልቅ በአሁን ጊዜ በባንኮች መካከል በሰፊው እየታየ ያለው የሰው ኃይል መነጣጠቅ ጐልቶ መታየቱንም ጠቅሰዋል፡፡ ባንኮች ቅርንጫፎቻቸውን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያስፋፉ መምጣታቸው ደግሞ መነጣጠቁ የበለጠ እንዲጠነክር ምክንያት እንደሆነም ሳያመለክቱ አላለፉም፡፡ ይህንን ክፍተት ለመድፈንም ባንካቸው የሠራተኞችን ፍልሰት ለመከላከል፣ ገበያውን ማዕከል ያደረገ የደመወዝ ማስተካከያና የጥቅማ ጥቅሞች ማሻሻያ ማድረጉን ጠቁመው፣ ወደፊትም ተጨባጭ ሁኔታዎችን እየፈተሽን ማሻሻያዎች ማድረጉን ይቀጥላል ብለዋል፡፡

  አቢሲኒያ ባንክ በ2007 በጀት ዓመት 32 አዳዲስ ቅርንጫፎችን የከፈተ ሲሆን፣ ይህም የባንኩን ቅርንጫፎች ቁጥር 132 አድርሶታል፡፡ እንደ ባንኩ መረጃ ከዚህም በኋላ ተጨማሪ ቅርንጫፎችን ይከፍታል ተብሏል፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ ባንኮች በመደበኛነት ሲከፍቷቸው ከነበሩ ቅርንጫፎች በተለየ ሁኔታ ንዑስ ቅርንጫፎችን ከፍተው ውስን አገልግሎቶችን መስጠት የሚችሉበትን አሠራር በመፍቀዱ፣ በዚሁ መሠረት ንዑስ ቅርንጫፎችን እከፍታለሁ ብሏል፡፡ በብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት ንዑስ ቅርንጫፎቹ በጊዜ ሒደት ወደ መደበኛ ቅርንጫፍነት የሚያድጉበት ሁኔታ ያለ ሲሆን፣ ይህንኑ መመርያ ታሳቢ ተደርጐ በዚህ በጀት ዓመት አንድ ኮርፖሬት ቅርንጫፍ፣ 20 መደበኛ ቅርንጫፎችና 32 ንዑሳን ቅርንጫፎችን በመክፈት የቅርንጫፎቹን ቁጥር ከ185 በላይ ለማድረስ ዕቅድ መያዙንም የቦርድ ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡   

      

   

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች