Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዝንቅ‹‹ማን ሃይ ይበለው››

  ‹‹ማን ሃይ ይበለው››

  ቀን:

  ቀድሞ በኢትዮጵያ ምድር እንደአሁኑ ተሽከርካሪ ባልነበረበት ወቅት ለከተማዋም ሆነ ለገጠሩ ሕዝብ በሰላምም ሆነ በጦርነት ወቅት የፈረስ አገልግሎት ከፍተኛ ነበር፡፡ በመሆኑም ባለቤቶቹ በጥንቃቄ ይዘው በቂ መኖ እየሰጡ በክብር ይገለገሉበት እንደነበርና አቅማቸው ሲደክምና አገልግሎታቸው ሲያከትም ደግሞ እቤት አውለው እየጠበቁ በሞቱ ጊዜ ባይለቀስላቸውም በወግ ይቀበሩ እንደነበር አዛውንቶች የሚያወሱት ነው፡፡

  የአገልግሎታቸው ዓይነት ተለውጦ፣ በየከተማው ለሰውና ለዕቃ ማጓጓዣ የሚሆኑ ጋሪዎች መጎተት ዓይነተኛ የዕለት ተዕለት ተግባራቸው ሆኗል፡፡

  እነዚህ ፈረሶች ያለ በቂ መኖ፣ ያለዕረፍትና ያለርኅራሔ ቢፈጥኑም ባይፈጥኑም በዱላ እየተነረቱ፣ በአለንጋ እየተሞሸለቁ፣ ለባለቤቶቹ የዕለት ተዕለት ገቢ ማስገኛ ሆነው ከቆዩ በኋላ፤ አቅማቸው ሲደክምና ዓይናቸው ማየት ሲሳነው፣ ጀርባቸውና ኮቴአቸው ቁስል በቁስል ሲሆንና የአገልግሎት ዘመናቸው ካከተመ በኋላ፣ ባለቤቱ ውለታውን ረስቶ አውጥቶ ለጅብ እራት ይጥላቸዋል፡፡ አንዱ የከነፈ መኪና ገድሎ እንዲያሳርፋቸውም በየአውራ ጎዳናው ላይ ይተዋቸዋል፡፡ ለምሳሌ (ከአያት አደባባይ እስከ ሚካኤል ቤተክርስትያን ባለው መንገድ ፎቶውን ይመልክቱ)፡፡

  ታዲያ እንደዚህ ሌት ተቀን መሀል መንገድ የቆሙትን ፈረሶች ሁሉም እያየ ሃይ ሳይላቸው አይቀሬውን ሞት ብቻቸውን ሳይሆን የሚቀበሉት፣ ያለ ፍጥነት ገደብ የሚከንፉ ባለታክሲዎች፣ ሲኖ ትራኮች ሕፃናትና አዛውንቶች የያዙ የቤት መኪናዎች ላይም አደጋ አድርሰው ነው፡፡ በሚከሰተው አደጋ ስንቱ ከቤቱ ወጥቶ እንደቀረ? አካለ ስንኩል እንደሆነ? ቤቱ ይቁጠረው፡፡ ይህ የዕለት ከዕለት ክስተት ነው፡፡ ለዚህ ተጠያቂው ማን ይሆን?

  ታክሲና ሲኖትራክ የሚያሳቅቁን አንሶ እንዲህ መሀል መንገድ ላይ ቆመው ውለው የሚያድሩትን ፈረሶች ‹‹አላየሁም፣ አልሰማሁምና አልናገርም›› ከማለት በዘለለ፣ ግንዛቤ እንዲሰጥና አውጥተው የሚጥሉም ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ይደረግልን፡፡

  በእንድርያስ መንገሻ ቆቱ

  ****************

  ርግብና ጥጃ

  ያባቴ አገር ጥጃ – ታስራ ‘ምትፈታ

  የናቴ አገር ርግብ – ክንፏ ያልበረታ

  (በመሳ – – – ለመሳ)

  ይች፣  ነጻነቷን አይታ፣

        ከጋጣ ወጥታ፣

        መርገጫዋን ስታ፣

        እግሯን የምትፈታ፡፡

        

  ያች፣   ሐርነቷን አምና

         ከጎጆ መንና

         ማረፊያዋን ስታ

         ክንፏን የምትፈታ፡፡

  (አምናለሁ!)

  ሁለቱም ያድጋሉ፤ በራሳቸው ፋና

  ወደ ጋጣ ከታች፣ ወደ ጎጆ መላሽ – አሳሪ ይጥፋና፡፡  

  • በአካል ንጉሴ፣ ፍላሎት፣ 2006 ዓ.ም.

  ****************

  ነፃ ምሳ የለም

  በአንድ ወቅት ይኖር የነበረ ንጉሥ አማካሪዎቹን ወደ ቤተ መንግሥቱ በማስጠራት፣ ለቀጣዩ ትውልድ ሊተላለፍ የሚችል ጥበብ አዘል መልዕክት እንዲጽፉለት አዘዘ፡፡

  አማካሪዎቹም ከበርካታ ቀናት ቆይታ በኋላ ንጉሡ ያዘዛቸውን ጥበብ አዘል መልዕክት በበርካታ ጥራዞች ጽፈው ቀረቡ፡፡ ንጉሡ ግን፣ “የጻፋችሁት በጣም የረዘመ ነው፡፡ ሕዝቡ ሊያነበው እንዲችል አሳጥራችሁ ጻፉት” አላቸው፡፡

  ከቀናት በኋላ የንጉሡ አማካሪዎች ቀጣዩን ትውልድ ያንጻል ያሉትን ጥበብ የያዘ አንድ ጥራዝ ይዘው ቀረቡ፡፡ ነገር ግን የንጉሡ ሐሳብ አልሞላም፡፡ አንዱ መጽሐፍ አጥሮ አንድ ምዕራፍ ሆነ፡፡ ይህም ቢሆን ለንጉሡ አጥሮ የቀረበ አልነበረም፡፡

  አንድ ገጽ እንኳን ቢሆን ለንጉሡ ረጅም እንደሆነ የተረዱት አማካሪዎቹ፤ በስተመጨረሻ ቀጣዩን ትውልድ የሚያንጽ ያሉትን ጥበብ አዘል መልዕክት በአንድ ዐረፍተ ነገር አዘጋጅተው ቀረቡ፡፡ ትውልዱን የሚጠቅመው መልዕክትም “ነፃ ምሳ የለም” የሚል ነበር፡፡ ይህም ማለት ያለአንዳች ልፋትና ድካም የሚገኝ ፍሬ ያለው ነገር የለም ለማለት እንደሆነ አማካሪዎቹ ያሰፈሩት ነጥብ ያስረዳል፡፡

  • አሸናፊ ደምሴ፣ የኢሕአዴግ የማርያም መንገድ፣ 2007 ዓ.ም.

  ****************

  ታዳጊው በስህተት ሙሉ ማራቶን ሮጠ

  በአሥራዎቹ ውስጥ የሚገኝ ታዳጊ የግማሽ ማራቶን ማብቂያውን ባለማወቅ ሙሉ ማራቶን ማለትም 26.2 ማይል (42 ኪሎ ሜትር) እንደሮጠ ወላጆቹን በመጥቀስ አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

  ታዳጊው ኢቫን ሜጉስ በሩጫው የተሳተፈው ትምህርት ቤቱን በመወከል ሲሆን፣ ቤተሰቦቹ ግማሽ ማራቶን (13.1 ማይል) ማብቂያ መስመር ላይ ቢጠብቁትም ሊያገኙት አልቻሉም፡፡ በነገሩ የተደናገጡት ወላጆችም የኢቫንን ፎቶግራፍ ለፖሊስ ሰጡ፡፡ ፖሊሶቹም ኢቫንን በሩጫ መስመሩ ላይ ያገኙት ሲሆን ማራቶኑን በመፈፀሙ በመጨረሻ አብረውት ፎቶግራፍ ተነስተዋል፡፡

  ****************

  ሞታለች የተባለችው ሴት ኢንተርኔት ቤት ተገኘች

  በምሥራቅ ቻይና የ14 ዓመት ታዳጊ እያለች ከቤተሰቦቿ ቤት የጠፋችው ዥኦ የን፣ ከአሥር ዓመት በኋላ በሌላ ከተማ ውስጥ በኢንተርኔት ጌም ሱስ ተጠምዳ፣ የአንድ ኢንተርኔት ቤት ኃይለኛ ተጠቃሚ ሆና መገኘቷን የቻይና ሞርኒንግ ፖስት ዘግቧል፡፡

  የ24 ዓመት ወጣት ሆና የተገኘችው የን፣ ፖሊስ ሲያገኛት ራሷን ቀይራ በሀሰተኛ መታወቂያ ስትንቀሳቀስ ነበር፡፡

  ወጣቷ ላለፉት አሥር ዓመታት ያገኘቻቸውን ትንንሽ ሥራዎች እየሰራች በኢንተርኔት ቤቱ ታድር እንደነበር ተዘግቧል፡፡ አብዛኛውን ጊዜዋን የምታሳልፍ የነበረው በኢንተርኔት ቤቱ ጌም በመጫወት ሲሆን፣ የካፌው ተጠቃሚዎች ገንዘብ እንደሚያዋጡላትም በዘገባው ተገልጿል፡፡

  ሀሰተኛ መታወቂያ ይዛ በመገኘቷ ወጣቷ መቶ ፓውንድ የተቀጣች ሲሆን፣ ከብዙ ማቅማማት በኋላ ቤተሰቦቿን ለማግኘት ተስማምታለች፡፡

  እናቷ ልጄ አንድ ቀን ልትደውል ትችላለች በሚል ተስፋ ላለፉት አሥር ዓመታት ስልኳን አለመቀየሯን ተናግራለች፡፡ የን ሕጻን ሳለች ትጮህባትና ትቆጣት እንደነበርም አምናለች፡፡

  ****************

  ስዊዘርላንድ ኒቃብ የለበሱ ሴቶችን እቀጣለሁ አለች

  የስዊዘርላንድ ቲቺኖ ክልል ኒቃብ ለብሰው ሕዝብ በሚንቀሳቀስበት ቦታ የሚታዩ ሴቶችን 6500 ፓውንድ እንደምትቀጣ ማሳወቋን የዘ ኢንዲፔንደንት ዘገባ ያመለክታል፡፡

  የክልሉ ፓርላማ ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው ሰኞ ኅዳር 13 ቀን 2008 ዓ.ም. ሲሆን፣ ከዚህ ውሳኔ የተደረሰው በአውሮፓ የሽብር ጥቃት ሥጋት ማየልን ተከትሎ ነው፡፡ ስለዚህም በጣሊያን ድንበር በምትገኘው የስዊዘርላንድ ግዛት ቲቺኖ፤ በሚገኙ ሬስቶራንቶች፣ የገበያ ማዕከሎችና መሰል ቦታዎች ላይ ኒቃብ መልበስ ወንጀል ሆኗል፡፡ ይህ ወንጀል የሚሆነው ለዜጎቹ ብቻም ሳይሆን ለቱሪስቶችም ጭምር መሆኑን ዘገባው ያሳያል፡፡ ሌሎች ዓይነት ፊት መሸፈኛዎችና ጭምብሎች ግን አልተከለከሉም፡፡

  ውሳኔውን ፓርላማው ሳያፀድቀው እ.ኤ.አ. 2013 ላይ፣ የክልሉ ኗሪዎች ጉዳዩን በሦስት አራተኛ ድምፅ እንደደገፉት የሮይተርስ ዘገባ ያሳያል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ኃይሎች ላይ ጥቃት አልፈጸምኩም አለ

  የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ...

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...