ሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ከተመሠረተ ጀምሮ የተለያዩ የምርምር ውጤቶችን በተለይ በግብርና ምርምሮቹ ይታወቃል፡፡ ይህን ዩኒቨርሲቲ በተጨማሪ በአሁኑ ሰዓት ደግሞ ባህል፣ በሕክምና፣ በሥርዓቱ፣ እየተሳተፈና ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ በቅርቡም ለስፖርቱ ዕድገት ትልቅ ችግር የሆነው የስፖርት አካዳሚ እጥረት ለማቃለል ከፍተኛ ወጪ በመመደብ አስገንብቷል፡፡ በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የውስጥና የውጪ የስፖርት ውድድር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የውጭ የስፖርት ውድድሮች ኃላፊና የስፖርት ሳይንስ መምህር አቶ አስቻለው አያሌው፣ የአካዳሚው ግንባታ የተጀመረው ከዛሬ 3 ዓመት በፊት እንደሆነና ወጪውም ሙሉ በሙሉ በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የተሸፈነ ሲሆን፣ ጠቅላላ ወጪውም እስከ አንድ ቢሊዮን ብር ሊደርስ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ደረጃውም አንድ ኢንተርናሽናል አካዳሚ ላይ ሊኖር የሚገባውን በሙሉ የያዘ እንደሆነ አክለዋል፡፡ ይህ ለአገሪቱ ተጨማሪ፣ ለምሥራቅ ኢትዮጵያ ደግሞ የልቀት ማዕከል፣ ለአካባቢውም እንዲሁም ለዩኒቨርሲቲው ትልቅ አገልግሎት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡ ግንባታው በአፍሮ ፂዮን ኮንስትራክሽን የተካሄደ ሲሆን፣ ስታዲየሙ ከአሥር ሺሕ በላይ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም እንዳለውና በዚህ ዓመት ተጠናቆ አገልግሎት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡ በአጠቃላይ አካዳሚው በ13,000 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ መሆኑን ጭምር ኃላፊው አስረድተዋል፡፡