Sunday, August 14, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  በደቡብ ክልል ድርቅ የመታት ማረቆ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ወ/ሮ አይሻ ጩሜሮ በደቡብ ክልል በጉራጌ ዞን፣ ማረቆ ወረዳ ነዋሪ ናቸው፡፡ የ10 ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ አይሻ ልጆቻቸው አባት አጠገባቸው ባይኖሩም ቤተሰቦቻቸውን በሚገባ እየመሩ የተሻለ ሕይወት ሲመሩ ቆይተዋል፡፡

  በማሳቸው የሚያመርቱት ምርት በአካባቢው ካሉ አርሶ አደሮች በተለይም ከሴት አርሶ አደሮች ይልቅ በጥሩ አምራችነት ስለሚያስመስባቸው አንቱ ከሚባሉት አንዷ ሆነው ይጠቀሳሉ፡፡ በሴት ጉልበታቸው ያመርቱ የነበረው ምርት ቤተሰቦቻቸውን ከማስተዳደር አልፎ ልጆቻቸው ራሳቸውን ችለው እንዲንቀሳቀሱ ደግፎ የተለያዩ የንግድ ሥራዎችን እንዲሠሩ አስችሏቸዋል፡፡ ልጆቻቸው ራሳቸውን ችለው እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግም በአካባቢው የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ጋሪዎችን ገዝተው መስጠታቸውን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ እንዲህ ያሉት ተጨማሪ የቢዝነስ ሥራዎች ባይሠሩ እንኳ የሚያመርቱት ምርት የሚያስገኘው ገቢ ቤተሰቦቻቸውን ለማስተዳደር አያንስም ነበር፡፡

  እንደ ወ/ሮ አይሻ ገለጻ በአንድ የመኸር የምርት ዘመን ከ80 ኩንታል በላይ የሚያመርቱ ስለመሆናቸው ይናገራሉ፡፡

  የበልግ ምርታቸው ከታከለበት ደግሞ የተትረፈረፈ ምርት ይኖራቸው ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን የቀደመው አምራችነታቸው ጠፍቷል፡፡ 80 ኩንታል ስንዴና በቆሎ ይጠብቁበት የነበረው ማሳቸው አሥር ኩንታል ያልሞላ ፍሬ ብቻ ተገኘበት፡፡ ይህ የሆነው ወይዘሮ አይሻ በመድከማቸው፣ እርሻቸውን በአግባቡ ባለመንከባከባቸው ሳይሆን እርሳቸው በሚኖሩበት ወረዳና በአጐራባች አካባቢዎች የተከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ አካባቢያቸውን በድርቅ እንዲመታ በማድረጉ ነው፡፡

  የተትረፈረፈ ምርት ያፍሱበት የነበረው ማሳቸው ዘንድሮ የተመኙትን ያህል ያለመስጠቱ እርሳቸውንና መሰሎቻቸውን ተፈታትኖ ‹‹ዕርዳታ ይሰጠን›› እንዲሉ አስገድዷቸዋል፡፡

  በ2007 የምርት ዘመን ለዘር፣ ለማዳበሪያና ለሌሎች የእርሻ ግብዓቶች ግዥ ከሚጠበቅባቸው ስድስት ሺሕ ብር ውስጥ ሦስት ሺሕ ብር ያወጡ ሲሆን፣ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ምርት ሲደርስ ምርቱን ሸጬ እከፍለዋለሁ ብለው በሙሉ ልብ በብድር  የወሰዱት ግብዓት ነበርና የሦስት ሺሕ ብር ዕዳ መግባታቸው አሳስቧቸዋል፡፡ ዘንድሮ የሚሰበሰቡት ምርት ይህንን ዕዳ ለመክፈል እንደማያስችላቸው በማመን ‹‹መንግሥት ይርዳኝ›› የሚል ቃል እንዲያወጡ አስገደዳቸው፡፡ መንግሥት ይርዳኝ የሚለውን ቃል ለማውጣት እልህ የገባቸው ወ/ሮ አይሻ፣ ‹‹የዘንድሮ ዕዳዬን ብቻ ይለፈኝ›› ብለው አከሉ፡፡

  ዕርዳታ የለመኑትም ተገደው መሆኑን የተናገሩት ወ/ሮ አይሻ፣ የተገኘው ምርት ተሸጦ ብድር መክፈል የሚያስችላቸው ቢሆንም 10 ልጆቻቸው መብላት አለባቸውና ያለኝ ሁሉ ሰጥቼ ምን ልሆን ነው የሚል ሥጋት ስለገባቸው ነው፡፡ የቀድሞ ጥንካሬያቸውም ታክሎበት ከሌሎች የተሻለ ጥሪት ያላቸው መሆኑ በጃቸው እንጂ በወረዳቸው በድርቁ ምርት የጠፋባቸውና ችግር ውስጥ ወድቀው የዕለተ ዕርዳታ እየተደረገላቸው ከሚገኙ ከስምንት ሺሕ በላይ ተረጂዎች ስም ዝርዝር ውስጥ አልገቡም፡፡ ይሁን እንጂ የዘሩት ስንዴና በቆሎ በመበላሸቱ ቀሪ ወራቶች አሳሳቢ እንዲሆንባቸው አድርጓል፡፡ ድርቁ ለሥራ ቆፍጣና የነበረው እጃቸውን ለዕርዳታ እንዲዘረጉ አስገድዷቸዋል፡፡ ‹‹አንድም ጊዜ ለዕርዳታ እጄን ዘርግቼ አላውቅም፤›› የሚሉት ወ/ሮ አይሻ አሁንም ዕርዳታ የጠየቅሁት ለዘንድሮ ብቻ ነው በማለት አጋጣሚውን ኮንነዋል፡፡ እንደ ወ/ሮ አይሻ ሁሉ ብዙ ጠንካራ አምራቾችን የተፈታተነ ክስተት ነው፡፡ ድርቅ በማረቆ ወረዳ ካሉ ነዋሪዎች 20 በመቶውን ወይም ከስምንት ሺሕ በላይ የሚሆኑትን የዕለት ዕርዳታ እንዲጠብቁ አድርጓቸዋል፡፡ በደቡብ ክልል የተከሰተው ድርቅ ከሌሎች ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ቢሆንም ማረቆን ጨምሮ በአጠቃላይ በክልሉ የድርቁ ሰለባ የሆኑ የዕለት ደራሽ ተረጂዎችን ቁጥር በመቶ ሺዎች አድርሷል፡፡ 

  የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ደሴ ዳልኬ እንደገለጹት፣ በክልሉ በ2007 ዓ.ም.   የበልግ ዝናብ እጥረት ባስከተለው ድርቅ በሐምሌ 2007 ዓ.ም. 278 ሺሕ ተጐጂዎች የዕለት ዕርዳታ ፈላጊ ሆነዋል፡፡

  በአሁኑ ወቅት የተረጂዎቹና የዕለት ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተብለው ተለይተው ዕርዳታ እየተሰጣቸው የሚገኙት ተረጂዎች ቁጥር ከ617 ሺሕ በላይ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

  የተከሰተውን የድርቅ ተፅዕኖ ለመቋቋም መንግሥት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉ የዘንድሮን ድርቅ የተለየ ሊያደርገው ይችላል ይላሉ፡፡ ከተዘራው ውስጥ 96 ሺሕ ሔክታሩ በከፍተኛ ደረጃ ተጐድቷል፡፡ ይህም የምግብ እጥረት አስከትሏል፡፡ የዘንድሮው ከመቼውም ጊዜ በላይ የባሰ ቢሆንም፣ ይህን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል አቅም በመገንባት ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ እየተሠራ እንደሆነ አቶ ደሴ ገልጸዋል፡፡

  ከድርቁ ጋር በተያያዘ በተፈጠረው ተፅዕኖ ሕፃናት ጤና ላይ ችግር እንዳይፈጠር ቤት ለቤት በደተደረገ ማጣራት ማገገሚያ እንዲቆዩ ተደርገው ከነበሩ ሕፃናት ውስጥ ግማሽ ያህሉ (4,700) ወደ ነበሩበት አቋም ለመመለስ ተችሏል፡፡ ይህ ቁጥርም ቢሆን ተሻሽሎ አሁን 200 ሕፃናት ብቻ በማገገሚያ ይገኛሉ ተብሏል፡፡

  የአየር ንብረት ለውጡ የሚያሳርፈውን ተፅዕኖ ለመቋቋም በቂ ዝግጅት መደረጉን የገለጹት አቶ ደሴ አሁንም የዕለት ደራሽ ፈላጊዎች እየተለዩ ዕርዳታ እየተሰጣቸው እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡

  በደቡብ ክልል ማረቆ ወረዳ የዕለት ዕርዳታ ለመቀበል ከተለዩት ነዋሪዎች ውስጥ አቶ ቁፌሮ ደለቦ፣ ኅዳር 16 ቀን 2007 ዓ.ም. የሚቀበሉት ዕርዳታ ለሦስተኛ ጊዜ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ በመኸርም በበልግም የዘሩት እህል የጠፋባቸው አቶ ቁፌሮ በእጃቸው የቀረ ምንም አልነበረምና ዕርዳታ ከሚከፋፈልበት መጋዘን በራፍ  ወረፋ እየጠበቁ ነው፡፡

  በቤተሰብ 15 ኪሎ ግራም እየታሰበ የሚሰፈረውን የስንዴ ዕርዳታ ለመቀበል ተራውን የሚጠባበቀው ሌላው የአካባቢው ነዋሪም የዘንድሮ ችግር የከፋ ነውና መንግሥት ትኩረት ሊሰጠን ይገባል ብሏል፡፡

  በአንዳንድ ኦሮሚያ ወረዳዎች እንደታየው በደቡብ ክልል ድርቅ በተጐዱ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ዕርዳታ እያስፈለገን ተረጂዎች ሰንጠረዥ ውስጥ አልተካተትንም ሲሉ ይደመጣል፡፡ የዕርዳታ እደላው አድሏዊነት መንግሥት ሊመለከት የሚገባው ጉዳይ ነው ይላሉ፡፡

  አቶ ደሴ ዳልኬም ሆኑ ሌሎች የዞንና የወረዳ አመራሮች ይህ ችግር እንዳይኖር እየተሠራ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ይሁን እንጂ ችግሩ የለም፣ አልተከሰተም ማለት   እንደማይችሉ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

  አቶ ደሴ ዳልኬ እንደሚሉት፣ ችግሩ በተለያየ መንገድ የሚታይ ቢሆንም ጭራሹኑ የለም አይባልም፡፡ ነገር ግን ቅድሚያ የሚሰጣቸው እየተለዩ ዕርዳታውን እንዲያገኙ በመደረጉ ድርቁ ያስከተለውን ችግር መቋቋም እየተቻለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ጉዳዩ በቀውስ አስወጋጅ ኮሚቴ እየታየ ዕርምጃ የሚወሰድበት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

    በቀጣይ ወቅት ያለውን ችግር ለመቅረፍና የተሻለ ሥራ ለመሥራት ከ600 ሺሕ ሔክታር በላይ በመስኖ ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አቶ ደሴ ገልጸዋል፡፡

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች