Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ኒያላ ኢንሹራንስ 101 ሚሊዮን ብር አተረፈ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  – ብርሃን ባንክ 138 ሚሊዮን ብር ማትረፉን ይፋ አደረገ

  ኒያላ ኢንሹራንስ እ.ኤ.አ. በ2014 በጀት ዓመት ከታክስ በፊት 101 ሚሊዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ፡፡

  ኩባንያው ያገኘው ትርፍ በ20 ዓመት ታሪኩ ከፍተኛው ትርፍ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ የኒያላ ኢንሹራንስ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ከማል መሐመድ ኅዳር 16 ቀን 2008 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ለኩባንያው ባለአክሲዮኖች ዓመታዊ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ ኒያላ ኢንሹራንስ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ያልተጣራ 101.6 ሚሊዮን ብር ማትረፉን አቶ ከማል በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል፡፡

  ኩባንያው በበጀት ዓመቱ 86.9 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን፣ ይህም ካለፈው በጀት ዓመት የ32 በመቶ ብልጫ እንዳሳየ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡ ኒያላ ኢንሹራንስ ያገኘው 101 ሚሊዮን ብር ትርፍ በግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ታሪክ ውስጥ ከፍተኛው ትርፍ መሆኑን ያወሱት አቶ ከማል፣ ኩባንያው ይህን ሊያሳካ የቻለው አዳዲስ ደንበኞች ለማፍራት የሚያስችሉ ዕርምጃዎች በመውሰዱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

  ኩባንያው ከሁሉም የኢንሹራንስ ዘርፎች 343.5 ሚሊዮን የዓረቦን ክፍያ መሰብሰቡና የ135.4 ሚሊዮን ብር የካሳ ጥያቄ መቅረቡ በሪፖርቱ ተዘርዝሯል፡፡

  የኒያላ ኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ያሬድ ሞላ ኩባንያቸው የአምስት ዓመት የቢዝነስ መርሐ ግብር ነድፎ መንቀሳቀስ በጀመረበት የመጀመሪያ ዓመት ጠንካራ የገንዘብ አቅም ለመፍጠር እንደቻለ ተናግረዋል፡፡

  የኩባንያው ጠቅላላ ሀብት ከ615 ሚሊዮን ብር ወደ 833.2 ሚሊዮን ብር እንዳደገና ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲወዳደር የ35 በመቶ ዕድገት እንዳሳየ ተገልጿል፡፡ የኩባንያው የተፈረመ ካፒታል ወደ 300 ሚሊዮን፣ የተከፈለ ካፒታል ደግሞ ወደ 168.5 ሚሊዮን ብር ማደጉም ተነግሯል፡፡

  በሌላ በኩል በአክሲዮን ድርሻ ልክ የሚገኝ ክፍያ ከ1,396 ብር ወደ 659 ብር አሽቆልቁሏል፡፡ አቶ ያሬድ በአክሲዮን ድርሻ ልክ የሚገኝ ክፍያ መጠን መቀነስ የኩባንያውን አፈጻጸም እንደማያሳይ ይከራከራሉ፡፡ ‹‹ኩባንያችን ትልልቅ ኢንቨስትመንት ለማድረግ የካፒታል መጠኑን በከፍተኛ መጠን በማሳደጉ፣ የአክሲዮን ክፍያ መጠን ሊቀንስ ችሏል፡፡ ይህ ጥሩ ማሳያ ሊሆን አይችልም፤›› ብለዋል፡፡

  በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ አገልግሎት ሽፋን መጠን በጣም አነስተኛ መሆኑን አቶ ያሬድ ተናግረዋል፡፡ ስለኢንሹራንስ አገልግሎት ጠቀሜታ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑ በአገሪቱ የኢንሹራንስ ሽፋን መጠን 0.6 በመቶ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በኬንያ የኢንሹራንስ ሽፋን 2.9 በመቶ፣ በደቡብ አፍሪካ ደግሞ 14 በመቶ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ የኢንሸራንስ ጠቀሜታ ለኅብረተሰቡ ማስተማር ተገቢ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በሌሎች አገሮች የሕይወት ኢንሹራንስ ለኢንሹራንስ ኩባንያዎች ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ የተናገሩት አቶ ያሬድ፣ በኢትዮጵያ የሕይወት ኢንሹራንስ ሽፋን እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡

  ኒያላ ኢንሹራንስ በማይክሮ ኢንሹራንስ የሰብልና እንስሳት የመድን ዋስትና በመስጠት ቀዳሚ ኩባንያ ሲሆን፣ ምንም እንኳ ዘርፉ አትራፊ ባይሆንም አገልግሎቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡ ኤልኒኖ ያስከተለው የአየር መዛባት ኒያላ ኢንሹራንስን በርካታ የካሳ ክፍያዎች እንዲከፍል አስገድዶታል፡፡ ‹‹በዚህ ወቅት ከአርሶ አደሩና ከአርብቶ አደሩ ጎን ለመቆም በመቻላችን ደስተኞች ነን፤›› ብለዋል፡፡

  ኒያላ በአዲስ አበባ አዲስ ዋና መሥሪያ ቤት ለመገንባት ማቀዱን አስታውቋል፡፡ ባለ18 ፎቅ ዘመናዊ ሕንፃ ቦሌ መንገድ ኦሎምፒያ አደባባይ አቅራቢያ ለመገንባት ዝግጅቱን በማጠናቀቅ ላይ ነው፡፡ በአዳማ ከተማ የሚኘውን የኩባንያውን ባለአንድ ፎቅ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አፍርሶ ዘመናዊ ሕንፃ ለመገንባት ታቅዷል፡፡

  ኒያላ በመቋቋም ላይ በሚገኘው የኢትዮጵያ የጠለፋ ዋስትና ኮርፖሬሽን ላይ የአምስት በመቶ አክሲዮን ድርሻ በ50 ሚሊዮን ብር ወጪ ገዝቷል፡፡ የጠለፋ ዋስትና ኮርፖሬሽን የሚቋቋመው በአንድ ቢሊዮን ብር ካፒታል ሲሆን፣ በብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት አንድ ባለአክሲዮን መግዛት የሚችለው የአክሲዮን ድርሻ ከአምስት በመቶ መዝለል የለበትም፡፡ በመሆኑም ኒያላ ብሔራዊ ባንክ የፈቀደለትን አምስት በመቶ በ50 ሚሊዮን ብር የገዛ ሲሆን፣ 25 ሚሊዮን ብር ቅድሚያ ክፍያ ሙሉ በሙሉ ከፍሏል፡፡

  የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ከተጋረጡበት ችግሮች መካከል ዋጋ ሰበራና የባለሙያ እጥረት በዋነኝነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ገበያው የሚመራው በአገልግሎት ጥራትና ቅልጥፍና ሳይሆን በዋጋ ላይ ያተኮረ በመሆኑ፣ የመድን ሽፋን አገልግሎት ክፍያ (የዓረቦን ሽያጭ) እያሽቆለቆለ መምጣቱንና ይህም አሳሳቢ እንደሆነ አቶ ያሬድ ጠቁመዋል፡፡

  የተሽከርካሪ መድን ዋስትና ዛሬም አክሳሪ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ የኒያላ ኢንሹራንስ ማርኬቲንግና ቢዝነስ ዲቭሎፕመንት ዋና መኮንን አቶ ተገኝ ማስረሻ፣ የተሽከርካሪ መድን ዋስትና ፈታኝ የሥራ ዘርፍ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ተሽከርካሪ መጠን 400,000 አካባቢ ቢሆንም በትራፊክ አደጋ ከቀዳሚ አገሮች ተርታ መሆናችን ይታወቃል፡፡ የተሽከርካሪ መድን ዋስትና የምንሰጠው ደስ ብሎን ሳይሆን ግዴታችን ስለሆነ ነው፤›› ያሉት አቶ ተገኝ፣ ኒያላ ኢንሹራንስ በትራፊክ ደኅንነት ዙሪያ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሰፊ ሥራ በመሥራት ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

  እ.ኤ.አ. ከ2014 እስከ 2015 ለኒያላ የ84.1 ሚሊዮን ብር የተሽከርካሪ የመድን ካሳ ጥያቄ የቀረበ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት 22.2 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በኢትዮጵያ 16 የግልና አንድ የመንግሥት ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ይገኛሉ፡፡ ከብሔራዊ ባንክ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፣ እ.ኤ.አ. በ2015 አጠቃላይ የዓረቦን ሽያጭ 5.6 ቢሊዮን ብር ነው፡፡

  የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው በእንጭጭ ዕድሜ ላይ እንደሚገኝ የሚገልጸው ብሔራዊ ባንክ፣ ዘርፉ ለአገሪቱ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ያለው አስተዋጽኦ ከአንድ በመቶ በታች እንደሆነ ይጠቁማል፡፡

  ኒያላ ኢንሹራንስ እ.ኤ.አ. 1996 የተቋቋመ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት 48 ባለአክሲዮኖችና 274 ሠራተኞች አሉት፡፡ የኩባንያው አጠቃላይ ሀብት 833.2 ሚሊዮን ሲደርስ 6.2 በመቶ የገበያ ድርሻ እንዳለው ይነገራል፡፡

  ይህ በዚህ እንዳለ ብርሃን ኢንተርናሽናል ባንክ አክሲዮን ማኅበር ኅዳር 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ባካሄደው 6ኛ መደበኛና 2ኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባዔ፣ እ.ኤ.አ. ሰኔ 30 ቀን 2015 በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የባንኩ አጠቃላይ ሀብት ካለፈው ዓመት የ48 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 4.17 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታውቋል፡፡ ባንኩ በበጀት ዓመቱ 138.5 ሚሊዮን ብር ትርፍ ያስመዘገበ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት የ13.9 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ 

  በካፒታል ረገድም ባንኩ ብሔራዊ ባንክ እ.ኤ.አ. እስከ ሰኔ 30 ቀን 2016 ባንኮች እንዲያሟሉ ያስቀመጠውን የ500 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል በማሟላት፣ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ የተከፈለ ካፒታሉን ወደ 573 ሚሊዮን ብር እንዳደረሰ ገልጿል፡፡

    ከተመሠረተ ስድስት ዓመት ያቆጠረው ብርሃን ባንክ፣ በበጀት ዓመቱ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ሲሠራ ከነበረበው ሥራ መካከል አንዱ ተደራሽነቱን የማስፋትና የተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ መሆኑን አስታውቆ፣ በዚህም 27 ተጨማሪ ቅርንጫፎችን በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በመክፈት በአጠቃላይ የቅርንጫፎቹን ቁጥር ወደ 72 ማደረሱን አስታውቋል፡፡ በሌላ በኩል የደንበኞቹን ቁጥር ለማሳደግ መሥራቱንና በበጀት ዓመቱ መጨረሻ የባንኩ አጠቃላይ የደንበኞች ቁጥርም 108,283 በመድረሱ፣ ካለፈው ዓመት አኳያ የ82.9 በመቶ ዕድገት እንደታየበት አስፍሯል፡፡ የባንኩ ሠራተኞች ቁጥርም 1,181 መድረሱ ታውቋል፡፡

  በአጠቃላይ ባንኩ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሚያገለግል ስትራቴጂካዊ ዕቅድ በመንደፍ ውጤታማ ለመሆን እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቆ፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት ለደንበኞቹ ለማዳረስ በቅርቡ በተለያዩ የገበያና የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት በካርድ ክፍያ መፈጸም የሚያስችሉ የሽያጭ ማዕከል ማሽኖችን ለመትከልና የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡  

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች