Monday, August 15, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናጠቅላይ ሚኒስትሩ የገቡትን ቃል ተግባር ላይ እንዲያውሉ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተገለጸ

  ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገቡትን ቃል ተግባር ላይ እንዲያውሉ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተገለጸ

  ቀን:

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በፓርላማ በተሰየሙበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ ለሕዝብ የገቡትን ቃል በተግባር እንዲያውሉ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተገለጸ፡፡  

  ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ሲሰየሙ በቀጥታ ሥርጭት በተላለፈው ንግግራቸው፣ በአገሪቱ ሥር ሰዶ የቆዩትን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ችግሮች ለመፍታት ቁርጠኛ እንደሆኑና በዚህም የአገሪቱ ሕዝብ ከጎናቸው እንዲቆም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግርም በርካታ ኢትዮጵያውያን መደሰታቸውን ሲናገሩ ተደምጧል፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉት ንግግርና የገቡት ቃል ተግባር ላይ እንዲውል፣ የአገሪቱ ሕዝብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡

  በሰሜን ሸዋ ዞን መሀል ሜዳ ከተማ በመምህርነት ሙያ የተሰማሩት አቶ ከበርኩ ታዬ፣ ‹‹በሕይወቴ እንደዚህ ያስደሰተኝ ንግግር ሰምቼ አላውቅም፤›› ብለዋል፡፡ አቶ ከበርኩ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያዊነትን በመስበክ በጎሳና በብሔር የተከፋፈለን ሕዝብ በአገራዊ ጉዳይ ላይ አንድ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችል ንግግር አድርገዋል፡፡ የገቡትን ቃል በተግባር እንዲያውሉ የአገሪቱ ሕዝብ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል፡፡

  ‹‹በሐሳብና በአመለካከት የአገሪቱ ሕዝብ እንዲግባባና በአገሪቱ ያንዣበበውን ችግር በጋራ እንድንታገል የሚያስችል ንግግር አንፀባርቀዋል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን ይህን ሐሳባቸውንና ራዕያቸውን በተግባር ፈጽመው ለሕዝቡ ማሳየት አለባቸው፡፡ ይህ ሲሆን ግን የአገሪቱ ሕዝብ ከጎናቸው ሳይለይ መሆን አለበት፤›› በማለት አክለዋል፡፡

  በቢሾፍቱ ከተማ በንግድ ሥራ ላይ የሚገኙት አቶ ሙሉነህ ግርማ በበኩላቸው የአቶ ከበርኩን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡ ‹‹የኢትዮጵያን ስም ከሃያ ጊዜ በላይ ጠርተዋል፡፡ ይህ በራሱ ልዩ ክስተት ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉት ንግግር እንከን የለሽ ቢሆንም ንግግራቸውን በተግባር አውለው ሕዝባቸውን ማስደሰት አለባቸው ሲሉ ጠቁመዋል፡፡ በአገሪቱ ተንሰራፍቶ የሚገኘው የብሔርተኝነትና የጎሰኝነት አስተሳሰብ ግን ትልቅ ፈተና ሊሆንባቸው እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ የአገሪቱ ወጣቶች የሚጠይቋቸውን የዴሞክራሲ፣ የኢኮኖሚና የፍትሕ ጥያቄዎች ጊዜ ሳይሰጡ ምላሽ መስጠት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡

  ይህን ሲያደርጉ ግን የአገሪቱ ሕዝብ ከጎናቸው ሊቆም እንደሚገባና ችግሩን በጋራ ለመፍታት ቁርጠኛ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

  በአዲስ አበባ አንድ የግል ትምህርት ቤት በማስተማር ሙያ ላይ ተሰማርተው የሚገኙት አቶ ጎይቶም ዘርዓይ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር በማድነቅ፣ ‹‹የአገሪቱን ችግሮች ጊዜ ሳይሰጡ መፍታት አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹በነፃነት ተንቀሳቅሶ መሥራትና ሀብት ማፍራት የሚቻልባት አገር ማድረግ ይጠይቃቸዋል፤›› ብለዋል፡፡ በተለይም ከህዳሴ ግድቡ ጋር ተያይዞ በግብፅና በኤርትራ መንግሥታት በኩል የሚታየውን የጥቅመኝነትና የቡድንተኝነት አባዜ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገር ውስጥ ያሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱና ዓላማቸውን ለሕዝቡ እንዲያስተዋውቁ ከማድረግ ባሻገር፣ በአገሪቱ ሥር ሰዶ የሚገኘውን የመልካም አስተዳደር፣ የሙስናና የፍትሕ ችግር ለመፍታትም ቁርጠኛ መሆናቸው መልካም ነው ብለዋል፡፡ ከዓመት ዓመት እየተንከባለለና ብዙ ችግር እያስከተለ ያለውን የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥታት የፖለቲካ ልዩነትን ለመፍታት መንግሥታቸው ዝግጁ እንደሆነ አክለው ገልጸዋል፡፡

  በአፋር ክልል ዋና ከተማ ሰመራ የሚኖሩት አቶ አቡበከር አደም በኢትዮጵያና በኤርትራ መንግሥታት መካከል ያለውን የፖለቲካ ልዩነት ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸውን ጠቃሚ ነገር ብለውታል፡፡ ነገር ግን ብዙ ወጣቶች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ ጥያቄ እያቀረቡና በዚህ ላይ ያላቸውን አቋም አለማንፀባረቃቸው ቅር እንዳሰኛቸው ተናግረዋል፡፡

  የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር እንዳስደሰታቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን ሲናገሩ የተደመጠ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ አልፎም የተለያዩ አገሮች መሪዎች የደስታ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ደስታቸውን ከገለጹ አገሮች መካከል ኬንያ፣ ሱዳን፣ ሶማሌላንድ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ቱርክ፣ አሜሪካና የሌሎች አገሮች መሪዎች ይገኙበታል፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር በርካታ ኢትዮጵያውያን መደሰታቸውን እየተናገሩ ቢገኝም፣ የገቡትን ቃል ያሳካሉ? ወይስ አያሳኩም? ማለት ብቻ ሳይሆን  በተቻለ መጠን ድጋፍ ማድረግ ይገባል እያሉ ነው፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...