Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ለአርሶ አደሮች የሚቀርበው ማዳበሪያ ላይ የዋጋ ጭማሪ ተደረገ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  በዓለም አቀፍ ገበያ ከዩሪያ በስተቀር በሌሎች የማዳበሪያ ዓይነቶች ላይ  የዋጋ ጭማሪ ባይደረግም፣ ብር ከዶላር ጋር ያለው ምጣኔ በ15 በመቶ እንዲቀንሰ በመደረጉ ምክንያት ለአርሶ አደሮች በሚቀርበው ማዳበሪያ ዋጋ ላይ ጭማሪ ተደረገ፡፡

  ለ2010/2011 ምርት ዘመን መንግሥት ከአንድ ሚሊዮን ቶን በላይ አምስት ዓይነት ማዳበሪያዎችን ጨረታ አውጥቶ ግዥ ፈጽሟል፡፡

  ማዳበሪያዎቹ ኤንፒኤስ፣ ኤንፒኤስ ቦሮን፣ ኤንፒኤስ ዚንክና ኤንፒኤስ ዚንክ ቦሮን ናቸው፡፡ አንዱ ደግሞ በኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ዘንድ የሚታወቀው ዩሪያ ነው፡፡ የአራቱ ማዳበሪያዎች የዓለም አቀፍ ገበያ ዋጋ ከአምናው ምርት ዘመን ጋር ተመሳሳይ ቢሆንም፣ በዩሪያ ማዳበሪያ ላይ ግን ጭማሪ ታይቷል፡፡

  የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የግብርና ግብዓቶች ግብይት ዳይሬክተር አቶ ሰይፉ አሰፋ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ 550 ሺሕ ቶን ዩሪያ ማዳበሪያ ለመግዛት ዕቅድ ተይዞ ነበር፡፡ ነገር ግን በዓለም አቀፍ ገበያ የዋጋ ጭማሪ በመደረጉ፣ ሦስት ጊዜ ጨረታ ቢወጣም መግዛት አልተቻለም፡፡

  ‹‹ዩሪያ ማዳበሪያ የግድ መግዛት ስለሚያስፈልግ አምራቾችን በቀጥታ በማግኘት 500 ሺሕ ቶን ተገዝቷል፤›› ሲሉ አቶ ሰይፉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ባለፈው ዓመት የአንድ ቶን ዩሪያ ማዳበሪያ ዋጋ 257 ዶላር ነበር፡፡ በዚህ ዓመት ግን የአንድ ቶን ዋጋ 320 ዶላር ሆኗል፡፡

  ዩሪያ ማዳበሪያ ባለፈው ዓመት በኩንታል ከአንድ ሺሕ ብር በታች በሆነ ዋጋ ለአርሶ አደሩ የቀረበ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት ብር ከዶላር ጋር ያለው ምጣኔ በ15 በመቶ እንዲቀንስ በመደረጉ ምክንያት የአንድ ኩንታል ዩሪያ ማዳበሪያ የመሸጫ ዋጋ 1,150 ብር መግባቱ ተመልክቷል፡፡

  የኤንፒኤስ ማዳበሪያ ዓይነቶችም እንዲሁ በዓለም ገበያ ላይ የዋጋ ጭማሪ ባይደረግባቸውም፣ የብር የመግዛት አቅም በመዳከሙ ምክንያት የመሸጫ ዋጋቸው ላይ ጭማሪ ተደርጓል፡፡

  ባለፈው ዓመት የኤንፒኤስ ማዳበሪያ የአንድ ኩንታል ዋጋ ከአንድ ሺሕ ብር በታች ቢሆንም፣ ሩቅ በሚባለው ሁመራ 1,200 ብር ሲገባ ቅርብ በሚባለው አዳማ ደግሞ 1,050 ብር በኩንታል ተሸጧል፡፡

  የኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ የማዳበሪያ ፍላጎት በዓይነትም በመጠንም ጨምሯል፡፡ በ2008/2009 ምርት ዘመን ስምንት ሚሊዮን ኩንታል የተጠቀመው የግብርና ዘርፍ፣ በ2009/2010 ዓ.ም. ምርት ዘመን ደግሞ 13 ሚሊዮን ኩንታል አስፈልጎታል፡፡

  በቅርቡ ከሪፖርተር ጋር ቆይታ ያደረጉት የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትሩ ኢያሱ አብርሃ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ባለፈው ምርት ዘመን 13 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለመግዛት 400 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተዳርጓል፡፡ በዚህ ዓመት የሚያስፈልገውን 15 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለመግዛት 600 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ይደረጋል ብለው ነበር፡፡

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች