Monday, August 8, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናበኦሮሚያ የተከሰተው ተቋውሞ የሦስት ሰዎችን ሕይወት ቀጠፈ

  በኦሮሚያ የተከሰተው ተቋውሞ የሦስት ሰዎችን ሕይወት ቀጠፈ

  ቀን:

  – በጎንደር ማረሚያ ቤት ቃጠሎም የ17 ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል

  የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን ላይ በተነሳው ተቃውሞ፣ በኦሮሚያ ክልል ያሉ ዩኒቨርሲቲዎችና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመጋጨታቸው የሦስት ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፡፡ መንግሥት የሟቾች ቁጥር ሦስት መሆኑንም አረጋግጧል፡፡ በሰሜን ጎንደር ዞን ማረሚያ ቤቶች መምርያ የደረሰው የእሳት አደጋ ለ17 ሰዎች መሞት ምክንያት መሆኑም ታውቋል፡፡

  ከሁለት ሳምንት በፊት በተቀሰቀሰውና የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን ላይ ተቃውሞ ለማቅረብ ተነሳ በተባለው ግጭት፣ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞንና በምዕራብ ወለጋ ጨሊያ ለሦስት ሰዎች ሕይወት መጥፋት መንስዔ  ሆኗል፡፡

  ድርጊቱ የፀረ ሰላም ኃይሎች እንደሆነ መንግሥት ያስታወቀ ሲሆን፣ በሌሎች ዘገባዎች ድምፃቸውን ያሰሙ ግን ማስተር ፕላኑ ያስከትለዋል ያሉትን ውጤት በመቃወም በተማሪዎችና በነዋሪዎች የተነሳ የመብት ጥያቄ ነው ብለውታል፡፡ ማስተር ፕላኑ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ አርሶ አደሮችን የሚያፈናቅል በመሆኑ፣ ተግባራዊ እንዳይሆን በክልሉ የተለያዩ ሥፍራዎች ተቃውሞ መነሳቱን ያስረዳሉ፡፡

  ተቋውሟቸውን በተለያዩ ከተሞች ለማብረድ የተሰማራው የመንግሥት የፀጥታ ኃይል ያልተመጣጠነ ኃይል በመጠቀም የመብት ጥሰት እንደፈጸመ እነዚሁ ወገኖች አመልክተዋል፡፡ በሒደቱም የተጎዱና ለእስር የተዳረጉ የተቃውሞው ተሳታፊዎች ቁጥር በርካታ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በተለይ የመማር ማስተማር ሒደቱ መስተጓጎልና እስካሁንም ሙሉ በሙሉ እንዳልቀጠለ ተጠቁሟል፡፡

  ማስተር ፕላኑ የኦሮሚያን ራስን በራስ የማስተዳደርና ማንነትን ጠብቆ የመቆየት ሕገ መንግሥታዊ መብት የሚፃረርና የኦሮሞ ሕዝብ ከመሬቱ ያለውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትም ለሌሎች አሳልፎ የሚሰጥ ነው ተብሎ ባለፉት ሁለት ዓመታት ተቃውሞ ሲቀርብበት ነበር፡፡ የክልሉ መንግሥት ግን ይህን የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ግጭትና ብጥብጥ እንዲነሳ ያደረጉት ፀረ ሰላም ኃይሎች እንደሆኑ የገለጸ ሲሆን፣ ማስተር ፕላኑ ኦሮሚያን ከማዘመን ባሻገር የፌዴራል ሥርዓቱን የማሻሻልም ሆነ የኦሮሚያ ገበሬዎችን በማፈናቀል የሚቆረስ መሬት እንደሌለ አስታውቋል፡፡ በሒደቱ የመንግሥትና የግለሰቦች ንብረት እንደወደመም አመልክቷል፡፡

  የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ኢብራሂም ሐጂ በሰጡት መግለጫ፣ በፀረ ሰላም ኃይሎች ግፊት በተፈጠረው ግርግር በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል ብለዋል፡፡ ድርጊቱም እየተጣራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለተፈጠሩት ረብሻዎች ተጠያቂ የሚሆኑ ግለሰቦች ለሕግ እንዲቀርቡ ፖሊስ እየሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ፖሊስ ከረብሻው ጋር ግንኙነት አላቸው ያሉ ግለሰቦቹን በቁጥጥር ሥር ማዋሉ ታውቋል፡፡

  የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ፣ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላን ፀድቆ ሥራ ላይ እንዳይውል ጠይቋል፡፡ ማስተር ፕላኑ የሚፀድቅ ከሆነ ሰላማዊ ሠልፍ እንደሚጠራም አስታውቋል፡፡

  በሌላ በኩል በሰሜን ጎንደር ዞን ማረሚያ ቤቶች መምሪያ ኅዳር 12 ቀን 2008 ዓ.ም. በደረሰ የእሳት አደጋ የ17 ታሳሪዎች ሕይወት ማለፉ ታውቋል፡፡ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ በአደጋው ወቅት በተፈጠረ ጭንቅንቅና ግርግር ተረጋግጠው 16 ሰዎች ሕይወታቸው እንዳለፈና አንድ ታራሚ ደግሞ ሊያመልጥ ሲሞክር በተወሰደ ዕርምጃ በጥይት ሕይወቱ እንዳለፈ ገልጿል፡፡ በአደጋው የሞቱትና በጥይት ዕርምጃ የተወሰደባቸው ግለሰቦች ቁጥር በመንግሥት ከተገለጸው ላቅ ያለ እንደሆነ የሚናገሩ አሉ፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የአገሪቱ ባንኮች ካፒታል 199.1 ቢሊዮን ብር ደረሰ

  ከታክስ በኋላ 50 ቢሊዮን ብር ማትረፋቸውን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ የአገሪቱ...

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...