- አቶ ከተማ ከበደ የባንክ ሥራ ተክተው አለመሥራታቸውን ጠቅላይ ፍርድ ቤት አረጋገጠ
ኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከስድስት ዓመታት በፊት ጀምሮ፣ በጣና ሐይቅ ላይ የተንሰራፋውንና በርካታ ኢትዮጵያውያን ለማጥፋት እየተረባረቡ የሚገኙትን እምቦጭ አረም፣ ሙሉ በሙሉ እንዲወገድ የ20 ሚሊዮን ብር ዕርዳታ ሰጠ፡፡
በፌዴራል ማረሚያ ቤቶቸ አስተዳደር በቃሊቲ ማረሚያ ቤት በእስር ላይ የሚገኙት የኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከፍተኛ ባለድርሻና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ከተማ ከበደ፣ ዕርዳታውን ያደረጉት በወኪላቸውና በማኅበሩ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ በአቶ ቦጋለ ማሞ አማካይነት ነው፡፡ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ አቶ ከተማ ዕርዳታውን ያደረጉት በሁለት መንገድ ነው፡፡ በጥሬ ገንዘብና ማሽን በመግዛት፡፡ ስጦታው የተበረከተው ማክሰኞ መጋቢት 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ለአማራ ክልል መንግሥት የአካባቢና ደን ጥበቃ ዋና ዳይሬክተር በላይነህ አየለ (ዶ/ር) ሲሆን ነው፡፡ በጥሬ ገንዘብ 15 ሚሊዮን ብርና አምስት ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ማሽን መሆኑን አቶ ቦጋለ ተናግረዋል፡፡
አቶ ከተማ ‹‹የእኔና የድርጅቴ መኖር ደስ የሚለውና ውጤታማ የሚሆነው ከአገሬ ጋር ነው፤›› በማለት፣ ከታሰሩበት ማረሚያ ቤት ሆነው ዕርዳታው እንዲደርስላቸው በላኩት መልዕክት መሠረት ተግባራዊ መሆኑንም አክለዋል፡፡ እንደ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፣ በጥሬ ገንዘብ የተሰጠው አሥር ሚሊዮን ብር ዕርዳታ ሰባት የአረም ማስወገጃ ማሽን ሊገዛ ይችላል፡፡
የአማራ ክልል አካባቢና ደን ጥበቃ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር በላይነህ አየለ ዕርዳታውን አስመልክቶ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ አንድ ማሽን ተገዝቶ አረሙን የማስወገድ ሥራ ተጀምሯል፡፡ ነገር ግን ማሽኑ አረሙን ከሰበሰበ በኋላ ወደ ውጭ መጣል ስለሚያስፈልግ፣ ይኼንን ችግርና በአጠቃላይ እምቦጭ አረምን ለማስወገድ፣ የኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለቤት ያደረጉት ዕርዳታ ጥሩ ቁመና ላይ እንደሚያደርሳቸው አስረድተዋል፡፡ ከማሽን ጋር በተያያዘ የነበረውን ችግር ሥር ነቀል በሆነ መንገድ እንደሚፈታላቸውም አክለዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መድቦ ወደ ጣና ሐይቅ የሚያስገባውን መንገድ እየገነባ መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተር አቶ ከተማ በለገሱት ገንዘብ የሚገዙት ማሽኖችም ሆኑ ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ገዝቶ በዕርዳታ የሰጠውን ማሽን፣ ወደ ሐይቁ ለማስገባት ሥራውን በማጣደፍ ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
እስካሁን በሌሎች ግለሰቦችና ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ከገዛው ማሽን ጋር ሦስት ማሽኖች መናገራቸውን ጠቁመው፣ ለቀሪ ማሽኖች መግዣ የሚሆን በቂ ገንዘብ ከኬኬ ማግኘታቸውን በድጋሚ ገልጸዋል፡፡ የሚያስፈልጋቸው ለሥራ ማስኬጃና ለተለያዩ ጉዳዮች ብቻ በመሆኑ፣ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንና ሌሎች ያገባናል የሚሉ አካላት የተጀመረውን ጥረት ከዳር እንዲያደርሱ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በሌላ በኩል አቶ ከተማ ከበደ ዓቃቤ ሕግ መሥርቶባቸው የነበረውን ‹‹የባንክ ሥራ ተክቶ መሥራት ወንጀል›› የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሰጠው ብይን ‹‹ገንዘብ ማበደር የባንክ ሥራን ተክቶ ሠርቷል አያስብልም›› ብሎ በነፃ ማሰናበቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በብይኑ ያልተደሰተው ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚው ችሎት አቤቱታውን አቅርቦ ‹‹ያስቀርባል›› የተባለ ቢሆንም፣ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የሥር ፍርድ ቤትን ብይን ከመረመረ በኋላ፣ የሥር ፍርድ ቤት ብይን ‹‹የሚነቅፍ አይደለም›› በማለት የሥር ፍርድ ቤት ብይን አፅንቶታል፡፡