- እንኳን አደረስዎት ክቡር ሚኒስትር?
- ምን እንኳን አደረሰህ ትለኛለህ?
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- እኔ መደወል ነበረብኝ?
- አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
- በጣም የባህሪ ለውጥ እያመጣህ ነው፡፡
- ምን አደረኩ ደግሞ?
- በፊት በዓል ከመድረሱ በፊት ትደውል ነበር፡፡
- አሁንስ መደወሌ መቼ ይቀራል ብለው ነው?
- እሱ ብቻ ሳይሆን ስንትና ስንት ስጦታ ነበር የምታዥጎደጉደው፡፡
- ልክ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ቤቴን እኮ የዶሮ ማርቢያ ነበር የምታደርገው፡፡
- በፊት ነበራ፡፡
- ምን እሱ ብቻ ለበዓል እኮ ቤቴ የበግ ማርቢያ ነበር የሚመስለው፡፡
- ምን ይደረግ ብለው ነው?
- ከዚያም አልፎ ቤቴ ቄራ እስኪመስል የበሬና የበግ ማቆያ ነበር የሚመስለው፡፡
- አውቃለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እነዚያ በሬዎች ዝም ብለው በዓይኔ እየተዘዋወሩ ነው፡፡
- ልክ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በዚህኛው በዓል ግን የታሉ?
- አሁንማ ብዙ ነገር ተቀይሯል፡፡
- ምንድነው የተቀየረው?
- ያው አሁን ጊዜው መቀየሩን ያውቃሉ፡፡
- ምን አንተም እንደ ሌሎቹ ዶላር ምናምን ጨመረ ልትለኝ እንዳይሆን?
- እሱም እንዳለ ሆኖ ሌሎችም ለውጦች አሉ፡፡
- መቼም የዋጋ ግሽበቱ እንዳትለኝ?
- ከእነዚህ በላይ በጣም የተለወጠ ነገር አለ፡፡
- ምንድነው የተለወጠው ነገር?
- ይኸው እናንተ ራሳችሁ ጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ አይደላችሁ እንዴ?
- ሰውዬ ምንም የተለወጠ ነገር የለም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ጥልቅ ተሃድሶውስ?
- እሱ ለሚዲያ ጥቅም ነው፡፡
- እኔ ግን ፓርቲያችሁ እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ ለውጦች ያሉ እየመሰለኝ ነው፡፡
- አትሸወድ ምንም ለውጥ የለም፡፡
- እኔ ግን እውነተኛ ተሃድሶ ውስጥ ገብቼ አቁሜያለሁ፡፡
- ምንድነው ያቆምከው?
- እርስዎን መቀለብ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ተናደው ከሚስታቸው ጋር እያወሩ ነው]
- ስሚ ያ ሰውዬ ምን እንዳለኝ ታውቂያለሽ?
- የቱ ሰውዬ?
- ቤታችን እንደ ከብት ማደለቢያ በየበዓሉ የሚያጨናንቀው ነዋ፡፡
- ምነው ጠፋ ግን?
- ኧረ የሚገርም ሰው ሆኗል፡፡
- ባይገርምህ ሰሞኑን ይመጣል ብዬ እየጠበቅኩት ነው፡፡
- ሰውዬው ባክሽ የልብ ልብ ተሰምቶታል፡፡
- ምን አደረገህ?
- ይኸው በዚህኛው በዓል ምንም የለም፡፡
- ምንም ነገር አያመጣም እያልከኝ ነው?
- ምንም የለም ስልሽ፡፡
- እየቀለድክ መሆን አለበት፡፡
- እውነቴን ነው ሁሉም ፊታቸውን አዙረውብኛል፡፡
- ስማ ቤተሰባችን እኮ ብዙ የለመደ ስለሆነ ሁሉንም ማድረግ አለብን፡፡
- ምን እያልሽ ነው?
- ዶሮውም፣ በጉም፣ በሬውም መገዛት አለበት፡፡
- እንደዚያ ከሆነ ምን ያህል እንደምትፈልጊ ንገሪኝ?
- እንግዲህ ዶሮ 500 ብር ነው ብለዋል፡፡
- ዶሮ 500 ብር?
- አዎን፣ በግ ደግሞ አምስት ሺሕ ብር ነው፡፡
- ለበግ አምስት ሺሕ?
- አዎን፣ በሬ ደግሞ ጥሩ ሠንጋ 50 ሺሕ ብር ነው፡፡
- ምን?
- በአጠቃላይ ለበዓሉ 60 ሺሕ ብር መድብልኝ፡፡
- ከየት አመጣዋለሁ ብለሽ ነው?
- ይኼን ሁሉ ቤትና ሕንፃ እያከራየህ ከየት አመጣዋለሁ ትላለህ?
- ለማንኛውም 60 ሺውን ከየት እንደማመጣው አውቃለሁ፡፡
- ከየት ልታመጣው?
- መንግሥት ደመወዜን ከፍ እንዲያደርገው እጠይቃለሁ፡፡
- ስንት?
- 60 ሺሕ!
[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ ቢሯቸው ገባች]
- እንግዳ አለ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ቀጠሮ የለኝም እኮ?
- ቀጠሮ ያልያዘ እንግዳ ነው፡፡
- ታዲያ ያለቀጠሮ ለምን አናግረዋለሁ?
- አንገብጋቢ ጉዳይ ነው ብሎኝ ነው፡፡
- እሺ አስገቢው፡፡
[እንግዳው ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ገባ]
- ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር?
- ጤና ይስጥልኝ፡፡
- ምን እየተሠራ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- አልገባኝም?
- እንዴት ነው ያን የመሰለ ተቋም የሚዘጋው?
- የቱ ተቋም?
- ያኔ ስታወሩ እኮ ዝም ብላችሁ ሕዝቡን ለማስደሰት መስሎኝ ነበር፡፡
- ስለምንድነው የምታወራው?
- ስለማዕከላዊ ነዋ፡፡
- እኛ ለሕዝቡ የገባነውን ቃል አናጥፍም፡፡
- እናንተ ስለሕዝብ ብቻ ነው እንዴ የምታስቡት?
- ድሮ ስለማን እናስብ?
- እኛም እኮ የሕዝቡ አካል ነን፡፡
- እናንተ ማን ናችሁ?
- እኛ ማዕከላዊ ያለን ገራፊዎች ነና፡፡
- ገራፊ ነህ እንዴ?
- ክቡር ሚኒስትር ገራፊ ቢልዎት ዝም ብሎ ዓይነት ገራፊ እንዳልመስልዎት?
- እንዴት?
- የስንቱን እግር መሰልዎት ሽባ ያደረግኩት፡፡
- እ. . .
- የበርካቶችንም ጥፍር ነቅያለሁ፡፡
- ምን አልከኝ?
- ለማንኛውም እኔ ከዓመት ዓመት ኮከብ ገራፊ ተብዬ ዋንጫ የምወስድ ነኝ፡፡
- ይገርማል፡፡
- ከዚያም አልፎ በተለያዩ አገሮች እየተዘዋወርኩ ዓለም አቀፍ ልምዶችን የቀሰምኩ ገራፊ ነኝ፡፡
- ሰውዬ ምን እያወራህ እንደሆነ ታውቃለህ?
- ክቡር ሚኒስትር እኔ ለሥርዓቱ ታማኝ የሆንኩ ጭፍን ደጋፊ ነኝ፡፡
- አሁን ምን ይደረግልኝ ነው የምትለው?
- ተቋሙ ከተዘጋ እኛን እኮ አውላላ ሜዳ ላይ ልንወድቅ ነው፡፡
- ስማ ወቅቱ የፍቅርና የምሕረት ዘመን ነው፡፡
- እና እኛ ገራፊዎች ሜዳ ላይ እንውደቅ?
- ታዲያ እኔ ምን ላድርግህ?
- መፍትሔ እንዲሰጡኝ ነዋ፡፡
- ምን ዓይነት መፍትሔ?
- ለዘመናት የሠራሁበት የሥራ ልምድ መና ሊቀር ነው፡፡
- እ. . .
- ሜዳ ላይ ልወድቅ ነው፡፡
- ሥራ ነው የምትፈልገው አይደል?
- በሚገባ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በመጀመርያ ከጓደኞችህ ጋር ተደራጁ፡፡
- ከዚያስ?
- ከገራፊነት የሥራ መደብ ወደ ሌላ ትቀየራላችሁ፡፡
- ወደ ምንነት?
- ወደ ዘላፊነት!
[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ደላላ ወዳጃቸው ይደውልላቸዋል]
- ክቡር ሚኒስትር ከሰዎች ጋር ሳወራ እኮ አንድ የቢዝነስ ሐሳብ መጥቶልኝ ነው፡፡
- የምን የቢዝነስ ሐሳብ ነው?
- ክቡር ሚኒስትር እርስዎ ከአንድ አይሉ ሁለት ሦስት ቤቶች በከተማችን ወሳኝ ቦታዎች ላይ አሉዎት፡፡
- ሕንፃ ፈልገህ ነው?
- ኧረ ኤምባሲና የውጭ ድርጅቶች ኃላፊዎች የሚከራዩት ቤት ነው እንጂ?
- እንዲያውም በቅርብ ኮንትራቱ የሚያልቅ ትልቅ ቤት አለኝ፡፡
- አጋጣሚው ይገርማል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የምን አጋጣሚ ነው?
- ይኸው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤት እስኪሠራላቸው ድረስ ትልቅ ቤት መከራየታቸው አይቀርም፡፡
- እሱማ እውነት ነው፡፡
- ታዲያ የእርስዎን ቤት ለምን አያከራዩትም?
- እሳቸው የእኔን ቤት ላይወዱት ይችላሉዋ?
- ሙሉ ለሙሉ ቤቱን መቀየር እንችላለን፡፡
- እንዴት?
- ከሴራሚክ ጀምሮ፣ በሩን ቢሉ ሁሉን ነገር መቀየር እንችላለን፡፡
- እሱ ጥሩ ሐሳብ ነው፡፡
- ፈርኒቸሩን ከራስዎ ድርጅት መቀየር እንችላለን፡፡
- የምታወራው ነገር ጥሩ ይመስላል፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ይኼ አጋጣሚ እንዳያመልጠን?
- ምን እናድርግ?
- ቤቱ ያለበት ቦታ ተፈላጊ ስለሆነ በጥሩ ዋጋ ማከራየት እንችላለን፡፡
- እሱማ ግልጽ ነው፡፡
- እኔ አደራ የምልዎት ኮሚሽኔን ነው፡፡
- እሱ ችግር የለውም፡፡
- በቃ እኔ የማውቃቸው ሰዎች ዘንድ ወሬውን አስወራለሁ፣ የእርስዎ ቤት መሆኑ ግን መታወቅ የለበትም፡፡
- እሱ ላይ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡
- ስለእሱ አያስቡ፡፡
- ሌላ የሚያሳስበኝ ነገር አለ፡፡
- ምንድነው?
- እኔ የማከራየው በምን እንደሆነ ታውቃለህ?
- በምንድነው?
- በዶላር!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከሌላ ሚኒስትር ጋር እያወሩ ነው]
- ክቡር ሚኒስትር እንኳን አደረሰዎት፡፡
- እንኳን አብሮ አደረሰን፡፡
- ሰሞኑን ብደውል ብደውል ጠፉ፡፡
- ያው መንግሥታችን አዲስ የያዘውን የዕርቅና የሰላም አቅጣጫ በመከተል ከሕዝቡ ጋር እየሠራሁ ነው፡፡
- ማን አዘዝዎት ክቡር ሚኒስትር?
- በራሴ ተነሳሽነት፡፡
- ከላይ ትዕዛዝ ሳይመጣ እንዴት በራስዎ ተነሳሽነት ይሠራሉ?
- እኔ እኮ አገሬን ስለምወድ ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር በጣም ተለውጠዋል ማለት ነው?
- እንዴት?
- አገሬን ማለት ጀመሩ?
- ምን ችግር አለው?
- እርስዎ አገሬን ሲሉ አምቼ አላውቅም ብዬ ነው፡፡
- መቀየር አልችልም?
- እኔ የሚገርመኝ እንዴት ሁሌ ሐሳብዎን እንደሚቀይሩ ነው፡፡
- የቢዝነስ ሰው ስትሆን ሁሌም የሚያዋጣህን መንገድ መከተል አለብህ፡፡
- ለማንኛውም እንዲህ ሲገለባበጡ እንዳይቀጩ ነው የምፈራው፡፡
- አገለባበጡን ስለማውቅበት ስለእሱ አትቸገር፡፡
- የእርስዎ ለውጥ እኮ ከውስጥ ስላልሆነ አይዘልቅም፡፡
- እኔ የሚያዋጣኝን ነው የምከተለው፡፡
- ስለዚህ ስለኢትዮጵያዊነት እያቀነቀኑ ነው?
- የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር እኮ ኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያ ላይ ብቻ ነበር፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ተቀይሬአለሁ እያሉ ነው?
- አንተ ስለኢትዮጵያ ምንም አይሰማህም?
- እኔ ከድሮውም አገሬን ወዳድ ነኝ፡፡
- ለማንኛውም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር አንደኛዋ በጣም መስጣኛለች፡፡
- የትኛዋ?
- ‹‹እኛ ስንኖር ኢትዮጵያዊ፣ ስንሞት ኢትዮጵያ ነን፤›› ያሉት ነዋ፡፡
- ለእርስዎ ግን እሱ አባባል የሚሠራ አይመስለኝም፡፡
- ምን?
- ለእርስዎ የሚሆነው ሌላ ነው፡፡
- ምንድነው እሱ?
- ሲኖሩ ሙሰኛ፣ ሲሞቱ ሌባ!