በታላቁ የኢትዮጵያ ግድብ ግንባታ ምክንያት ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር የፈጠረችውን አለመግባባት፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ጣልቃ ገብታ እንድትሸመግላት ጠየቀች፡፡
ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ጥያቄውን ተቀብለው ጥረት መጀመራቸውን ጠቁመዋል፡፡ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥም የአቡዳቢ ልዑልና የኤምሬትስ ጦር ኃይል ምክትል አዛዥ ሼክ መሐመድ ቢን ዛያድ አልናያን፣ ከሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አል በሽርና ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር እንደተወያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በአፍሪካ ጉዳዮች የግብፅ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ረዳት ሚኒስትር አምባሳደር ሞና ኦመር፣ ግብፅ በኢትዮጵያ ግድብ ግንባታ ላይ የዓረብ አገሮችን ተሳትፎ ከግድቡ ግንባታ ይፋ መሆን ጀምሮ ስትጠይቅ የነበረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ግብፅ በአሁኑ ወቅት ከባህረ ሰላጤው የዓረብ አገሮች ጋር በመነጋገር በህዳሴው ግድብ ላይ ጣልቃ እንዲገቡ እየተወተወተች ያለችው፣ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል የተጀመረው ውይይት ውጤት ማምጣት ባለመቻሉ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ከሁለት ሳምንታት በፊት ወደ ተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ቢያቀኑም፣ ዋነኛው የመወያያ ርዕስ የዓረብ አገሮች የኤርትራ ወደብን በመጠቀም በየመን ላይ የጀመሩት የጦር ጥቃት፣ በኢትዮጵያ ላይ ለፈጠረው ሥጋት መተማመኛ ለማግኘት እንደነበረ ይታወሳል፡፡
በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል በዚህ ውይይት ወቅት የህዳሴው ግድብ አጀንዳ ስለመሆኑ የተባለ ነገር የለም፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ተቋርጦ የነበረው የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን በህዳሴው ግድብ ግንባታ ላይ የሚያደርጉት ውይይት ባለፈው ዓርብ መጀመሩ ታውቋል፡፡
ዓላማውም የህዳሴው ግድብ ግንባታ በግብፅና በሱዳን ላይ ተፅዕኖ ያደርስ እንደሆነ ለመገምገም የተመረጡ ሁለት ኩባንያዎች መካከል ያለውን አለመግባባት ለመፍታት፣ ወይም ሌላ አጥኚ ለመምረጥ የሚቻልበትን ይወስናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡