[ክቡር ሚኒስትሩ አረፋፍደው ቢሮ ሲገቡ ጸሐፊያቸውን አገኟት]
- ክቡር ሚኒስትር ምነው አረፈዱ?
- ብለሽ ብለሽ እኔን መቆጣጠር አማረሽ?
- አይ ልቆጣጠርዎት ፈልጌ እንኳን አይደለም፡፡
- ታዲያ ምን ፈልገሽ ነው?
- እንግዶች ነበሩዎት ብዬ ነው፡፡
- የምን እንግዳ?
- የውጭ ኢንቨስተሮች፡፡
- ቀጠሮ ነበራቸው?
- ቀጠሮ እንኳን አልነበራቸውም፡፡
- ታዲያ ምን ፈልገው መጡ?
- አይ አገራቸው ሊሄዱ ስለሆነ ነው፡፡
- እና እኔ ቪዛ ሰጪ ነኝ አሏቸው?
- የለም ስጦታ ይዘው መጥተው ነው፡፡
- የምን ስጦታ?
- የገና ስጦታ፡፡
- ገና ደረሰ እንዴ?
- የፈረንጆች ገና ደርሷል፡፡
- እና እኔ ምን አገባኝ?
- አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እኔ የኒዮሊበራሎችን ገና ምን ቆርጦኝ ነው የማከብረው?
- ያው በዚህ በዓል ስጦታ የመስጠት ባህል ስላላቸው ነው፡፡
- ነገርኩሽ እኮ እኔ የኒዮሊብራሎችን ባህል አላከብርም፡፡
- ስለዚህ ስጦታው ይመለስ?
- እ…
- ስጦታውን ልመልስላቸው ወይ?
- ለመሆኑ ምንድነው ያመጡት?
- ወይን ነው፡፡
- የምን አገር ወይን?
- የፈረንሣይ ወይን ነው፡፡
- እኮ እኔ የኒዮሊብራሎችን ወይን ልጠጣ?
- ምን አለበት?
- እኔ ኪራይ ሰብሳቢ አይደለሁማ፡፡
- የአገራችን ቢሆን ይጠጡት ነበር?
- አዎና፡፡
- ለምን?
- የአገራችን ልማታዊ ወይን ነዋ፡፡
- ለማንኛውም ኬክም አምጥተዋል፡፡
- እሱንም አልፈልግም፡፡
- ለምን ክቡር ሚኒስትር?
- ነገርኩሽ እኮ እኔ የኒዮሊብራሎችን ኬክ አልበላም፡፡
- እሱም የኪራይ ሰብሳቢዎች ነው?
- አዎና፡፡
- ልማታዊው ታዲያ ምንድነው?
- ድፎ ዳቦ ነዋ፡፡
- ባለሥልጣን ግን ስጦታ መቀበል ይችላል?
- ዋናው ስጦታው አይደለም፡፡
- ታዲያ ምኑ ነው?
- ሰጪው ማን ነው? የሚለው ነው ጥያቄው፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- ሰጪው ልማታዊ ነው ወይስ ኪራይ ሰብሳቢ የሚለው ነው ነጥቡ፡፡
- ስለዚህ ልማታዊና ኪራይ ሰብሳቢ ስጦታም አለ ነው የሚሉኝ?
- በሚገባ፡፡
- ስለዚህ ኬክና ወይን የኪራይ ሰብሳቢ ስጦታዎች ናቸው?
- እህሳ፡፡
- እኔ የምለው ቤት፣ መኪናና ቼክ የመሳሰሉት ስጦታዎች ምን ዓይነት ስጦታዎች ናቸው?
- ልማታዊ ስጦታዎች፡፡
[የክቡር ሚኒስትሩ ወዳጅ ዳያስፖራ ደወለላቸው]
- እንዴት ነህ ልማታዊው ዳያስፖራ?
- እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
- እኔማ እየለማሁ ነው፡፡
- በስንት ፐርሰንት እየለሙ ነው?
- የእኔ እንኳን ከአሥር ፐርሰንትም ሳይበልጥ አልቀረም፡፡
- ኧረ አሥር ፐርሰንት ሲያንስብዎት ነው፡፡
- ያው ከአገሪቷ በላይ ማደጌ ጥያቄ እንዳያስነሳብኝ ነው፡፡
- እንደዚህ ዓይነት ጥያቄ ቢነሳብዎትም ችግር የለውም፡፡
- እንዴት የለውም?
- ጥያቄው ልማታዊ ነዋ፡፡
- ልማታዊ ዳያስፖራ ይሉሃል እንዲህ ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር አገሪቷ ሰላም ናት ግን?
- ምን ትሆናለች ብለህ ነው?
- አይ አንዳንድ ብጥብጦች አሉ ሲባል ሰምቼ ነው፡፡
- ኧረ በጣም ሰላም ነን፡፡
- ሁሉም ነገር ሰላም ነው?
- ይኸው እኔ እንግዲህ ቢሮዬ ነኝ፣ ሕዝቡም መንገድ ላይ በሰላም እየተንቀሳቀሰ ነው፣ መኪኖችም በሰላም እየተጓዙ ነው፣ በአጠቃላይ ሁሉም ሰላም ነው፡፡
- ሰላም ከሆነ ደስ ይላል፡፡
- እንዲያውም አሁን በመስኮቴ ምን እያየሁ እንደሆነ ታውቃለህ?
- ምን እያዩ ነው?
- ነጭ እርግብ፡፡
- አይ ክቡር ሚኒስትር እኔም አረጋግጫለሁ፡፡
- ምን አረጋገጥክ?
- አገሪቷ ሰላም መሆኗን፡፡
- እሱ ነው የምልህ እኮ፡፡
- ታዲያ የእንግሊዝ መንግሥት ያወጣው ምንድነው?
- ምን አወጣ?
- ትራቭል አለርት፡፡
- ምንድነው እሱ?
- ያው ወደ ኢትዮጵያ ዜጐቻቸው እንዳይጓዙ የሚል መግለጫ ነው፡፡
- ለምንድነው እንዳይጓዙ ያሉት?
- ብጥብጥ ስላለ፡፡
- ወሬኞች በላቸው፡፡ እኔ እኮ የሚገርመኝ አንድ ነገር ነው፡፡
- ምንድነው የሚገርምዎት?
- ሰላም ሲኖር ወደ ኢትዮጵያ ሂዱ ብለው ለምን መግለጫ አያወጡም?
- በጣም የሚያስገርም ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለማንኛውም የማደርገውን እኔ አውቃለሁ፡፡
- ምን ሊያደርጉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ተመጣጣኝ የሆነ ዕርምጃ እኛም እንወስዳለን፡፡
- ምን ዓይነት ዕርምጃ?
- ትራቭል አለርት እናወጣለን፡፡
- የምን ትራቭል አለርት?
- ዜጐቻችን ወደ ምዕራቡ ዓለም እንዳይጓዙ ነዋ፡፡
- ለምን ክቡር ሚኒስትር?
- እዛ ባለው ብጥብጥ እንዳይጐዱ፡፡
- ይሻላል?
- ተረቱ እንደዛ ነዋ የሚለው፡፡
- ምን ይላል?
- እሾህን በሾህ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ወዳጃቸው ሚኒስትር ጋ ደወሉ]
- ሰማኸልኝ አይደለ ያወጡትን መግለጫ?
- የምን መግለጫ ክቡር ሚኒስትር?
- እነዚህ ኒዮሊብራሎች ያወጡት መግለጫ ነዋ፡፡
- ምን አሉ ደግሞ?
- ኢትዮጵያ ውስጥ ብጥብጥ ስላለ ወደዛ እንዳትሄዱ ብለው ዜጐቻቸውን ከለከሏቸው፡፡
- በቃ አንድ ነገር ኮሽ ሲል ለማራገብ ማን ብሏቸው?
- አንዳንዴ ደግ መሆን ግን ጥሩ አይደለም ልበል?
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- እኛ ፈረንሣይ እንደዚያ ስትታመስ አንድ ነገር ብለናል?
- በጭራሽ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዲያውም ለአየር ንብረት ለውጡ ስብሰባ ሄደናል አይደል እንዴ?
- በሚገባ እንጂ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ስለዚህ ለዚህ ተመጣጣኝ የሆነ ምላሽ መስጠት አለብን፡፡
- ለነገሩ እኛ ተመጣጣኝ ሳይሆን ከፍ ያለ ምላሽ በመስጠት ነው የምንታወቀው፡፡
- ስለዚህ ተመጣጣኝ ሳይሆን ላቅ ያለ ምላሽ እንስጥ ነው የምትለኝ?
- እህሳ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በምን እንጀምር?
- ያው የእኛ ዜጐች በአብዛኛው የሚወጡት በድንበር ነው፡፡
- ስለዚህ እነሱ ‘Vigilant’ ሁኑ እንዳሉት ሁሉ እኛም ዜጐቻችን ድንበር ሲሻገሩ እንደ ቆቅ ‘Vigilant’ ሁሉ ማለት አለብን፡፡
- ያው ‘Crowd’ ያለበትን ቦታ ‘Avoid’ አድርጉ ብለዋል፡፡
- ስለዚህ የእኛም ዜጐች ድንበር ሲያቋርጡ በቡድን ሳይሆን ነጠላ ነጠላ እየሆኑ ማቋረጥ አለባቸው ማለት አለብን፡፡
- ለእንግሊዞቹስ ምን ዓይነት ምላሽ እንስጥ?
- አሁን የእነሱ አገር የጐርፍ ችግር አለ አይደል?
- አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ስለዚህ ለዜጐቻችን ሕይወት ጐርፉ ስለሚያሠጋ እንዳይጓዙ መግለጫ እናውጣ፡፡
- እምቢ ብለው የሚሄዱ ካሉስ?
- ቢያንስ ታንኳ ይዘው እንዲሄዱ እንንገራቸው፡፡
- እ…
- ያልቻሉት ደግሞ ላይፍ ሴቨር ይዘው ይሂዱ ማለት አለብን፡፡
- ግን የእኛ ዜጐች ወደዛ ባይጓዙ እነሱ ምን ይጐዳሉ?
- በአፍጢሙ ሲወድቅ ይመለከታሉ፡፡
- ምኑ?
- ኢኮኖሚያቸው፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ከሰዓት በኋላ ቢሮ ከገቡ በኋላ አማካሪያቸው አርፍዶ ሲገባ አገኙት]
- ምን ሆነህ ነው ያረፈድከው?
- ክቡር ሚኒስትር በአገሪቱ ችግር ነው ያረፈድኩት፡፡
- አገሪቷ እየተመነደገች ባለችበት ወቅት የምን የማርፈድ ችግር ነው የምታወራው?
- አገር አቀፍ ችግር ነው ልልዎት ፈልጌ ነው፡፡
- ከፀረ ልማት ኃይሎች ጋር እያበርክልኝ ነዋ፡፡
- አልገባዎትም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምኑ ነው ያልገባኝ?
- ለነገርዎ እርስዎ ቤትዎም ጀነሬተር አለ፤ ቢሮዎም ጀነሬተር አለ፡፡
- ስለእሱ ማውራት ትተህ ባቡር እኮ የተገጠመው እንዲህ ዓይነት የማርፈድ ሰበብ ላለመስማት ነው፡፡
- ባቡሩ እኮ ነው ችግሩ፡፡
- ጭራሽ ባቡሩ ነው ችግሩ ትለኛለህ?
- አዎን ኤሌክትሪክ ተቋርጦ መሀል ላይ ቆመ፡፡
- ምን?
- አዎን፣ ከዛም ታክሲ ማግኘት ስላልቻልኩ በእግሬ ነው የመጣሁት፡፡
- እና ባቡሩ ቆሟል እያልከኝ ነው?
- ኤሌክትሪክ ከሌለ ታዲያ በምን ይሠራል?
- ለምን በከሰል አይሠራም?
- በምን ከሰል?
- አገር ምድሪቷ ከሰል አይደለች እንዴ?
- ክቡር ሚኒስትር ባቡር የሚሠራበት ከሰል ግን ይለያል፡፡
- ምን ዓይነት ከሰል ነው?
- የድንጋይ ከሰል ነው፡፡
- እኮ ይኼን ሁሉ ድንጋይ ማክሰል ነዋ፡፡
- የቱን ድንጋይ?
- በየመንገዱ የፈጠጠውን ድንጋይ ነዋ፡፡
- ነገሩ በደንብ የገባዎት አልመሰለኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምኑ ነው ያልገባኝ?
- ከሰል ተጠቅመን ባቡሩን ማንቀሳቀስ አንችልማ፡፡
- ለምን አንችልም?
- አየሩን ይበክለዋላ፡፡
- ነዳጅስ መጠቀም አንችልም?
- እሱን ደግሞ ዋጋውን አንችለውም፡፡
- እንዲያውም ሐሳብ መጣልኝ፡፡
- የምን ሐሳብ?
- ለወጣቱ አዲስ ሥራ መፍጠር አለብን፡፡
- እሱማ የሁልጊዜ ዕቅዳችን ነው፡፡
- ስለዚህ በወጣት ክንፍ ውስጥ አዲስ ክንፍ መመሥረት አለብን፡፡
- ምን ዓይነት ክንፍ?
- የባቡር ገፊ ክንፍ!