Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ካሩቱሪ ለሁለተኛ ጊዜ ሐራጅ ወጣበት

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  – መሥራቹ ንግድ ባንክ ያወጣውን ሐራጅ አሳግጃለሁ ቢሉም ማረጋገጫ አልተገኘም

  የህንዱ ካሩቱሪ ግሎባል ሊሚትድ በእህት ኩባንያው ካሩቱሪ አግሮ ፕሮዳክትስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ በኩል ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተበደረውን 55.8 ሚሊዮን ብር ሊከፍል ባለመቻሉ ሐራጅ ተባለ፡፡ ባለፈው ዓመትም በ65 ሚሊዮን ብር ዕዳ ባንኩ ሐራጅ አውጥቶበት እንደነበር ሪፖርተር መዘመገቡ አይዘነጋም፡፡

  ኩባንያው ካለበት 65 ሚሊዮን ብር ውስጥ 10 ሚሊዮን ብር ብቻ በአንድ ዓመት ውስጥ ለባንኩ ከፍሏል፡፡ በመሆኑም ንግድ ባንክ ለ55.8 ሚሊዮን ብር የብድር ዕዳ ያወጣው የሐራጅ ማስታወቂያ እንደሚያመለክተው፣ ካሩቱሪ በጋምቤላ ክልል ለብድር ማስያዣነት ያስመዘገበው 100 ሺሕ ሔክታር መሬትና ሌሎች ንብረቶች በሐራጅ ተሽጠው ብድሩን ለማስመለስ ለጨረታ ቀርበዋል፡፡ በመጪው ማክሰኞ ታኅሳስ 12 ቀን 2008 ዓ.ም. ጨረታው እንደሚከፈት የሚጠበቀው ሐራጅ፣ 100 ሺሕ ሔክታሩን ጨምሮ በዚያው መሬት ላይ የለማ 7,645 ሔክታር እርሻ፣ መጋዘን፣ የሠራተኞች መኝታ ቤትና ተገጣጣሚ ቤትን ለጨረታ አቅርቧል፡፡

  ሪፖርተር ከንግድ ባንክ ባገኘው መረጃ መሠረት፣ ባንኩ የካሩቱሪ ንብረት የነበሩ ሁለት ተጨማሪ የውኃ መቆፈሪያ ማሽነሪዎችን ሸጦ ለዕዳ ማገገሚያነት አውሏል፡፡ የንግድ ባንክ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም መኩሪያ ለሪፖርተር እንዳረጋገጡት፣ ሁለቱ ማሽነሪዎች በጠቅላላው 2.6 ሚሊዮን ብር አካባቢ ተሸጠው ገንዘቡ ለባንኩ ገቢ ተደርጓል፡፡

  የካሩቱሪ መሥራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሳይ ራማክሪሽና ካሩቱሪ በበኩላቸው ንግድ ባንክ፣ ‹‹የአገሪቱን ሕጎች የሚጥስ፣ ተገቢነት የጎደለውና እዚህ ግባ ለማይባል ጉዳይ…›› በማለት የገለጹትንና ባንኩ ያወጣውን የሐራጅ ማስታወቂያ እንዳሳገዱ በኢሜል ለሪፖርተር ቢገልጹም፣ ንግድ ባንክ በበኩሉ እስካለፈው ዓርብ የሥራ ሰዓት ማብቂያ ድረስ እንዲህ ያለው የሐራጅ ማሳገጃ ሰነድ እንዳልደረሰው አቶ ኤፍሬም ገልጸዋል፡፡ ይህም ሆኖ ካሩቱሪ ጨረታው ከሚያበቃበት ከመጪው ማክሰኞ በፊት ከሚጠበቅበት ዕዳ ውስጥ 25 በመቶውን በመክፈል ጨረታውን የማሳገድና የመደራደር መብት ሕጉ እንደሚፈቅለት አስታውቀዋል፡፡

   ከዚህ ባሻገር ካሩቱሪ ከዘመን ባንክ ጋርም በብድር ዕዳ ምክንያት እስከ ፍርድ ቤት የደረሰ መካረር ውስጥ ገብቶ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህንን ያመኑት ራም ካሩቱሪ፣ በፍርድ ቤት የነበረው ሒደት በስምምነት ተቋጭቶ በአሁኑ ወቅት ለዘመን ባንክ የሚከፈል 26 ሚሊዮን ብር ዕዳ ኩባንያቸው እንዳለበት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 

  ለሃምሳ ዓመታት በሚቆይ የሊዝ ስምምነት መንግሥት ለካሩቱሪ የሰጠው መሬት እጅግ ዝቅተኛ በሚባል ዋጋ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ኩባንያው ከስድስት ዓመት በላይ በተሰጠው እርሻ ቦታ ላይ ተገቢውን ልማት ማከናወን ሳይችል ቆይቷል፡፡ በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የግብርና ኢንቨስትመንትና መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አበራ ሙላት ዓምና በጉዳዩ ላይ ተጠይቀው ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ፣ ኩባንያው ይጠበቅበት የነበረውን ሥራ ማከናወን ሳይችል ቀርቷል፡፡

   ካሩቱሪ በገባበት አስተዳደራዊ ቀውስ ምክንያት ለኪሳራ ከመዳረጉም በላይ፣ ወደ መዘጋቱ እያዘገመ ያለ ኩባንያ ለመሆን እንደበቃ አቶ አበራ መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡ ኩባንያውን በቦርድ የሚመሩት 19 ግለሰቦች ሲሆኑ፣ በመካከላቸው በተፈጠረ የአመራር ችግር ኩባንያው ለኪሳራ ተዳርጎ እያለ፣ በአንፃሩ መንግሥት ለኢንቨስትመንት የሚመች ዕድል እንዳልፈጠረለት በመግለጽ ስም ማጥፋቱን አቶ አበራ ኮንነው ነበር፡፡ በዝቅተኛ ገንዘብ ከተሰጠው የሊዝ መሬት ባሻገር በርካታ ማሽነሪዎችን ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገባ እንደተፈቀደለትም ጠቅሰው ነበር፡፡ የፋይናንስ ችግሮች አጋጥመውትም፣ ለአገር ውስጥ ኩባንያዎች ብቻ የፈተቀደውን የማሽነሪ ማከራየት ሥራ ለካሩቱሪ ብቻ ተፈቅዶለት ሲሠራ እንደነበር አቶ አበራ አስታውሰዋል፡፡ ኩባንያውም ይህንን እውነታ በዓመታዊ ሪፖርቱ መጥቀሱን ሪፖርተር አረጋግጧል፡፡

  ይሁንና ሰሞኑን ስለሚገኝበት ሁኔታና ስለታዩ ለውጦች ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠየቁት አቶ አበራ፣ ሚኒስቴሩ ባለው የሚዲያ ግንኙነትና አሠራር ቢሮክራሲ ሳቢያ በቀጥታ መግለጫ ከመስጠት እንደሚቆጠቡ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ይሁንና ከዚህ በፊት ሪፖርተር በዘገበው ዜና ላይ ኩባንያቸው ከእንግዲህ እምነት የሚጣልበት እንዳልሆነ፣ ቀውስ ውስጥ የሚገኝና ኪሳራ ውስጥ የወደቀ ኩባንያ ሆኗል ተብሎ የቀረበበትን ትችት ክፉኛ ያጣጣሉት ራም ካሩቱሪ፣ ምንም እንኳ የእርሻ አፈጻጸማቸው የሚያበሳጭ መሆኑን ቢያምኑም በዚህ ደረጃ ስለኩባንያቸው መገለጹ ግን እንደ ወንጀለኛ መቆጠራቸውን የሚጠቁም አድርገው እንደሚወስዱት ተናግረዋል፡፡ ንግድ ባንክን ጨምሮ የመንግሥት ባለሥልጣናትንና የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴርን የኮነኑት ካሩቱሪ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ዘመቻ እንደተከፈተባቸው፣ ሪፖርተርን ጨምሮ ሚዲያው እሳቸውንና ኩባንያቸውን ለማሳቀል እንደተነሱ በመጥቀስ ለመብታቸው የትኛውንም ሕጋዊ መንገድ እንደሚጠቀሙ በመግለጽ ለማስጠንቀቅም፣ ለማስፈራራትም ሞክረዋል፡፡

  ካሩቱሪ ከጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት 300 ሺሕ ሔክታር መሬት በሊዝ ወስዶ ነበር፡፡ ኋላ ላይ ከፌደራል መንግሥት ጋር በተደረገ ድርድር ኩባንያው የወሰደው የመሬት መጠን ወደ አንድ መቶ ሺሕ ሔክታር እንዲቀንስ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡ ካሩቱሪ በሊዝ ለወሰደው መሬት በሔክታር ሃያ ብር ያህል መክፈሉም ይታወቃል፡፡

  ይሁንና ካሩቱሪ 300 ሺሕ ሔክታር መሬት እንዲሰጠው እንዳልጠየቀ፣ ይልቁንም የማልማት አቅሙ 10 ሺሕ ሔክታር መሬት እንደነበር ካሩቱሪ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ሦስት መቶ ሺሕ ሔክታር መሬት እንዲሰጡኝ አልጠየቅሁም፡፡ የጋምቤላ ክልል ኃላፊዎች ግን ሦስት መቶ ሺሕ ሔክታር መሬት እንሰጥሃለን ቢሉኝም እኔ ማልማት የምችለው አሥር ሺውን እንደሆነ ገልጬ ነበር፤›› በማለት የገለጹት ካሩቱሪ፣ ይሁንና የክልሉ ባለሥልጣናት ከ300 ሺሕ ሔክታር በታች እንደማይሰጧቸው ገልጸው እሳቸው በሚስማሙበት ዋጋ በሊዝ እንዲገዙ ባለሥልጣናቱ እንዳግባቧቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

  የንግድ ባንክን ዕዳ አከፋፈል በተመለከተ ተጠይቀው፣ ያለባቸውን ዕዳ የሚከፍሉት በሌላ ትልቅ ኩባንያ ላይ ያላቸውን 100 ሚሊዮን ብር ማግኘት ሲችሉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ኩባንያቸው ከንግድ ባንክና ዕዳ አለበት ካሉት ኩባንያ ጋር የሦስትዮሽ ስምምነት በመፈረም ዕዳውን ለመክፈል እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይሁንና አቶ ኤፍሬም ለሪፖርተር እንዳረጋገጡት፣ ባንኩ እንዲህ ያለውን ነገር የማያውቀውና በጽሑፍም የደረሰው ምንም ነገር የለም፡፡

  ባለፈው ዓመት የእርሻ መሣሪዎችና ቁሳቁሶች ሽያጭ ለማካሔድ ማስታወቂያ ማውጣቱን ተከትሎ ካሩቱሪ ትኩረት ስቦ እንደነበር ይታወሳል፡፡  ራም ካሩቱሪ በወቅቱ ከሪፖርተር ስልክ ሲደወልላቸው፣ ከህንድ ባንጋሎር ከተማ ሆነው አስተያየት መስጠታቸውም ይታወሳል፡፡ ኩባንያቸው በርካታ ፈተናዎች ቢገጥሙትም ለሽያጭ ያቀረባቸው ማሽነሪዎች ግን ከአገር ለመውጣት በማሰብ ሳይሆን፣ ኩባንያው አገር ውስጥ ያለበትን የባንክ ዕዳ ለመክፈል ያደረገው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ኩባንያቸው ከንግድ ባንክ፣ ከዘመን ባንክና ከዳሸን ባንክ ብድር ወስዷል፡፡ ጠቅላላ ያለበት የብድር ዕዳ 170 ሚሊዮን ብር ያህል መሆኑን የጠቀሱት ራም ካሩቱሪ፣ ይህንን ዕዳ ባለፈው ዓመት እንደሚዘጉ ገልጸው ነበር፡፡ ይሁንና አሁንም ድረስ በባንክ ዕዳ ጥያቄ እየቀረበባቸው ይገኛሉ፡፡ ለሽያጭ ቀርበው የነበሩት ማሽነሪዎች ዋጋ 15 ሚሊዮን ብር እንደነበርና አገልግሎት ሰጥተው በትርፍ ንብረትነት የተመዘገቡ ንብረቶች ላይ የሽያጭ ማስታወቂያ በማውጣት ሽያጭ መከናወኑን በወቅቱ ተናግረዋል፡፡

  ካሩቱሪ በኢትዮጵያ አንድ ሚሊዮን ቶን በቆሎ፣ ሩዝ፣ የፓልም ተክልና ሌሎች የግብርና ውጤቶችን ለማምረት አልሞ መነሳቱ ይታወሳል፡፡ ራም ካሩቱሪ ይህንን ህልማቸውን ለማሳካት አሁንም ቁርጠኛ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ስለኩባንያው ለመነጋገር በጠሩት ስብሰባም የኩባንያው ችግሮች ላይ ውይይት መደረጉን ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ኩባንያው ማስተካከል አለበት ያላቸውን ችግሮች ማስተካከሉን፣ በአሁኑ ወቅት በአራት ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ ከ30 ሺሕ ቶን በላይ በማልማቱ ለጎረቤት አገሮች ለመሸጥ እንደሚፈልግ አስታውቋል፡፡ ሆኖም ከጋምቤላ አዲስ አበባ ምርቱን ማጓጓዝ የሚጠይቀው የትራንስፖርት ወጪ ከፍተኛ በመሆኑ፣ በደቡብ ሱዳን በኩል ምርቱን ለማውጣት ብቸኛው አማራጭ እንደነበር ራም ካሩቱሪ ገልጸው ነበር፡፡

  ካሩቱሪ ገና ከመምጣቱ ጀምሮ ነቀፋ ሲሰነዘርበት ቆይቷል፡፡ የተሰጠውን መሬት መነሻ በማድረግ በዓለም የስቶክ ገበያ ሽያጭ ማካሄዱ የኩባንያውን የካፒታል አቅም ጥርጣሬ ላይ እንደጣለው የሚገልጹ አልታጡም፡፡ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ካሩቱሪን ጨምሮ ሌሎች ሰፋፊ እርሻ ለማልማት መሬት በወሰዱና ባላለሙት ላይ ጀርባቸውን ማዞራቸው ተሰምቷል፡፡ አቶ አበራ በቅርቡ በተካሄደ የሚኒስቴሩ ስብሰባ ወቅት እንዳስታወቁት፣ ከእንግዲህ ውጤታማ ባልሆኑ ባለሀብቶች ላይ የካሩቱሪ ዓይነት ዕርምጃ ይወሰዳል፡፡

  ካሩቱሪ ግሎባል ሊሚትድ ኢትዮጵያን ሜዶውስ፣ ሱሪያ ብሎሶምስ፣ ሺቫ ፓክስ የተባሉትን ጨምሮ ካሩቱሪ አግሮ ፕሮዳክትስ የተባሉትን ኩባንያዎች በአባልነት ያስተዳድራል፡፡

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች