Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  በሕገ መንግሥቱ ዋስትና የተሰጣቸው መሠረታዊ መብቶች ይከበሩ!

  ኅዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም. የፀደቀው የአገሪቱ ሕገ መንግሥት፣ የአገሪቱ ሕዝብ ሉዓላዊነት መገለጫ መሆኑ ተደንግጓል፡፡ ሕገ መንግሥቱ የአገሪቱ የበላይ ሕግ በመሆኑ ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሠራር፣ እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት እንደማይኖረው ተደንግጓል፡፡ ማንኛውም ዜጋ፣ የመንግሥት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማኅበራት፣ እንዲሁም ባለሥልጣኖቻቸው ሕገ መንግሥቱን የማስከበርና ለሕገ መንግሥቱ ተገዥ የመሆን ኃላፊነት እንዳለባቸው ተደንግጓል፡፡ በዚህ ሕገ መንግሥት ከተደነገገው ውጪ በማናቸውም አኳኋን የመንግሥት ሥልጣን መያዝ የተከለከለ መሆኑና አገሪቱ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የአገሪቱ ሕግ አካል መሆናቸውም ተደንግጓል፡፡ ይህ ሕገ መንግሥት ዋስትና የሰጣቸው መሠረታዊ የሆኑ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችም በስፋት ተዘርዝረው ሰፍረዋል፡፡

  በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 10 መሠረት ሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶች ከሰው ልጅ ተፈጥሮ የሚመነጩ፣ የማይጣሱና የማይገፉ በመሆናቸው የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይከበራሉ፡፡ ይህ የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነ ሕገ መንግሥት ያጎናፀፋቸውና ዋስትና የሰጣቸው መሠረታዊ መብቶች መከበር ለሕግ የበላይነት፣ ለሰላም፣ ለዕድገት፣ ለሰብዓዊና ለዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡ ዜጎች በሕግ የበላይነት ጥላ ሥር በሰላም ሥራቸውን እንዲያከናውኑ፣ በአገራቸው ሁለንተናዊ ጉዳዮች ባለቤት እንዲሆኑ፣ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ እንዲከናወንና ተጠያቂነት እንዲሰፍን፣ ማንኛውም የመንግሥት ባለሥልጣንና የሕዝብ ተመራጭ ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ እንዲሆን፣ የአገሪቱ ሀብት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲከፋፈልና ለመሳሰሉት ጠቃሚ ጉዳዮች ይረዳል፡፡

  ሕገ መንግሥቱ እ.ኤ.አ በ1948 የፀደቀውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሁለንተናዊ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን በውስጡ ያካተተ የዜጎች አለኝታ ነው፡፡ መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች በሚለው ክፍሉ የሕይወት፣ የአካል ደኅንነትና የነፃነት መብቶችን በዝርዝር ይዟል፡፡ የሰዎችን ነፃነት የሚጋፉ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች የተከለከሉ መሆኑንም ያትታል፡፡ የክብርና የመልካም ስም፣ የእኩልነት፣ የግል ሕይወት የመከበርና የመጠበቅ፣ የሃይማኖት፣ የዕምነትና የአመለካከት፣ የአመለካከትና ሐሳብን በነፃነት የመያዝና የመግለጽ፣ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ፣ የመደራጀት፣ የመዘዋወር፣ የዜግነትና የመሳሰሉት መብቶችና ነፃነቶች የሠፈሩበት ሕገ መንግሥት ነው፡፡ በተጨማሪም ፍትሕ የማግኘት፣ የመምረጥና የመመረጥ መብት ከሕዝብ የተለያዩ መሠረታዊ ነፃነቶች ጋር ዋስትና ያገኙበት ሕገ መንግሥት ነው፡፡

  ይህንን የመሰለ ሕገ መንግሥት ተይዞ ላለፉት ሃያ ዓመታት ሲዘለቅ፣ ብዙዎቹ መብቶች በአግባቡ ሊከበሩ ባለመቻላቸው ችግሮች ሲፈጠሩ ይታያል፡፡ ከማንም በላይ ሕገ መንግሥቱን የማስከበር ኃላፊነት ያለበት መንግሥት በተለይ መሠረታዊ የሚባሉትን መብቶችና ነፃነቶች በሰባራ ሰንካላ ምክንያቶች ተግባራዊ እንዳይሆኑ በማድረጉ ሳቢያ የታመቁ ብሶቶች ድንገት ይፈነዳሉ፡፡ በግብታዊነት የሚፈነዱ ተቃውሞዎች ምክንያት የሚደመጡበት መድረክ ማጣት ነው፡፡ መንግሥት በቁጥጥሩ ሥር ያሉትን መገናኛ ብዙኃን የስኬቶቹ ማወደሻ ስላደረጋቸው፣ የተለዩ አመለካከቶችን ወይም አቤቱታዎችን አይሰማም፡፡ በተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚዘጋጁ ሰላማዊ ሠልፎችና ብሶቶች መስተናገድ ስላልቻሉ የታመቁ ብሶቶች ድንገት ሲፈነዱ ከቁጥጥር ውጪ ይሆናሉ፡፡ ለዜጎች ሕይወት መጥፋት፣ ለአካል ጉዳትና ለንብረት ውድመት ምክንያት ይሆናሉ፡፡ እነዚህ ችግሮች በተደጋጋሚ ታይተዋል፡፡

  በሕገ መንግሥቱ የሠፈሩት መሠረታዊ መብቶች ቢከበሩ ኖሮ፣ ለመንግሥት ድንገት ደራሽ እየሆኑ አገሪቱን ለቀውስ የሚዳርጉ ችግሮች አይፈጠሩም ነበር፡፡ ችግሮች ተፈጥረው ብዙ ውድመት ከደረሰ በኋላ በመንግሥት አፀፋ ፕሮፓጋንዳ የሚሰሙ የመግለጫ ጋጋታዎች፣ የችግሩን መንስዔ አውቆ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ ሰበብ ፈላጊነት ጎልቶ ይታይባቸዋል፡፡ በሕገ መንግሥቱ የሉዓላዊነት ባለቤትነትን እንደተጎናፀፈ የተደነገገለት የአገሪቱ ሕዝብ ተሳትፎ ይገድብና የማድበስበስ ድርጊት ውስጥ ይገባል፡፡ ለምሳሌ ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ለተከሰተው ሁከት ምክንያት የሆነው የጋራ ማስተር ፕላን ያለሕዝቡ ፍላጎት ተግባራዊ እንደማይሆን በክልሉ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ ተነግሯል፡፡ ከሕዝቡ ጋርም ውይይት እየተደረገ እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡ ነገር ግን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃንን አየር የሞላው “በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች የተነሳውን ብጥብጥ አንዳንድ የ… አካባቢ ነዋሪዎች ተቃወሙ” የሚል መግለጫ ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ ሕዝብ ማስተር ፕላኑንም ሆነ ሌሎች ችግሮችን በተመለከተ ምን እያለ እንደሆነ ለምን ጎልቶ አይሰማም? ይኼ ፈጽሞ ተዘንግቷል፡፡ በግራም በቀኝም ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች ምን እያሉ ነው? የሚሰማ ነገር የለም፡፡

  በሌላ በኩል በተነሳው ሁከት ምክንያት በተቃውሞ አድራጊዎችም ሆነ በመንግሥት በኩል በርካታ ዜጎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ብዙዎች ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ ከፍተኛ ግምት ያለው ንብረት ወድሟል፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ከሕግ የበላይነት ይልቅ የአመፅ መንገድ በመመረጡ ነው፡፡ ድምፃቸው እንደታፈነባቸው የሚሰማቸው ወገኖች ሕገ መንግሥቱ ያረጋገጠላቸው መብትና ነፃነት ባለመከበሩ ምክንያት ሁከት ማንሳታቸው ሳይነገር፣ ከበስተጀርባ ስላሉ ኃይሎች በብዛት ሲነገር ይሰማል፡፡ አንድ ዜጋ መሠረታዊ መብቶቹ ከተከበሩለትና በአገሩ በነፃነት እየኖረ መሆኑን ማረጋገጥ ከቻለ፣ ከድህነት ሊያወጣው የሚችልን ልማት ሊቃወም አይችልም፡፡ ሌላ ፍላጎት ላላቸው ኃይሎችም መሣሪያ አይሆንም፡፡ መንግሥት ይህንን በፍጥነት በማጤን ሕገ መንግሥቱን ማስከበር አለበት፡፡ ሕገ መንግሥቱ ሳይከበር ቀርቶ ድንገተኛ አመፅ እየተከሰተ የዜጎችን ሕይወት የሚቀጥፍበት ምንም ዓይነት ሰበብ ሊኖር አይገባም፡፡ መንግሥትም በግብታዊነት የሚፈነዱ ብጥብጦች ከሕግ የበላይነት መጥፋት ጋር የተያያዙ መሆናቸውን የግድ ማመን አለበት፡፡ ከበስተጀርባ አሉ የሚባሉ ኃይሎች አመፁን የመምራት ዕድል የሚያገኙት ዜጎች መብታቸው ሳይከበርላቸው ሲቀር መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ የሕዝብን መሠረታዊ መብቶች የሚጋፉ ተግባራት ይወገዱ፡፡

  መንግሥትን የሚመራው ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ከአጋሮቹ ጋር የፓርላማውን መቀመጫዎች ሙሉ በሙሉ ከተቆጣጠረ በኋላ፣ የዜጎች ድምፅ የሚሰማባቸውን መድረኮች አለመክፈቱ ትልቁ ፈተና ነው፡፡ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የተለዩ ድምፆች ካልተሰሙባቸው፣ አመለካከትን በነፃነት የሚገልጹባቸው መድረኮች ከሌሉ፣ ሰላማዊ ሠልፎችና ሕዝባዊ ውይይቶች ካልተከናወኑ፣ የዜጎችን ሐሳቦች የሚያስተጋቡ የሲቪል ማኅበራት ከጠፉ፣ በፖለቲካ ምኅዳሩ መጣበብ ምክንያት የፖለቲካ ፓርቲዎች ከተልፈሰፈሱና መሠረታዊ መብቶች ካልተከበሩ ዴሞክራሲ ማለት ምን ማለት ነው? ሕገ መንግሥቱ ካልተከበረ በጽሑፍ ሠፍሮ መቀመጡ ምን ይጠቅማል? እነዚህንና ሌሎች ተጓዳኝ ጥያቄዎችን ከልብ በመቀበል የተዘጋጉ በሮች ካልተከፈቱ ችግሩ የአገር ነው፡፡ ብዙ ተለፍቶበታል የሚባልለት የፌዴራል ሥርዓት በሕገ መንግሥቱ መሠረት ካልተመራ የአገር ህልውና አደገኛ አጣብቂኝ ውስጥ ይገባል፡፡

  ዜጎች መሠረታዊ መብቶቻቸው ሲከበሩላቸው በአገሪቱ ልማት ግንባር ቀደም ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ የልማቱ አጋር ብቻ ሳይሆኑ መሪ ተዋናይ ሆነው አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡ የልማቱ ትሩፋትም በእኩልነት ይዳረሳል፡፡ አንዱ እየበላ ሌላው ተመልካች አይሆንም፡፡ ሦስቱ የመንግሥት አካላት (ሕግ አውጪው፣ ሕግ ተርጓሚውና አስፈጻሚው) በተጠያቂነት መንፈስ እየተናበቡ ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ፡፡ የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ የፍትሕ መስተጓጎልና ሙስና የአገር በሽታ መሆናቸው ያከትማል፡፡ ይህ ሁሉ በትክክል ሥራ ላይ የሚውለው ሕገ መንግሥቱ ሲከበር ብቻ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱን በተግባር ሥራ ላይ አለማዋልና የተለመደው እሰጥ አገባ ውስጥ መግባት የትም አያደርስም፡፡ ይልቁንም ችግር በችግር ላይ እየደራረበ ለማያስፈልግ ትርምስ ይዳርጋል፡፡ ዜጎች በአገራቸው በነፃነት አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲራመዱ ከተፈለገ፣ በሕገ መንግሥቱ ዋስትና የተሰጣቸው መሠረታዊ መብቶች ይከበሩ!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ባንኮች እንዲዋሀዱ እስከ ማስገደድ ሊገባ እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ ጠቆመ

  በአሁኑ ወቅት የባንኮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ችግር የሚሆንና የውጭ...

  ለኬንያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚሸጥበት ታሪፍ ማሻሻያ ተደረገበት

  በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ስምምነቱ የተጠናቀቀው የኢትዮጵያና የኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል...

  አዲስ አበባ እንዳይገቡ በተከለከሉ ዜጎች ጉዳይ የኦሮሚያና አማራ ክልሎች ተወያይተው ችግሩ እንዲፈታ አደረጉ

  ለሳምንታት በርካታ ቅሬታ ሲነሳበት የነበረውና ከአማራ ክልል በደብረ ብርሃን...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...

  ለኬንያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚሸጥበት ታሪፍ ማሻሻያ ተደረገበት

  በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ስምምነቱ የተጠናቀቀው የኢትዮጵያና የኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁና የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጨው ሁለተኛው ተርባይን ሥራ መጀመሩ፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የፈጠረው ደስታ ቃላት ከሚገልጹት...

  የሥጋት ደመና ተወግዶ ሰላም ይስፈን!

  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደቡብ የአገሪቱ ክፍል ክልል ለመሆን የፈለጉ የተለያዩ ዞኖች እየተሰባሰቡ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ እያቀረቡ ናቸው፡፡ ለብቻችን ክልል መሆን አለብን የሚሉ ዞኖችም...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር ሕዝቦችና ለአፍሪካውያን ነፃነትም ተምሳሌት ናት፡፡ የጥንቶቹ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን የሚያኮራ ተግባር ፈጽመው ያለፉት፣ ከአገራቸው በፊት የሚቀድም...