- ከውሳኔው በፊት የሕገ መንግሥታዊነት ክርክር ተከስቶ ነበር
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌደሬሽን ምክር ቤት በጋራ ባካሄዱት ስብሰባ፣ አራተኛው አገር አቀፍ የሕዝብና የቤት ቆጠራ እንዲራዘም ወሰኑ፡፡ የተወሰኑ አባላት በቀረበው የማራዘሚያ ሐሳብ ሕገ መንግሥታዊነት ላይ ጥያቄ አንስተዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ የማራዘሚያ የውሳኔ ሐሳቡን ያፀደቀው በአንድ የተቃውሞ በአብላጫ ድምፅ ነው። በመሆኑም ዘንድሮ ይካሄዳል ተብሎ ዝግጅት ሲደረግበት የነበረው የሕዝብና ቤት ቆጠራ፣ በ2011 ዓ.ም. አመቺ በሆነ ወቅት እንዲካሄድ ተራዝሟል።
ለሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ጉባዔ የውሳኔ ሐሳቡን ያቀረበው የሕዝብና የቤት ቆጠራ ኮሚሽን ነው፡፡ ኮሚሽኑ የቆጠራ ጊዜው እንዲራዘምለት ካቀረባቸው ምክንያቶች መካከል፣ ባለፉት ጊዜያት በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተው የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ በዚህም የተነሳ የሰዎች ከመደበኛ መኖሪያቸው መፈናቀልና የፀጥታ መደፍረስ በዋነኝነት ተጠቅሰዋል።
በተከሰቱት ችግሮች ምክንያት ቆጠራውን ለማካሄድ ከሚጠየቀው ዓለም አቀፍ መሥፈርት አንፃር ብቁ አለመሆኑን ኮሚሽኑ ያቀረበው ውሳኔ ሐሳብ ያስረዳል። ሁለቱ ምክር ቤቶች በጋራ ጉባዔያቸው ያራዘሙት የሕዝብና ቤት ቆጠራ በሕገ መንግሥቱ መሠረት መካሄድ የነበረበት በየአሥር ዓመቱ ቢሆንም፣ በ1997 ዓ.ም. በሕገ መንግሥቱ ላይ በተደረገ ማሻሻያ ከአሥር ዓመት በላይ ሊራዘም እንደሚችል ተወስኗል። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ስለመደረጉ በርካታ የሕግ ባለሙያዎችም ሆኑ ፖለቲከኞች መረጃ የላቸውም። መረጃው ያላቸውም ቢሆኑ እስካሁን ስለተደረገው ማሻሻያ ሕጋዊነት ይጠይቃሉ።
በ1997 ዓ.ም. መካሄድ የነበረበት የሕዝብና ቤት ቆጠራ በ1997 ዓ.ም. መካሄድ ከነበረበት አገር አቀፍ ምርጫ ጋር በመገጣጠሙና ሁለቱንም ኃላፊነቶች በአንድ ዓመት ማካሄድ ከፍተኛ በጀት የሚጠይቅ በመሆኑ፣ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ የውሳኔ ሐሳብ ቀርቦ ቆጠራው የሚካሄድበት የጊዜ ገደብን የሚደነግገው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ በከፊል እንዲሻሻል መደረጉን የሪፖርተር መረጃዎች ያመለክታሉ።
በወቅቱ የፌዴሬሽንና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች፣ እንዲሁም የሁሉም ክልሎች ምክር ቤቶች በተናጠል ባካሄዱት ስብሰባ የቀረበላቸውን የውሳኔ ሐሳብ በማፅደቅ፣ የሕዝብና ቤት ቆጠራ የሚካሄድበት የጊዜ ወሰንን በተመለከተ የሚደነግገውን የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 103(5) እንዲሻሻል አድርገዋል።
የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 103(5)፣ ‹‹የሕዝብና ቤት ቆጠራ በየአሥር ዓመቱ ይካሄዳል። በውጤቱም መሠረት የምርጫ ክልሎችን አከላለል የምርጫ ቦርድ በሚያቀርበው ረቂቅ መሠረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ይወስናል፤›› በማለት ይደነግጋል።
ነገር ግን በ1997 ዓ.ም. የተደረገው ማሻሻያ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 103(5) ይዘት ላይ ‹‹የሕዝብና ቤት ቆጠራ በየአሥር ዓመቱ ይካሄዳል›› ከሚለው ቀጥሎ፣ ‹‹ሆኖም ቆጠራውን ለማካሄድ ከአቅም በላይ ችግር ስለመኖሩ የተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በጋራ ስብሰባ ካረጋገጡ የቆጠራው ዘመን እንደ ሁኔታው ሊራዘም ይችላል፤›› የሚል ድንጋጌ በማሻሻያነት የአንቀጹ አካል እንዲሆን ተወስኗል።
ከዚህ በኋላ በ1997 ዓ.ም. መካሄድ የነበረበት ቆጠራ በ1999 ዓ.ም. እንዲካሄድ ሁለቱ ምክር ቤቶች ወስነዋል።
በወቅቱ የተደረገው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሕገ መንግሥቱን የተከተለ አለመሆኑን፣ በዚህም የተነሳ ማሻሻያው ሕጋዊ ተቀባይነት አለው ብለው እንደማያምኑ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያ አቶ አብዱ ዓሊ ሒጅራ ይከራከራሉ።
በወቅቱ የተደረገው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሕገ መንግሥቱ የሚሻሻልበትን ሕገ መንግሥታዊ መሥፈርት ተከትሎ አለመሻሻሉን፣ ተሻሻለ የተባለው አንቀጽ መሻሻሉን በተመለከተ እስከ ዛሬ ድረስ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ አለመውጣቱ የሕዝብና ቤት ቆጠራ የሚካሄድበት የጊዜ ወሰንን በተመለከተ በሕግ ቅቡል የሆነ ማሻሻያ ተደርጓል ለማለት እንደሚቸገሩ አቶ አብዱ ያስረዳሉ፡፡
ክርክራቸውን ለማጠናከርም በ2008 ዓ.ም. ተሻሻሎ በድጋሚ የታወጀውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ ቁጥር 6/2008 ይጠቅሳሉ።
በዚህ ደንብ አንቀጽ 59 ላይ ‹‹የሕገ መንግሥት ማሻሻያ በሚኖርበት ጊዜ እያንዳንዱ ማሻሻያ ቁጥር ተሰጥቶት በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ መታተም ይኖርበታል፤›› የሚል ድንጋጌ መያዙን፣ በቀጣዩ ንዑስ አንቀጽ ሥር ደግሞ ‹‹እያንዳንዱ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ በሚታተመው ሕገ መንግሥት መጨረሻ ላይ ‘ማሻሻያ’ የሚል ርዕስ ተሰጥቶት ይካተታል፤›› የሚል ድንጋጌ መቀመጡን፣ ነገር ግን ከ13 ዓመታት በፊት ተሻሻለ የተባለው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽን በተመለከተ በተጠቀሰው ድንጋጌ መሠረት የታተመ ሕገ መንግሥት ወይም ነጋሪት ጋዜጣ አለመኖሩን ያብራራሉ፡፡
በሕግ ተቀባይነት ያለው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ተደርጓል ብለው እንደማያምኑ የሚገልጹት የሕግ ባለሙያው አቶ አብዱ፣ ለጊዜው ለግንዛቤ እንዲረዳ ማሻሻያውን በመቀበል ክርክራቸውን ሲቀጥሉ፣ ‹‹ተደረገ በተባለው ማሻሻያ መሠረት ቢሰላ እንኳን ቆጠራው መካሄድ የነበረበት ወይም በተባለው ማሻሻያ መሠረት መራዘም የነበረበት በ2009 ዓ.ም. ነበር፡፡ ምክንያቱም በ1999 ዓ.ም. የተደረገው ቆጠራ አሥረኛ ዓመት የነበረው በ2009 ዓ.ም. በመሆኑ ነው፤›› ብለዋል።
ሰኞ ሚያዚያ 22 ቀን 2010 ዓ.ም. ሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ጉባዔያቸውን ከማካሄዳቸው በፊት በተናጠል በየራሳቸው ምክር ቤት በውሳኔ ሐሳቡ ላይ የተወያዩ ሲሆን፣ በሁለቱም ምክር ቤቶች ቀደም ሲል የተደረገው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሕጋዊነት ላይ ከፍተኛ ክርክር ተካሂዷል።
ፌዴሬሽን ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ያካሄደው የተናጠል ስብሰባ ጠንከር ያለ ነበር።
(በ1997 ዓ.ም. መካሄድ የነበረበት) ሦስተኛው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ የተራዘመበት ሒደት ሕግ ሆኖ ባለመፅደቁ ይራዘም ከሚለው ውሳኔ በፊት፣ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 103 ንዑስ አንቀጽ 5 ሊሻሻል ይገባል በማለት፣ የተወሰኑ የምክር ቤቱ አባላት ጥያቄ አንስተዋል።
በሌላ በኩል ቁጥራቸው በዛ ያሉ የምክር ቤቱ አባላት የነበረው ሒደት በሕዝብ ተወካዮች፣ በፌዴሬሽን እንዲሁም በክልል ምክር ቤቶች አብላጫ ድምፅ አግኝቶ እንደፀደቀ በማስታወስ የቀረበው ረቂቅ እንዲፀድቅ ተከራክረዋል።
በተነሳው ክርክር መግባባት ባለመቻሉ ወደ ድምፅ መስጠት የተሸጋገረ ሲሆን በዚህም የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ በ90 ድጋፍ፣ በአሥር ተቃውሞና በሦስት ድምፀ ተዓቅቦ አልፏል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሦስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሦስተኛ ልዩ ስብሰባ ይኼው የሕዝብና የቤት ቆጠራን የማራዘም አጀንዳ ቀርቦ ተመሳሳይ ክርክር ተደርጎበታል። በምክር ቤቱ የተነሳው ክርክር በፌዴሬሽን ምክር ቤት ከተደረገው ጋር ተመሳሳይ ነበር። በ1997 ዓ.ም. የተደረገው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሕጋዊነት እዚህም የክርከሩ ጭብጥ ነበር።
‹‹ፓርላማው ነው ለሕገ መንግሥቱ ተጠሪ? ወይስ ሕገ መንግሥቱ ነው ለፓርላማው ተጠሪ የሆነው?›› ሲሉ አንድ የምክር ቤቱ አባል ማሻሻያው በነጋሪት ጋዜጣ አለመታተሙ፣ ማሻሻያውን ሕገ መንግሥታዊ እንደማያደርገው ሞግተዋል።
በፓርላማው የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አማኑኤል አብረሃ ማሻሻያው አለመታተሙ ስህተት እንደሆነና በፍጥነት እንዲታተም እንደሚደረግ፣ ነገር ግን ማሻሻያው በሕግ መሠረት የተፈጸመ ስለመሆኑ ምላሽ ሰጥተዋል።
የፓርላማው የተናጠል ስብሰባ የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ በሦስት ተቃውሞና በአንድ ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ አፅድቆታል። ከዚህ ሒደት በኋላ የሕዝብና ቤት ቆጠራ የሚካሄድበትን ጊዜ ለማራዘም የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ለሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ቀርቦ፣ በአንድ ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል።