ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡና በሕገወጥ መንገድ አገር ውስጥ የገቡ መድኃኒቶች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
ባለሥልጣኑ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ 29 ካርቶን የተለያዩ አይነት መድኃኒቶች፣ 449 ፓኬት ሕገወጥ ናርኮቲክ መድኃኒቶች እንዲሁም ከ600 ፓኬት በላይ ቤጋ 50 መድኃኒቶች ባቲ መግቢያ ላይ ተይዘዋል፡፡
የኮምቦልቻ ገቢዎችና ጉምሩክ ከባለሥልጣኑ ጋር በመተባበር ባደረገው ክትትል፣ መድኃኒቶቹ በቁጥጥር ሥር ሲውሉ፣ መድኃኒቱን ጭኖ በነበረው አይሱዙ መኪና ውስጥ የነበሩ ሁለት ተጠርጣሪ ግለሰቦች ጉዳይም በሕግ መያዙን ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡