Monday, August 8, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  መንግሥት ከካሩቱሪ ላይ ከ98 ሺሕ ሔክታር በላይ መሬት ነጠቀ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  – ለ18 ኩባንያዎች ማስጠንቀቂያ ሰጠ

  በኢትዮጵያ እርሻ ኢንዱስትሪ ውስጥ ብዙ ሲነገርለትና ሲጠበቅ የቆየው የህንዱ  ካሩቱሪ አግሮ ፕሮዳክት ኩባንያ ባስመዘገበው ዝቅተኛ ሥራ አፈጻጸም ማስጠንቀቂያ ሲሰጠው ቢቆይም፣ ሊሻሻል ባለመቻሉ ታኅሳስ 18 ቀን 2008 ዓ.ም. መሬቱን ተነጠቀ፡፡

  የአዲስ አበባ ከተማ ጠቅላላ ስፋት 54 ሺሕ ሔክታር ሲሆን፣ ካሩቱሪ የአዲስ አበባ ከተማን ሁለት እጥፍ ለማከል 8,000 ሔክታር መሬት ብቻ የቀረውን 100 ሺሕ ሔክታር መሬት ለማልማት በመያዝ ለዓመታት በይዞታው ሥር አቆይቷል፡፡

  ነገር ግን ብዙ የተባለለት ይህ ኩባንያ ላለፉት ስድስት ዓመታት ከ1,200 ሔክታር የበለጠ ማልማት ባለመቻሉ፣ በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ሥር የሚገኘው የኢትዮጵያ ግብርና ኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ ታኅሳስ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ፣ በኩባንያው ይዞታ ሥር የሚገኘውን 98.8 ሺሕ ሔክታር መሬት በመንጠቅ ወደ መሬት ባንክ ገቢ እንዲሆን አድርጓል፡፡

  ኩባንያው ያለማው መሬት ብቻ በይዞታው ሥር እንዲቆይ መወሰኑን፣ በኢትዮጵያ ግብርና ኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጄኔራል ተፈርሞ የወጣው ደብዳቤ ያመለክታል፡፡

  ካሩቱሪ የፌዴራል መንግሥት የክልሎችን መሬት በውክልና ተረክቦ ከማስተዳደሩ በፊት፣ ከጋምቤላ ክልል 300 ሺሕ ሔክታር መሬት መረከቡ ይታወሳል፡፡

  ነገር ግን የክልሎችን መሬት በውክልና ተረክቦ የሚያስተዳድረው የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ካሩቱሪ ይህንን መሬት ሊያለማው እንደማይችል በተደረገ ውይይት በማረጋገጡ፣ ሁለት መቶ ሺሕ ሔክታር መሬት በመቀነስ አዲስ ውል እ.ኤ.አ. በ2010 ተፈራርሟል፡፡

  ለካሩቱሪ የተሰጠው መሬት የሚገኘው በጋምቤላ ክልል ኑዌር ዞን፣ ጂካዎ ወረዳና ኢታንግ ልዩ ዞን ለ50 ዓመታ በሚቆይ የሊዝ ውል በርካሽ ዋጋ እንደተሰጠው ይታወሳል፡፡

  ካሩቱሪ በዚህ መሬት ላይ ጥራጥሬ፣ የፓልም ዛፍ፣ ሩዝና ሸንኮራ አገዳ ለማልማት ዕቅድ ይዞ ነበር፡፡ ኩባንያው ከሚኒስቴሩ ጋር በገባው ውል መሠረት የተረከበውን መሬት እ.ኤ.አ. በ2012 ሙሉ በሙሉ ማልማት ነበረበት፡፡

  የኢትዮጵያ ግብርና ኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ ሕዝብ ግንኙነት ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል ዘነበ ለሪፖርተር እንደገለጹት ግን፣ ካሩቱሪ የተሰጠውን መሬት ማልማት አልቻለም፡፡ 1,200 ሔክታር መሬት ብቻ ማልማቱን ጠቅሰዋል፡፡

   ይሁንና በቅርቡ የተበደረውን ብድር በወቅቱ ባለመክፈሉ ምክንያት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሐራጅ አውጥቶበት እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በባንኩ የሐራጅ ማስታወቂያ ላይ ካሩቱሪ አለማ የተባለው መሬት 7,500 ሔክታር እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ካሩቱሪ ሐራጅ የተባለው ለሁለተኛ ጊዜ እንደሆነና በፍርድ ቤት ዕግድ አስወጥቶ የሐራጅ ሒደቱ እስከ መጪው ጥር 10 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ እንዲቆም ማስደረጉን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡

  ‹‹የሥራ አፈጻጸሙን እንዲያስተካክል በርካታ ማስጠንቀቂያዎች ተሰጥተውታል፡፡ መንግሥትም የተቻለውን ድጋፍ ሁሉ ሰጥቶታል፤›› በማለት መንግሥት ያሳየውን ትዕግሥት አቶ ዳንኤል ገልጸው፣ ከብዙ ማስታመም በኋላ ይህ ዕርምጃ ሊወሰድበት እንደቻለ አስረድተዋል፡፡

  የካሩቱሪ አግሮ ፕሮዳክትስ ኩባንያ መሥራችና ማኔጅንግ ዳይሬክተር ሳይ ራክሪሻና ካሩቱሪ ኤጀንሲው ስለወሰደው ዕርምጃ ሪፖርተር ጥያቄ አቅርቦላቸው ነበር፡፡

   በአዲስ ዓመት በዓል ምክንያት ከአገር ውጭ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ‹‹ማንኛውም ሰው የሕግ የበላይነት ማክበር ይገባዋል፤›› በማለት በኢሜይል ምላሽ ከሰጡ በኋላ ተወስዷል የተባለውን ዕርምጃ እውነተኛነት እንደሚጠራጠሩ በምላሻቸው ገልጸዋል፡፡ ትክክለኛውንና እውነተኛውን ነገር ካጣሩ በኋላ ምላሽ እንደሚሰጡበት አስታውቀዋል፡፡

  ጠበቃቸው አቶ መስፍን አሰፋ በበኩላቸው ተወሰደ ስለተባለው ዕርምጃ ምንም እንደሚያውቁና ደንበኛቸውም ከአገር ውጭ በመሆናቸው ስለጉዳዩ ምንም ዓይነት አስተያየት ለመስጠት የሚያስችላቸው መረጃ እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡

  ራም ካሩቱሪ ከጥቂት ቀናት በፊት ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ባለሥልጣናት መሬታቸውን ለመውሰድ ቢሞክሩ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንደሚሞግቷቸው አስጠንቅቀው ነበር፡፡ ክትትል የሚያደርግባቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት እንጂ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር እንዳልሆነና በእሳቸው የእርሻ መሬት ላይ እንደማይመለከተው በመግለጽ ሞግተዋል፡፡

  ይሁንና የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የግብርና ኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ በበኩሉ፣ ለሰፋፊ እርሻዎች ኃላፊነት ያለበት መሆኑን፣ ክትትልና ቁጥጥር የማድረግ ሥልጣን እንዳለው አሳይቷል፡፡ ራም ካሩቱሪ ከሪፖርተር ጋር ያደረጉት ቆይታ በርካታ አነጋጋሪ ሐሳቦችን የተንፀባረቁበት ሲሆን፣ የሰጧቸው አስተያየቶች የመንግሥት አካላትን በተለይም ሚኒስቴሩን ቅር ማሰኘታቸው ታውቋል፡፡

  ካሩቱሪ ብቻ አይደለም ዕርምጃ የተወሰደበት፡፡ ሌላኛው የህንድ ኩባንያ ቢኤችኦ ፕሮጀክት መሬት ተነጥቋል፡፡ ቢኤችኦ በጋምቤላ ክልል ለምግብ ዘይት የሚሆን የፓልም ዛፍ ለማምረት 27 ሺሕ ሔክታር ተረክቦ ነበር፡፡

  ይህ ኩባንያ በየዓመቱ ዘጠኝ ሺሕ ሔክታር እያለማ በሦስት ዓመት ውስጥ ሙሉውን እንዲያጠናቅቅ ውል ቢገባም፣ በገባው ውል መሠረት ሥራውን አላካሄደም፡፡

  በዚህ መሠረት ኩባንያው ማልማት ያልቻለው 22 ሺሕ ሔክታር ተነጥቆ የመሬት ባንክ ውስጥ እንዲገባና የተቀረው አምስት ሺሕ ሔክታር ኩባንያ በእጁ እንዲቆይ፣ በኢትዮጵያ ግብርና ኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጄኔራል በአቶ አበራ ሙላት ፊርማ ታኅሳስ 18 ቀን 2008 ዓ.ም. የወጣው ደብዳቤ ያመለክታል፡፡

  አቶ ዳንኤል ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከካሩቱሪና ከቢኤችኦ በተጨማሪ ሌሎች 18 ኩባንያዎች የመጀመርያና የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡

  የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በአገሪቱ ሰፋፊ እርሻ ታሪክ እነዚህ ኩባንያዎች ከፍተኛ ለውጥ ያመጣሉ የሚል ከፍተኛ ተስፋ ጥለው እንደነበር በተለያዩ ጊዜያት ሲገለጽ ቆይቷል፡፡

  ኩባንያዎቹ ሰፋፊ መሬቶች በመውሰዳቸው ምክንያት የመሬት ቅርምት ነው ተብሎ ሲወገዝ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

  ብርሃኑ ፈቃደ እና ውድነህ ዘነበ

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች